CURRENT

መንግሥት የሚከበረው ሕዝብን አክብሮ ሲያስከብር ነው!

By Admin

November 17, 2017

ሕዝብና መንግሥት ሆድና ጀርባ ከሚያደርጓቸው ምክንያቶች መካከል አንደኛው የግልጽነት መጥፋት ነው፡፡ ግልጽነት ሲጠፋ መተማመን አይኖርም፡፡ መተማመን በሌለበት መከባበር አይታሰብም፡፡ መከባበር ከቤተሰብ ይጀምራል፡፡ ከዚያም ወደ ጎረቤት ተሻግሮ ወደ ማኅበረሰቡ ይደርሳል፡፡ በዚህ መሠረት መራመድ ሲቻል በአገር ደረጃ መከባበር ባህል ይሆናል፡፡ አገር የፀና መሠረት ሊኖራት የሚችለው የአገረ መንግሥት ግንባታ (Nation Building) በተሳካ መንገድ መከናወን ሲችል ብቻ ነው፡፡ ይህ ይሳካ ዘንድ ደግሞ በግልጽነትና በተጠያቂነት ላይ የተመሠረተ ሥርዓት መፈጠር አለበት፡፡ ይህ ዓይነቱ ሥርዓት የአገሪቱ ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤት የሆነውን ሕዝብ ያማከለ ሲሆን፣ ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ለሕግ የበላይነት ነው፡፡ ሕግ ሲከበር ደግሞ የሚከበሩ ሕዝብና መንግሥት አሉ ማለት ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ አገሪቱን ችግር ውስጥ እየተከተቱ ያሉ ችግሮች መነሻቸው የግልጽነትና የተጠያቂነት መጥፋት ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡

አገሪቱን በሚያስተዳድሩ ባለሥልጣናት መካከል መከባበር ከሌለ ሌላው ራስ ምታት ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ መሠረት በፌዴራልና በክልል መንግሥታት ውስጥ ባሉ የተለያዩ መዋቅሮች መካከል ያለው የሥራ ግንኙነት በሕግ የተገደበ ከመሆኑ አንፃር፣ በግለሰብ ኃላፊዎች መካከል ያለው ግንኙነት ሕግን ብቻ የተከተለ መሆን አለበት፡፡ አሠራራቸው ለሕዝብ ግልጽ መሆንና ተጠያቂነትን ጭምር ያካተተ በመሆኑ፣ ግንኙነታቸው በመከባበር ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ይጠበቃል፡፡ ይህ ዓይነቱ አሠራር ተግባራዊ መሆን እያቃተው ግን አንድ አጋጣሚ ሲፈጠር የሚመጣው መረጃ የተለያየ እየሆነ በሕዝብ ላይ መደናገር ይከሰታል፡፡ በተደጋጋሚም ይስተዋላል፡፡ ይህ ደግሞ የሥልጣን ባለቤት በሆነው ሕዝብ ላይ ከፍተኛ መጠራጠርና አመኔታ ማጣት ያስከትላል፡፡ ሕዝብ መንግሥት እንደማያከብረውና ሥፍራ እንደማይሰጠው እንዲሰማው ያደርጋል፡፡ ሊኖር የሚገባውን በጎ ግንኙነት እያበላሸ ለሁከትና ለትርምስ በር ይከፍታል፡፡

ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግም ሆነ የሚመራው መንግሥት የሚታወቁበት ጉዳይ በጣም አሰልቺ በሆኑ ስብሰባዎች መብዛት ነው፡፡ በሕዝብ ስም በሚካሄዱ ስብሰባዎች ሳቢያ የአገልግሎቶች አሰጣጥ ከመስተጓጎሉ በተጨማሪ፣ ከስብሰባዎቹ ማጠቃለያ የሚገኘው ውጤት ለሕዝብ ፋይዳ ቢስ ነው፡፡ ሕዝብ የሚያቀርበው ጥያቄ ሌላ፣ የስብሰባዎቹ ምላሽ ሌላ እየሆነ መደናገር ይፈጠራል፡፡ ሕዝብ ሕመሜ ይኼ ነው ብሎ በግልጽ ሲያቀርብ ለሕመሙ መፈወሻ ተብሎ የሚቀርበው መድኃኒት በፍፁም አይገናኝም፡፡ ኢሕአዴግ በሚታወቅበት የመሸፋፈን ጎጂ ልማድ አማካይነት በርካታ ነገሮች እየተድበሰበሱ ይታለፉና ጊዜያቸው ደርሶ ሲፈነዱ ለአገር መከራ ይሆናሉ፡፡ እውነታውን መደበቅ መፍትሔ እንደማያመጣ እየታወቀ በዝግ ስብሰባዎች በሌሉ ጉዳዮች ላይ ጊዜን ማባከን ለምን አስፈለገ? መፍትሔ የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ለምን በግልጽ በአደባባይ ተነግረው አይገላለጡም? ሌላው ቀርቶ የዝግ ስብሰባዎችን ቃለ ጉባዔ ጭምር ለሕዝብ ይፋ በማድረግ የተነጋገርነው በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ነው ለምን አይባልም? ከዚያ አልፎ ተርፎም በቀጥታ ሥርጭት የአገሪቱ ዋነኛ ችግሮች ለሕዝብ ቀርበው ለምን አይደመጡም? ሕዝቡ ራሱ የመፍትሔ ሐሳቦችን እንዲያበረክት ለምን አይደረግም? በሕዝብ ስም እየተነጋገርን ነው ከተባለ የግልጽነቱ ጥግ እዚህ ድረስ መሆን ነበረበት፡፡ ሕዝብ በገዛ ጉዳዩ ባይተዋር ሲሆን የተናቀ ይመስለዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ያለው ትውልድ ቀደም ባሉት ዓመታት ዓይነት የፕሮፓጋንዳ ሥልቶች የሚታለል አይደለም፡፡ የዘመኑ ቴክኖሎጂ ባፈራቸው መሣሪያዎች አማካይነት በቀላሉ መረጃዎችን ያገኛል፡፡ እነዚህ መረጃዎች በተለያዩ ይዘቶችና ቅርፆች ስለሚደርሱትና የተለያዩ ትንታኔዎችን ስለሚያገኝ፣ ለተለመደው ፕሮፓጋንዳ የመጋለጥ ዕድሉ በጣም አነስተኛ ነው፡፡ ከዚህ በፊት የነበረው ትውልድና የአሁኑ እየተለያዩ ያሉትም በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ከዘመኑ ጋር የሚመጥን ግልጽነትን የተላበሰ አሠራር አለማስፈን ከትውልዱ ጋር ከማጋጨት ባለፈ፣ በሕዝብና በመንግሥት መካከል ያለውን ልዩነት የበለጠ ይጨምረዋል፡፡ ሕዝብ መንግሥትን ማመን አቅቶት ሌሎች አማራጮችን መመልከት ሲጀምር ችግሩ እየሰፋ ይሄዳል፡፡ ኢሕአዴግ እንደ ገዥ ፓርቲነቱና አገርን እንደ መምራቱ ይህንን ማመን አለበት፡፡ የ21ኛው ክፍለ ዘመን አስተሳሰብ የአንድ ጎራ የበላይነትን ሳይሆን ሰጥቶ መቀበል የሚለውን መርህ የሚቀበል በመሆኑ፣ ኢሕአዴግ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ይህ መርህ ሥራ ላይ እንዲውል በማድረግ ሕዝብን ማረጋጋት አለበት፡፡ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን አክብሮ እነሱ የሚስተናገዱበትን ምኅዳር ማመቻቸት ተገቢ ነው፡፡ የፖለቲካው ምኅዳር በመከባበር የሚስተናገዱበት ካልሆነ ሕዝብን ያስኮርፋል፡፡ እያስኮረፈም ነው፡፡

በተደጋጋሚ እንደምንለው ይህ ጨዋ ሕዝብ ቢታደል ኖሮ የሥልጣኑ ባለቤት እሱ ነበር፡፡ ይህ ኩሩ ሕዝብ በስመ አውቅልሃለሁ እየተሸነገለ ፍላጎቱ ሊፈጸም ባለመቻሉ ላለፉት ሁለት ዓመታት አገሪቱ ነውጥ ውስጥ ናት፡፡ ሕዝብ ጥያቄ ያነሳባቸው ጉዳዮች ምላሽ ያገኙ የነበሩት በትክክል መነጋገርና መወሰን ሲቻል ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን የሕዝብ ጥያቄዎች አቅጣጫቸውን እየሳቱ ለብሔር ግጭት ሲዳርጉ፣ የአገሪቱ አንጡራ ሀብት የፈሰሰባቸው የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ተረጋግተው የመማር ማስተማር ሒደቱ መቀጠል ሲያቅተው፣ ከዛሬ ነገ ምን ይመጣ ይሆን የሚሉ ሥጋቶች በየቦታው ሲሰሙ፣ በአንድ ወቅት የአንፃራዊ ሰላምና መረጋጋት ተምሳሌት የነበረች አገር ላይ የነውጥ ደመና ሲያንዣብብ፣ ወዘተ. ቆም ብሎ ማሰብ ማንን ይጎዳል? የመንግሥት ዋነኛው ሥራ ሕዝብን ማክበርና ፍላጎቱን መፈጸም ነው፡፡ ይህንን ተግባራዊ ማድረግ ለምን ያቅታል? ችግሮችን እየሸፋፈኑ በመጡበት መንገድ መቀጠል አላዋጣ ሲል፣ ለዘመኑ የሚመጥን አሠራር ማስፈን ተመራጭ ነው፡፡ ይህ ነው ለሕዝብና ለአገር የሚበጀው፡፡

በታሪክ እንደሚታወቀው በዓለም አቀፍ ደረጃ ግልጽነት የጎደላቸው መንግሥታት እንዲገለሉ ተደርገዋል፡፡ በሕዝባቸው ዘንድም ተቀባይነት አጥተዋል፡፡ ሕዝብ መንግሥት አላከበረኝም ብሎ ሲያስብ አምርሮ ይጠላዋል፡፡ ይህንን ዓይነቱን የመረረ ስሜት ማስተካከል የሚቻለው ግልጽነትን በማስፈን ለአገረ መንግሥት ግንባታ መደላድል ለመፍጠር ጥረት ሲጀመር ነው፡፡ የእያንዳንዱ ዜጋ ድምፅ ዋጋ እንዳለው ሁሉ፣ የእያንዳንዱ ዜጋም ጥያቄ ዕውቅና ሊሰጠው ይገባል፡፡ ሕዝብ ይህንን በተግባር መመልከት ሲጀምርና የተሳትፎ መጠኑ ሲጨምር መረጋጋት ይገኛል፡፡ የውይይት ባህሎች እየዳበሩ በነፃነት መነጋገር ይለመዳል፡፡ የሕግ የበላይነት እየሰፈነ ሕገወጥ ድርጊቶች አደብ እንዲገዙ ሲደረግ፣ በስመ አውቅልሃለሁ ባይነት በሕዝብ ላይ የሚያላግጡ ይገታሉ፡፡ ፋይዳ በሌላቸው ስብሰባዎች የሚባክነው ጊዜና ሀብት ለልማት ይውላል፡፡ ዴሞክራሲ በአንድ ጊዜ የሚገነባ ሥርዓት ባይሆንም፣ ሒደቱ በሕዝብ ባለቤትነት እየተመራ መስመር እንዲይዝ ጥርጊያው ይመቻቻል፡፡ ከሕዝብ ፈቃድና ፍላጎት ውጪ የሆኑ ተግባራት ተቀባይነት እያጡ፣ በሕዝብ ይሁንታ ላይ የተመሠረቱ ውሳኔዎች ተግባራዊ መደረግ ይጀምራሉ፡፡ መከባበርና መተባበር ብሔራዊ ዓርማ ይሆናሉ፡፡ ለግጭትና ለሁከት ክፍተት ስለማይፈጠር የሰላም አየር ይነፍሳል፡፡

ኩሩዎቹና አስተዋዮቹ ኢትዮጵያውያን የሚታወቁት መከባበር በሚባለው የጋራ እሴታቸው ነው፡፡ አንዱ የሌላውን ብሔር፣ ቋንቋ፣ ባህል፣ የአኗኗር ዘይቤና የመሳሰሉትን እያከበረ ከመኖርም በላይ ተጋብቶ የተዋለደው መከባበር በሚባለው ትልቁ እሴቱ ነው፡፡ ይህ እሴት ደግሞ ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ተፋቅረውና ተሳስበው እንዲኖሩ ረድቷቸዋል፡፡ ለዘመናት ወራሪዎችን በጀግንነት እያሳፈሩ የዘለቁትም በዚህ ፅኑ እሴት ነው፡፡ አገር የሚመሩ ሰዎች በየደረጃው ባሉ ሹማምንት ካልተከበሩ፣ የጦር መሪዎች በዕዝ ጠገጉ መሠረት ካልተከበሩ፣ ምሁራንና የአገር ሽማግሌዎች በዜጎች ካልተከበሩ፣ ዜጎችም እርስ በርሳቸው ካልተከባበሩ አዲሱ ትውልድ ምን ይወርሳል? በተለይ በርካታ ጥያቄዎች እየተነሱ ባሉበት በዚህ አሰሳቢ ጊዜ አገርን መታደግ የሚቻለው መከባበር ትልቅ ሥፍራ ሲሰጠው ነው፡፡ በአጉል ዕብሪት ውስጥ ተጀቡኖ መናናቅ ትርፉ ውድቀት ነው፡፡ ዕብሪት ውድቀትን ከማፋጠን ውጪ ለማንም ምንም አይፈይድም፡፡ ከምንም ነገር በላይ ደግሞ ሕዝብን አለማክበር የጥፋቶች ሁሉ ጥፋት ነው፡፡ ለዚህም ነው መንግሥት የሚከበረው ሕዝብን አክብሮ ሲያስከብር ነው የሚባለው!

ethiopianreporter