Artcles

መቼም ቢሆን ከልማት ጉዟችን አንደናቀፍም!

By Admin

November 17, 2017

መቼም ቢሆን ከልማት ጉዟችን አንደናቀፍም!

አባ መላኩ

የኢትዮጵያ ህዝቦች ዛሬ ዴሞክራሲያዊ አንድነት የሰፈነባት አገር መፍጠር ችለዋል፡፡ ዜጎቿ ከዚህ ደረጃ ለመድረስ የቻሉት የህይወትና የአካል ጉዳት የጠየቀውን እልህ አስጨራሽ ትግል በማድረግ ነው። ቀድሞ የምልዓተ ህዝቡ የትግል ውጤት አምባገነኑን የደርግ ሥርዓት ማስወገድ ነበር። አሁን ላይ ደግሞ ዋናው ጠላታቸው የሆነውን ድህነት ገጥመው የድላቸውን ውጤት ማጣጣም ጀምረዋል።

ከስኬቶቻቸው ውስጥ መጥቀስ ካስፈለገ ገጠርን ከከተማ ያስተሳሰሩ ሰፋፊ የመሠረተ ልማትና የማህበራዊ ግልጋሎት አውታሮችን ዋነኞቹ ናቸው። በዚህም ግዙፍ ሀብት በመመደብ ልማትን ማፋጠንና የህዝብ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ ይህ የመሠረተ ልማት ዝርጋታና የማህበራዊ ተቋማት መስፋፋት ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ስትገለፅበት ከነበረው የድህነትና ኋላ ቀርነት ተምሣሌትነት በሂደት አላቅቋታል።  

በመጀመሪያው አምስት ዓመታት በተተገበረው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድን  ታሳቢ ያደረጉ ሁኔታዎች ተመቻችተዋል። የሁለተኛ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ምዕራፍ ለመተግበር ሌላ ዕቅድ ተነድፎና የዝግጅት ምዕራፉ ተጠናቅቆ ወደተግባር ከተገባ ሦስተኛው ዓመት ተይዟል።   

በዚህ ዕቅድ መጠናቀቂያ ዘመን አገሪቱ ወደ ዝቅተኛው የመካከለኛ ገቢ ላይ እንደምትደርስ ይጠበቃል። ይህም በ2017 ዓ.ም ትደርስበታለች ለተባለው የመካከለኛ ኢኮኖሚ የዕድገት ደረጃ መደላድል እንደሚፈጥር ይታመናል።

እንዲህም ሆኖ በዚህ ስኬታማ ጉዞ ላይ የኢትዮጵያ ህዝቦች የድል ምዕራፍ ላይ አሁንም ዋነኛ ጠላት ከፊት ለፊቱ ተጋርጠውበታል፡፡ ይኸውም ድህነት ዋነኛ አጀንዳ መሆኑ ነው። ኪራይ ሰብሳቢነት በተለይ በከተሞች ከባድ ፈተና ሆኗል።  

የኢትዮጵያ ህዝቦችም በእያንዳንዷ የድህነት ማስወገድ ጉዟቸው ውስጥ ጉልበታቸውን የሚፈታተነውን አካል በጠላትነት ፈርጀው የተባበረ ክንዳቸውን እያሳረፉ ይገኛሉ።  

በ5ኛው ጠቅላላ ምርጫ የህዝቡን ሙሉ ይሁንታ አግኝቶ መንግሥት የመሠረተው በኢሕአዴግና አጋሮቹ የሚመራው ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት፤ በህዝቡ የተቀናጀ የፀረ ድህነት ትግል ውስጥ ወደኋላ የሚጎትቱ አመለካከቶችና ተግባራትን ለማስወገድና የህዝቡን የፀረ ኪራይ ሰብሳቢነት ትግል ለመምራት አጀንዳ ቀርፆ መንቀሳቀስ ጀምሯል፡፡ በአጀንዳው ዙሪያም ህዝቡ በሙሉ አቅሙ ለመሳተፍ ቁርጠኝነቱን አሳይቷል፡፡

በዚህ ወቅት የህዝቡንና የመንግሥትን ትግል ለማኮላሸት ታጥቀው የተነሱ ፀረ ሠላምና ጥገኛ ኃይሎች በተለያዩ አካባቢዎች ርብርብ ሲያደርጉ ይስተዋላሉ። ይህ ጥረታቸው የመጨረሻ መፍጨርጨር መሆኑ ይታወቃል። ሁኔታዎችን ተረጋግቶ ማስተዋል የጎደላቸው የተወሰኑ የኅብረተሰብ አካላትን አሳስተው ችግር ውስጥ መክተታቸው ግን አልቀረም።

ዛሬ ላይ ሞቅና ቀዝቀዝ እያለ በነበረው የፀረ ኪራይ ሰብሳቢነት ትግል ሂደት ሁለት ቦታ ረግጠው የነበሩ አካላት በየጊዜው ከየተቀበሩበት ሁሉ ሳይቀር ነፍስ ዘርተው ብቅ ማለት ጀምረዋል። ይሁንና ግን ህዝብና መንግሥት አንድ ሆነው የመረረ ትግል ለማድረግ መወሰናቸው ሳይገባቸው አልቀረም። ይህ የተደራጀ የህዝብና የመንግሥት የፀረ ኪራይ ሰብሳቢነት ትግል እንደማይለቃቸው ጠንቅቀው አውቀዋል።    

በ1999 ዓ.ም በወጣው የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ስትራቴጂ ላይ በፀረ ድህነት ትግል ውስጥ ከሚገጥሙ ፈተናዎች አንዱ በኪራይ ሰብሳቢ ኃይሎች ውሰጥ የሚደበቁ ትምክህትና ጠባብነት መሆናቸው በግልፅ ሰፍሯል። በዚህ መፅሃፍ ገፅ 84 ላይ “ህዝቡ ከኪራይ ሰብሳቢነት ተጠቃሚ ባይሆንም ከፖለቲካዊ ኢኮኖሚው ተፅዕኖ ውጭ ስለማይሆን ለመንግሥትና ለኪራይ ሰብሳቢ ኃይሎች ባለህ ቀረቤታ ፍርፋሪ ይገኛል የሚል እምነት እንዲይዝ በሚያደርጉ ኃይሎች አስተሳሰብ ሥር እንዲወድቅ ስለሚደረግ በአካባቢ፣ በኃይማኖት፣ በብሄር ወዘተ…‘ላንተ ቆመናል’ በሚሉ አካላት አዝማሚያ ይኖረዋል” ይላል፡፡

በአንድ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሣለኝ በመልካም አስተዳደር ዙሪያ ውይይት በተካሄደበት አንድ መድረክ ላይ እንዲህ ብለው ነበር። “ካሁን በኋላ ሃሳባችንን እዚህ ጨርሰን እንውጣ፡፡ ውይይቱን ጨርሰን ስንወጣ የአካባቢና አብሮ አደጋችን እንዳይጠቃብን የሚለውን አሰተሳሰብ ማቆም አለብን” የሚለው ቁርጠኝነት የተሞላበት ንግግር ተጠቃሽ ነው።

አሁን ባለንበት ወሣኝ ወቅት ላይ ኪራይ ሰብሳቢነትን የማድረቅና መልካም አስተዳደር የማስፈን ትግል ጫፍ ላይ ደርሷል፡፡ እዚህ ላይ ኢሕአዴግ ዕድለኛ ሊያሰኘው የሚገባ ጉዳይ አለ፡፡ ህዝቡ እያንዳንዷን ክፍተት ለይቶ የመናገር ድፍረቱ በእጅጉ ጨምሯል፡፡ ህዝቡ በግልፅ እንዲናገር ህገ መንግሥቱ ያጎናፀፈው መብት ቢሆንም እንዲናገር ያስገደደው ግን ለአገሪቷ ልማት ካለው ቀናኢነትና ተቆርቋሪነት ነው፡፡

በየደረጃው በሚታዩ መድረኮች በህዝቡ የሚስተዋለው ግልፅ አቋም በፍርፋሪ ሳይሆን በሥራና ዘላቂ ልማት በማረጋገጥ ብቻ የአገራችን ዕድገት እንደሚረጋገጥ ግልፅ አቋም ተይዟል። ይህ እንደ ኢሕአዴግ ላለ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመር የያዘ ድርጅት የህዝብን ተሳትፎ ባረጋገጠ መልኩ አገር ለመምራት ስለሚረዳ ዕድለኛ ነው፡፡

በዚህ ሂደት ግን ኪራይ ሰብሳቢ ኃይሉ ያለ የሌለ አቅሙን በመጠቀም መሸሸጊያ ለማግኘት ሲፍጨረጨር ይስተዋላል። ለዓመታት ህዝብን ከህዝብ የማለያየት አጀንዳ ሲያራምድ ቆይቷል። በመካከላቸው ከፍተኛ ቅራኔ ያላቸው ትምክህተኛና ጠባብ ኃይሎች ሳይቀሩ አንድ ግንባር ላይ የተሰለፉበት ሁኔታ የመፈጠሩ ጉዳይ ለዚህ ሁነኛ ማሣያ ነው፡፡ ሰሞኑን ከበኦሮሚያ እና በኢትዮጵያ ሶማሌ አንዳንድ አካባቢዎች የታየው ግጭት ከማሣያዎቹ ውስጥ አንዱ ነው፡፡   

መንግሥትና ህዝብ በያዙት ቁርጠኛ አቋም የተደናገጡና በጉዳዩ ላይ ተሳታፊ ሆኖ የነበሩ አካላት በትግሉ ሂደት ተጠያቂ መሆናቸው አይቀርም። ሂደቱም ተጀምሯል። ተጠናክሮም ይቀጥላል።

ከዚም በተጨማሪም ግርግሩን ተጠቅመው መንግሥትን በኃይል በመገልበጥ ሥልጣን ለመያዝ ምኞት ያላቸው ጠባብና የትምክህት ኃይሎች ሴራቸውን ጎንጉነዋል፡፡ እነዚህ ኃይሎች በተለይ በኢትዮጵያ የሚከናወኑ የልማት ፕሮጀክቶችን ለማደናቀፍ ግብ የሌለው ጥረታቸውን ቀጥለዋል፡፡

በተለይ በሦስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡ ኃይሎች የጠባብነትና የትምክህት ያልተሳካ ጋብቻ በመፍጠር በህዝብ አመኔታ ወደሥልጣን መውጣት ሲያቅታቸው የመጨረሻ ዕድላቸው በዚህ አመፅ ለማሳካት የሚሞክሩ ናቸው፡፡ ዋና መንደርደሪያቸው በየትኛውም መልኩ ሥልጣን በመያዝ አገሪቷን ለኒዮሊበራል ኃይሉ አሳልፎ በመስጠት የራሳቸውን የግልና የቡድን ጥቅም ማደለብ ነው፡፡

የኪራይ ሰብሳቢዎች አጀንዳ ለህዝቡ ምንም ጥቅም ባይሰጥም ህዝቡ በአካባቢና በኃይማኖት ወይም በሌላ ስሜት ሰለባ በማድረግ እነሱ ወደ ቀረፁት አጀንዳ በማስገባት መጠቀሚያ ለማድረግ መሞከር ነው። ሁሌም አንግበው የሚይዙት አጀንዳ የህዝብን ጥቅም የሚያረጋግጥ ባለመሆኑ ወደፊትም ቢሆን ይሳካላቸዋል ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው፡፡ ሰሞኑን በኦሮሚያ እና በኢትዮጵያ ሶማሌ አንዳንድ አካባቢዎች የተነሳው ግጭት በዚህ ቅኝት የሚታይ ነው፡፡

መንግሥት የማረጋጋት ሥራውን እያከናወነ ለችግሩ ተጠያቂ የሚሆኑ ኃይሎችን ለህዝብ በማጋለጥ ተገቢውን ህጋዊ ቅጣት እንዲያገኙ እያደረገ ነው። የሀሳቡ ጠንሳሽና አራማጆች በየምሽጋቸው ተደብቀው አይቀሩም፤ ከህዝብ እይታም አያመልጡም፤ ተገቢውን ዋጋ ያገኛሉ፡፡

የነዚህ የጠባብ ኃይሎች ዋና ዓላማ የኪራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳደር ትግሉን ለመጥለፍ ነው። መንግሥት ህዝብን አሳትፎ እነዚህን ኃይሎች የማጋለጥ ሥራ ማከናወን ይጠበቅበታል፡፡ ፀረ ሠላም ኃይሎች ሊገነዘቡት የሚገባ ቁምነገር ነገር ቢኖር መቼውንም ቢሆን ከልማት ጉዟችን እንደማያስቆሙን ነው፡፡