Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ማስጠንቀቂያም ሆነ ማስፈራሪያ አይሰማንም!

0 548

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ማስጠንቀቂያም ሆነ ማስፈራሪያ አይሰማንም!

አባ መላኩ

ግብጻዊያን  አሰዋን  ግድብ  ከውሃ  ማጠራቀሚያነቱ  ባሻገር ተጨማሪ ትርጉም እንደሚሰጡት ሁሉ፣ ታላቁ  የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብም  ለእኛ ኢትዮጵያዊያኖች ከኤኮኖሚያዊ ጠቀመሜታው  ባሻገር የሚያስተላልፈው  ምልዕክት እንዳለ መታወቅ ይኖርበታል።  ታላቁ  የህዳ ግድባችን   ለእኛ ኢትዮጵያዊያን “ይይቻላል መንፈስን የፈጠረ”፣ እንደአድዋ ጦርነት ሁሉ ዜጎችን በአንድ መንፈስ በማሰበሰብ ዳግም ጥቁርና ደሃ  ህዝቦች የፈለጉትን ማድረግ እንደሚችሉ ያስመሰከርንበት፣  ተለያይተዋል ለሚሉን ጠላቶቻችን አንድነታችንን ያሳየንበት  ፕሮጀክት ነው። የአሰዋን ግድብ  ለግብጻዊያን  የብሄራዊ  ኩራታቸው  የአንድነታው  መገለጫ  እንዲሆን   በየሚዲያዎቻቸው እንደሚገልጹት  ሁሉ ታላቁ የህዳሴ ግድብም ለእኛ  ኢትዮጵያዊያን  ተመሳሳይ ትርጉም ያለው በመሆኑ ማንም ሊያስቆመው  እንደማይችል  ሊታወቅ  ይገባል።  ለፕሮጀክቱ  ስኬታማነት  በማንኛውም ረገድ  ከመንግስታችን  ጎን  እንደምንሰለፍ እኛ እትዮጵያዊያኖች ደግመን ደጋግመን  ገልጸናል።

 

ባሳለፍነው  ሳምንት መገባደጃ ላይ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ በካይሮ የተካሄደው የኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን የውሃ ሚኒስትሮች ስብሰባ ያለውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ አንዳንድ  መገናኛ ብዙሃን ግብጽ ኢትዮጵያን አስጠነቀቀች  በማለት  ሲዘግቡ ተመልክተናል። የህዳሴው ግድብ በብድር ወይም በእርዳታ የሚካሄድ ፕሮጀክት ባለመሆኑ ኢትዮጵያን ማንም ሊያስጠነቅቃትም ሆነ ሊያስፈራራት አይቻለውም። ከኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት የሚጠበቀው ወሰን ተሻጋሪን ወንዞችን  በዓለም ዓቀፉ መርህ መሰረት ለመጠቀም የሚያስችለውን መንገድ መከተላል  ብቻ ነው። የኢፌዴሪ መንግስት ህዝባዊ መንግስት ነው። የአባይን ውሃ አጠቃቀምን በተመለከተም እየተገበረ ያለው መርህም  ውሃውን እኩል እኩል እንጠቀም የሚል መርህን ሳይሆን “ፍትሃዊ ተቃሚነት” የሚል  ነው።    

 

የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችንን በቅርቡ  በኳታር  ያደረጉትን  ጉብኝትን ተከትሎ በርካታ በአረብኛ ቋንቋ የሚሰራጩ መገናኛ ብዙሃን የህዳሴ ግድብን ኳታር ትደግፋለች የሚሉ ዘገባዎችን ይዘው ወጥተው ነበር።  ይሁንና  አቶ ኃ/ማርያም ግድቡን በተመለከተ የሰጡት ምላሽ እጅግ አስደስቶኛል።  “የህዳሴው ግድብ  ያለማንም ድጋፍ በኢትዮጵያውያን ወጪ ብቻ  የሚገነባ ፕሮጀክት ነው” ይህ የሚያመላክተው ማንም ቢደግፈውም ሆነ ቢቃወመው የሚያመጣው ነገር የለም የሚል እድምታን ያለው ነው።

የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ እንዳሉት ለግብጻዊያን ውሃ የሞትና የህይወት ጉዳይ በመሆኑ  ግብጽ በአባይ ወንዝ ላይ ያላትን የውኃ ድርሻ ማንም ሊነካባት አይችልም ሲሉ መናገራቸውን በርካታ በግብጽ ሚዲያዎች ዘግበውታል። እውነት ነው ውሃ ለግብጻዊያኖች  ብቻ ሳይሆን ለመላው የዓለም ህዝብ ህይወት ነው። ይሁንና ይህ አባባል ፍትሃዊነት የጎደለው ይመስለኛል። ይህን ግድብ ኢትዮጵያ ለሃይል ማመንጫነት እንጂ ለመስኖ ልትጠቀምበት እንደማትችል በርካታ ዋቢዎችን አጣቅሳ አገራችን  ለተፋሰሱ አገራት ብቻ ሳይሆን ለዓለም አሳውቃለች። መስማት ካልፈለጉ እንጂ ኢትዮጵያ ሁኔታዎችን በአግባብ አሳውቃለች።

ግብጻዊያን እየፈለጉ ያሉት  በአባይ ወንዝ ላይ  ግብጽ የነበራት የቅኝ ግዛት ስምምነት አሁንም  ተግባራዊ እንዲሆን ነው። ይህ ነው ኢፍትሃዊነት እና አንባገነንነት ነው። የህዳሴውን ግድብ በተመለከተ ኢትዮጵያ ከተፋሰሱ አገራት ህዝቦችን  ሊያቀራርብና  ሊያስማማት  የሚችሉትን  ነገሮች ሁሉ   ተግብራለች።  እውነት እንነጋገር ከተባለ አገራችን  ግብጻዊያንን ለማገባባት ከግማሽ መንገድ በላይ ተጉዛለች። ግብጻዊያን ግን ከቆሙበት የተንቀሳቀሱ አይመስለኝም።  የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የተፅዕኖ ግምገማ፣ የውኃ ሙሌትና አለቃቀቅ ላይ ጥናት ቢደረግም፣ ግብፅ የቅኝ ግዛት ዘመኑን እ.ኤ.አ. የ1959 ስምምነት  በማጣቀስ   ይህ ስምምነት ተግባራዊ ካልሆነ በማለት  አሁንም የሙጥኝ እንዳለች ነው።  

 

አንዳንድ የግብጽ ፖለቲከኞችና ምሁራን እኛ ኢትዮጵያዊያኖች  የህዳሴው ግድብ  በጠብታ ደማችን እየገነባን ያለ ፕሮጀክት መሆኑን በአግባቡ የተረዱት አይመስለኝም።  የግድቡ ግንባታ እየተጠናቀቀ በመሆኑ ከዚህ በኋላ ስለግድቡ  አስፈላጊነት  ማውራት የረፈደበት አስተሳሰብ ይመስለኛል። አሁን መከተል የሚገባው ስለውሃ  አሞላልና አለቃቀቅ ድርድር ማድረግ  እንጂ ስለአረጁና አፈጁ ውሎች ማውራት አይመስለኝም።  የኢፌዴሪ መንግስት የዲፕሎማሲ  የበላይነቱን  ካሳየባቸው ነገሮች አንዱ  ታላቁ  የህዳሴውን ግድብ  ድርድር ስኬት  እንደሆነ  ይሰማኛል።  የታላቁ የህዳሴ ግድብን  በተመለከተ  የኢፌዴሪ መንግስት ከቀድሞ  ጀምሮ የሚያራምደው  ፍትሃዊ  የውሃ ክፍፍል መርህ  መንግስታችን በዓለም ዓቀፍ መድረኮች ሁሉ በአሸናፊነት እንዲወጣ አድርጎታል።  በመጪው ታህሳስ  በመሪዎች ደረጃ በግብፅ ካይሮ የሚካሄደው ድርድር መፍትሄ የሚያመጣ ይሆናል። ይሁንና ግብጻዊያኖች ራሳቸውን ሊያዩ ይገባል። ድርድር ሰጥቶ መቀበል ማለት እንጂ ግትር ሃሳብ ይዞ የእኔ ብቻ ነው ትክክል ማለት አይደለም።

 

ሱዳናዊያኖች  ከኢትዮጵያ ጎን ተሰልፈው የታላቁን የህዳሴ ግድብ  ፕሮጀክት የደገፉት ኢትዮጵያን ስለወደዷት ሳይሆን እውነታውን መርምረው  የፕሮጀክቱን ጠቃሚነት በመረዳታቸው  ነው። ሱዳንም ሆነች ግብጽ   ከህዳሴው ግድብ ዋንኛዋ ተጠቃሚ አገራት ናቸው።  ምክንያቱም ይህ ፕሮጀክት ስራ ሲጀምር   እነዚህ አገራት በተመጣጣኝ ክፍያ  የኤሌክትሪክ ሃይል ተጠቃሚ ይሆናሉ፣  ዓመቱን ሙሉ ተመጣጣኝ ውሃ ፍሰት ከማግኘታቸውም ባሻገር ከደለል  ይታደጋሉ። ከሁሉም በላይ ደግሞ የወንዙ ቀጣይ ህይወት አስተማማኝ ይሆናል። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ግድቧን  ከደለል ለመታደግ ስትል በርካታ የአካባቢ ልማት ስራዎችን በመስራት ላይ በመሆኗ የወንዙ ቀጣይ ህይወት አስተማማኝ ይሆናል። የአባይ ውሃ ፍሰት ከመቶ አመታት ወዲህ እጅጉን የቀነሰበት ወቅት ቢኖር ባለፉት ጥቂት ዓመታት እንደሆነ ጥናቶች ያመላክታሉ። ለዚህ ዋንኛ ምክንያቱ  ድግሞ አብዛኛው ውሃ የሚመነጭባት  ኢትዮጵያ  ደኖች  በመመንጠራቸው  ሳቢያ  በረሃነት በመስፋፋቱ ነው።

አንዳንድ የግብጽ ሚዲያዎች  ግብጽ ጉዳዩን ለተባበሩት መንግስታት ዓለም አቀፍ የሽምግልና ወይም የድርድር  መድረክ ልትወስደው ትችላለች ሲሉ ዘግበዋል።  ይህ ለአገራችን ትልቅ ድል ይመስለኛል።  ምክንያቱም ኢትዮጵያ እየተከተለች ያለችው  ፍትሃዊ መርህ  በዓለም ዓቀፉ ምድረክ  የሚያስመሰግናት  እንጂ የሚያስወቅሳት  የሚችል ባለመሆኑ ነው። አንዳንድ ግብጻዊያን ስለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በቂ መረጃ ያላቸው አይመስለኝም። ምክንያቱም የሚሰጧቸው አስተያየቶች እጅግ ይወርዱብኛል። ለአብነት ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የግንባታ ወጪው ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያዊያኖች የሚሸፈን ሆኖ ሳለ ፕሮጀክቱን እከሌ የተባለአገር ሊደግፈው ነው፣ እከሌ ደገፈው በማለት ሶስተኛ አካልን  በግድቡ ዙሪያ ለማስገባት ጥረት ሲያደርጉ ተመልክተናል ። በቅርቡ እንኳን  ጠቅላይ ሚኒስትራችን ኳታርን በመጎብኘታቸው አንዳንድ ግብጻዊያንን አላስደሰታቸውም። Al-Bashaer  የተሰኘ የግብጽ ሚዲያ  ኳታር የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን በመርዳት የግብጽን የውኃ መጠን ለመቀነስ ወጥናለች ሲሉ የግብጽ የተወካዮች ምክር ቤት አባል ሜጀር ጄነራል Mahmoud Mohieldin፣ መግለጻቸውን አግባብነት የጎደለው አስተያየት ይመስለኛል። እኚሁ ግለሰብ  የኳታር እና የአትዮጵያ ግንኙነት ለእኛ ትልቅ ጉዳያችን በመሆኑ በቅርበት ልንከታተለው ይገባል ብለዋል። ኢትዮጵያ ከኳታር ጋር የሚያገናኛት እጅግ በርካታ ጉዳዮች እንዳሏት መገንዘብ ተገቢ ነው።

 

ኢትዮጵያ ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ከማንም ዕርዳታም ይሁን ብድር ጠይቃም አታውቅም። ታላቁ የህዳሴ ግድብ በውጭ አካል የገንዘብም ይሁን የቁሳቁስ እርዳታ ያልተደረገበት በኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ   አንጡራ ሃብት ብቻ  የሚገነባ  አገራዊ ፕሮጀክት ነው። ለዚህ ነው፤ የታላቁ  የኢትዮጵያ ህዳሴው ግድብ  ለእኛ ኢትዮጵያዊያኖች ከኤኮኖሚያዊ ጠቀመሜታው  ባሻገር   የአንድነታችንና  የአብሮነታችን  ማሳያ  ነው የምንለው።  የአሰዋን ግድብ  ለግብጻዊያን  የብሄራዊ  ኩራታቸው  የአንድነታቸው  መገለጫ  እንደሆነ   በየሚዲያዎቻቸው እንደሚገልጹት  ሁሉ ታላቁ የህዳሴ ግድብም፣ ለእኛ ኢትዮጵያዊያኖች  በተመሳሳይ ትርጉም ያለው ፕሮጀክት ነው። ለፕሮጀክቱ  ስኬታማነት ሁሉም አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ በሚያስፈልገው  ነገር ሁሉ    ከመንግስታችን  ጎን  እንደምንሰለፍ  ሊታወቅ ይገባል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy