Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ስለወጣቶች ተጠቃሚነት ኮንትሮባንዲስቶችን መጠራረግ  

0 292

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ስለወጣቶች ተጠቃሚነት ኮንትሮባንዲስቶችን መጠራረግ  

ስሜነህ

የሰላም እጦት የሚያስከትለውን ዘርፈ ብዙ ችግር ከኢራቅ፣ ከሊቢያ፣ ከሶሪያ፣ ከጎረቤቶቻችን ደቡብ ሱዳንና ሶማሊያ፣ እንዲሁም ከየመን በላይ ብዙ ምስክሮች መጥቀስ አያሻም። በየሀገራቱ በተፈጠሩ ትርምሶችና ሁከቶች ዜጎች ለዘመናት የለፉበትና የደከሙበትን ሃብትና ንብረት እንዲያጡ፣ ለዓይን ይስቡ የነበሩ ውብና ማራኪ ከተሞቻቸው በቀናት ውስጥ ወደፍርስራሽነት ሲለወጡ ለመመልከትና ውድ የሆነው የሰው ልጅ ህይወትም ድንገት ሆኖ ሲቀር መመልከት እንኳንስ ለእነርሱ ያልደረሰበትን ሁሉ ስጋት ላይ የጣለና እያስቀጨ የሚገኝ ድርጊት ነው።

በየሃገራቱ በተከሰተው መቋጫ የለሽ ቀውስም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቻቸው ለአስከፊ ረሃብና ስደት፣ ጉስቁልና፣ ለአካል ጉዳትና ሞት ከመዳረግ ባለፈ ሌላ ያስገኘላቸው አንዳች ፋይዳ እንደሌለም አይተናል። እነዚህ ሀገራት በቀላሉ ሊወጡ ከማይችሉበት ዕልቂት ውስጥ እንዲገቡ ያደረጋቸው መንግስቶቻቸው ለተፈጠሩ ችግሮች ፈጥነው እልባት ባለመስጠታቸው መሆኑ ላይ መላው ዓለም ይስማማል።

በእኛም ሃገር ከላይ የተመለከቱት ሃገራትን አይነት እንድንሆን የተለያዩና የሰው ህይወትን ጨምሮ በቢሊዮን በሚገመት የንብረት ውድመቶች በሚገለጽ ደረጃዎች ተደርጎ የነበረው የአምናና ካቻምና ሙከራ ህይወት ዘርቶ በሶማሌ ኦሮሞ ክልሎች ብዙ ዋጋ አስከፍሎን አልፏል። እነዚህ ሙከራዎች በዚህ ብቻ ሳያበቁ አንፃራዊ  ለሆነ የፖለቲካ አለመረጋጋትም ምክንያት ሆነዋል። የእኛውን ሃገር ለየት የሚያደርገው ደግሞ በአብዛኛው ሁከቶችና ግጭቶች  ላይ ወጣቶች የተሳተፉበት መሆኑ ነው። በእነዚህ ግጭቶች ሳቢያ በአሳዛኝ ደረጃ የወጣቶችና ሌሎች ዜጐች፣ እንዲሁም የፀጥታ አስከባሪ ሃይሎቻችን ህይወት ተቀጥፏል። ቀላል የማይባል ንብረትም ወድሟል። የዜጐች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ተስተጓጉሏል፡፡ በዚህ የተነሳ ደፋ ቀና ብለው ሰርተው ኑሮአቸውን ለማሸነፍ የሚንቀሳቀሱ ዜጐች ለፈተናዎች ተዳርገዋል።

ይህን የመሰለው ችግር በየአካባቢው እንዲቀሰቀስ ምክንያት የሆኑ ወቅታዊ ችግሮች እንደነበሩ ባይካድም፣ ከተከሰተበት ሁኔታና ከደረሰው የህይወትና የንብረት ጉዳት በመነሳት ወጣቶቹ አካባቢ ያልተሰራ እና ይልቁንም ለምሬት ያበቋቸው መሰረታዊ ምክንያቶች ያሏቸው መሆኑን ለመገመት አይከብድም ።ያም ሆነ ይህ ውጫዊ ምክንያቶች ለጥፋት ተልእኮ መሳሪያ ሆነው ሊያገለግሉ የሚችሉት በውስጥ ያሉ ችግሮች እስካልተፈቱ ድረስ ብቻ መሆኑ የማያከራክር እውነታ ነው።ከላይ በተመለከቱት ሃገራት የውጭ ሃይሎች እንዳሻቸው ገብተው ለመፈንጨት ያበቃቸው መንግስታቱ የህዝባቸውን የልብ ትርታ በቶሎ አዳምጠው መፍትሄ መስጠት አለመቻላቸው መሆኑ አያጠያይቅም።በእኛም ሃገር የሆነው ሙከራ በቅርጽ ይለያይ እንደሆነ እንጂ በይዘት ተመሳሳይ ነው።በሙከራው ሂደት ዋነኛ ተዋናይ የነበሩት ጽንፈኞች እና የውጭ ቅጥረኞች ቢሆኑም የሃገሪቱን ህዝብ ከከፊል በላይ የሆነውን ወጣት ታሳቢ ያደረገ የትምህርት ስርአት ቢዘረጋም ተመጣጣኝ የሆነ የስራ እድል አለመመቻቸቱ እና ከተማረው ህዝብ ጋር የሚመጥን የአስተዳደር ስርአት አለመዘርጋት ዋነኛው ምክንያት  እንደሆነ በመንግስት በኩል ታምኖበታል።

ስለሆነም ልክ መስከረም 30 ቀን 2009 ዓ.ም የኢፌድሪ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ለሁለቱ ምክር ቤቶች ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የወጣቶች ተንቀሳቃሽ ፈንድ የሚቋቋም መሆኑን ማስታወቃቸው እና ዋነኛ መፍትሄ ተደርጎ የነበረ መሆኑም ይታወሳል። ለፈንዱ ማቋቋሚያም 10 ቢሊዮን ብር መመደቡ በወቅቱ የተመለከተ ሲሆን ገንዘቡ በምን መልኩ ጥቅም ላይ ሊውል እንደሚችል መመሪያ ከመዘጋጀት ባለፈ የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውና፤  ወደመሬት የወረደ መሆኑም ከተገለጸልን ሰነባብቷል። ያም ሆኖ ግን ይህ ፈንድ በአግባቡ መሬት ላይ መውረድ እንዳልቻለ የሚያረጋግጡ መረጃዎች እየወጡ ባሉበት ሰአት ላይ የ2010 ማሻሻያ ሞሽንን በተመለከተ ጠቅላይ ሚንስትሩ ባቀረቡት ማብራሪያም የወጣቶች ስራ እድል አሁንም በመፍትሄነት ተቀምጧል።ግን ደግሞ ይህ ፈንድ በራሱ የግጭት መነሻ ለሚሆነው የኢፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ተጋላጭ እንዳያደርገን አመራሩን ከኪራይ ሰብሳቢነት ማጽዳት ቀዳሚ አጀንዳ ሊሆን ይገባዋል የሚለው ሰሚ ያጣ ጩኸት አሁን ተቀባይነትን ያገኘ ይመስላል።ተቀባይነትን ያገኘባቸውን ምክንያቶች ከመመልከታችን አስቀድሞ የማንቀሳቀሻ ፈንዱን የአፈጻጸም ደረጃ መመልከት የመምከኑን ምክንያት ለመረዳት ግማሽ መንገድ ይወስደናል።  

የአሥር ቢሊዮኑ ብር የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ ይፋ ከሆነ በኋላ በተደጋጋሚ ጉዳዩን በተመለከተ የሚመለከታቸው ባለድርሻ ተቋማት በወጡት መግለጫዎች እንደተመለከተውም ሆነ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዳጸደቀው ከተማ ከገጠር ሳይል በየአስተዳደሩ ባሉ መዋቅሮች ሥራ አጥ የሆኑና ከዚህ ቀደም በአነስተኛና ጥቃቅን ተደራጅተው ብድር ያልወሰዱ ሦሰት ሚሊዮን ያህል ወጣቶች ብድሩን አግኝተው ወደ ሥራ ለመግባት የሚችሉ እንደሆነ ተመልክቶ ነበር። ይህን ተከትሎም ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 34 ባሉት ክልል ውስጥ ከሆኑት ሥራ አጦች አሥረኛን ያቋረጡ፣ ከቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች እንዲሁም ከዩኒቨርሲቲዎች በተለያዩ ሙያዎች የሠለጠኑ ወጣቶች የፈንዱ ተጠቃሚ ለመሆን ተመዝግበው ነበር።

ያም ሆኖ ግን እውነታው በመሬት ላይ የተለየ ሆኖ መገኘቱ ተረጋግጧል። በመሬት ላይ ስራ አጥ ወጣቱን የገጠመው ከላይ ከተመለከተው በተጻራሪ ነው። ማንኛውም ከአሥር ቢሊዮኑ ብር ተጠቃሚ ለመሆን የሚመጣ ሁሉ ማሟላት የሚገባው አሥር መሥፈርት ሆኖ መገኘቱ የችግሩ የመጀመሪያ ምክንያት ነው። የነዋሪነት መታወቂያ፣ ከዚህ ቀደም ከአዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም ያለመበደራቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ፣ የጋብቻ ሁኔታ ሠርተፍኬት፣ ቅድሚያ ክፍያ ማስቀመጥ፣ የትምህርት ማስረጃ ማሟላትና ከወረዳው ጥቃቅንና አነስተኛ የድጋፍ ደብዳቤ ማምጣት፣ ንግድ ፈቃድ ማውጣት የሚሉትን ተጨምሮ አሥሩን መሥፈርት ማሟላት ወጣቱን ተስፋ ያሳጣና የአንዳንዶቹ መስፈርቶች ምክንያታዊነትም ከአላማው አንጻር ጥያቄ የሚያጭሩ ሆነው ተገኝተዋል። ወጣቶች ተብሎ የጋብቻ ሰርተፍኬትና ስራ አጥ ተብሎ ተቀማጭ ሂሳብ የሚሉት ነገሮች ለኪራይ ሰብሳቢ ሃይሉ ካልሆነ በስተቀር ስለምን መስፈርት ሆነው መቅረባቸው ግራ የሚያጋባ ነው።

በየተቋማቱ ሄዶ በአጭር ጊዜ ውስጥ የምስክር ወረቀት ማግኘትም ሆነ ደብዳቤ የማጻፍ ሂደቱ ከባድ ስለነበር ብድር መጠየቅ የጀመሩ ወጣቶች ግን መሀል ላይ ሂደቱን ለማቋረጥ መገደዳቸውም ሌላኛው ምክንያት ነው ።አሥሩን መሥፈርት ለማሟላት በየተቋማቱ ያለው አሠራር ቀልጣፋ አለመሆን፣ አንዱ የሚያውቀውን አንዱ አለማወቁ፣ ብድሩን ከማግኘት አስቀድሞ የኢንተርፕራይዙ አባላት በሚጠይቁት ብድር ልክ አሥር በመቶ ማግኘት አቅቷቸውና ከወረዳ ክፍለ ከተማ ያሉ ምልልሶች ተስፋ አስቆርጧቸው ሂደቱን ያቋረጡ መኖራቸውን የተመለከቱ መረጃዎች ወጥተዋል።  

ከ”የከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ” የወጡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በገንዘቡ ለመጠቀም በገጠርም በከተማም ሦስት ሚሊዮን ሥራ አጥ ወጣቶች የተመዘገቡ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 1.02 ሚሊዮን ያህሉ በሁሉም ክልሎች ከሚገኙ ከተሞች ናቸው። እነዚህ ተመዝግበዋል። ይሄው መረጃው አያይዞ እንደገለፀው ከአሥር ቢሊዮኑ የወጣቶች ተዘዋዋሪ ብድር (ፈንድ)፣ በከተማም በገጠርም፤ በአጠቃላይ 4.716 ቢሊዮን ብር ወደታች የወረደ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ለከተማ ሥራ አጥ ወጣቶች የወረደው ደግሞ 1 ቢሊዮን 379 ሺሕ 342 ብር ከ63 ሳንቲም ነው፡፡

ሥራ አጥ ወጣቶቹን መመዝገብ፣ መለየትና ሥልጠና መስጠት፣ ሥልጠና ወስደውም ኢንተርፕራይዝ መመሥረት በራሱ ጊዜ የወሰደ መሆኑን የሚያመለክተው ኤጀንሲ፤ ወደ ተጨባጭ ተግባሩ ለመግባት በነበረው ሒደት መዘግየት ቢኖርም ገንዘቡ ከተለቀቀ በኋላ ግን ክልሎች ወጣቱን ወደ ሥራ ለማስገባት እየተንቀሳቀሱ ነው። ሆኖም የወጣቶቹ ዝግጁነትና የታየው የክልሎች የማስፈጸም አቅም ውስንነት ሥራው በፍጥነት እንዳይከናወን አድርጓል።

አጠቃላይ በከተማና በገጠር ከወረደው 4.716 ቢሊዮን ብር መካከል ጥቅም ላይ የዋለው ወይም የተሠራጨው 2 ቢሊዮን 181 ሚሊዮን 679 ሺሕ 777 ብር ነው። ይህም የወረደው ገንዘብ ሙሉ ለሙሉ ጥቅም ላይ እንዳልዋለ ያሳያል። አሥር ቢሊዮኑ ብር የወጣቶች ተዘዋዋሪ ብድር ለ2009 በጀት ዓመት የተያዘ ቢሆንም፣ ወደ ሥራ ሲገባ ከወሰደው ጊዜ አንፃርና ከተፈጠረው የአሠራር ክፍተት አኳያ ገንዘቡን ሙሉ ለሙሉ በበጀት ዓመቱ ለታለመለት ተግባር ማዋል አልተቻለም።

ከ2008 ዓ.ም ማብቂያ ጀምሮ 2009 ዓ.ም ውስጥም በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ላይ ያለመረጋጋት እንደነበር የሚያስታውሰው ኤጀንሲ፤ ከዚህ ጋር ተያይዞ ብድሩን ለወጣቶች ለማድረስ ችግር ፈጥሮ የነበረ መሆኑን ያወሳል። በኦሮሚያ የነበረውን ችግር በጥልቅ ተሃድሶ ገምግመው የአመራር ለውጥ በማድረግ የሄዱት ርቀት ጥሩ ነው የሚለው ኤጀንሲ፤ ከዚህ በፊት የገጠማቸው በኪራይ ሰብሳቢነት አንደኛ ዘርፍ ማለትም በቀድሞ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ የሚባለው የፈጠረው እክል መሆኑንም ይገልጻል። ኦሮሚያ ላይ የገጠመውና ወጣቱ ሆ ብሎ እንዲነሳ መንስኤ የሆነውም በአካባቢው የተፈጥሮ ሀብትና አቅሙ እያለ ይህን ሀብት የተወሰነ  ባለሀብት ብቻ ሲጠቀምበት ማየቱና ሥራ ዕድል ስላልተፈጠረለት ነው። አመራሩ የወሰደው ዕርምጃም፣ የተፈጥሮ ሀብት ለልማት ሲሰጥ ለተወሰነ ጊዜ ሆኖ የመነሻ ጥሪት ማፍሪያ በመሆኑና ጥቃቅንና አነስተኛ ስትራቴጂ ላይ የተቀመጠውን የጣሰ በመሆኑ የፈጠረውን ኢፍትሐዊ አሠራር ለማስተካከል ነው። አንድ ባለሀብት የተፈጥሮ ሀብት ላይ ብቻ ሳይሆን ሼዶች ላይም ቢሆን በቦታው መቆየት የሚችለው አምስት ዓመት ብቻ  ስለሆነም ክልሉ በጥቂት ባለሀብት የተያዘውን የተፈጥሮ ሀብት አብዛኛው ኅብረተሰብ እንዲጠቀምበት አድርጎ ሥራውን መሥራት ችሏል።

የአማራ ክልል ሲታይ፣ ከዚህ በፊት ከየዩኒቨርሲቲው ተመርቆ የሚወጣውን ወጣት ወደ ሥራ ማስገባቱ ላይ ትልቅ ክፍተት ነበር። አሁን በአንድ ጊዜ ከ34 ሺሕ በላይ ከዩኒቨርሲቲ የተመረቁትን በየሙያቸው አደራጅቶ ወደ ሥራ እንዲገቡ አድርጓል። ቅጥር ላይም ብዙ ዓመት የሥራ ልምድ የሚጠይቀውን ዝቅ አድርገው ወጣቱ ሥራ እንዲይዝ አድርገዋል። ጠቅላይ ሚንስትሩ በሞሽን ማብራሪያቸው ያረጋገጡትም ይህንኑ ነው። ከዚህ በፊት የነበረው ሲታይ በየደረጃው የሚገኘው አመራር ኮንትሮባንዲስቱን እንጂ ወጣቱን ትኩረት አድርጎ አልሰራም፤ለወጣቱ የገባነውን ቃል ሳይሆን የፈጸመው ለኮንድሮባንዲስቱ የገባውን ቃል ነው ፤ በንግድ፣ በአገልግሎት፣ በኮንስትራክሽን፣ በከተማ ግብርና እንደሚሠማራ ተናግረን ወደ ሥራው የገቡት ኮንትሮባንዲስቶች ናቸው።  

ደቡብም በተወሰኑ አካላት የተያዘውን የተፈጥሮ ሀብት ሕጋዊ መስመርና አሠራር ተከትሎ ለወጣቱ የሚተላለፍበት መንገድ ላይ እየሠራ መሆኑን የሚያመለክቱት መረጃዎች፤በ2009 በጀት ዓመት ለሥራ አጥ ወጣቶች ይውላል ከተባለው አሥር ቢሊዮኑ ብር የወጣቶች ተዘዋዋሪ ብድር ግማሽ ያህሉ እንኳን ጥቅም ላይ አልዋለም። ቀሪው ገንዘብ ክልሎችና ከተሞች የተሰጣቸውን ብር ሲጨረሱ የሚለቀቅ ቢሆንም፣ ክልሎችና ከተሞች ከተለቀቀላቸው ገንዘብ አንፃር ለወጣቱ ያሠራጩት ጥቂቱን ነው።ኦሮሚያ ለመጨረሱ ምልክት እያሳየ ሲሆን ሌሎቹ ክልሎች ግን ብዙ ርቀት የሚቀራቸው መሆኑን ከተመለከቱት መረጃዎች አንጻር ጉዳዩ ሲመዘን የአመራር ችግር ስለመኖሩና ይኸው ችግር ወደፊትን አስጊ ቢያደርገው ተገቢ ይሆናል። ስለሆነም እንደከዚህ ቀደሙ የገጭቶች መነሻን ከስራ አጥነት እና ከመልካም አስተዳደር ችግሮች ጋር ብቻ በማያያዝ ተወስኖ የነበረው መንግስት ከግጭቶች በስተጀርባ ኮንትሮባንዲስት አመራሮች ስለመኖራቸው ተቀብሎ ወደእርምጃዎች ማኮብኮቡ ተገቢና ተቀባይነት የሚኖረው ይሆናል።  

በዚሁ መሰረት በአገሪቱ ውስጥ እየተከሰቱ ላሉ ሕገወጥ ሠልፎችና ግጭቶች የክልሎች አመራሮች ኃላፊነት እንደሚወስዱ፣ የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት አስታውቋል። የጽሕፈት ቤት ኃላፊና የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ዓርብ ኅዳር 1 ቀን 2010 ዓ.ም. በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አዳራሽ የተካሄደው የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤትና የክልል ደኅንነት ምክር ቤት ስብሰባ ሲጠናቀቅ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፣ የክልሎች አመራሮች እየተካሄዱ ያሉ ሕገወጥ ሠልፎችንና ግጭቶችን ማስቆም አለባቸው። የአሸባሪዎችን ባንዲራ ይዘው ሕገወጥ ሠልፍ የሚያደርጉ አካላት እንዳሉ የጠቆሙት ሚኒስትሩ፣ ይህንን አደገኛ እንቅስቃሴ የክልል አመራሮች የማስቆም ግዴታ ምክር ቤቱ እንደጣለባቸው ገልጸዋል።

ካለፈው መስከረም ወር ጀምሮ በሶማሌና በኦሮሚያ አዋሳኝ አካባቢዎች በነበረው ግጭት ተሳታፊ የነበሩ የፀጥታ አካላትና ከፍተኛ አመራሮች እንደነበሩ ጠቁመው፣ እነዚህ ሰዎች በብሔራዊ ደኅንነት መለየታቸውንና በቅርቡም ሕጋዊ ዕርምጃ እንደሚወሰድባቸው መግለጻቸው በእርግጥም ከየግጭቶቹ በስተጀርባ ስራ አጥነትና የመልካም አስተዳደር ችግር ብቻ ሳይሆን በዋናነት ኮንትሮባንዲስቶችና ኪራይ ሰብሳቢ አመራሮች መሆናቸውን ነው። በመሆኑም፣ ሳይቃጠል በቅጠል ነውና የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችንን ሀሳብ በመደገፍ ከጎናቸው ልንቆም ይገባል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy