Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ሰላምን ለማረጋገጥ የሚሰራ ምክር ቤት

0 326

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ሰላምን ለማረጋገጥ የሚሰራ ምክር ቤት

                                               ታዬ ከበደ

የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት ሰብሳቢ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በቅርቡ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሰጥተው ነበር። በማብራሪያቸው ላይም ምክር ቤቱ በአገሪቱ የሚከሰቱ የሰላምና ፀጥታ መደፍረስ እንዲሁም ግጭቶችን ለመፍታት እቅድ አውጥቶ መንቀሳቀሱንና ለችግሩ ተጠያቂ የሆኑ አካላትን ህግ ፊት እንዲቀርቡ እያደረገ አስታውቀዋል። እንዲሁም ችግሮቹን ለመፍታት ህዝቡን በዋናነት በማሳተፍ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

የፌደራል እና የክልል የፀጥታ አካላት በተቀናጀ ሁኔታ ያለ አግባብ መጠቀም የሚፈልፈጉ አካላትን ከዚህ ድርጊታቸው ለማስቆም እና በዘላቂነት ይህን ድርጊት ለማጥፋት እንዲሁም ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ስራ መጀመሩን ገልጸዋል።

በኦሮሚያ እና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች አንዳንድ አዋሳኝ አካባቢዎች ላይ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ የተፈናቀሉ 100 ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎችን በዘላቂነት ለማቋቋም ግብረሃይል በአፋጣኝ ተቋቁሞ እንደሚሰራ የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አገሪቱ በአሁኑ ወቅት በሰላማዊ ሁኔታ ውስጥ እንደምትገኝ አስታውቀዋል።

በፓርቲዎች መካከል ምንም ዓይነት ችግር አለመኖሩን፣ ይሁንና በአመራሩ የሚታዩ ችግሮች መኖራቸውም ተገልጿል። አመራሩ የትኛውም አካባቢ ያለ ህዝብ የእኔ ህዝብ ነው ብሎ ያለማሰብ የአቋም ችግር እንዳለበትም አልሸሸጉም።

በሌላ በኩል የፀጥታ አካላት ማስከበር ያለባቸውን ህገ መንግስቱን እና ህገመንግስታዊ ስርዓቱን ሆኖ ሳለ ጥቂት የፀጥታ አካላት በደም እና በጎሳ ለይቶ ህዝብን የማየት አዝማሚያ ተስተውሎባቸዋል።

አንዳንድ የፀጥታ አካላት በግጭት ውስጥ ተሳትፈው በመገኘታቸው እርምጃ እንደተወሰደባቸው ተመልክቷል። ወደፊትም በዚህ መሰል ድርጊት ውስጥ የተገኙትን አካላት ተጠያቂ እንዲሆኑ የማድረግ ስራ በተከታታይ እንደሚቀጥል በመግለጫው ላይ ተገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት አገራችን ውስጥ ዘላቂ ሰላምን የማስፈን ስራ በአፋጣኝ መከናወን ይኖርበታል። ለዚህ ደግሞ ከ1994 ዓ.ም ጀምሮ በአዋጅ የተቋቋመውና ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ስራውን ሲያከናውን የመጣው የኢትዮጰያ ብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት ኃላፊነት ተጥሎበታል።

ምክር ቤቱ በህገ መንግስቱ መሰረት የተቋቋመና አገራችንን ለስጋት የሚዳርግ ጉዳይ ሲከሰት እየሰራ የመጣ ነው። አዲስ አይደለም። በመሆኑም በአዋጅ ከተደነገገበት ጊዜ አንስቶ ሰላምን በሚያረጋግጡ ጉዳዩችን እያከናወነ ነው። በኦሮሚያና በሱማሌ አንዳንድ አዋሳኝ አካባቢዎች የተከሰተውን ችግር የመፍታት ሃላፊነት አለበት።

ዘላቂ ሰላም በአገራችን ውስጥ ማረጋገጥ ካልተቻለ ምንም ዓይነት የልማት ስራዎችን ማከናወን አይቻልም። ያለ ሰላም አንዳችም ነገር መፈፀም እንደማይቻል የሁሉም አገር ህዝብ በሚገባ ያውቃል። አንድ ሀገር ሰላምን ለማስፈን ሰላምን ሊያረጋግጡ የሚችሉ አዋጆችን ሊያወጣ ይችላል። አዋጁ ግን በህዝቡ ይሁንታ ሊደገፍ ካልቻለ ተፈፃሚነቱ አጠራጣሪ ይሆናል።

እርግጥም ህዝቡ ያልደገፈው አዋጅ የታለመለትን ግብ ሊመታ አይችልም። ይህም የሰላም ዋነኛው ምሶሶና ማገር የዚያች ሀገር ህዝብ እንጂ አዋጅ ሊሆን እንደማይችል የሚያሳይ ነው። ለዚህም ነው የፅሑፌን ርዕስ ‘ሰላም በህዝብ ፍላጎት እንጂ በአዋጅ አይጠበቅም!’ ያልኩት።

ከአገራችን ህዝብ በላይ የሰላምን ጥቅም በሚገባ የሚያውቅ ያለ አይመስለኝም። ላለፉት 26 ዓመታት በተፈጠረው አስተማማኝ ሰላም ውስጥ ያገኘውን የልማትና የዴሞክራሲ ትሩፋቶችን ጠንቅቆ ያውቃልና። እናም ስለ ሰላም ሲነሳ የመጀመሪያውና ቀዳሚው እማኝ ሊሆን የሚችለው የአገራችን ህዝብ ነው።

በቅርቡ በአገራችን አንዳንድ አካባቢዎች በውጭ ሃይሎችና በሀገራችን የውስጥ ተላላኪዎቻቸው ቅንጅታዊ እኩይ ሴራ ሁከት ተፈጥሮ ነበር። ሁከቱን በቁጥጥር ስር ማዋል እንዲቻልም በህገ መንግስቱ መሰረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወጥቶ እንደነበር እናስታውሳለን። ይህ አዋጅም በወቅቱ ሰላሙን ተነጥቆ በነበረው የየአካባቢዎቹ ህዝቦች በባለቤትነት ስሜት ድጋፍ ያለው ስለነበረ ከፍተኛ ውጤት ማግኘት ተችሏል። በዚህም ምክንያት አዋጂ እንዲነሳ ተደርጓል።

ከዚያም በኋላ ቢሆን በአንዳንድ የሱማሌና የኦሮሚያ አዋሳኝ ድንበሮች አላስፈላጊ ግጭት ተከስቷል። በኦሮሚያም ክልል ጥቂት ቦታዎች ላይ አላስፈላጊ ግጭቶች ተከስዋል። ይህ ሁኔታ በፌዴራሊዊ ስርዓቱ የተፈጠረ አይደለም።

ፌደራላዊ ሥርዓቱ በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፎ ሰላምን ዕውን ያደረገ ነው። ልማትን ያረጋገጠና በዚህም የህዝቦችን ፍትሃዊ የሃብት ተጠቃሚነትን ዕውን ያደረገ እንዲሁም ከሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር የዴሞክራሲ ባህል ግንባታን መገንባት የቻለም ነው፡፡

መቻቻልንና ዴሞክራሲያዊ አንድነትንም እያጠናከረ ነው፡፡ ምንም እንኳን ሥርዓቱ እነዚህን ውጣ ውረዶችን ተሻግሮ ሀገራችንንና ህዝቦቿን ዛሬ ላይ ላሉበት አስተማማኝ ቁመና ቢያበቃትም ቅሉ፤ አሁንም ተግዳሮቶችን እያስተናገደ ነው፡፡

ተግዳሮቶቹን መፍታት የሚቻለው በሥርዓቱ ብቻ ነው። እርግጥ ሀገራችን ውስጥ እየተተገበረ ያለው ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ትናንት ቀደም ሲል የጠቀስኳቸውን ውጣ ውረዶችን እየፈታና ችግሮችን እያረመ የመጣ በመሆኑ እነዚህ ተግዳሮቶች እየፈታ ነው፡፡

ዛሬ ሥርዓቱን ተግዳሮቶቹ እየፈተኑት ቢሆኑም፤ የችግሮቹ አራማጅ ኃይሎች የዘመናት ጥያቄያቸውን በህገ መንገስቱ ያረጋገጡት የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ባለመሆናቸው፤ ከመንግስት ጋር ሆነው በሥርዓቱ አማካኝነት ተግዳሮቶቹን እየፈቱ ይቀጥላሉ፡፡ ነገም ይሁን ከነገ ወዲያ ሌሎች ተግዳሮቶች ቢያጋጥማቸውም ዋስትናቸው ዴሞክራሲያዊና ፌደራላዊ ሥርዓቱ በመሆኑ በህግ አግባብ መሻገራቸው አይቀርም፡፡

ለዚህ ደግሞ በአዋጅ የተቋቋመው የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት ተግባሩን እንደሚወጣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ ምክር ቤቱ የአገሪቱን ብሔራዊ ደህንነት ባልተጠበቀ ሁኔታ ከሚከሰቱም ሆነ አመጣጣቸው ሊታይ ከሚችል አደጋዎችና ፈተናዎች በመጠበቅ ረገድ ተጨማሪ ዋስትና የሚያስገኝ ነው፡፡

በተለይም በህግ ከተሰጠው ተግባሮች ውስጥ አንዱ የሆነውንና ለአገሪቱ ብሔራዊ ደህንነት የስጋት ምንጭ የሆኑ ሁኔታዎችን በመገምገም ሊወሰዱ ስለሚገባቸው እርምጃዎች ሃሳብ አቅርቦ ከህዝቡ ጋር በመሆን ተግባራዊ ያደርጋል፡፡ የአገሪቱን ብሔራዊ ደህንነት ለማስጠበቅ የሚወዱ እርምጃዎችን የሚመለከቱ የአፈፃፀም መመሪያዎችን ማመንጨት እና የሀገሪቱን ብሔራዊ ደህንነት በሚነካ ማናቸውም ጉዳይ ላይ መክሮ አፈፃፀሙን በየጊዜው ለህዝቡ ያቀርባል፡፡ ይህም ምክር ቤቱ በህዝቦች ተሳታፊነት የአገራችንን ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ ለማረጋገጥ የሚችል መሆኑን የሚስረዳ ነው፡፡  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy