Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በዳያስፖራው የሚላከው የውጭ ምንዛሪ 78 በመቶ በሕገ ወጥ መንገድ እንደሚገባ ተጠቆመ

0 367

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በውጭ አገር ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ አትዮጵያውያን ወደ ኢትዮጵያ የሚላከው የውጭ ምንዛሪ 78 በመቶ ህገወጥ በሆነ መንገድ እንደሚገባ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዳያስፖራ ቢዝነስ ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ አመለከቱ፡፡ ዳያስፖራው በሩብ ዓመቱ የ600 ሺ 397 የአሜሪካ ዶላር ቦንድ መግዛቱም ተጠቁሟል፡፡

የዳያስፖራ ቢዝነስ ጉዳዮች የ2010 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ሥራ አፈጻጸምን ትናንት በገመገመበት ወቅት የዳያስፖራ ቢዝነስ ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አክሊሉ ኃይለሚካኤል እንደተናገሩት፤ በቅርብ በተደረገው ጥናት በውጭ አገር በሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ አትዮጵያውያን ወደ አገሪቱ የሚላከው የውጭ ምንዛሪ 78 በመቶ በህገወጥ መንገድ ወደ አገር ውስጥ እየገባ ሲሆን፤ ችግሩን ለማሻሻል ጥናቶች እየተደረጉ ነው፡፡

የውጭ ምንዛሪ በሕጋዊ መንገድ እንዲገባና ኢኮኖሚውን እንዲያግዝ ለማድረግ የተንቀሳቃሽ ስልክ የባንክ አገልግሎት እንዲስፋፋ፣ የፋይናንስ አገልግሎቶች በሁሉም ቦታ ተደራሽ እንዲሆኑ፣ ገንዘብ አስተላላፊ ወኪሎች እንዲበዙና ውድድር እንዲኖር ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ሚኒስትር ዴኤታው አስረድተዋል፡፡

የዳያስፖራ ፖሊሲ ዋና ውጤት በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን በኢኮኖሚው በማሳተፍ ለአገሪቱ ምጣኔ ሃብታዊ ዕድገት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ባለፈው ዓመት ነጥብ ቢሊዮን ዶላር ከዳያስፖራው መገኘቱን አስታውሰዋል፡፡

እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ፤ ዳያስፖራው በጥራጥሬ፣ ቅባት እህሎች፣ በቡናና በቁም እንስሳት ስጋ ምርት ላይ እየተሳተፈ ሲሆን፤ በቀጣይ በማኑፋክቸሪንግና በጨርቃ ጨርቅ ምርት ላይ መሳተፍ አለበት፡፡ በመሆኑም ለዳያስፖራው ምቹ ሁኔታ መፍጠር፣ በቂ መረጃ የሚያገኝበትን አሰራር መዘርጋት፣ የኢንቨስትመንት ዕድል አደራጅቶ ዳያስፖራው እንዲነሳሳ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በተለይ መረጃ፣ እውቀት፣ ክህሎትና ከውጪ ጋር የመረጃ ትስስር ያለው አካል እንደመሆኑ በዓለም አቀፍ ገበያ ተኮር ኢንቨስትመንት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይጠበቃል፡፡ ወደ አገሪቱ በመምጣት በተለያዩ ዘርፎች የሚያገለግሉበትን አጋጣሚ መፍጠርና ኢኮኖሚውን በተግባር የሚደግፉበት አሰራር ማመቻቸትም ይገባል፡፡

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዳያስፖራ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀኔራል ዳይሬክተር አቶ ደመቀ አጥናፉ ዳያስፖራው በአገሪቱ ህዳሴ የበኩሉን አስተዋፅኦ እንዲወጣ ለማድረግ በተደረገው ጥረት በ2010 በጀት ሩብ ዓመት ውስጥ የ600 ሺ 397 የአሜሪካ ዶላር ቦንድ እንዲገዙ ተደርጓል፡፡ በቦንድ ግዥው ከተሳተፉ ዳያስፖራዎች መካከል የ424 ሺ ዶላር ቦንድ በመግዛት በመካከለኛው ምስራቅ አገራት ከፍተኛ ሽያጭ መመዝገቡን አስረድተዋል፡፡

በኢንቨስትመንት፣ በንግድና በቱሪዝም መስኮች መሰማራት ለሚፈልጉ 171 የዲያስፖራ አባላት በመረጧቸው ክልሎች እንዲሰሩ ድጋፍ የተደረገ ሲሆን፤84 በኦሮሚያ፣ 33 በአዲስ አበባ፣ 22 በደቡብ፣ 14 በአማራ፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ በአፋር፣ በትግራይ፣ በጋምቤላና በድሬዳዋ ሁለት ሁለት መሰማራት ችለዋል፡፡ 45 የዳያስፖራ አባላትም የቢዝነስ ኢንቨስትመንት ፈቃድ በማውጣት በመሰማራት ላይ መሆናቸውን አቶ ደመቀ አብራርተዋል፡፡

ዑመር እንድሪስ

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy