Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በትግል የተገኘው ድል፤ በትግል ፀንቶ ይቀጥላል ክፍል ሁለት

0 506

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በትግል የተገኘው ድል፤ በትግል ፀንቶ ይቀጥላል

 

አሜን ተፊሪ

 

ክፍል ሁለት

 

ይህ ሁኔታ እስከ ግንቦት 1983 ዓ.ም. ከቀጠለ በኋላ ያ የታሪክ ምዕራፍ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከደርግ ውድቀት ጋር አብሮ ተዘጋ፡፡ ኢትዮጵያ ከአፈና አገዛዝ ወደ ዴሞክራሲ፣ ከከፊል ፊውዳልና ከፊል ካፒታሊስታዊ ስርዓት ወደ ታዳጊ የገበያ ኢኮኖሚ ስርዓት ተሸጋገረች፡፡ ደርግ በሶቭየት ህብረት ሞዴል የገነባው የዕዝ ኢኮኖሚ ካለ ብዙ ምስቅልቅል ደረጃ በደረጃ እንዲናድ ከተደረገ በኋላ ሐገራችን ታዳጊ የገበያ ስርዓት አቅጣጫን በመከተል ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት በአዲስ ፈለግ ስትጓዝ ቆይታለች፡፡ ያለፍንባቸው ሃያ ሰባት ዓመታት በርግጥም በሁሉም የህይወት መስኮች የሐገራችን የማሽቆልቆል ምዕራፍ የተዘጋባቸው አዲስ እና የማያቋርጥ የዕድገት ምዕራፍ የተከፈተባቸው ዓመታት ነበሩ፡፡

 

በእነዚህ ዓመታት ለዘመናት ከኖርንባቸውና ከተጓዝንባቸው አቅጣጫዎች የተለዩ አዳዲስ መንገዶች ተከትለናል፡፡ በቅድሚያ ሐገራችን ከምንም ነገር በላይ በዴሞክራሲ እጦት የምትሰቃይ ሐገር እንደሆነች በመገንዘብ የተሟላ ዴሞክራሲን ለማስፈን ጥረት ተደርጓል፡፡ መጀመሪያ በሽግግሩ ወቅት ቻርተር የጀመረው የዴሞክራሲ ለውጥ ሂደት፣ በህገ-መንግስቱ ተሟልቶና ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተደርጓል፡፡ በህገ መንግስት አርቃቂ ኮሚሽን ተዘጋጅቶ የቀረበውና ሁሉንም አማራጭ ድንጋጌዎች ለህዝብ ውይይት ያቀረበው ረቂቅ ህገ-መንግስት በ1986 ዓ.ም እስከ አስራ ስምንት ሚሊዮን የሚደርሱ ዜጎች ከመከሩበት በኋላ በህዝብ በተመረጡ ተወካዮች እንዲፀድቅ ተደርጓል፡፡

 

በዚህ ዴሞክራሲያዊ አኳኋን የፀደቀው ህገ-መንግስታችን በይዘቱም ቢሆን ዴሞክራሲያዊና የተዋጣለት ነበር፡፡ ማንኛውም ዴሞክራሲያዊ ህገ-መንግስት አሟልቶ ሊይዛቸው የሚገባ ዴሞክራሲያዊ ድንጋጌዎችን ይዟል፡፡ በተጨማሪም ህገ-መንግስታችን በሌሎች ህገ-መንግስቶች ተፈልገው የማይገኙ ተጨማሪ ዴሞክራሲያዊ አንቀፆችን ይዞ የተቀረፀ ከመሆኑም በላይ በተግባርም በኢትዮጵያ የሚገነባውን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የሚገዛና የሚመራ የማዕዘን ድንጋይ ሆኖ ይገኛል፡፡ የዜጎችና የማህበረሰቦች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን አሟልቶ በመጓዝ የተቀረፀው ህገ-መንግስታችን እነሆ በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲገነባ ያስቻለን ቁልፍ የለውጥ መሣሪያችን ለመሆን በቅቷል፡፡

 

በዚህ ዴሞክራሲያዊ ህገ-መንግስት ከሌሎች መሰል አገሮች በተለየ ሁኔታና ደረጃ መንግስታዊ ስልጣን የህዝብ መገልገያ መሣሪያ መሆን እንዳለበትና በዚሁ በመመራት የሚገነባው ስርዓትም ይህን ያለማወላወል ለማረጋገጥ የሚያስችል ማዕቀፎችን ይዞ እንዲዋቀር ተደርጓል፡፡ ህገ-መንግስታችን የሐገሪቱ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ አቅጣጫ የህዝብና የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚያስችሉ መሠረታዊ መርሆች እንዲመራ አድርጓል፡፡ በዚህም ባህርይው በሐገራችን የህዝብን ተጠቃሚነት የሚያሰፋ በተለይ ደግሞ በድህነትና በጉስቁልና የሚኖሩ ህዝቦችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከምንም ነገር በላይ ትኩረት እንዲሰጥ ያደረገ ዴሞክራሲያዊና ተራማጅ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ለመገንባትም እጅግ የተመቸ ሁኔታ የፈጠረ ነበር፡፡

 

በተጨማሪም ኢህአዴግ የሚመራው መንግስት ቀርፆ ያስፈፀማቸው ትክክለኛ የፖሊሲ አቅጣጫዎች ሐገሪቱ በፈጣን የዕድገት ምህዋር ውስጥ እንድትገባ ለማድረግ ያስቻለ እና ከሞላ ጎደል ከመላው የአፍሪካ አህጉር አማካይ የዕድገት ምጣኔ ጋር ሲነፃፀር በእጥፍ ከፍ ብሎ የሚታይ የዕድገት ግስጋሴ የፈጠረ ነበር፡፡

 

ልማት፣ ዴሞክራሲና ሰላም የማይነጣጥሉ ሐገራዊ ግቦች እንዲሆኑ ያደረገው ይህ ድርጅት፤ ዛሬ መገንባት የጀመረውን የዴሞክራሲያዊ ስርዓት የሚፈታተኑ ልዩ ልዩ ችግሮች ገጥመውታል፡፡ የህዝብ መብት እና ጥቅም እንዲከበር አልሞ የተነሳው ድርጅት፤ ይህን ግብ ከዳር ለማድረስ በሚያደርገው ትግል ልዩ ልዩ ውስጣዊና ውጫዊ ፈተናዎች ገጥመውታል፡፡ ከእነዚህ ፈተናዎች አንዱ የኅብረተሰብ ህይወት መለወጫ መሣሪያ አድርጎ የሚመለከተውን የድርጅት እና የመንግስት ሥልጣን ወደ ዝርፊያ መሣሪያነት ሊቀይር የሚችል የጥገኝነት አስተሳሰብና እንቅስቃሴ ነበር፡፡

ድርጅቱ ይህ የገጠመው የጥገኛ ዝቅጠት አደጋ መሠረታዊ ምንጩ ምን እንደሆነ ያውቃል፡፡ ችግሩን ከአመራሩ ማህበራዊ ምንጭ ጋር አያይዞ ይመለከተዋል፡፡ አመራሩ ከንዑስ ባለሃብት መንደር የፈለቀ በመሆኑ፤ ከማህበራዊ ምንጩ የተነሳ የያዘውን ሥልጣን ቀስ በቀስ ያለአግባብ  የመጠቀም ዝንባሌ ሊያሳይ እና መንግስታዊ እና ድርጅታዊ ስልጣንን የግል ህይወቱን መቀየሪያ መሣሪያ ሊያደርገው ይችላል፡፡ ይህ አመራር ከንዑስ ባለሃብት መደባዊ ተፈጥሮው የተነሣ፤ ትግሉ (በተለይ የአርሦ አደሩ ትግል) የተጠናከረ ሆኖ በሚገኝበት ጊዜ አብዮታዊ የአመራር ሚና የሚጫወት ይሆናል፡፡ ከዚህ ለየት ባለና አርሶ አደሩ በተቀዛቀዘ ሁኔታ በሚያልፍበት ጊዜ ደግሞ በያዘው ስልጣን ራሱንና የቅርብ ወዳጆቹን እየጠቀመና እየተጠቃቀመ በመጓዝ ወደ ግል ብልፅግና ሊሸጋገር የሚችል ነው፡፡

 

ይህ ዝንባሌ በንድፈ ሃሳብ የሚታወቅ ከመሆኑ በተጨማሪ በሐገራችን ሁኔታ በተጨባጭ መከሰት የጀመረው፤ ኢህአዴግ ወደ ስልጣን በመጣ ማግስት ነበር፡፡ ስለሆነም በሁሉም ክልሎችና ብሔራዊ ድርጅቶች የመንግስት ስልጣን በያዙ ግለሰቦች ዘንድ ቀስ በቀስ በስልጣን የመጠቀም አዝማሚያቸው እየጠነከረ መሄድ ጀመረ፡፡ ይህም ደርጅታችን የአርሦ አደሩ ጥያቄዎች የነበሩትን የዴሞክራሲና የብሔር እኩልነት፣ ራስን በራስ የማስተዳደርና የምርት ነፃ ተጠቃሚነት መብቶችን በማረጋገጡ የአርሦ አደሩ ትግል ስለተቀዛቀዘ አመች ሁኔታ ስለተፈጠረለት የታየ ዝንባሌ ነበር፡፡

 

ከዚህ በመነሳት ሲታይ እንደ እኛ በሐገራዊ የለውጥ ሂደት ውስጥ ከሚያጋጥሙት ፈተናዎች አንዱና መሠረታዊው የመንግስትን ስልጣን አላግባብ ለመጠቀምና በዚህም እየታገዙ ለመበልፀግ ማሰብና መንቀሳቀስ ነው፡፡ ይህ ዝንባሌ እስከ ተወሰነ የዕድገት ደረጃ አብሮ የሚቆይና በማንኛውም ሁኔታ ቸል ሳይባል ሊታገሉትና ሊቆጣጠሩት የሚገባ ዝንባሌ ነው፡፡ ይህ ዝንባሌ አርሦ አደሩ የነበሩት ጥያቄዎች ሁሉ ተመልሰውለት በሰላም አርሶ መብላት በሚፈልግበት ወቅት ይበልጥ የተመቸ ሁኔታ እንደሚፈጠርለት ግንዛቤ ተይዞ ተገቢው ጥንቃቄና ትግል ካልተደረገበት በስተቀር ስርዓቱን ለአደጋ የሚያጋልጥ መሆኑ የማያጠያይቅ ነው፡፡ በ1993 እና በ1994 ዓ.ም የተካሄደው ድርጅታዊ ተሃድሶ ዋነኛ መነሻዎችም እነዚህ ነበሩ፡፡

 

ተሃድሶው እስከ ተወሰነ የታሪክ ምዕራፍ በተለይ ደግሞ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ኢኮኖሚ የተሟላ ልዕልና እስኪይዝ ድረስ ባለው የለውጥ ምዕራፍ፣ የመንግስት ስልጣን በማያቋርጥ ደረጃ ከታለመለት ዓላማ ውጭ የግል ብልፅግና መሣሪያ ሊሆን የሚችልበት ዕድል እንዳለ፣ ከዚህም አልፎ ይህ ዝንባሌ ከስርዓቱ ጋር በማይነጠል ሁኔታ አብሮ የሚኖርና ቀጣይ ትግል የሚጠይቅ እንደሆነ ድርጅቱ ያውቃል፡፡ በአንፃሩ ይህን ችግር ለመቋቋም አስፈላጊ የሆነው የህዝብ ትግል ደግሞ እንደሁኔታው ሊኖርም ላይኖርም፣ሊቀዛቀዝም ላይቀዛቀዝም እንደሚችል ተገዝቧል፡፡

 

ይህ የህዝብ ትግል በሌለበት ጊዜ ሁሉ የመንግስት ስልጣንን ካለአግባብ የመጠቀም ዝንባሌ ከመኖሩ አልፎ፣ የበላይነት ሊይዝ ይችላል፡፡ ስለሆነም በመፍትሄ ደረጃ የህዝቡን ትግል በቀጣይነት ማረጋገጥ እንደሚገባ፣ ለዚህም ሲባል በህብረተሰባችን ውስጥ ዴሞክራሲና ልማትን ማስፋፋትና የህዝብን ተጠቃሚነት እያረጋገጡና እያሰፉ መሄድ ያስፈልጋል፡፡ ባለፉት አስራ አምስት ዓመታት በአገራችን የጥገኛ ዝቅጠት አደጋን ለመመከት የሚያስችል እንቅስቃሴ የጀመርነው ከዚህ በመነሳት ነው፡፡

 

ሆኖም የልማታዊነት አስተሳሰብ የበላይነቱን ባልያዘበት ነባራዊ ሁኔታ ኪራይ ሰብሳቢነት እና ወኪሎቹ የሆኑት ትምክህትና ጠባብነት፣ እንዲሁም ሃይማኖትን ሽፋን ያደረገ ፅንፈኝነት ሰፊ የመንሸራሸሪያ ምህዳር በማግኘታቸው ዳግም ችግር ውስጥ ገብተናል፡፡ የዳግም ተሐድሶው አስፈላጊነት የሚመነጨው ከዚህ ነው፡፡ አሁን አስቀድመን የምናውቃቸው ችግሮች ተከስተው፤ የጥገኛ ዝቅጠት ኃይሉ በብሔሮች መካከል ቅራኔን በመፍጠር አንድነታችንን ለማላላት እየተፈታተነን ይገኛል፡፡

 

ይሁንና እነዚህ ኃይሎች በህዝቦች ጽኑ ትግል ተሸናፊ መሆናቸው የማይቀር ነው፡፡ ኢህአዴግ እንደ ግንባር ከተመሰረተ ወዲህም ያጋጠሙትን ችግሮች ራሱን ማዕከል አድርጎ ከነምንጫቸው በጥልቀት ሲፈትሽ፤ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ሲያስቀምጥና መላ ህዝቡን ከጎኑ በማሰለፍም ለመታረም ሲተጋና የገጠሙትን ፈተናዎች እየተሸገረ ተጉዟል፡፡ በዚህም የሀገራችንን ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት እያረጋገጠ መጥቷል፡፡

 

በ2008ዓ.ም ማገባደጃ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴና የኢህአዴግ ምክር ቤት ባስቀመጡት አቅጣጫ መሰረት በግንባሩና በአባል ፓርቲዎች በሚገኙ ሁሉም መዋቅሮች እየተካሄደ ያለው ዳግም በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄም የዚሁ የድርጅቱ ነባር መሰረታዊ ባህርይ ውጤትና መገለጫ ነው፡፡

 

ኢህአዴግ የተሃድሶ መስመሩን በመንግስታዊ ፖሊሲና ስትራቴጂ መልክ በመቅረፅና ወደ ህዝቡ በማስረፅ ትግሉን አጠናከረ፡፡ በመቀጠልም ፖሊሲና ስትራቴጂዎቹን በዓመታዊ ዕቅድ መልክ በማዘጋጀት ወደ ትግበራ ሽግግር አደረገ፡፡ እነሆ ላለፉት አስራ ሳበት ዓመታት በዚህ የተሃድሶ አቅጣጫ እየተመራን በመንቀሳቀስ አገራችን በተሟላ የለውጥ ምህዋር ውስጥ እንድትገባ ለማድረግ ቻልን፡፡

 

በዚህ የተነሳም መላው አፍሪካ በአማካይ ከ6 በመቶ ባልበለጠ ዓመታዊ ዕድገት ሲራመድ፣ አገራችን ግን ባለ ሁለት አሃዝ ዕድገት እያስመዘገበች ልትቀጥል ቻለች፡፡ በዚህ ዕድገት ብዙሃኑ የአገራችን ህዝቦች ተጠቃሚ እንዲሆኑ በተደረገው ርብርብ ከድህነት ወለል በታች የሚኖሩ ዜጎቻችን ቁጥር ከ54 በመቶ ወደ ሃያ ሁለት በመቶ እንዲወርድ ለማድረግና በከተማም በገጠርም ልማት ተስፋፍቶ የህዝብ ተጠቃሚነት እንዲጨምር ለማድረግ ተቻለ፡፡ በማህበራዊ ልማት መስክ ትምህርትና ጤና ተስፋፉ፡፡ የመሰረተ ልማት አውታሮች ግንባታ ተጠናከረ፡፡ እነዚህ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማት ውጤቶች ዴሞክራሲያችንን ይበልጥ የሚያጎለብቱና የሚያጠናክሩ ከመሆን አልፈው ራሱን የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታችንን ደግሞ ለዚሁ ተብለው በሚወሰዱ ርምጃዎች አጠናከርን፡፡ በዚህ የተነሳ አገራችን ኢትዮጵያ ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት በሁሉም መስኮች በቀጣይነት እያደገች ስትጓዝ የቆየች አገር ልትሆን በቃች፡፡

 

ሆኖም የልማታዊነት አስተሳሰብ የበላይነቱን ባልያዘበት ነባራዊ ሁኔታ ኪራይ ሰብሳቢነት እና ወኪሎቹ የሆኑት ትምክህትና ጠባብነት፣ እንዲሁም ሃይማኖትን ሽፋን ያደረገ ፅንፈኝነት ሰፊ የመንሸራሸሪያ ምህዳር በማግኘታቸው ዳግም ችግር ውስጥ ገብተናል፡፡ የዳግም ተሐድሶው አስፈላጊነት የሚመነጨው ከዚህ ነው፡፡ አሁን አስቀድመን የምናውቃቸው ችግሮች ተከስተው፤ የጥገኛ ዝቅጠት ኃይሉ በብሔሮች መካከል ቅራኔን በመፍጠር አንድነታችንን ለማላላት እየተፈታተነን ይገኛል፡፡

 

ይሁንና እነዚህ ኃይሎች በህዝቦች ጽኑ ትግል ተሸናፊ መሆናቸው የማይቀር ነው፡፡ ኢህአዴግ እንደ ግንባር ከተመሰረተ ወዲህም ያጋጠሙትን ችግሮች ራሱን ማዕከል አድርጎ ከነምንጫቸው በጥልቀት ሲፈትሽ፤ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ሲያስቀምጥና መላ ህዝቡን ከጎኑ በማሰለፍም ለመታረም ሲተጋና የገጠሙትን ፈተናዎች እየተሻገረ ተጉዟል፡፡ በዚህም የሀገራችንን ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት እያረጋገጠ መጥቷል፡፡

 

በ2008ዓ.ም ማገባደጃ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴና የኢህአዴግ ምክር ቤት ባስቀመጡት አቅጣጫ መሰረት በግንባሩና በአባል ፓርቲዎች በሚገኙ ሁሉም መዋቅሮች እየተካሄደ ያለው ዳግም በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄም የዚሁ የድርጅቱ ነባር መሰረታዊ ባህርይ ውጤትና መገለጫ ነው፡፡

 

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በፖለቲካ አለመረጋጋት ውስጥ ብትሆንም አሁንም አስገራሚ የሆነውን የኢኮኖሚ እድገት ቀጥላለች። እ.ኤ.አ በ2000 ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሁለተኛዋ ብዙ ቁጥር ያለው ህዝብ እና በዓለም ሦስተኛዋ የድሃ ድሃ ሀገር የነበረች ቢሆንም፤ አሁን ግን ታሪክ ተቀይሮ ሀገሪቱ ከ2000 እስከ 2016 ባለው ጊዜ ውስጥ ሦስተኛዋ የዓለማችን ፈጣን ሀገር በመሆን 31 በመቶ የሚሆነውን ህዝቧን ከድህነት አረንቋ አውጥታለች።

 

አንዳንድ የመገናኛ ብዙሃን ‹‹በቀጣይ አምስት ዓመታት የሐገሪቱ የብርሃን ተስፋ ደምቆ ይቀጥላል›› በሚል ስለተስፋችን ያወራሉ፡፡ ‹‹እስከ 2022 የኢትዮጵያ ጠቅላላ ሐገራዊ ምርት (ጂዲፒ) ዕድገት በየዓመቱ 6.2 በመቶ›› ያድጋል የሚሉት ሚዲያዎች የአይ.ኤም.ኤፍን ትንበያ ዋቢ በማድረግ ነው፡፡

 

‹‹የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የአገልግሎት እና የእርሻ ዘርፍ ላይ ትኩረት ያደረገ ነው›› የሚለው የዓለም ባንክ ስለ ሐገራችን የኢኮኖሚ ዕድገት ምስክርነቱ እየሰጠነው፡፡ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የማኑፋክቸሪንግ ማዕከል ለመሆን እየሰራች እንደምትገኝ የገለፁት የመገናኛ ብዙሃን፤ በያዝነው ዓመት ተጨማሪ አራት የኢንዱስትሪ ፓርኮች እንደምታስመርቅ ጠቅሰዋል፡፡ በቀጣዩ ወር የአዳማ እና የድሬዳዋ የኢንዱስትሪ ፓርኮች እንደሚመረቁ እና የቂሊንጦ እና የቦሌ ለሚ ሁለት የኢንዱስትሪ ፓርኮች በመጪው የካቲት ወር ለምረቃ እንደሚበቁ ገልፀዋል፡፡

 

ከቂሊንጦ የኢንዱስትሪ ፓርክ በስተቀር በሦስቱ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት ዘርፍ የሚሠሩ መሆናቸውን የጠቀሱት የውጭ የመገናኛ ብዙሃን፤ የሐገር ውስጥ እና የውጭ ባለሀብቶችን ለመሳብ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት ስትራቴጂ መሠረት ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ኩባንያዎች ተስማሚ የሆነ አካባቢ ለመፍጠር እየሰራች መሆኑን አስታውሰዋል፡፡ ታዲያ ይህን ብሩህ ተስፋ ጠብቆ ለመጓዝ የዳግም ተሐድሶ ትግሉን ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡ በትግል የተገኘው ድል፤ በትግል ፀንቶ ይቀጥላል፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy