Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ሰላማችን የፈጠረው ምርታማነት

0 284

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ሰላማችን የፈጠረው ምርታማነት

                                                      ቶሎሳ ኡርጌሳ

በያዝነው ዓመት የመኽር ወቅት የሚገኘው ምርት ከፍተኛ ነው። በአገር አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ደረጃ የሚመዘገብ ነው። በዚህም ለምርት መጠኑ ማደግ ምክንያት በዋነኝነት ሊጠቀስ የሚችለው በአገራችን የተረጋገጠው ሰላም ነው።

ከዚህ በተጨማሪ መንግስት ከሚመለከታቸው ጋር ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ አብሮ በመሰራቱ ነው። ይህ የምርት መጠን ማደግ የህዝቡን የኑሮ ውድነት ችግር በዘላቂነት ሊፈታ ይችላል። በውጤቱም የህብረተሰቡን የኑሮ ሁኔታ በማረጋጋት ረገድ የሚኖረው ሚና የላቀ መሆኑ አያጠያይቅም።

በአንድ አገር ውስጥ ሰላም ካለ እንዲሁም ቅንጅታዊ አሰራር መፍጠር ከተቻለ ምንም ነገር ማድረግ እንደሚቻል የመኸሩ ምርት ውጤት ሁነኛ ማሳያ ነው ማለት ይቻላል። ርግጥ ሰላም ለኢትዮጵያ ህዝብ ትልቅ ዋጋ ያለው ጉዳይ ነው።

የሀገራችን ሀዝብ ትናንት ያለፈበት አስከፊ መንገድ ዛሬ ያገኘውን አስተማማኝ ሰላም ገለል አድርጎ ቦታውን እንዲረከበው ቅንጣት ያህል ፍላጎት የለውም። በትውስታነት የኋሊት የሚሸሸውና ዳግም እንዳይመጣም ዶሴውን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የዘጋው የያኔው አባጣና ጎርባጣ መንገድ ተመልሶ እንዳይመጣ ለሰላሙ ፀር የሆኑ ሃይሎችን በማውገዝ፣ በማጋለጥና ተገቢውን ትምህርት እንዲወስዱ በማድረግ በባለቤትነት መንፈስ የመንቀሳቀስ ፍላጎቱ መሰረት ይኸው ይመስለኛል።

እንደ እውነቱ ከሆነ ይህ ህዝብ ከመቼውም ጊዜ በላይ ለሰላም ዘብ የሚቆምና ሰላም በምንም ሊተካ የማይችል እሴት መሆኑን ለማወቅ ነጋሪ የሚያሻው አይደለም። እንዲያውም እርሱው ራሱ ለሌላው ምሳሌ ሆኖ ስለ ሰላም ከራሱ እንዲማር እያደረገ ነው።

ርግጥ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ህዝብ ለሰላም ይህን ያህል ዋጋ የሰጠው የሞት ሽረት ጉዳይ የሆኑትን ልማትንና ዴሞክራሲን ለማምጣት ያደረገው እልህ አስጨራሽ ትግል የኋሊት እንዳይቀለበስበት ከመፈለግ መሆኑ ከማንም የሚሰወር አይደለም። ሰላም ከቁሳቁስ መጥፋትና መውደም ጋር ብቻ እንደማይያያዝ የሚገነዘበው፤ ነገ የሚገነባው ትልቅ ምጣኔ ሃብት ያለውና ለዘመናት ተነፍጎት የነበረው የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባት ስር እንዲሰድ ስለሚሻ መሆኑም እንዲሁ።

የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ህዝብ ከ26 ዓመታት በላይ የተራመዳቸው የልማት አባጣና ጎርባጣ ውጣ ውረዶች በአሁኑ ወቅት የሚቀራቸው ተጨባጭ ለውጦች ቢኖሩም፤ ከትናንቱ በተሻለ ቁመና እንደሚገኙ ያውቃል። ይህ የሆነውም ራሱ ለሰላም ካለው ቀናዒ እሳቤ መሆኑ አይካድም።

እርሱንም በተሻለ ማማ ላይ እንደሚያወጡት በልማቱ ውስጥ ተዋናይ የሆነው ማንኛውም ዜጋ በየደረጃው ተጠቃሚ እየሆነ መምጣቱን ራሱን ዋቢ አድርጎ መቅረብ የሚችል ህዝብ ነው።

ትክክለኛ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ካሉ፣ ህዝቡን ከዳር እስከ ዳር የሚያንቀሳቅስ ልማታዊ መንግስት ካለና በዚሁ መሪ አካል አስተባባሪነት ብሎም በህዝቡ የባለቤትነት መንፈስ የሚዘወር ሰላም እስካለ ድረስ፤ ሰርቶ መለወጥና ማደግ የማይቻልበት ምንም ምክንያት የለም። ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ አጥጋቢ ውጤት ማፈስ የማይቻልበት አንዳችም ምድራዊ ምክንያት አይኖርም።

አምባገነኑና የዕዝ ኢኮኖሚ መርህን የሚከተለው የደርግ ሥርዓት ከመውደቁ በፊት የሀገራችን ምጣኔ ሃብታዊ አሃዝ ከዜሮ በታች እንደነበር የማይዘነጋው ይህ ህዝብ፤ ስለ ሰላም ቀናዒ ሆኖ ፊቱን ወደ ልማት ማዞሩ ትክክለኛ ውሳኔ ነው። አምባገነኑ ስርዓት እንደወደቀም በአንድ በኩል ሰላምን የማረጋጋት፣ በሌላ በኩል ደግሞ የደቀቀውን ኢኮኖሚ ለማቃናት የከፈለውን ከባድ መስዕዋትነት ለዛሬ ምርትና ምርታማነትን እንዲያሳድግ ያደረገው ይህ ህዝብ፤ የትናንቱ መስዕዋትነት እንዲሁ መና ሆኖ እንዳልቀረ በማያሻማ ሁኔታ ይገነዘባል።

ከዛሬ 26 ዓመት በፊት ተራራ የሚያክለውን የሀገሪቱን ድህነት ለመዋጋት የተለያዩ መርሆዎችን ቢሰንቅም የሚፈለገው ዓይነት ለውጥ እንዳልመጣና ለረጅም ጊዜ በሀገራችን ውስጥ ተንሰራፍቶ የነበረውን የድህነት አዙሪትን ለመቀልበስ እንዳልተቻለ በማወቁ ሌላ መንገድ እንዲቀየስ ማስፈለጉን የሚያስታውሰው ይህ ህዝብ፤ ቅንጅታዊ ርብርብ ካለ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚቻል የተገነዘበ ነው። ይህ ግንዛቤውም በየትኛውም ልማትን አደናቃፊ ሃይል ፍላጎት የሚገታ አይደለም።

ርግጥ ከዛሬ ሁለት አስርት ተኩል ዓመታት በፊት በአንድ በኩል የሀገሪቱን ሰላም ማረጋጋትና የታጠቁ ሃይሎችን ወደ ልማት የማዞር ስራ፣ በሌላኛው ዘውጉ ደግሞ ፈጣንና ተከታታይ ልማትን የማምጣትና ሁሉንም ዜጋ በየደረጃው ተጠቃሚ የሚያደርግ ፖሊሲና ስትራቴጂን እውን ለማድረግ የወሰደው ጊዜና የጠየቀው ሁሉን አቀፍ መስዕዋትነት ከዚህ ህዝብ አዕምሮ ውስጥ በቀላሉ የሚፋቅ ይሆናል ብሎ ማሰብ አይቻልም።

ለዚህ ማሳያ ይሆን ዘንድ ሰላሙም እውን ሆኖ የታሰበው ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት በማስመዝገብ ሂደት ውስጥ ሁሉም ዜጋ ድህነት በሚባለው አንገት አስደፊ በሽታ ላይ እንዴት እንደዘመተና እስከ የመጀመሪያው ተሃድሶው ድረስ ሲጀመር ከዜሮ በታች የነበረውን ኢኮኖሚ ወደ አምስት ነጥብ አንድ በመቶ እንደምን ከፍ ሊያደርገው እንደቻለ ከዚህ ሰላም ወዳድ ህዝብ የሚሰወር አይደለም፤ ዋነኛው ተዋናይ እርሱው ነበርና። ይህም በቅንጅት መስራት ከተቻለ ምንም ነገር ማድረግ እንደሚቻል ከልማት አኳያ ቀዳሚ ትምህርት የወሰደበት ወቅት ነው ማለት የሚቻል ይመስለኛል።

ከቀዳሚው ተሃድሶ በኋላም የተገኘው እድገት የድህነትን አከርካሪ በሚፈለገው መጠን መስበር እንዳልተቻለ፣ በወቅቱ የተከሰቱት የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት፣ የኪራይ ሰብሳቢነት፣ የጥበትና የትምክህት አመለካከቶች ከልማታዊና ተራማጅ እሳቤዎች ጋር ግጭት መፍጠራቸው የህዝቡን የማደግ ህልም ሊያመክኑትና ወደ ጨለማው መንገድ ይዘውት ሊሄዱ እንደ ነበር ይህ ህዝብ የሚያውቀው ነው። እነዚያ አስተሳሰቦች በወቅቱ ባይቀጩ ኖሮ፣ ዛሬ የተገኘው ሁለንተናዊ ለውጥ ሊመጣ እንደማይችል የተገነዘበ ህዝብ ነው።

ከዛሬ 16 ዓመታት በኋላም ቢሆን የነበሩት የተዛቡ አስተሳሰቦች ከሞላ ጎደል በመታረማቸውና መንግስትም ድህነትን ለመቀነስ በወሰዳቸው ሰፋፊ ርምጃዎች ባለ ሁለት አሃዝ ዕድገት ማስመዝገብ መቻሉ የሰላም መኖር ምን ያህል ፋይዳ እንደነበረው ያውቃል።

የሀገራችን ህዝብ በአምባገነኑ የኤርትራ መንግስት የተቃጣበትን ወረራ ፈጥኖ በመመከት፣ ውሰጠ ድርጅት ህፀፆችን በአስቸኳይ ፈትቶ ፊቱን ወደ ልማት ባይመልስ ኖሮ፤ ያለ ሰላም በጦርነትና በንትርክ ጊዜውን ያጠፋ እንደነበር ግልፅ ይመስለኛል። ይህን ደግሞ ከዚህ ህዝብ በላይ ሊገነዘብ የሚችል አካል ከቶም ሊኖር የሚችል አይመስለኝም።

በመሰረቱ የኢትዮጵያ ህዝብ በፌዴራል ስርዓቱ እየተመራ ከራሱ ተሞክሮዎች እየተማረ የሚያጋጥሙ ችግሮችን መፍታት የለመደ በመሆኑ ለመፍትሔዎችም ቅርብ ነው። ከህይወት የሰላ ትምህርት ቤት ባለመኖሩ ይህ ህዝብ ከትናንት ዛሬ፣ ከዛሬ ነገንና ከነገ በስቲያን የሚተልም በመሆኑ ምንም ነገር ማከናወን የመቻል ብቃትን ያዳበረ ነው።

በተለይም ሰላምን የሚያጎሉ፣ ልማትን የሚያፋጥኑና ንትርክን የሚያስቀሩ መንገዶችን እየተከተለ ከአንዴም ሁለቴ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዶችን እውን አድርጎ የተጀመረውን የፀረ ድህነት ዘመቻ አጠናክሮ ቀጥሏል።

በተለይም የሀገራችን ኢኮኖሚ እምብርት የሆነው የግብርናው ዘርፍ ይህን ተግባር እንዲወጣ አርሶ አደሩ በቅንጅታዊ አሰራር ጠንካራ ውጤት እያሰመዘገበ መምጣቱ የዚህ ሃቅ ሁነኛ አመላካች ነው። በያዝነው ዓመት የመኸር ምርት ከ345 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መጠበቁም የዚህ ውጤት ነው።

ታዲያ ከዚህ በመነሳት በአንድ ሀገር ውስጥ ሰላም ካለ፣ የሚያሰራ ፖሊስንና ስትራቴጂን የሚነድፍ መንግስት እንዲሁም በፖሊሲዎቹና ስትራቴጂዎቹ አማካኝነት ተቀናጅቶ መስራት ከተቻለ እንዲህ ምርታማነትን ማፈስ የማይቻልበት ብሎም ህዳሴያችንን የማናረጋግጥበት ምንም ምክንያት ሊኖር አይችልም። እናም ለሁለንተናዊ ዕድገታችን ሲባል ሰላማችን ሊበዛ ግድ መሆኑን የትኛውም ወገን ሊገነዘበው ይገባል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy