Artcles

ምርቱ የዋጋ ንረትን ያረጋጋል!

By Admin

November 22, 2017

ምርቱ የዋጋ ንረትን ያረጋጋል!

                                                    ታዬ ከበደ

በያዝነው ዓመት በአገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ  ምርት  ይሰበሰባል። ካለፉት ዓመታት ብዙ ጭማሬ ያለው ነው። የዘንድሮው ምርት በውጭ ምንዛሬ ለውጥ ምክንያት በአገር ውስጥ ሊፈጠር የሚችለውን የዋጋ ንረትን በማረጋጋት ረገድ ቁልፍ ሚና ይኖረዋል።

ታዲያ ምርቱ በአግባቡ መሰብሰብ አለበት። በተለይም በየአካባቢው የሚታዮን እንደ ተምች ወረርሽኝ ያሉ ችግሮችን ለመቋቋም ዘመናዊና ባህላዊ ዘዴዎችን በመተግበር እንዲሁም ምርጥ ተሞክሮዎችን ለማስፋፋት የሚያግዙ ሥራዎችን ማከናወን ይገባል።

እንደሚታወቀው ሁሉ መንግስት የማስፋት ስትራቴጂን በመጠቀም በአነስተኛ የአርሶ አደር ማሳ ላይ ለውጥ ማምጣት ተችሏል። ይህም በአነስተኛ ማሳ ላይ ብዙ ምርት ማግኘት ያስቻለ፣ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ የላቀ ሚና ተጫውቷል። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የተመሰረተው በግብርና ላይ እንደመሆኑ መጠን፤ የአርሶ አደሩ የአመራረት ዘይቤ መለወጡ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ተችሏል።

በዚህም ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ ምርቶችን በበቂ ሁኔታ ማምረት ተችሏል። ይህም አጠቃላይ የሀገሪቱን ምጣኔ ሃብት ዕድገት ከፍ አድርጓል። በተለይ ባለፉት 10 ዓመታት የተገኘው ምጣኔ ሃብታዊ ዕድገት የምርትና ምርታማነት ማደግ ውጤት ነው።

ባለፉት ዓመታት መንግሥት ግብርናውን ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር አማራጭ የሌለው መፍትሔ መሆኑን ተገንዝቦ ሲሰራ ቆይቷል። በያዝነው ሁለተኛው የልማት ዕቅድ ላይም በመጀመሪያው የዕቅድ ዓመት ላይ የተገኘውን አመርቂ ውጤት ይበልጥ አጎልብቶ ለመቀጠል እየተሰራ መሆኑን መረጃዎች ያስረዳሉ።

የግብርና ልማት መዋቅራዊ ለውጥ ማምጣት ይችል ዘንድ በበሁለተኛው አምስት ዓመቱ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ትኩረት ተሰጥቶታል። እንደሚታወቀው አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ለእርሻ ሊውል የሚችል ሰፊና ለም መሬት እንዲሁም የአርሶ አደሩ ጉልበት አለ። በሀገሪቱ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ታዲያ ይህ ግብርናው ውጭ ከፍተኛ እምቅ ሐብት ነው።

ይህ ሐብት ለዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል እየፈጠረ ሲሆን፤ ገና ምንም ያልተነካ እምቅ በመሆኑም ውጤት ሊያመጣ የሚችል ነው። ሀገሪቱን ለመለወጥ ወሳኙ ሃብት ተደርጎ መወሰዱም እንዲሁ።

ቀደም ሲል እንደገለፅኩት ምርትና ምርታማነት በማደጉ ሳቢያ የአርሶ አደሩ ህይወት በአያሌው ተለውጧል። እንዲያውም በአንዳንድ አካባቢ የሚገኙት አርሶ አደሮች ትርፍ አምራች እንዲሆኑ አስችሏቸዋል።

ይህ ትርፍ አምራችነታቸውም ከተጠቃሚነታቸውባሻገር ሌሎች አካባቢዎች በተፈጥሮአዊው የድርቅ አደጋ በሚጠቁበት ወቅት የሚፈጠረውን ክፍተት እየሞሉ ነው። ምርትና ምርታማነት በማደጉ ሳቢያ ከፍተኛ ምርት እንደሚገኝ ይታሰባል።

ተባዮችን በባህላዊ መንገድ መከላከል ከአቅም በላይ በሚሆንበት ወቅትም ፀረ- ተባይ ኬሚካሎችን በመርጨትና በመከላከል በአሁኑ ወቅት በጥሩ ሁኔታ ማሳ ላይ የሚገኘውን ምርት ወደ ጎተራው እስኪገባ ድረስ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ርብርብ ማድረግ ይኖርባቸዋል። በተለይ የሚገኘው ምርት በተምች ወረርሽኝ እንዳይጠቃ ብርቱ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል።

ይህን ጥረት የሁሉም አካል መሆን አለበት። ለመንግስት ወይም ለአርሶ አደሩ ብቻ የሚተው አይደለም። ሁሉም በኃላፊነት ንፈስ ሊንቀሳቀስ ይገባል። ይህ ሲሆንም ምርቱ የሚጠበቀውን ያሀል ይሆንና በምንዛሬ ለውጥ ሳቢያ ለሚፈጠረው የዋጋ ንረት የበኩሉን አስተዋጽኦ ያበረክታል።

ላለፉት ዓመታት የግብርናው ዘርፍ ባሳየው እድገት የአገራችን የኑሮ ሁኔታ እንዲረጋጋ ማድረግ ተችሏል። እንደሚታወቀው ሁሉ መንግሥት አነስተኛ ይዞታ ላላቸው አርሶ አደሮች ምን ያህል ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ በተደጋጋሚ ገልጿል። ይህን የመንግሥትን ፖሊሲ ትክክለኛነት ለማረጋገጥም ተችሏል።

እንደሚታወቀው ሁሉ የዋጋ ንረት እንዳይከሰት መንገስት እየሰራ ነው። ከመሰረታዊ ፍጆታ እቃዎችና ሸቀጦች ስርጭት አኳያም መንግስት ስንዴን፣ ዘይትንና ስኳርን ጨምሮ እና የዋጋ ንረት እና እጥረት እንዳይከሰት የዋጋ ቁጥጥር ማድረግ ጀምሯል። የምንዛሬ ማሻሻያውን ተከትሎ ምንም ዓይነት የኤሌክትሪክና የውሃ ታሪፍ ጭማሪም አይደረግም።

ማሻሻያው ሀገሪቱ ለድርቅ ያልተጋለጠችበትና ከፍተኛ የመኸር ሰብል ምርት በሚገኝበት ጊዜ እንዲደረግ መወሰኑ በገበያው ያለውን የምርት መጠን እንዳይጓደል እና የእህል ዋጋ ንረት እንዳይኖር የሚያደርግ ነው።

ከማሻሻያው በፊት ከውጭ የመጡ ምርቶችን በመጋዘን አከማችተው ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች  ላይ ቁጥጥር እየተደረገ ነው። እርምጃ የመውሰድ ስራውም ተጠናክሮ ይቀጥላል። ገበያውን ለማረጋጋት የጅምላ መሸጫ ሱቆች መሰረታዊ ሸቀጦችን በበቂ ሁኔታ እንዲያቀርብ ይደረጋል።

ይህ ሁሉ የመንግስት ጥረት ህዝቡ በዋጋ ንረት እንዳይጎዳ ለማድረግ የታሰበ መሆኑ ግልጽ ነው። እርግጥ ለዜጎቹ ሃላፊነት የሚሰማው መንግስት የሚያደርገው ይህንኑ ነው። መንግስት ለህዝቡ የገባውን ቃል መቼም አጥፎ ስለማያውቅ ይህንንም በማድረግ ሃላፊነቱን እንደሚወጣ በተለያዩ ጊዜያት የፈፀማቸው ተግባራት ህያው ምስክር ናቸው።

በተለያዩ ወቅቶች መንግስት የዋጋ ግሽበትን ለማረጋጋት ተከታታይ የሆኑ ልማታዊ እርምጃዎችን በመውሰድ የህዝቡን ጥያቄ መልሷል። የዋጋ ግሽበቱ ባለ ሁለት አሃዝ በነበረበት በዚያ ወቅት፤ ህብረተሰቡ እንዳይጎዳ ስግብግብ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ በመውሰድ እንዲሁም መሰረታዊ የሆኑ የፍጆታ ዕቃዎችን ራሱ በማስገባትና በሸማቾች ማህበራት አማካኝነት አከፋፍሏል።

በአሁኑ ሰዓት ምጣኔ ሃብታችን በፍጥነት እያደገ መሆኑ ይታወቃል። አሁን ባለንበት ሁኔታ በኤክስፖርትና በኢምፖርት መካከል ክፍተት መኖሩ ግልፅ ነው። ጉድለቱ እየሰፋ መጥቶ የተጠቀሰው ደረጃ ላይ መድረሱ ግን ያሳስባል።

በእነዚህ ዓመታት የታየው ደካማ የኤክስፖርት አፈፃፀም አስተማማኝ የውጪ ምንዛሬ ግኝት በማረጋገጥ ለፈጣን ዕድገታችን አስፈላጊ የሆኑ መሣሪያዎችና ዕቃዎች ከውጪ በማስገባት ዕድገታችን ለማስቀጠል አና ከውጪ ብድርና ዕርዳታ ጥገኝነት ለመላቀቅ ትልቅ ማነቆ ሆኗል።

በግብርናም ምርታማነቱ መሻሻል ያሳየ ቢሆንም በሚፈለገው ደረጃ ባለመድረሱ ለኤክስፖርት የምናቀርባቸው የግብርና ውጤቶች በመጠን፣ በጥራትና በዓይነት ውሱን ናቸው ማለት ይቻላል። ታዲያ እነዚህን ሁኔታዎች መቀየር ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ተገቢው ትኩረት ተደርጎ የተገኘውን የግብርና ምርት በአግባቡ ሰብስቦ ጥቅም ላይ ማዋል ይገባል።

በአሁኑ ወቅት የተገኘው የግብርና ምርት እድገት ምርቱን በአግባቡ መሰብሰብ ከተቻለ መንግስት እየወሰዳቸው ካሉ የዋጋ ማረጋጋት ስራዎች በተጨማሪ ምርቱ የነበረውን ክፍተት በመሸፈን የአገር ውስጥ ገበያን ያረጋጋል። ይህም ተጠቃሚው ህብረተሰብ ኪስ በማይጎዳ ዋጋ ዋና ዋና የግብርና ምርቶችን እንዲጠቀም ያስችለዋል።