Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

መንግስትና ገበያውን የማረጋጋት ጥረቱ

0 300

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

መንግስትና ገበያውን የማረጋጋት ጥረቱ

                                                        ደስታ ኃይሉ

መንግስት ገበያው እንዲረጋጋ ጥረት እያደረገ ነው።  የዋጋ ንረት የህዝቡን ኑሮ እንዳይጎዳ ለመከላከል ህጋዊ እርምጃዎችን ከመውሰድና በገበያው ላይ በእጥረትነት የሚታዩ ሸቀጦችን ከማቅረብ ባሻገር የማስተማር አቅጣጫንም እየተከተለ ነው።

በዚህም ነጋዴው ህብረተሰብ ህዝብን ከመጉዳት አስተሳሰብ መራቅ እንዳለበት፣ ትኩረቱን በፍትሃዊ ትርፍ ማግኘት ላይ እንዲያደርግ የትምህርት አቅጣጫዎችን ቀይሶ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል። በዚህም አገራችን ውስጥ በየትኛውም ዘርፍ የህግ የበላይነት ለድርድር እንዳይቀርብ የማድረግ ስራዎችን እያከናወነ ነው።

መንግስት የውጭ ምንዛሬ ተመን ማሻሻያውን ተከትሎ ሊፈጠሩ የሚችሉ የዋጋ መናር ስጋቶችን ለመከላከል አስቀድሞ ተዘጋጅቷል። በዚህ መሰረትም መንግስት ከምንዛሬ ተመን ማሻሻያው ጋር በተያያዘ ምንም ዓይነት የነዳጅና የትራንስፖርት ዋጋ ጭማሪ እንዳይከሰት እንደሚደረግ ገልጿል።

ከመሰረታዊ ፍጆታ እቃዎችና ሸቀጦች ስርጭት አኳያም መንግስት ስንዴን፣ ዘይትንና ስኳርን ጨምሮ እና የዋጋ ንረት እና እጥረት እንዳይከሰት የዋጋ ቁጥጥር ማድረግ ጀምሯል። የምንዛሬ ማሻሻያውን ተከትሎ ምንም ዓይነት የኤሌክትሪክና የውሃ ታሪፍ ጭማሪም አይደረግም።

አገሪቱ ለድርቅ ያልተጋለጠችበትና ከፍተኛ የመኸር ሰብል ምርት በሚገኝበት ጊዜ በመሆኑ በገበያው ያለውን የምርት መጠን እንዳይጓደል እና የእህል ዋጋ ንረት እንዳይኖር የሚያደርግ ነው።

እንደሚታወቀው ሁሉ የኢትዮጵያ መንግስት ለህዝቡ የሚቆረቆር ነው። የኢትዮጵያ መንግስት ድህነትን ለመቅረፍ ብሎም ለማጥፋትና የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር መንግስት ዘርፈ ብዙ የሆኑ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተግባራትን አከናውኗል፤ በማከናወን ላይም ይገኛል። እነዚህ ተግባራትም ውጤታማነታቸውን በገሃድ ባስመሰከሩ ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎችና ፕሮግራሞች የተመሩ በመሆናቸው፤ በመላው ሀገሪቱ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት ችለዋል፡፡

በተለይም ካለፉት አስር ዓመታት ጀምሮ፣ ለዚያውም የዓለም ኢኮኖሚና የፋይናንስ እንቅስቃሴ ችግር ላይ በነበረበት ወቅት ጭምር ኢትዮጵያ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ መቻሏን ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅትና ሌሎች ተቋማት ጭምር የመስከሩት ሃቅ ነው፡፡

የተገኘው ኢኮኖሚያዊ ዕድገትም ሁሉንም የሀገሪቱን ዜጋ በየደረጃው ተጠቃሚ ያደረገ መሆኑን ከኢትዮጵያ ህዝብ በላይ ማንም ሊመሰክር አይችልም፡፡ ለምን ቢባል የችግሩ ባለቤትም ይሁን የምፍትሔው አካል እርሱው ስለሆነ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ሀገርን በማሳደግ ህዝብን ከድህነት ለማላቀቅ የሚያደርገው ሰፊ ርብርብ ለደቂቃ ሳይዘናጋ ወደ ፊት እየገሰገሰ ይገኛል፡፡

በመሆኑም እያስመዘገበው ባለው ፈጣን፣ ቀጣይና ተከታታይ የኢኮኖሚ ዕድገትን ተከትሎ፣ ቀደም ባሉት ዓመታት ተከስተው የነበሩ የዋጋ ንረቶችን ለመቆጣጠር የተከተለው አቅጣጫ የሀገራችን የልማት እንቅስቃሴ ሳይደናቀፍ እንዲቀጥል ያደረገ ነው።

ይህ ሃቅም ልማታዊውና ዴሞክራሲያዊው መንግስት ገቢራዊ ያደረጋቸው ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎችና ፕሮግራሞች ምን ያህል ትክክለኛ መሆናቸውን የሚያረጋጥ ነው፡፡ እናም በዚህ ፅሑፍ ይህን የመንግስትን ውጤታማ የዋጋ ንረትን ቁጥጥር ርምጃን ለውድ አንባቢዎቼ ለማመላከት እሞክራለሁ። አብረን እንዝለቅ።…

መንግስት ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በገበያው ላይ የተፈጠረውን የዋጋ ንረት በሀገራችን ልማት ቀጣይነት ላይ የራሱን የሆነ ተፅዕኖ እንዳይፈጥር ፈጣን ምላሽ መስጠት መቻሉን ሁላችንም የምናስታውሰው ዕውነታ ነው፡፡

ባለፉት ዓመታት ወሳኝ የልማት ትግል በመካሄድ ላይ ከሚገኝባቸው መስኮች አንዱ የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነትን ለመቆጣጠር ያደረገውንና አሁንም እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ የምንዘነጋው አይደለም፡፡ በተለያዩ ጊዜያት እንደተገለፀው የተፈጠረውን የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት ለመቆጣጠር ያስችላሉ ተብለው የታመነባቸው እርምጃዎች ተጨባጭ ለውጥ ያሳዩ ናቸው፡፡  

እንደሚታወቀው ሁሉ ሀገራችን በተመረጠ ሁኔታ የመንግስት ጣልቃ ገብነት ባለበት የነጻ ገበያ ሥርዓት መመራት ከጀመረች ከ26 ዓመታት በላይ ዕድሜን አስቆጥራለች፡፡ ይህም በሀገር ውስጥ ፈጣን፣ ዘላቂ፣ ተወዳዳሪና ከተጽዕኖ የፀዳ የንግድ ሥርዓት እንዲሰፍን ያስቻለ ነው፡፡ የገበያ ስርዓቱ ሸማቹም ሆነ አምራቹ ያለምንም ጣልቃ ገብነት የንግድ ልውውጡን እንዲያካሄድ ሙሉ ነጻነት የሰጠ ከመሆኑም ባሻገር፤ ልማታዊ ባለሀብት በጥራትና በብዛት እንዲፈጠርም የማይተካ ሚና ተጫውቷል፤ በመጫወት ላይም ይገኛል፡፡

እርግጥ መንግስት የነፃ ገበያ ሥርዓቱን ከመዘርጋት ጀምሮ ስር እንዲሰድ በማድረግ በኩል የአንበሳውን ድርሻ ይዞ ችግሩን በቁርጠኝነት እየተወጣ ይገኛል፡፡ እንደሚታወቀው ሁሉ ለዋጋ ንረትና ለኑሮ ውድነት ምክንያት ሊሆኑ ችለው ከነበሩት ጉዳዮች አንዱ ሀገራዊ መሰረት የነበራቸው ምርቶች ላይ ተንተርሶ የተፈጠረው የገበያ ዋጋ መናር ክስተት ነበር፡፡

በተለይም ከአምስት ዓመታት በፊት የሀገራችን የግብርና ምርቶች በከፍተኛ መጠን እያደጉ በነበሩበት ወቅት በከተሞች ውስጥ ምርቶች ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ አሳይተው እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡

እርግጥ የህብረተሰቡ ገቢ እየጨመረ በሄደ ቁጥር ለመሰረታዊ ሸቀጦች ያለው ፍላጎት አብሮ ሊጨምር መቻሉ ነባራዊ ዕውነት ነው። የግብርና ምርት አቅርቦት በእጅጉ አድጎ በነበረበት በዚያ ወቅት የሸቀጦች ፍላጎት አብሮ በማደጉ ምክንያት ዋጋው ከተገመተው በላይ በላቀ ደረጃና ፍጥነት ሊጨምር መቻሉ አይካድም፡፡

እርግጥም ባለፉት ዓመታት ለታየው የዋጋ ንረት አንዱ ምንጭ የእህል ዋጋ ያለማቋረጥ መጨመር ነበር፡፡ ይህ ሁኔታ የተፈጠረው ለገበያው የሚቀርበው ትርፍ ምርት ኢኮኖሚው በሚፈልገው ልክ አለማደጉን ተከትሎ እንዲሁም የገበያው ተዋንያን የእህል ዋጋ እንዲጨምር ለማድረግና ይጨምራል ከሚለው ግምት በመነሳት የሚያቀርቡትን መጠን መቀነሳቸው ብሎም ዋጋውን በቀጣይነት በመጨመራቸው ነው፡፡

አንድን ምርት ከአምራቹ ወደ ተጠቃሚው ለማድረስ በርካታ የግብይት ሰንሰለቶችን ማለፉ የግድ በመሆኑ፤ እነዚህ ሰንሰለቶች በየምዕራፉ ተገቢ ያልሆነ ወጪን ማስከተላቸውና ይህም በሸቀጦች የመሸጫ ዋጋ ላይ የሚንጸባረቅበት ሁኔታ እንዲከሰት ማድረጉን እናስታውሳለን፡፡

በልማት መፍጠን ምክንያት ሊመጡ የሚችሉ የፍላጎቶችም ሆኑ የዋጋ ጭማሪዎች ሊገቱ የሚችሉት በዘላቂነት ልማቱን በማፋጠን መሆኑ ይታመናል፡፡ በመሆኑም መንግስት ይህን ሃቅ በጥልቀት ተገንዝቦ ለተፈጠረው የገበያ አለመረጋጋት ዘላቂ መፍትሄ ሊሰጡ የሚችሉ የልማት ስራዎችን አከናውኗል፤ በማከናወን ላይም ይገኛል፡፡ ዛሬም በተፈጠረው የዶላር ምንዛሬ ጭማሪ ሳቢያ አነስተኛ ገቢ ባላቸው ዜጎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ መንግስት ተግቶ የሚሰራ ይሆናል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy