NEWS

ሙስና የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣንንም ግብር ከፋዩንም እንዳስመረረ ነው

By Admin

November 25, 2017

በሀገሪቱ የከፍተኛ ግብር ከፋዮች 1 ሺህ 145 ብቻ ሲሆኑ፥ በቁጥር አነስተኛ የሆኑት እነዚህ ግብር ከፋዮች የሀገር ዉስጥ ግብር ሽፋንን ከ60 በመቶ በላይ እንደሚይዙ ይነገራል።

ባለስልጣኑ ዛሬ 300 ከሚሆኑ ከፍተኛ ግብር ከፋዮች እና የሙያ ማህበራት ጋር በ2009 በጀት አመት ታቅደዉ በተፈቱ እና በ2010 እንዱፈቱ በታቀዱ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ላይ ዉይይት አድርጓል።

በውይይቱም ባለስለጣኑ ባለፈው በጀት አመት የነበሩትን ክፍተቶች ለመሙላት ያከናወናቸውን ስራዎች እንስቷል።

ከጉሙሩክ ዋጋ ትመና እና ፍትሃዊነት ጋር በተያያዘ የነበረዉ የመልካም አስተዳደር ችግር፣ የቀን ገቢ ግመታ ፍታሃዊነት እና የታክስ ኦዲት አወሳሰን በ2009 አመተ ምህረት ዋነኛ ችግሮች ነበሩ ተብሏል።

ግብር ከፋዮቹ ባለስልጣኑ በአጠቃላይ አሰራሩን መፈተሽ አለበት ባይ ናቸው።

ከፍተኛ ግብር ከፋዮች ሙስና እና የመልካም አስተዳድር ችግር መክፋቱን በማንሳት፥ “ቅሬታዎችን ይዘን ወደ ባለስልጣኑ ብናመራም ችግራችንን የሚፈቱልን አካላት የውሳኔ አሰጣጥ ላይ ክፍተቶች አሉባቸው” ነው የሚሉት።

በተደጋጋሚ እንዲህ ያሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች በባለስልጣኑ ላይ ሲነሱ ቆይተዋልና ይህን እንዴት መፍታት አልተቻለም ሲል ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ባለስልጣኑን ጠይቋል።

የባለስልጣኑ የደንበኞች አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ዮሴፍ ሽፈራው የመልካም አስተዳደር ችግርን በአንድ ጀንበር መፍታት አይቻልም ይላሉ።

በግብር አከፋፈል ላይ የሚቀረቡ ቅሬታዎች አፈታት አሁን ላይ 70 በመቶ መድረሱን የሚናገሩት ዳይሬከተሩ፥ 90 በመቶ ለማደረስ እየተሰራ ነዉ ብለዋል።

አሁን ላይ ባለስልጣኑ ደንበኞችን ለእንግልት እና ለተጨማሪ ወጪ የሚደርጉ አሰራሮችን እየፈተሸ መሆኑን ዳይሬክተሩ አንስተዋል።

ባለፈዉ በጀት አመት በሙስና የተጠረጠሩ የባለስልጣኑ 69 ሰራተኞች ከስራ እንዲባረሩ በማድረግ በህግ እንዲጠይቁ ተደርጓል።

አሁን ላይ ባለስልጣኑ የውስጥ እና የዉጭ ችግሮችን በማየት በዚህ ዓመት ከከፍተኛ ግብር ከፋዩ ጋር አብሮ ሊያሰሩ የሚችሉ እቅዶች ወጥተዋል ነዉ ያሉት ዳይሬክተሩ።

አቶ ዮሴፍ በከፍተኛ ግብር ከፋዩ በኩል ያሉ ችገሮችንም አንስተዋል።

አሁንም የጉሙሩክ ኬላዎች ላይ መደራደር፣ የግብር እፎይታ እና ከቀረጥ ነፃ የሚገቡ እቃዎች ለሌላ አላማ ማዋል የሚሉትን ዘርዝረዋል።

የሽያጭ መመዝገቢያ አጠቃቀምና ካለደረሰኝ ግብይት መፈፅምም የሚሉት አሁንም በእነዚህ ግብር ከፋዮች ዘንድ ችግር ሆነው መቀጠላቸውን ነው የገለፁት።

ዘንድሮ በመጀመሪያዉ ሩብ ዓመት ብቻ ካለደረሰኝ ሲገበያዩ የተገኙ 90 ድርጅቶች መኖራቸዉን እና ከዚህ ጋር ተያይዞ ከ131 ግለሰቦች በፍታብሄር እና በወንጀል እንዲጠየቁ መደረጋቸውን ለችግሮቹ መኖር እና ለተወሰደው እርምጃ ማሳያ ብለው አንስተዋል።

አቶ ዮሴፍ አሁንም ባለስልጣኑ ካለደረሰኝ ግብይት የሚፈፅሙ አካላትን ለህግ የማቅረቡ ስራ ይቀጥላል ነዉ ያሉት።

ከፍተኛ ግብር ከፋዮችን የሚያስተናግዱ የኦዲት ባለሙያዎች አነስተኛ መሆናቸዉ በመድረኩ ተነስቷል።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሞገስ ባልቻ መስሪያ ቤታቸው ልምድ ያላቸዉ የታክስ ኦዲተሮች ከስራ እንደሚለቁበት እና እነሱን የመተካቱ ሂደት ረዥም ጊዜ እንደሚወስድ በማንሳት፥ አሁን ላይ ግን ችግሩ እየተቀረፈ መሆኑን በምላሻቸው ጠቅሰዋል።

ከታክስ ኦዲት ፍትሃዊነት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችም ከሁለቱ አካላት በኩል ሀላፊነት ካለመወጣት የሚመነጩ ናቸው ብለዋል ዋና ዳይሬክተሩ።

ባለሰልጣኑ የግብር ስርዓት የለዉጥ እቅድ አውጥቶ ወደ ስራ በመግባቱ አጠቃላይ አሳረሩ ላይ ማሻሻያዎች እየታዩ መሆኑን ተናግረዋል።

ባለስልጣኑ ከከፍተኛ ግብር ከፋዮች ጋር ያደረገዉን ውይይት በተመሳሳይ በየደረጃው ከሚገኙ ግብር ከፋዮች ጋር እንደሚያደርግ በዚሁ ወቅት አስታውቀዋል።