Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ምንዛሪውና ሳያጣ የነጣው ገበያችን

0 321

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ምንዛሪውና ሳያጣ የነጣው ገበያችን

                                                                                 ይልቃል ፍርዱ

ጥቂት የማይባለው የእኛ ሀገር ነጋዴ ብዙ ችግሮች አሉበት፡፡ ነግዶ ማግኘት ማትረፍ የሚቻለው ሀገር ሰላም ሲሆን፤ ሕዝብ ሰላም ውሎ ሰላም ሲያደር ነው፡፡ ለሁሉም መሰረቱ ሰላም ነው፤ የሀገር ሰላም ከሌለ ነግዶ ማትረፍ፤ በሀብት ላይ ሀብት መከመር ይቅርና የያዘውንም እንደሚያጣ፣ ንግዱም እንደሚቆም የተረዳና የተገነዘበ አይደለም፡፡ ከገንዘብም በላይ ሀገርና ሕዝብ ይቀድማል፡፡

የእኛ ነጋዴዎች በሀገርና በሕዝብ ፍቅር ሳይሆን በገንዘብና በንዋይ ፍቅር ያበዱና የሰከሩ ናቸው፡፡ አንዲት ለውጥ እንደሰሞኑ የዶላር ምንዛሪ ማሻቀብ አይነት ሲመጣ ተንደርድረው የሚጎዱት የራሳቸውን ወገን ነው፤ ሸማች ደንበኛቸውን እንደወገን ሳይሆን እንደ ጠለት እየቆጠሩ በሕዝብ ችግር ለመክበር የሚራወጡ፤ የተትረፈረፈ ትርፍ ፍለጋ በገዛ ወገናቸው ላይ ቁማር የሚጫወቱ ርሕራሄና ሰብአዊነት የሌላቸው ናቸው፡፡

ጥቂት የማይባሉ ነጋዴዎቻችን ሕዝብን የሚጎዱ፣ የሚያስለቅሱ፣ የሕዝብ ችግር ለእነሱ የተለየ ደስታና ፈንጠዝያ የሚሆንላቸው፣ በስቃዩና በችግሩ የሚፈነድቁ ናቸው፡፡ አንዳንዴም መንግስት ግብር ገብሩ ሲላቸው የሚወስደው እርምጃ ተገቢና ትክክል ነው የሚያስብሉ ብዙ ምክንያቶች አሉ፡፡ የእኛ ነጋዴ ለራሱ ወገን ላይ መጨነቅ ማሰብ የሚባል አስተሳሰብ የሌለው ነው፡፡

የእኛ አገር ኪራይ ሰብሳቢ ነጋዴዎች የሆነ አጋጣሚን ተጠቅመው የዘረፋ ሰይፋቸውን የሚመዙ፣ በግፍ ሕዝብን የሚመዘብሩና የሚገፉ የሚያስለቅስ ናቸው፡፡ ከሕግና ከዋጋ ተመን በላይ የሚሸጡ፣ የሸቀጦችን እጥረት ሆን ብሎ ለመክበር ሲሉ የሚፈጥሩ፣ ምርቱ እያለ የለም በማለት/በመደበቅና በስውር ዋጋ ጨምሮ በመሸጥ የሚከብሩ፣ ስኳር ቤትና መጋዘናቸው ደብቀው ሕዝብ ሲንጫጫ “ለመክበር ግዜው አሁን” ነው ብለው የሚያሰሉ፤ በሕጻናት እምባና ለቅሶ የሚደሰቱ ነጋዴዎች እየሆኑበት ህዝብ ተቸግሯል።

ወደፊት የታማኝና ቅን ነጋዴዎች ቁጥር እየቀነሰ፤ የአጭቤው ቁጥር እየጨመረ እንዳይሄድ ያሰጋል። መተሳሰብ፣ ሕግን ተከትሎ መስራት፣ ሕዝባዊ አገልግሎትን በአግባቡ መስጠት ብሎ ነገር የሞኝ ተግባር ተደርጎ በመቆጠር ላይ ነው። ስለዚህ መንግስት የተመነው ግብር ልክ ነበር ማለት ነው ያስብላል፡፡

ነጋዴው በግፍ ከሕዝብ እያስለቀሰ ከሚሰበስበው ገንዘብ ወደደም ጠላም ለመንግስት ግብር መክፈል አለበት፡፡ በሙስናውና በኪራይ ሰብሳቢነቱም ውስጥ ከደላላው ጋር በመመሳጠር ከጀርባ ሆኖ ቁልፍ ሚና የሚጫወት፣ ለምክበር ሲል የህዝብና የመንግስትን ሀብት የሚዘርፍ/የሚያዘርፍ፣ ባልሰራበት ለመክበር የሚጣደፍ ብዛቱ የትየለሌ ነው።

መንግስት ትንሽ የደመወዝ ጭማሪ ለሰራተኛው ካደረገ በምቀኝነትና በክፋት ውስጡ  የሚንበገበገው ነጋዴ ሸቀጡና ምርቱ ሞልቶ በገበያ ተርፎ እያለ ቶሎ ብሎ የሸቀጦች ዋጋ ይጨምራል፡፡ በዚህ ደግሞ የበለጠ ተጎጂው  የመንግስት ሠራተኛው ነው፡፡

በተለዩ ምክንያቶች በገበያው ውስጥ የእቃዎች፣ የሸቀጦች እጥረት ሲያጋጥም ዋጋቸው ሊጨምር ይችላል፡፡ በገበያው ላይ በብዛት ሲገኙ ደግሞ እንዲቀንሱ ይደረጋል፡፡ በአለማችን ላይ የሸቀጦችም ሆነ የእቃዎች ዋጋ አንዴ ከተጨመረ ተመልሶ የማይወርድባት ሀገር ኢትዮጵያ ብቻ አይደለችም ማለት ይከብዳል፡፡

የእኛ ነጋዴ የዘልማድ ነጋዴ ነው፡፡ አንዴ ዋጋ ተጨምሮ ምርቱ ሲትረፈረፍ ተመልሶ ዋጋው ወደነበረበት እንደሚመለስ እያውቅም፤ ቢያውቅም ስለመቀነስ ጆሮው አይሰማም፡፡ ይሄ ደግሞ የገበያ ህግጋትን ከመጣሱም በላይ ሕዝቡን በእጅጉ ይጎዳል፡፡

ስለዚህም መንግስት ሕዝቡ እንዳይጎዳ የተለየ ጥናት ማድረግ፤ የተለየ ውሳኔም መስጠት፤ እንደ “አለ በጅምላ” አይነት የተለየ ገበያም ማደራጀት ይጠበቅበታል፡፡ በሀገራችን የሚመረቱትና ጤፍ፣ አተር፣ ባቄላ፣ ምስር ወዘተ ወዘተ የመሳሰሉ ምርቶች ከአውሮፓ አልመጡም፡፡ በየግዜው ዋጋው እየጨመረ የሚሄድበት ታሪክ ምንድነው? ብሎ መጠየቅ፤ ማጥናት ይገባል፡፡ ይሄ ሁሉ ነጋዴውና ደላላው በመመሳጠር በሕዝብ ላይ የሚፈጽመት ታላቅ ወንጀል ሲሆን፤ በሌላም በኩል ሕዝብን የማስከፋት የማሳመጽ ስራም እየሰሩ ነው፡፡

እኔ ልክበር፤ ሕዝብን ደግሞ አንተ እንደፈለገህ ሁን፤ ካለህ ግዛ፣ ከሌለህ ተወው የማለት ያህል ነው፡፡ የእኛ ነጋዴ ሕዝባዊ አገልግሎት እንደሚሰጥ የሕዝብ አገልጋይ እንደሆነ በቅጡ የተረዳ አይነትም አይደለም የሚባለውም ለዚህና ለዚህ ነው። ሕዝብ አልገዛህም ካለው ካመጸ ሸቀጡን ታቅፎት እጁ ላይ ዋጋ ሳያወጣ፣ በገንዘብ ሳይለወጥ ዋጋውም እንዲወርድ ሊያደርገው ይችላል፡፡ አለመታደል ሆኖ፣ ይሄንን በቅጡ የተረዳና ሙያውን በአግባቡ የተገነዘበ ነጋዴ አይደለም ያለን፡፡

በሀገሩ ሰው የሚጨክን ግዜና ወቅትን እየጠበቀ በሚፈጠሩት ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ውስጥ ዘርፎ ለመክበር የሚክለፈለፍ ነጋዴ ነው ያለን፡፡ አያትርፍ አይነግድ አይደለም እየተባለ ያለው፡፡ በአግባቡ መነገድ ማትረፍ አለበት፡፡ ከሕግና ከስርአት ውጪ ሕዝቡን መዝረፍ ሕዝቡን ማስለቀስ ግን የለበትም፡፡ የሕዝቡን የእለት ተእለት ኑሮ ገበያውን በማስወደድ ማናጋት የለበትም፡፡ በቀጣይ የአገሪቱን እድገት ማስቀጠል የሚቻለው የተረጋጋ የገበያ ስርአት ሲፈጠር ነው፡፡ ኑሮ ሊወደድ ቢችልም መንግስት ተገቢውን አቅርቦት በተለይ የመሰረታዊ ፍጆታ እቃዎች አቅርቦት ያደርጋል፡፡ ሌሎች ለሕዝቡ የሚጠቅሙ መንገዶችንም ይጠቀማል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በቅርቡ በተደረገው የዶላር ዋጋ ምንዛሪ በብር ላይ ጭማሪ ማድረጉን ተከትሎ የውጭ ምንዛሬ ተመን ማሻሻያ እርምጃው የሕዝቦችን ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ያለመ መሆኑን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ገልጾአል፡፡ ጽህፈት ቤቱ  ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው የውጭ ምንዛሬ ተመን ማሻሻያ እርምጃ የአገሪቷን ልማት ለማፋጠንና የሕዝቡን ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ያለመ መሆኑን ገልጾአል፡፡ ይህ አይነቱ እርምጃ ሲወሰድ በሸማቹ ሕብረተሰብ ላይ የሚያሳድረው መጠነኛ ጫና እንደሚኖር ታሳቢ በማድረግ፤ በመንግስት በኩል ችግሩን ለማቃለል የሚረዱ  ልዩ ልዩ እርምጃዎች በተጓዳኝ እንዲተገብሩ መሆኑን አስታውቆአል፡፡

ፅ/ቤቱ ሁኔታውን እንደመልካም አጋጣሚ በመውሰድ አንዳንድ ነጋዴዎች ያልተገባ ጥቅምን ለማግኘት እየሞከሩ መሆኑን ጠቅሶ ሸማቾችን ያሳተፈ አገር አቀፍና ክልላዊ ግብረ ኃይሎችን በማቋቋም ሕገወጦችን ለመቆጣጠር የሚያስችል እንቅስቃሴ በመደረግ ላይ መሆኑን ገልጾአል፡፡

መንግሥት ለረጅም ጊዜ በተካሄደ ጥናት ላይ ተመስርቶ በቅርቡ የውጭ ምንዛሬ ተመን ማሻሻያ እርምጃን ተግባራዊ ያደረገ ሲሆን፤ እርምጃውም የአገራችንን ልማት ማፋጠንንና የሕዝቦቻችንን ዘላቂ ተጠቃሚነት ማሳደግን ታላሚ ያደረገ ነው፡፡ ሌላ ምክንያት የለውም፡፡ ይህ ዓይነቱ እርምጃ ሲወሰድ በሸማቹ ሕብረተሰብ ላይ የሚያሳድረው መጠነኛ ጫና እንደሚኖር ታሳቢ በማድረግ ችግሩን ለማቃለል የሚረዱ ልዩ ልዩ እርምጃዎችንም በተጓዳኝ እንዲተገበሩ ተደርጓል፡፡

መንግስት ካስቀመጣቸው አቅጣጫዎች መካከል ሁኔታውን እንደመልካም አጋጣሚ በመውሰድ አንዳንድ ነጋዴዎች ያልተገባ ጥቅምን ለማግኘት በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ላይ የተጠናከረ ሕጋዊ ቁጥጥር ማድረግ አንዱ ሲሆን አስፈላጊውን የጥንቃቄ ዝግጅት አድርጎ ወደተግባር መግባቱን ገልጾአል፡፡ ምክንያታዊ ያልሆነ ኢፍትሐዊ መንገድን የተከተሉ አከፋፋዮችና ቸርቻሪዎች ከምንዛሬ ማሻሻያው በፊት ወደአገር የገቡ ሸቀጦችን ሆን ብለው በመደበቅ እና ከምንዛሬ ማሻሻያው በኋላ የገቡ በማስመሰል ያልተገባ ጥቅም ለማጋበስ በመጣር ላይ ይገኛሉ፡፡

በውድድር ላይ የተመሰረተ ሥራ ሰርተው ሕጋዊ ትርፍ ለማግኘት የሚጥሩ የመኖራቸውን ያህል በአቋራጭ የመበልጸግ መንገድን የሚከተሉ ጥቂት ነጋዴዎች የሚፈጥሩት ችግር ያለ በመሆኑ መንግስት ሸማቾችን ጭምር ያሳተፈ አገር አቀፍና ክልላዊ ግብረ ኃይሎችን በማቋቋም ሕገወጦችን ለመቆጣጠር የሚያስችል እንቅስቃሴ ጀምሮ ወደ ስራ ገብቶአል፡፡

ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እንደታየው ከነፃ ገበያ የውድድር መርህ ውጭ በሆነ አካሄድ ላይ ተሰማርተው የተገኙ ነጋዴዎች አስተዳደራዊ እርምጃዎች ተወስዶባቸዋል፡፡ ይህ እርምጃም ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ ነጋዴዎቹ እርምጃ የተወሰደባቸው ሸቀጦችን ሆን ብሎ በመጋዘን በማከማቸት ወይም በመደበቅ በሸቀጦች ላይ ያለአንዳች ኢኮኖሚያዊ ምክንያት የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ በማድረግና በመሳሰሉ ተግባራት ላይ ተሰማርተው በመገኘታቸው መሆኑ በተጨባጭ የተረጋገጠ ነው፡፡

ከአስተዳደራዊ እርምጃው በተጨማሪ አጥፊዎቹን ለሕግ ለማቅረብ የሚመለከተው አካል አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ሒደት የሚቀጥል ሲሆን መንግስት ለሕዝቦቹ ጥቅም መጠበቅ ሌት ተቀን እንደሚተጋው ሁሉ በሕዝብ ላይ የሚደርስን ማንኛውንም ጉዳት እንደማይታገስ በትምህርት ሰጪነቱ ሊወሰድ የሚገባው መሆኑን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን መግለጫ ያስረዳል፡፡

በየትኛውም የአገራችን ክፍል የሚገኙ ነጋዴዎች እንደወትሮው ሁሉ ሕግና ደንብን አክብረው በውድድር ላይ የተመሰረተ የንግድ ሥራቸውን ማካሄድ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ደንብን በመተላለፍ ያልተገባ ጥቅም ለማጋበስ የሚደረግ ሙከራ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ለተጠያቂነት የሚዳርግ ወንጀል መሆኑን በውል ሊገነዘቡት ይገባል፡፡

ቀደም ብለው የገቡ ሸቀጦችን ወደፊት በተጋነነ ዋጋ እሸጣለሁ በሚል እሳቤ በመጋዘን ማከማቸት ወይም መደበቅ አሁንም በፈለኩት ዋጋ መሸጥ እችላለሁ በሚል ድፍረት ሕዝብን ለመበዝበዝ መሞከር ወንጀል ነው፡፡ የነፃ ገበያ መርህን በመጣስ ዋጋን በስምምነት የመወሰን ተግባር ሁሉ የገበያ አለመረጋጋትን የሚያስከትል በመሆኑ በቸልታ የማይታለፍ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy