ሜቴክ የያዛቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶች መጓተት የፈጠረው ውዝግብ
- ‹‹አሻጥሮች እየተፈጸሙብኝ ነው›› ሜቴክ
- ‹‹ይህንን መስማት ያማል›› ስኳር ኮርፖሬሽን
- ‹‹ሕዝቡም እምነት እያጣ ነው እኛም ወደ መሰልቸት ደርሰናል›› የፓርላማ አባል
የኢትየጵያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) የያዛቸው ግዙፍ የስርኳና የማዳበሪያ ፋብሪካዎች ግንባታ መጓተት ላለፉት ዓመታት ሲፈጥር የነበረው ውዝግብ አሁንም መፈታት ባለመቻሉ፣ የፕሮጀክቶቹ ባለቤቶች በሆኑት የመንግሥት ተቋማትና በሜቴክ መካከል ውዝግቡ በድጋሚ ባለፈው ሳምንትም ተደምጧል፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሜቴክን የ2010 በጀት ዓመት ዕቅድና አንደኛ ሩብ ዓመት አፈጻጸም ረቡዕ ኅዳር 6 ቀን 2010 ዓ.ም. በገመገመበት ወቅት፣ ከዚህ ቀደም ሲያደርግ ከነበረው በተለየ መንገድ ሜቴክ የያዛቸው ፕሮጀክቶች ባለቤቶች የሆኑት የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽንና የኢትዮጵያ ኬሚካል ኮርፖሬሽን ከፍተኛ አመራሮችንም በዚሁ ስብሰባ ላይ እንዲገኙ አድርጓል፡፡ የ2010 ዓ.ም. ዝርዝር የሥራ ዕቅዳቸውንና የሩብ ዓመት አፈጻጸማቸውን የሜቴክ ከፍተኛ አመራሮች ሪፖርት ቢያደርጉም፣ የዋነኞቹ የስኳር ፕሮጀክቶች አፈጻጸም የቋሚ ኮሚቴውን አባላት አላስደሰተም፡፡ በመሆኑም በርካታ ጥያቄዎችን በኮሚቴ ደረጃ አቅርበዋል፡፡
‹‹የአሞ ኩራዝ ቁጥር አንድ ፕሮጀክት በ2009 ዓ.ም. ጥር ወር እንደሚጠናቀቅ በተለያዩ ጊዜ ለኮሚቴውና ለሚዲያ በይፋ ቢገለጽም፣ በተጨባጭ ግን በተባለው ወቅት ሳይጠናቀቅ ቀርቷል፡፡ እንደዚሁም ለፕሮጀክቱ ባለቤት ለመንግሥት ልማት ድርጅቶች ሚኒስቴርና ለእኛ ቋሚ ኮሚቴ በሰኔ ወር 2009 ዓ.ም. በጻፋችሁት ደብዳቤ፣ የኦሞ ቁጥር አንድ ስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክት ተከላ፣ የሙከራና የኮሚሽኒንግ ሥራ ተጠናቆ የምርት ሙከራ በስኬት ስለተጠናቀቀ ፋብሪካውን እንድትረከቡን እንጠይቃለን ብላችሁ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም ፕሮጀክቱ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ወደ ምርት መግባት አልቻለም፡፡ ምንድነው ችግሩ? በዚህ ዓመትስ ይጠናቀቃል?›› የሚል ጥያቄ በቋሚ ኮሚቴው ቀርቧል፡፡
የበለስ አንድ ስኳር ፋብሪካ ግንባታም በ2009 ዓ.ም. እንዲጠናቀቅ በዕቅድ ቢያዝም ወደ መጠናቀቂያው እንኳን እንዳልደረሰ፣ በዚህም የተነሳ ለፋብሪካው ግብዓት የሚሆን በብዙ ሺሕ ሔክታር ላይ ያረፈ የሸንኮራ አገዳ አርጅቶ በበርካታ ሚሊዮኖች ብር ወጪ እንዲሆን መደረጉን በመግለጽ፣ በ2010 ዓ.ም. መጨረሻ እንደሚጠናቀቅ ማረጋገጫ ትሰጣላችሁ ወይ? የሚል ጥያቄም በኮሚቴው ተነስቷል፡፡ የያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካን በ2010 ዓ.ም. ለማጠናቀቅ በመንግሥት በተቀመጠው ዕቅድ መሠረት በየወሩ ከሦስት እስከ አራት በመቶ ለማከናወን በ2009 መጨረሻ አካባቢ ሜቴክ ቢስማማም፣ እስከ ጥቅምት ወር 2010 መጨረሻ ድረስ ፋብሪካው በ2009 ሰኔ ወር ከነበረበት 43.3 በመቶ ከፍ ማለት የቻለው 0.28 በመቶ ብቻ እንደሆነ ተገልጾ ይህንን ፕሮጀክት ወደፊት እንዲያብራሩ ጥያቄ ቀርቧል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የሜቴክ የፋይናንስ አፈጻጸም ጤናማ ነው ወይ? በጥናት ላይ ተመሥርቶ ገበያ ተኮር የሆኑ ምርቶችን በጥራት አምርቶ ባለመቅረቡ ከፍተኛ የትራክተር ምርቶች ክምችትና ሌሎችም መኖራቸውን በማንሳት፣ ይህ ባለንበት ጤናማ የፋይናንስ ሥርዓት በሜቴክ ውስጥ ሊኖር ይችላል ወይ? የሚል ጥያቄም ቀርቧል፡፡
በተደጋጋሚ ጊዜ ከፕሮጀክቶቹ ባለቤቶች ጋር ሜቴክ እንደማይግባባና የችግሮች መነሻ ራሱ ሊሆን ይችላል ብሎ ወደ ውስጥ ከማየት ይልቅ፣ በሌሎች የውጭ ምክንያቶች አመራሩ የሚያሳስበው ለምን እንደሆነ ማብራሪያ እንዲሰጥበት ኮሚቴው ጠይቋል፡፡
ለጥያቄዎቹ ምላሽ መስጠት የጀመሩት የሜቴክ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ብርጋዴር ጄኔራል ጥጋቡ ፈትለ ናቸው፡፡ የፕሮጀክቱን መዘግየት አምነው በሰጡት ጥቅል አስተያየት፣ ‹‹እየሠራን፣ እየተማርን፣ እየተማማርን ስለምንሠራ የፕሮጀክቶች መዘግየት ይታያል፤›› ብለዋል፡፡ በመሆኑም ሜቴክ ውስጣዊ የአቅም ችግር እንዳለበትና ይህንንም ለመፍታት በጥረት ላይ መሆኑን ገልጸው፣ ነገር ግን ውጪያዊ ችግሮቹ የኮርፖሬሽኑን ጥረቶች የሚያሰናክሉ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ኦሞ ኩራዝ ቁጥር አንድ ፋብሪካ በአሁኑ ወቅት በቀን ስድስት ሺሕ ቶን ወይም የሙሉ አቅሙን አጋማሽ አገዳ የመፍጨትና ስኳር የማምረት የሚችል በመሆኑ፣ ስኳር ኮርፖሬሽን የዚህን ፋብሪካ ግማሽ አቅም እንዲረከብና ስኳር እየተመረተ ቀሪው የማጠናቀቅ ሥራ እንደሚከናወን ሜቴክ ጥያቄ አቅርቦ ውሳኔ እየተጠባበቀ መሆኑን፣ አሁንም ቢሆን እስከ ታኅሳስ ወር መጨረሻ ርክክብ ይካሄዳል ተብሎ እንደሚጠበቅ ብርጋዴር ጄኔራሉ ገልጸዋል፡፡
ይህ ፋብሪካ ግማሽ አቅሙን ቀደም ብሎ ወደ ሥራ ማስገባት የሚቻል ቢሆንም፣ ፋብሪካውን ለመሞከር ሸንኮራ አገዳ ስኳር ኮርፖሬሽን ተጠይቆ ከልክሎ እንደነበር፣ በኋላ ግን በመንግሥት ውሳኔ መፈቀዱን የጠቆሙት ብርጋዴር ጄኔራል ጥጋቡ፣ የተፈቀደውን ሸንኮራ አገዳ ሆነ ብለው ከድንጋይ ጋር ቀላቅለው በመላካቸው ሸንኮራ የሚፈጩ ማሽኖች መሰባበራቸውን ተናግረዋል፡፡ ‹‹የማሽኖቹን የመፍጨት ሥራ አስቁመን ቀሪውን የሸንኮራ አገዳ በጫኑ ተሽከርካሪዎች ላይ ፍተሻ ስናደርግ በአራቱ ላይ ድንጋዮች ተገኝተዋል፡፡ ይህንንም የስኳር ኮርፖሬሽን አምራች በተገኙበት ተማምነናል፡፡ ይህንን ወደ ሚዲያ መላክ ይቻላል፡፡ እኛ ግን በዚህ አናምንም፤›› ብለዋል፡፡ ሚዲያው ራሱ ሜቴክ ላይ የማጥላላት ዘመቻ እንደከፈተ የተናገሩት ብርጋዴር ጄኔራሉ፣ ‹‹ሜቴክ ላይ አሻጥር እየተፈጸመ ነው፤›› ብለዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በሜቴክ ሥር ያለው ኢት ፓወር ኢንዱስትሪ የሚያመርታቸው ትራንስፎርመሮች ላይ ተመሳሳይ የማጥላላት ዘመቻ ተፈጽሞ እንደነበር፣ በኋላ ግን በኮሚቴ ሲጣራ ራሱ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የተቃጠለ ትራንስፎርመር ከውጭ እያስገባ በሜቴክ ምርቶች ላይ እያሳበበ እንደነበር መረጋገጡን ጠቅሰው በማሳያነት አቅርበዋል፡፡ በኋላ ላይም በመንግሥት የተወሰነው ከውጭ የሚገዙ ትራንስፎርመሮች በሜቴክ ኢንዱስትሪ እንዲፈተሽ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡
አሁንም ቢሆን ሆን ተብሎ ማሽነሪዎች እንዲበላሹ ማድረግ፣ መለዋወጫዎች በሜቴክ ተመርተው እያለ ወደ ውጭ ግዥ እንደሚኬድ፣ ለሜቴክ ክፍያ እንደማይለቀቅና ብሔራዊ ባንክም ለግል ድርጅቶች የውጭ ምንዛሪ እየፈቀደ ሜቴክ ግን ማግኘት አለመቻሉን ጠቅሰዋል፡፡ በመሆኑም በሜቴክ በኩል ኦሞ ኩራዝ ቀጥር አንድንና በለስ ቁጥር አንድን በ2010 ዓ.ም. ሰኔ ወር ድረስ ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ ዕቅድ ቢያዝም፣ በተለይ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት አዳጋች እንደሆነና በለስ አንድን ለማስጀመር የኤሌክትሪክ ኃይል በወቅቱ ይቀርባል ተብሎ የሚታሰብ ባለመሆኑ በዕቅዱ መሠረት ማጠናቀቃቸውን እርግጠኛ መሆን እንደማይቻል ገልጸዋል፡፡
በያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካ የታየውን የመሬት መንሸራተት ለማስቆም የአቃፊ ግድግዳ መሰንጠቅንና የኩሊንግ ታወር መስመጥ ችግሮችን እልባት ለመስጠት፣ የባለሙያዎች ቡድን ከአማካሪው ኮሚቴና ከፕሮጀክቱ ባለቤት ከኢትዮጵያ ኬሚካል ኮርፖሬሽን ተውጣጥቶ በጋራ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይህ ፕሮጀክት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚጠይቅና በሚፈለገው ልክ ባለመገኘቱ፣ እንዲሁም ተጨማሪ ሥራዎች በመካተታቸው በዕቅዱ መሠረት ሊፈጽም አለመቻሉን አስረድተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅተ በአካባቢው (በመቱ) ረብሻ በመከሰቱ የፕሮጀክቱ ግንባታ እንዲቆምና ፕሮጀክቱ ላይ ጉዳት እንዳይደርስ በመከላከያ በመታዘዙ፣ ሥራ ቆሞ የፕሮጀክት ሠራተኞች የፀጥታ ሥራ ላይ መሠማራታቸውንና ይህም ቀላል የማይባል መጓተት እንደሚያደርስ ጠቁመዋል፡፡
ገበያ ተኮር ምርቶችን ጥናት ላይ ተመሥርቶ ባለማምረቱ ክምችት ተፈጥሯል የሚባለው እውነት ቢሆንም፣ የተባለውን ያህል ግን የሚጋነን አለመሆኑን ጠቅሰው የትራክተር ምርት ክምችት ግን ሜቴክንም እንዳሳሰበው ተናግረዋል፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ ያለወለድ በረጅም ጊዜ ብድር ለገበሬው ለመሸጥ ከክልሎች ጋር በመነጋገር ላይ ነን ብለዋል፡፡
የሜቴክ ፋይናንስ ጤናማ እንደሆነና ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ኦዲትና ሪፖርት ሥርዓት መተግበሩን ገልጸው፣ በአሁኑ ወቅት የተቋሙ ሀብት የሚቆጠርና ግልጽ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካ ጋር ተያይዞ ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር ቅሬታ የተፈጠረው የካሳ ክፍያ ላይ ችግር በመኖሩ እንደሆነ በማመን፣ ችግሩን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ገብረ እግዚአብሔር አርዓያ በተሰጠው ምላሽ ሙሉ በሙሉ አለመደሰታቸውን፣ አሁንም አመራሩ ለፕሮጀክቶቹ መጓተት የውጭ ምክንያት እየደረደረ መሆኑ ተገቢ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡ ‹‹በእኛ ላይ ዘመቻ ተከፍቷል የሚለው አነጋገር ጥሩ አይደለም፡፡ የሚዲያ ችግር ለእናንተ ብሎ የመጣ አይደለም፡፡ የፀጥታ ችግርም ወቅታዊና አገራዊ ችግር ሆኖ በሁሉም ላይ የመጣ እንጂ ሜቴክን ለይቶ አልመጣም፤›› በማለት አመራሩ ራሱን እንዲያይ በድጋሚ በማሳሰብ፣ የቋሚ ኮሚቴው አባላትና የፕሮጀክቶቹ ባለቤቶች አስተያየት እንዲሰጡ መድረኩን ክፍት አድርገዋል፡፡
የስኳር ኮርፖሬሽን አስፈጻሚዎች አቶ ወዮ ሮባና አቶ አብርሃም ደምሴ በሜቴክ ለቀረቡ በስኳር ፋብሪካዎች ችግሮችና በአሻጥር ወቀሳዎች ላይ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ የዚህ አገር ጠላት ካልሆነ በስተቀር በሌላ አቅም በውጭ ብድር በሚገነባ ፋብሪካ ላይ ምን ዓይነት ሰብዕና ያለው የስኳር ኮርፖሬሽን ሠራተኛ ነው፣ ድንጋይ ቀላቅሎ ለማሽን የሚሰጥ በማለት ሐዘን በተቀላቀለበት ስሜት ጠይቀዋል፡፡ ‹‹አሻጥር ነው ተብሎ መገለጹ ሕመም ነው የፈጠረብን፡፡ እንዴት በዚህ ደረጃ ይገለጻል፤›› ያሉት ምክትል ሥራ አስፈጻሚው፣ ተነጋግረን የፈታነውን ነገር በዚህ መልኩ ከመግለጽ ጥርጣሬው ካለ መነጋገር ይሻል ነበር፤›› ብለዋል፡፡ ከአዲስ የሸንኮራ አገዳ እርሻ ላይ ሲጫን ድንጋይ መቀላቀሉ የሚታወቅ የኢንዱስትሪው ችግር መሆኑንና በየጊዜው በነባር ፋብሪካዎች ላይም እንደሚከሰት ተናግረዋል፡፡
ባለፈው ዓመት በወንጂ ተመሳሳይ ችግር ተከስቶ ማሽን መሰበሩን የገለጹት ኃላፊው፣ በሌላው ዓለምም ቢሆን እንደሚከሰት ነገር ግን የእነርሱ ፋብሪካ ባዕድ ነገሮችን እንደ ማግኔት ለይቶ የሚይዝ ቴክኖሎጂ በመኖሩ መከላከል እንደሚችሉ አውስተዋል፡፡ በኢትዮጵያ ስኳር ፋብሪካዎች የሸንኮራ አገዳ ወደ ማሽን በሚገባበት ወቅት ባዕድ ነገሮችን የሚለይ ተቆጣጣሪ ሠራተኛ ማሽኑ ጋ የመለየት ተግባር የሚፈጽም መሆኑንና አልፎ አልፎ ተቆጣጣሪ ሠራተኛውን አልፎ ጉዳት እንደሚከሰትም አስረድተዋል፡፡
‹‹እኔ ከጄኔራሎችና ከኮሎኔሎች የትግል ልምድና የሕይወት ተሞክሮ የተሻለ ነገር ነበር የምጠብቀው፤›› ብለዋል፡፡
ኦሞ ኩራዝ አንድ ፋብሪካ በግማሽ አቅሙ ተጠናቆ ከሆነ ከነገ ወዲያ መረከብ እንደሚቻል የገለጹት እኚሁ ኃላፊ፣ እውነታው ግን ይህ ሳይሆን የስኳር ኮርፖሬሽን የውጭ አማካሪ ገምግሞ ያልተጠናቀቁ ሥራዎች በዝርዝር ተለይተው ለሜቴክ ሪፖርት መደረጉንም ተናግረዋል፡፡ የስኳር ፋሪካዎቹ ግንባታ መጓተት እየፈጠረ ያለው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ አንድምታን በመገንዘብ፣ በግማሽ አቅም ስኳር ማምረት ለፕሮጀክቱ ባለቤት በጉጉት የሚጠበቅ ጉዳይ እንደሆነ አክለዋል፡፡ ፕሮጀክቱ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆና ሙከራ ተደርጎ ብቁ መሆኑ ሲረጋገጥ ርክክብ እንደሚካሄድ በግንባታ ውሉ ላይ ቢቀመጥም፣ ኦሞ ኩራዝ አንድ በግማሽ አቅሙ ማምረት የሚችል ከሆነ ከውሉ በተቃራኒ ለመረከብ ኮርፖሬሽኑ ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ሌላው ምክትል ሥራ አስፈጻሚ በበኩላቸው በለስ አንድ ስኳር ፋብሪካ በዚህ ዓመት ወደ ሥራ ሊገባ የሚችለው በኤሌክትሪክ አቅርቦት ችግር ብቻ እንደሆነ መግለጹ ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ ምክንያቱን ሲያስረዱም በነባሮቹም ሆነ በአዲሶቹ ፋብሪካዎች የዲዝል ጄኔሬተር መቅረብ የፕሮጀክቱ አካል በመሆኑ፣ ኤሌክትሪክ እንደ ምክንያት ሊቀርብ አይገባም ብለዋል፡፡
የኬሚካል ኮርፖሬሽን የሥራ ኃላፊ የሆኑት አቶ ፈቃዱ አመንቴ በበኩላቸው፣ የያዩ ማዳበሪያ ፕሮጀክት እንዲዘገይ ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ፣ አገራዊ የሆነው የውጭ ምንዛሪ ችግር እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ የፀጥታ ችግሩ የካሳ ክፍያ ቅሬታ መሆኑንም አውስተዋል፡፡ በፕሮጀክቱ አካባቢ የሚኖሩ አርሶ አደሮች የመሬት ይዞታቸውን ሲለቁ ካሳ በሜቴክ በኩል ቢከፈላቸውም፣ በይዞታ ይለማ ለነበረ የቡና ተክል ግን ካሳ ባለመከፈሉ የተፈጠረ ቅሬታ መቀስቀሱን ተናግረዋል፡፡ ከሜቴክ፣ ከአካባቢው የዞን አስተዳዳሪዎችና ከኬሚካል ኮርፖሬሽን ኮሚቴ ተዋቅሮ መፍትሔ ለመስጠት እየተሞከረ መሆኑን፣ የመቱ ዩኒቨርሲቲ በጥናት ላይ የተመሠረተ መፍትሔ እንዲያቀርብ ኃላፊነት ተሰጥቶት ሪፖርት ሊያቀርብ ቀጠሮ በተያዘበት ወቅት የፀጥታ ችግር መከሰቱንም አስረድተዋል፡፡
የያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካ መቼ እንደሚጠናቀቅ ሜቴክ እቅጩን መናገር አለመቻሉ የፕሮጀክቱን ባለቤት በእጅጉ ያሳሰበው መሆኑን የገለጹት እኚህ ኃላፊ፣ ፕሮጀክቱ በመዘግየቱ ኬሚካል ኮርፖሬሽን በአሁኑ ወቅት በየወሩ 70 ሚሊዮን ብር የባንክ ወለድ እየከፈለ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ከውጭ ስለሚገባው ማዳበሪያ እንተውና ፋብሪካው ቢጠናቀቅስ ኢኮኖሚ ካለ አዋጭ ይሆናል ወይ የሚለው ጉዳይ ሥጋታችን ነው፤›› ብለዋል፡፡ የቋሚ ኮሚቴው አባላትም በተስፋ መቁረጥ ትችት አዘል ጥያቄዎችን አንስተዋል፡፡
‹‹እየተማርን እየሠራን በመሄዳችን ፕሮጀክቶቹ ሊጓተቱ ችለዋል ተብሏል፡፡ እየተማሩ መሥራት ችግር የለውም፡፡ ነገር ግን መማር እስከ መቼ ነው? ገደብ የለውም ወይ?›› ሲሉ አንድ የኮሚቴው አባል ጠይቀዋል፡፡
ሌላ የኮሚቴው አባል በበኩላቸው ያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካ መዘግየቱ ብቻ ሳይሆን፣ ሜቴክ ከተቋቋመበት ዓላማ ውጪ ለፋብሪካው ጥሬ ሀብት የሆነውን የድንጋይ ከሰል እያመረተ በመሸጥ ላይ መሆኑ ከአካባቢው ኅብረተሰብ ጋር ቅራኔ ውስጥ እያስገባው መሆኑን ጠቅሰው፣ ‹‹ይህንን ሥራ ሜቴክ እንዲሠራ የተቋቋመበት ሕግ ይፈቅድለታል ወይ?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
ለቀረቡት ጥያቄዎች የሜቴክ ኃላፊ ምላሽ ሲሰጡ በያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካ የድንጋይ ከሰል በማምረት የሰው ኃይል ሥልጠና መካሄድ መጀመሩንና የተመረተው የድንጋይ ከሰል እንዳይበላሽ ደግሞ በጠቅላይ ሚነስትሩ አማካሪ አርከበ ዕቁባይ (ዶ/ር) ምክረ ሐሳብ ተመርቶ እንዲሸጥ እየተደረገ እንደሆነ ጠቁመው፣ ይቁም ከተባለም መቆም ይችላል ብለዋል፡፡
የተቀሩት የኮርፖሬሽኑ አመራሮች በበኩላቸው የአገላለጽ ችግር እንጂ ሜቴክ የውስጥ ችግርን ለማየት በውስጡ ፈቃደኝነት እንደሌለ ተደርጎ መወሰድ እንደማይገባው ገልጸው፣ በዚህ ዓመት ከፕሮጀክቱ ባለቤቶች ጋር ተግባብቶ የመሥራት ዕቅድ መያዙንም ተናግረዋል፡፡
የክፍያ ችግር ግን ሊፈታ እንደሚገባ፣ ምክንያቱም የፕሮጀክቶቹ ውል ከተፈጸመ በኋላ የማቴሪያሎች ዋጋ መናርና የዲዛይን ለውጦች መኖራቸውን አውስተዋል፡፡ ቋሚ ኮሚቴውም ሜቴክ የውስጡ ችግሩን መመልከት ላይ አተኩሮ ከፕሮጀክቱ ባለቤቶቹ ጋር ገንቢ ውይይት ላይ በማተኮር እንዲሠራ አጽንኦት ሰጥቷል፡፡ ethiopianreporter