Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ሥርዓቱ የፈጠረው አብሮነት

0 365

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ሥርዓቱ የፈጠረው አብሮነት

                                                   ታዬ ከበደ

በአገራችን አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተው ግጭት ለማብረድ የየአካባቢው መስተዳድርና ማህበረሰብ የነበራቸው ሚና ከፍተኛ ነው። የየአካባቢው የህብረተሰብ ክፍሎች ግጭትን ለማብረድ በቅርብ ከሚገኘው መስተዳድር ጋር የሚያከናውናቸው ተግባራት እንደተጠበቁ ሆነው፤ ተፈናቃዩችን በመርዳትም ጭምር የሚያሳዩት አርአያነት ያለው ተግባር ሊደነቅ የሚገባው ነው። ይህ ሁኔታም ፌዴራላዊ ሥርዓቱ በህዝቦች ዘንድ የፈጠረው አብሮነት ማሳያ ነው ማለት ይቻላል።

የኢትዮጵያ ሕዝቦች ልዩነቶቻቸውን ጠብቀው በጋራ መኖር የሚችሉበትን ባህል እያዳበሩ መጥተዋል። በብዙ ቋንቋዎች መናገር ሳያስማማ እንደሚቀር ይመስላቸው ለነበሩ ሰዎች አሁን በበርካታ ቋንቋዎች እየተነጋገሩ መግባባት እንደሚቻል ማረጋገጥ ችለዋል። የኢትዮጵያ ህዝቦች ብዙ እምነቶችና የተለያዩ የኃይማኖት ተቋማት የሚከተሉ ሆነው ሲያበቁ በተግባር ግን ተከባብረው መኖር እንደሚቻል ያሳዩ የፌዴራል ስርዓቱ ልዩ መለያ ሆነዋል ማለት ይቻላል።

እርግጥም በኢፌዴሪ ህገ መንግስት መግቢያ ላይ የሰፈረው አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የመገንባት ስምምነት በተጨባጭ እየተሳካ እንደሆነ ያለፉት 26 ዓመታት ጉዞ በተጨባጭ ያሳየ ይመስለኛል። ዛሬ ሀገራችን ውስጥ ብዝሃነት የዴሞክራሲያዊ አንድነታችን መገለጫ ሆኗል። ይህም ቀደም ባሉት ጊዜያት ብዝሃነትን አስመልክተው ይራመዱ የነበሩ የተሳሳቱ አስተሳሰቦችን ሙሉ ለሙሉ የቀየረ ነው።

ዛሬ ኢትዮጵያ ውሰጥ የመደማመጥ፣ የመቻቻል፣ የመከባበርና የአጋርነት ታሪክ ህገ መንግሥታዊ ዋስትና በማግኘታቸው የአብሮነቱ እሴቶች ሊሆኑ ችለዋል። አንድ ማኅበረሰብ ማንነቱ እንዲከበርለት የሌላውን ማንነት ማክበር እንዳለበት በማመን በተናጠልና በጋራ ባህሎቻቸውንና ታሪካቸውን ማክበርና ማንፀባረቅ የተቻለበት ዘመን ላይ ደርሰናል። በአሁን ሰዓት በኢትዮጵያ የመገንጠል መብት ህገ መንግሥታዊ ዋስትና ቢያገኝም፤ የማኅበረሰብ ጥያቄ መሆኑ እያበቃለት ይገኛል። ግን በጊዜ ሂደት የነበሩት አስተሳሰቦች ከጋራ ተጠቃሚነት አኳያ እየተመዘኑ በመክሰም ላይ መሆናቸውን መናገር ይቻላል።  

እርግጥ የደርግ ወታደራዊ አገዛዝ በወደቀበት ማግስት የነበሩት የታጠቁ የፖለቲካ ኃይሎች አንዳንዶቹ ያነገቡት ዓላማ መገንጠልን እንደነበር አይዘነጋም። ሆኖም አብሮ በመኖር ሂደት የተገኘ ጥቅም እያደገና እየሰፋ ስለመጣ የመገንጠል አስተሳሰብ ማኅበረሰባዊ መሰረት አለው ብሎ ለመናገር የሚቻል አይመስለኝም።

የደርግ መንግሥት በወደቀ ማግስት ኢትዮጵያ ትበታተናለች የተባለውና በብዙዎች በቋንቋ ወይም በማንነት ላይ የተመሠረተ ፌዴራላዊ ሥርዓት ለአንድነት ዋስትና አይሰጥም ተብሎ የተነገረው አፈ ታሪክ መሰረት የሌለው ብቻ ሳይሆን የሀገራችን ህዝቦች ብዝሃነት ከግምት ውስጥ ያላስገባም መሆኑን በተግባር አረጋግጧል።

በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ብዝኃነት የሀገራችን ጉልበትና አቅም ሆኗል። ሀገራችን ውስጥ ያሉት የተለያዩ ማንነቶች በተናጠል ከሚያስገኙት ጥቅም ይልቅ በጋራ የላቀ ጥቅም እንደሚያገኙ አብረው በቆዩባቸው ጊዜያት ማረጋገጥ ችለዋል።

የሕዝቦችን መብት የሚፈታተንና ሰላማቸውን የሚያናጋ ኃይል በጋራ ታግለው ማሸነፋቸው የዚህ ማሳያ ነው። በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት የታየውን አብሮነትን እንዲሁም በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ ያለውን ከፍተኛ መነቃቃትና ተነሳሽነት ብቻ መጥቀስም ይቻላል። የኢትዮጵያ ህዝብ በአብሮነት ላይ የተመሠረተ ነገር ግን እንደ አንድ ማኅበረሰብ በአንድነት ለልማትና ዕድገት የሚነሳ ህዝብ መሆኑን በተግባር አሳይቷል።

አንዳንድ ወገኖች በብሔርና በጎሣ የተመሠረተ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አወቃቀር እንደማይሰራ ቢገልፁም፤ የኢትዮጵያ ተጨባጭ ልምድ የሚያሳየው ግን ከእነርሱ ምልከታ የተለየን ሁኔታ ነው። በጋራ ለአንድ ዓላማ መቆማችን የመጪው ዘመን ዕድላችን በር ከፋች እየሆነ ነው።

ይሁን እንጂ በፌዴራላዊ ስርዓቱ ውስጥ አብሮ መኖር የሚቻለው ማንነቶች የአገርና የሥርዓት ግንባታ ባለቤቶች ማድረግ ሲቻል እንደሆነ ያለፉት ዓመታት ልምድ ትምህርት ሰጥተው መውሰድ ይቻላል።

አንድነታችን ተከታታይና ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ማስመዝገቡን በርካታ ዓለም አቀፋዊ ተቋማት እማኝነታቸውን ሰጥተዋል። ስለሆነም የኢትዮጵያዊያን አንድነት ብዙ ማንነቶች ላሏቸው ሀገራት ምርጥ ትምህርት የሚሰጥ ነው ማለት ይቻላል።

ቀደም ሲል የጠቀስኳቸው አንድነታችንን የሚያጎሉ ጉዳዩች የፌዴራላዊ ስርዓቱ መሰረቶች ናቸው። እነዚህ መሰረቶች በስርዓቱ የፖለቲካ ግንባታ ውስጥ ወሳኝ ድርሻ አላቸው።  በኢፌዴሪ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ውስጥ ያለው አካሄድም ይህንኑ ሃቅ የሚደግፍ ነው።

የኢትዮጵያ ህብረ ብሔራዊ ፌዴራል ሥርዓት በልዩነታችን ውስጥ ላለው አንድነታችን እንዲሁም በውስጣችን ላሉ ማንነቶች የሰጠው መብት ከብዙ ፌዴሬሽኖች ጋር ሲነጻጸር የላቀና ብዙ ማንነቶች ላሏቸው ሀገራት ትምህርት የሚሰጥ ነው ማለት ይቻላል።

የኢፌዴሪ ህገ መንግስት ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ህዝቦች እና ኃይማኖቶች እኩል መሆናቸውንና አብሮ ለመኖር ያላቸውን ተስፋ በፌዴሬሽኑ ሰንደቅ ዓላማ መሃል በተቀመጠው ብሔራዊ ዓርማ የሚንፀባረቅ መሆኑን ይገልፃል። ሁሉም የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቋንቋዎች እኩል እውቅና ተሰጥቷቸዋል። እያንዳንዱ ክልልም የሥራ ቋንቋ የመምረጥ መብት እንዳለው በግልፅ ተደንግጓል።

የአገራችን ሕዝቦች የሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤቶችና የመንግሥት ሥልጣን ምንጮች መሆናቸው በህገ መንግስቱ ላይ ሰፍሯል። ሕገ መንግሥቱ የኃይማኖትና መንግሥትን መለያየት መርህ በማስቀመጥ መንግሥት ለሁሉም እምነቶች እኩል የማገልገል ግዴታን ጥሎበታል። ሰው ሁሉ በህግ ፊት እኩል የመሆኑን ያህል የትኛውም ማንነት ከሌላው የማይበልጥና የማያንስ መሆኑም ተረጋግጧል።

እያንዳንዱ ማንነት በቋንቋው የመናገር፣ የመፃፍ፣ ቋንቋውን የማሳደግና ባህሉን የመግለጽ፣ ታሪኩን የመንከባከብ መበት አለው። እንዲሁም እያንዳንድ ማንነት ራሱን የማስተዳደር ሙሉ መብት እንዲረጋገጥለት ተደርጓል።

የማንነታችን ልዩነት ካከበርን አንድነታችንና አብሮነታችን እውን ይሆናል። አብሮነታችን በሥርዓቱ መፍካት ይችላል። እየተባበርንም አገራችንን ሌሎች የደረሱበት የዕድገት ደረጃ ማድረስ እንችላለን። አብሮነታችን በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ ተረጋግጧል። አንድ ሆነን በጋራ እንደምንለማ ባለፉት ዓመታት ተመልክተናል። ነገም ይህ አብሮነታችን ተጠናክሮ የሚቀጥል ነው። ማንም ሊሸረሽረው አይችልም።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy