Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ብክነትን መከላከል ለላቀ ተጠቃሚነት

0 470

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ብክነትን መከላከል ለላቀ ተጠቃሚነት

ወንድይራድ ኃብተየስ

ጥናቶች እንደሚያመላክቱት ለአገራችን ምርት መቀነስ አንዱ ምክንያት በምርት ማሰባሰባሰብ ወቅት የሚፈጠር ብክነት ነው። ብክነት አርሶና አብርቶ አደሩን ብቻ ሳይሆን የአገር ኢኮኖሚንም በከፍተኛ ሁኔታ የሚጎዳ ነው። ብክነት ጥራት ላይም አሉታዊ ተጽዕኖ ይኖረዋል። የአገራችን የግብርና ስርዓት ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍተኛ መሻሻሎች እያሳየ ቢሆንም አሁንም በአብዛኛው ባህላዊ ስርዓትን የሚከተል በመሆኑ በምርት ብዛትም ሆነ ጥራት ላይ ከፍተኛ መሻሻል የሚፈልግ ነው። ይሁንና ግብርናችን አሁን ድርቅን መቋቋም ሁሉ የሚችልበት ሁኔታዎች እየታዩበት ነው።

በርካቶች በተበጣጠሰ እርሻና ኋላቀር አስተራረስ ዘዴ ግብርናችን መሻሻል ሊያሳይ አይችልም፤ እንኳን አገሪቱንህዝብ ሊቀልብ ይቅርና ራሱን አርሶና አርብቶ አደሩን መቀለብ አይችልም  ቢሉም  መንግስት በተከተለው  አሳታፊ  ፖሊሲዎች በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን  ዕቅድ ማጠናቀቂያ  ማለትም 2007 ዓ.ም ላይ  አገራችን  በምግብ ሰብል ራሷን ችላለች። ይህ ትልቅ ስኬት ነው።

አሁን ላይ ደግሞ የኢፌዴሪ መንግስት የአገሪቱን ኢኮኖሚ ከግብርና ወደ እዱስትሪ ለማሸጋገር  የሚያስችሉ ተግባራትን በማከናወኑ በአስቸጋሪ ሁኔታ እንኳን የአገሪቱ ኢኮኖሚ  ዕድገት  በማስመዝገብ ላይ ነው። ባለፉት ሁለት ዓመታት አገራችን በ50 ዐመታት ታሪኳ አይታው በማታውቅ ድርቅ ተመታ ሳለ እንኳን ኢኮኖሚው  ባለሁለት አሃዝ ዕድገት ማስምዝገብ ችሏል። ይህ የሚያመላክተው መንግስት የያዘው ዕቅድ ስኬታማነትን ያመላክታል። የአገሪቱን  ኢኮኖሚ ዕድገት ቀጣይነት ለማረጋገጥ መንግስት ከሚያከናውናቸው ተግባራቶች መካከል ግብርናውንና  ኢንዱስትሪውን ማስተሳሰስር አንዱና ቀዳሚው ነው። ይህ በመሆኑም ኢንዱስትሪውና አገልግሎት ዘርፉ ዕደገት በማሳየታቸው  በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንኳን  የአገሪቱ ኢኮኖሚ ባለሁለት አሃዝ   ዕድገቱን ቀጥሏል። ሌሎች ዘርፎች ዕድገት ማሳየት በመጀመራቸው የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ከአጠቃላይ የአገሪቱ ኢኮኖሚ  የነበረው አስተዋጽዖ ከጊዜ ወደ ጊዜ በመቀነስ ላይ ነው።

ይሁንና ግብርና አሁንም በርካታ የህብረተሰብ ክፍል የሚያሳትፍ  ዘርፍ በመሆኑ  የመንግስት  የትኩረት አቅጣጫ  ሆኗል።  ይህ ዘርፍ  በርካታ ዘጎችን የሚያቅፍ በመሆኑ በዚህ ዘርፍ የሚመዘገብ ዕድገት  በርካቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው። በመሆኑም በያዝነው ዓመት ይህን ዘርፍ   ቢያንስ የ8.0በመቶ ዕድገት  እንዲያስመዘግብ  መንግስት ግብ ተጥሎ በመሰራት ላይ ነው።

በሳለፍነው የበጀት ዓመት ግብርናው  እንደቀድሞው  ባይሆንም  የስድስት ነጥብ ሰባት  በመቶ  ዕድገት ማስመዝገብ ችሏል። ይህ ዕድገት በቀላል የሚታይ አይደለም። በእርግጥ  ለተከታታይ 15 ዓመታት  በአማካኝ  ስምንት በመቶ ዕድገት ሲያስመዘግብ ለቆየ  ዘርፍ  ቅናሽ ማሳየቱ በርካቶችን አላስደሰተም።  ይሁንና ይህ በቀላሉ የማይታይ ዕድገት ነው። በሌላ መልኩ ስንመለከተውም  የአገራችን የኢኮኖሚ መዋቅር ሽግሽግ ማድረግ በመጀመሩም  የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ  ፈጣን ዕድገት እያስመዘገበ  ባለበት ሁኔታም እንኳን  ከዓመት ዓመት  በኢኮኖሚው ውስጥ  የሚኖረው ድርሻ መቀነሱ አይቀርም። የህ የመንግስት ኢኮኖሚውን ትራንስፎርም  የማድረግ ፖሊሲ ትክክለኛነትን የሚያሳይ ነው።

ባለፈው ዓመት  የአገራችንን  የኢኮኖሚ ጥንቅርና ድርሻ  ስንመለከት ግብርና  የ36.3 በመቶ፣ ኢንዱስትሪ የ25.6 በመቶ ከዚህም ውስጥ ማኑፋክቸሪን ኢንዱስትሪ የ6.4 በመቶ እና የአገልግሎት ዘርፍ የ39.3 በመቶ ድርሻ ነበራቸው። ይህ የሚነግረን  የግብርና ተጽዕኖ በአገራችን ኢኮኖሚ ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ መቀነስ ማሳየቱን ነው።  ባለፈው ዓመት  አጠቃላይ የኢኮኖሚው ዕድገት  በአማካይ የ10.9በመቶ ማደጉን ያመለክታል። ይህ ዕድገት በፈታኝ ሁኔታ ውስጥ  ተሆኖ የተመዘገበ ዕድገት ነው።

በአገራችን ረዥም ጊዜ የተከሰተና በርካታ አካባቢዎችን  ያካለለና ድርቅ  በመከሰቱ ሳቢያ  በርካታ  የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች  የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ  ፈጣን  ዕድገቱን  ማስቀጠል  አይችልም የሚል ድምዳሜ ላይ  የደረሱ ቢሆንም ኢኮኖሚያችን  እንደቀድሞው ሁሉ  ዕድገቱን  ቀጥሏል።  በእርግጥ እነዚህ  የምጣኔ ሃብት  ባለሙያዎች  የተነሱባቸው ነጥቦች በርካታ አካባቢዎች በድርቅ መመታታቸው  እና አንዳንድ   ትርፍ አምራች አካባቢዎች  ደግሞ  ሁከት በመከሰቱ  እንዲሁም  በበርካታ  አካባቢዎች ላይ የበቆሎ ምርትን  በአሜሪካን መጤ ተምች  መጠቃቱ  ነበር። ይሁንና መንግስት እነዚህን ነገሮች በተቀናጀ ሁኔታ ማለፍ በመቻሉ በችግር ውስጥ እንኳን የአገሪቱን ኢኮኖሚ እድገት ማስጠበቅ ችሏል። ይህ ትልቅ ስኬት ነው።

የባለፈው ዓመት የአገራችን  የኢኮኖሚ ዕድገት  በዕትዕ ዘመን  ለማስመዝገብ ከታቀደው የ11.1 በመቶ ጋር  እጅግ ተቀራራቢ እንደሆነ ማየት ይቻላል።   የኢፌዴሪ መንግስት የአገሪቱን ህዳሴ ማረጋገጥ የሚያስችሉ ሰፊና ጥልቅ የሆኑ  ዕቅዶችን  በማዘጋጀትና  ለተግባራዊነታቸውም ህብረተሰቡን ማሳተፍ በመቻሉ ውጤታማ መሆን ተችሏል። የቅርብ ጊዜዎቹን እንኳን  ብንመለከት የመጀመሪያውንና  ሁለተኛውን ዕትዕ የአገራችን ፈጣን ልማት ቀጣይነት እንዲኖረው እንዲሁም ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በየደረጃው ፍትሃዊ ተጠቃሚ እንዲሆን አስችሏል። በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን በግብርናው  ዘርፍ  በአገር ደረጃ  ለማሳካት የተያዘው እቅድ  ግቡን መቷል። አገራችን በምግብ ሰብል ራሷን ችላለች።

በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን ደግሞ በአገር ደረጃ  በአገር ደረጃ የተረጋገጠውን ስኬት በቤተሰብ ደረጃ  ለመድገም መንግስት ሰፊ ርብርብ በማድረግ ላይ ነው። በዘንድሮው የመኸር ምርት  ቅድመ ምርት ትንበያ እንደሚያመላክተው ከ345 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይሰበሰባል።  ይህ ቅድመ ትንበያ ስኬታማ እንዲሆን  የምርት ማሰባሰቡ ስራ ትኩረት ተደርጎበት መሰራት ይጠበቅበታል። ጥናቶች እንደሚያሳዩት በአገራችን  ከ25 እስከ 30 በመቶ የሚሆን  ምርት የሚባክነው  በምርት ማሰባሰብ ወቅት ነው።  በመሆኑም  በምርት አሰባሰብ ወቅት  የሚደርሰውን ብክነት  መቀነስ ከተቻለ  አንዳንድ የአፍሪካ አገር  ዓመታዊ ምርት ሊሆን የሚችል ምርትን በተጨማሪነት ማግኘት ይችላል። በመሆነም ሁሉም ባለድርሻ አካላት የምርት ብክነትን ለመከላከል መስራት ይጠበቅባቸዋል።  

አርሶና አርብቶ አደሩ የግብርና ባለሙያዎችን ምክርን በመከተል እንዲሁም ቴክመኖሎጂዎችን  በመጠቀም  የምርት ብክነትን በመከላከል  ምርታቸውን  በማሳደግ ተጨማሪ ገቢ ማግኘት ይችላሉ።  መንግስት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ከሚያደርጋቸው ጥረቶች  ጎን ለጎን  የምርት ብክነትን ለመቀነስ የሚያስችሉ ተግባራቶችን  በማከናውን  ላይ ነው።  የምርት ብክነትን  በመከላከል  በሚሊዮኖች የሚቆጠር  ኩንታል ማትረፍ ይቻላል። ያለብዙ ድካምና  ያለብዙ  ወጪ ጠንቃቄ  በማድረግ  ብቻ  ተጨማሪ ጥቅም ማግኘት የሚቻልበት ሁኔታ በመኖሩ እያንዳንዱ ባለድርሻ አካላት የበኩሉን ድርሻ መወጣት ይኖርበታል።  

መንግስት  የአርሶና አርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት  ለማሳደግ  ግብርናውንና ኢንዱስትሪውን ለማስተሳሰር የሚያስችሉ ተግባራትን በማከናወን ላይ ነው። በአገራችን 12 የኢንዱስትሪ ፓርኮችንና እና 17  የግብርና ምርቶችን ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች  በሁሉም  የአገሪቱ አካባቢዎች  በመገንባት ላይ ነው።  እነዚህ ኢንዱስትሪዎች  ለአርሶና አርብቶ አደሩ  ምርቶች  ትልቅ ገበያ የሚፈጥሩ ናቸው። በመሆኑም አርሶና አርብቶ አደሩ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ  ምርት መጠንን  ከማሳደግ ባሻገር ለምርት ጥራትም ከፍተኛ  ትኩረት መስጠት ይኖርባቸዋል። የአገራችን ምርቶች ከፍተኛ ውድድር የበዛበትን  የዓለም ገበያ ሰብረው ሊገቡ የሚችሉት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለምርት ጥራት ትኩረት ሲሰጡ ብቻ ነው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy