Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ለራሷና ለአካባቢዋ ሰላም መስዕዋትነትን የምትከፍል ሀገር

0 557

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ለራሷና ለአካባቢዋ ሰላም መስዕዋትነትን የምትከፍል ሀገር

                                                 ቶሎሳ ኡርጌሳ

ኢትዮጵያ የውጭ ግንኝነቷን ፖሊሲ ተመርኩዛ ለራሷና ለአካባቢዋ ሰላም ስትል በርካታ መስዋዕትነቶችን የከፈለችና እየከፈለች ያለች ሀገር ናት፡፡ በተለይም በምስራቅ አፍሪካ የአል ቃዒዳ ክንፍ የሆነው አሸባሪው አል ሸባብን ለመዋጋት ሀገራችን ትግሏን አጠናክራ መቀጠሏ የዚህ መስዕዋትነት አካል ነው፡፡

እንደሚታወቀው ከመሰንበቻው የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ወደ ሶማሊያ መግባቱን ዘግበዋል፡፡ ይህን ዘገባ ተከትሎም የኢትዮጵያ መንግስት ምላሽ ሰጥቷል፡፡ “የኢትዮጵያ ሰራዊት ወደ ሶማሊያ የገባው ሽብርተኝነትን ለመዋጋት እንዲሁም ለሶማሊያ ጦር አጋርነቱንና ድጋፉን ለማሳየት ነው” ሲል ገልጿል። ድጋፉ የተለመደና  መደበኛ መሆኑን በመግለፅ ጭምር፡፡

ታዲያ ይህ ድጋፍ የሚመነጨው ከህገ መንግስታችን መሆኑ ግልፅ ነው። ህገ መንግስታችን የአካባቢውንና ጎረቤት ሀገሮችን ለጋራ ጥቅምና ሠላም እንዲሰሩ የሚጋብዝ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ መሰረት ጥሏል፡፡

ይህ እንደ ቀድሞዎቹ የውጭ ጉዳይና የደህንነት ፖሊሲዎች የሀገር ውስጥ ጉዳዮችን ቸል በማለትና ወደ ውጭ ያነጣጠረ ሳይሆን፤ በቅድሚያ በሀገር ውስጥ ሰላም በማስፈን በማረጋጋት ላይ ትኩረት በማድረግ  በአካባቢያችን ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም እንዲፈጠርና የጋራ ልማትና ትብብር እንዲጠናከር ማድረግ ነው፡፡  

የውጭ ጉዳይና የሀገራዊ ደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ ብሔራዊ ጥቅማችንን የማስጠበቅና ሀገራዊ ህልውናችንን የማረጋገጥ ተልዕኮ ያለው መሆኑ ርግጥ ነው፡፡ ፖሊሲው እንደሚያመለክተው ከማንኛውም ሀገር ጋር የሚኖረን ግንኙነት በመሰረታዊ ሀገራዊ ጥቅማችን ደህንነት ላይ የተመሰረተ፣ እንዲሁም የልማትና የዴሞክራሲ ሂደቱ ስር እየሰደደና የሀገራችን ዕድገት እየተፋጠነ በሄደ ቁጥር ለአደጋ ተጋላጭነታችን በከፍተኛ ደረጃ ለመቀነስ ያለመ ነው፡፡

ሀገራዊ ደህንነታችንን ለማስጠበቅ ዋናው መሣሪያ ልማትና ዴሞክራሲን በሀገር ደረጃ ማረጋገጥ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በዚህ ረገድ ተመስርቶም ዲፕሎማሲያችን በቂ ጥናት በማካሄድ አደጋዎችን ለመቀነስ፣ ግጭቶች ሲፈጠሩ በድርድር እንዲፈቱ ለማድረግ፣ በዚህ ሂደት ሊፈቱ ያልቻሉትን ለመከላከል አቅም መገንባት ተተኪ የሌለው ሚና እንደሚጫወት ፖሊሲው ያስረዳል፡፡

የኢፌደሪ መንግስት የሀገሪቱ ዋነኛ ጠላት ድህነት ነው የሚል ፅኑ እና ቁርጠኛ እምነት ከያዘ ቆይቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሀገሪቱ ከውርደት፣ ከኋላ ቀርነትና ከተለያዩ የስጋት ምንጮች ነጻ ልትሆን የምትችለው፤ ፈጣን የምጣኔ ሃብት ልማት፣ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታና መልካም አስተዳደር በተሳካ መንገድ ሲካሄዱና ህዝቡም በየደረጃው የዕድሉ ተጠቃሚ ሲሆን እንደሆነ በጥብቅ ያምናል፡፡

ይህን መነሻ በማድረግ በተለያዩ ጊዜያት የተቀረጹ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችን እንዲሁም ፕሮግራሞችና ፕሮጀክቶች በማዘጋጀት ካሁን በፊት ዘላቂ የልማትና ድህነት ቅነሳና ፈጣን ዘላቂ ልማት ድህነትን የመቀነስ ብሎም የማጥፋት ዕቅድ እንዲሁም ሌሎች የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ፕሮግራሞች በሚገባ ለማሳካት ተችሏል፡፡ ለሀገራዊ ህዳሴያችን መሰረት እየተጣለ ነው፡፡

ሆኖም ይህን የህዳሴ ጉዞ ሊያደናቅፍ የሚችል የአሸባሪነት ስጋት ቀጣናው ላይ አንዣቧል፡፡ አል ሸባብ በተሰኘው አሸባሪ ሃይል አማካኝነት። ይህ የሽብር ሃይል በሀገራችን ላይ ጀሃድ ያወጀ መሆኑ ይዘነጋም። የምስራቅ አፍሪካ ቀጣናን በሽብር ማዕበል ለመናጥ እየሰራ ነው። በተለይ ወንድም የሆነውን የሶማሊያ ህዝብ ቁም ስቅሉን እያሳየው ነው።

በቅርቡ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት አዲስ አበባ ተገኝተው ከኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ጋር ባካሄዱት ውይይት ኢትዮጵያ አል ሸባብን ለማጥፋት በሚደረገው ዘመቻ ላይ ድጋፍ እንድታደርግ ጠይቀዋል። የኢትዮጵያ ሰራዊት ከመሰንበቻው ወደዚያች ሀገር ያቀናበት መነሻም ይኸው ነው። ለዚህም ነው—የኢትዮጵያ መንግስት ሰራዊቱ ወደ ሶማሊያ የገባው አልሸባብን ለመዋጋት መሆኑን የገለፀው።

እንደሚታወቀው የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት የሀገራችንን ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም ህገ መንግስታዊ ስርዓታችን በአስተማማኝ እንዲጠብቅ ከተሰጠው ተልዕኮ ባሻገር፤ የጎረቤቶቻችንና የአካባቢያችንን ሰላምና መረጋጋት በማስጠበቅ ረገድ የበኩሉን ድርሻ እንዲጫወት ከተባበሩት መንግስታትና ከአፍሪካ ህብረት ተደጋጋሚ ጥሪዎች ይቀርቡለታል። ይህን ተልዕኮውን በዓለምና በአህጉር አቀፍ የሰላም ማስከበር ጥበቃዎችን በንቃት በመሳተፍ እየተወጣ ነው።

መከላከያ ሰራዊታችን ህዝብና መንግሥት የሰጡትን ተልዕኮ በቁርጠኝነት ተቀብሎ በተሰማራባቸው የግዳጅ አካባቢዎች ሁሉ በጠንካራ ህዝባዊ ወገንተኝነት ተግባሩን በብቃት፣ በጀግንነትና በሚያኮራ ሁኔታ በመፈፀሙ ሳቢያ በአካባቢው መንግስታት ተፈላጊነቱ እንዲጨምር አድርጎታል።

የሶማሊያ መንግስትም አል ሸባብ በሞቃዲሾ ከ350 በላይ ንፁሃን ዜጎችን መጨፍጨፉን ተከትሎ በቅርቡ የኢትዮጵያን ሰራዊት ድጋፍ የጠየቀው ከዚህ የሰራዊታችን ሁለንተናዊ ጥንካሬ በመነሳት መሆኑ አይካድም።

ከድህነትና ኋላቀርነት የመውጣት ዓላማን አንግበው ለስኬታማነቱ ከፍተኛ ርብርብ በማድረግ ላይ ለሚገኙት የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት፣ በተለይም ለፈጣን ልማት ቀጣይነት በመረባረብ ላይ የምትገኘው ሀገራችን ሽብርተኝነት በተለያዩ ጊዜያት ተፈታትኗታል። ሊያንበረክካት ግን አልቻለም።

ይህ ውጤት የተገኘው ደግሞ ለተግባሩ መስፋፋት ምቹ ሁኔታ የማይፈጥሩት ህዝባችንና መንግስት ባደረጉት የተቀናጀ ጥረት መሆኑ ግልፅ ነው። እናም ዛሬም የሽብርተኝነት አጋፋሪዎችን መዋጋት የግድ ይላታል። እናም ሌላኛው የሰራዊታችን ወደ ሞቃዲሾ ማቅናት ምክንያት ይኸው ይመስለኛል።

ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት በሶማሊያ ተጠልለው የሽብር ጥቃት ለማካሄድ የከጀሉ የአሸባሪዎችን ከንቱ ምኞቶች ሁሉ ከማምከን በተጨማሪ፤ የሽብር ምንጭን ለመከላከል ብሎም ለማድረቅ ያካሄደችው ፀረ ሽብር ዘመቻን ከማሳካት የገደባት አንድም ሃይል አልነበረም። ይህም የሀገራችንን ፀረ ሽብርተኝነት አቋም ያረጋገጠ ነበር።

ባለፉት ጊዜያት ሀገራችን በከፍተኛ ሁኔታ ተደራጅቶና በትልልቅ የጦር መሳሪያ ታግዞ በግንባር ሲዋጋ የቆየው አል ሸባብን ወደ አቅመ ቢስነት እንደለወጠችው የሚዘነጋ አይደለም። የሶማሊያን ህዝበ ወደ ሰላማዊ ኑሮው እንዲመለስ ማድረግ ችላም እንደነበር እንዲሁ።

ሽብርተኝነት ሶማሊያ ውስጥ እንደ ቀድሞው ስያሜውን እየቀያየረ ዳግም የሚደራጅበት ሁኔታ እንዳይኖር አድርጋም ነበር። ዛሬ በአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪና በኢትዮጵያ ሰራዊት ጠንካራ ክንድ የተደቆሰው አል ሸባብ የቀድሞ ይዞታዎቹን በማጣቱ ምክንያት የሚንቀሳቀስበት ሁኔታ በማክተሙ የአጥፍቶ መጥፋት ስልትን ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛል።

እናም ይህን ሃይል በመፋለምና መስዕዋትነት በመክፈል ለሶማሊያ ፌዴራላዊ መንግስትና ለሰራዊቱ ድጋፍ ማድረግ ያስፈልጋል። ይህ የሀገራችን አቋም ኢትዮጵያ አሸባሪነትን ለመዋጋት ያላት ቁርጠኝነት መገለጫ ነው።

በሀገር ቤት ሰላማችን፣ ልማታችንና ዴሞክራሲያችን እንዲያብብ ሽብርተኝነትን ከሚዋጉ ሃይሎች ጋር ተባብሮ መስራት ይገባል። ማገዝም ያስፈልጋል። የሰራዊታችን ወደ ሶማሊያ መግባት ይህን ቁርጠኛ አቋም የመተግባር አንድ አካል ነው።

ይህ ሁኔታም ኢትዮጵያ ለራሷና ለአካባቢው ህዝቦች ሰላም መስዋትነት የምትከፍል ሀገር እንድትሆን አድርጓታል። ይህ በመሆኑም ዛሬም ተልዕኮውን ሁሉ ህዝብን ይዞ የሚፈፅመው መከላከያ ሰራዊታችን ከሶማሊያ ህዝብ ጋር በመሆን የሽብር ቡድኑን ይበልጥ ትርጉም የሌለው ደረጃ እንደሚያደርሰው በርግጠኝነት መናገር የሚቻል ይመስለኛል።   

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy