Artcles

አቅምን ያገናዘበ የግብርና ሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂ

By Admin

November 29, 2017

አቅምን ያገናዘበ የግብርና ሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂ

                                                       ቶሎሳ ኡርጌሳ

መንግስት የግብርና ሜካናይዜሽንን ለማበረታታት ከሰሞኑ አንድ ውሳኔ አሳልፏል— የግብርና መሳሪያዎች ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ። ውሳኔው ይፋ የሆነው፤ ግብርናውን የሚያዘምን ቴክኖሎጂዎች የአቅርቦት እጥረትን ለመፍታት “የአነስተኛ አርሶ አደሩን አቅምና ፍላጎት ያገናዘበ የሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂ አቅርቦት ለተቀላጠፈ እድገት” በሚል መሪ ቃል በሀገር አቀፍ ለመጀመሪያ ጊዜ የሜካናይዜሽን ቀን በምስራቅ ጎጃም ዞን ባሶ ሊበን ወረዳ በተከበረበት ነው።

የግብርና ቴክኖሎጂን የመጠቀም ፍላጎት በአርሶ አደሩ ዘንድ እያደገ መምጣቱ ተገልጿል። በዓለም አቀፍ የሜካናይዜሽን ደረጃ ለ10 ሺህ ሄክታር መሬት 66 ትራክተሮች ጥቅም ላይ መዋል እንዳለበት ቢቀመጥም፤ በሀገሪቱ አሁን ላይ ጥቅም ላይ የሚውለው 2 ነጥብ 2 ትራክተር ብቻ ነው።

ታዲያ ይህን እጥረት በዘላቂነት ለመቅረፍ ዘመናዊ የእርሻ መሳሪያዎች ከቀረጥ ነጻ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ ተወስኗል። በዓሉ በተከበረበት ስፍራ ዘመናዊ መሳሪያዎችን በመጠቀም የሚያርሱ አርሶ አደሮች ተሞከሮም ተዳስሷል። በተለይ በዓሉ የተከበረበት ስፍራ የሚገኙ አርሶ አደሮች (ባሶ ሊበን ወረዳ) ከ22 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች 10 ኮምባይነሮችን በመጠቀም በዘመናዊ ዘዴ እርሻቸውን እያከናወኑ መሆኑ ተገልጿል። የእነዚህ አርሶ አደሮች ተሞክሮ ለሌሎች አካባቢዎችም መተላለፍ ይኖርበታል።

መንግስት የእርሻ መሳሪያዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ የወሰነው በሁለተኛው የዕድገትና ትራንሰፎርሜሽን ዕቅዱ ላይ የያዘውን ትልም ለማሳካት መሆኑ ግልፅ ነው። ይህም በአንድ በኩል የአርሶ አደሩን አስተራረስ ዘመናዊ ለማድረግና ምርቱም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆን ለማስቻል ነው።

መንግስት ለእርሻ ሊውል የሚችል ሰፊና ለም መሬት እንዲሁም የአርሶ አደሩን ጉልበት በመጠቀም በሀገሪቱ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት እየሰራ ነው። የግብርና ስራ ገና ምንም ያልተነካ እምቅ ሃብት በመሆኑ ውጤት ሊያመጣ የሚችል ነው።

በዕቅድ ዘመኑ የግብርና ዘርፍ በየዓመቱ ቢያንስ በአማካይ የስምንት በመቶ ዕድገት እንዲያስመዘግብ ተደርጎ ውጤት እየተገኘበት ነው። ምርጥ ተሞክሮ ያላቸውን አርሶ አደሮች ውጤት ወደ ሌሎች አርሶ አደሮች በማስፋፋት የዋና ዋና ሰብሎችን ምርት በእጥፍ ለማሳደግ እየተሰራ ነው። በዚህም መሠረት የግብርናን ዘርፍ አማካይ ዓመታዊ ዕድገት በመሠረታዊ አማራጭ ከነበረው ስምንት በመቶ ወደ 11 በመቶ ከፍ እንዲያደርገው ለማድረግ ታስቧል። ለዚህ ደግሞ የሜካናይዜሽን እርሻ የበኩሉን ሚና ይጫወታል።

መንግሥት ለዘመናዊ ግብርና ያልተደፈረውን የአገሪቱን አርሶ አደር የአስተራረስ ዘይቤ የመለወጥን አስፈላጊነት ተገንዝቦ በቀየሰው መስመር እነሆ የሚታየ ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ ነው። አርሶ አደሩ በድርቅ በቀላሉ መጠቃት ምክንያቱም ደግሞ የዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴ አለመኖር መሆኑ ርግጥ ነው። እናም ግብርናውን ማዘመን ይገባል።

በአሁኑ ወቅት አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ኑሮው እንዲሻሻል ተገቢ ትኩረት አግኝቷል። ለዚህም በቂ ማሳያዎችንም ማቅረብ ይቻላል። መንግሥት የዘመናት ቁጭቱን አገራዊ መሠረት ባላቸው አቅጣጫዎች የመፍታት ትግሉን እያካሄደ ነው። አርሶ አደሩ ከራሱ ተርፎ ለገበያ በማምረት ተጠቃሚ የሚሆንበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ፣ ሀገሪቱም ከግብርናው ዘርፍ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ ለማድረግ የሚያስችል የለውጥ ጎዳና ላይ መሆኗን አረጋግጧል።

ርግጥ በአርሶ አደሩ እጅ እንዳለ የሚታሰበው መሬት አነስተኛ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ካለችው መሬት የሚያገኘው ምርት ዝቅተኛ ነው። ይህን መንግሥት በሚገባ በመገንዘቡ ዘርፈ ብዙ የማሻሻል ጥረቶች አድርጓል። በውጤቱም አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮችን ይዞ ለውጥ  ማምጣት አይቻልም የሚለውን አስተሳሰብ መስበር ችሏል።

አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮች ትኩረት ከመስጠት ይልቅ ለሰፋፊ ሜካናይዜሽን እርሻዎች ትኩረት መስጠትና ለውጥ ማምጣትን የሚሰብኩ ወገኖች እንዳሉ ይታቃል። ሆኖም በአርሶ አደሩ አነስተኛ ማሳ ላይ ዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴን በመጠቀም ውጤት ማምጣት ይቻላል።

እንደሚታወቀው መንግሥት አነስተኛ ይዞታ ላላቸው አርሶ አደሮች ምን ያህል ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ በተደጋጋሚ ገልጿል። ይህን የመንግሥትን ፖሊሲ ትክክለኛነት ለማረጋገጥም ተችሏል። የሚታይና አሳማኝ ውጤት ማምጣትም እንደተቻለም ከአርሶ አደሩ በላይ ምስክር የሚያሻው አይመስለኝም። ቀደም ሲል በዘመናዊ አስተራረስ ዘይቤ እየተጠቀሚ እንዳሉ የገለፅኳቸው የባሶ ሊበን አርሶ አደሮች የዚህ ጥረት አካል ናቸው።

በዚህ የዘመናዊ አስተራረስ ዘዴ ኢትዮጵያ የአርሶ አደሩን ምርታማነት በማሳደግ፣ ለምርቱ ገበያ በማመቻቸትና ከግሉ ዘርፍ ጋር ትስስር በመፍጠር ምርትና ምርታማነትን አሳድጋ ተጠቃሚ በመሆን ላይ ትገኛለች።

አርሶ አደሩ የለውጥ መስመሩን ተረድቶ በእምነት ወደ ሥራው በመግባቱ በዓመት ሁለቴና ከዚያም በላይ ለማምረት ችሏል። እንዲሁም በከርሰ ምድርና በገጸ -ምድር ያለውን የውኃ ሃብት የመጠቀም ሰፊ ተግባር ያከናወነ ነው።

በውሃ ማቆር፣ የጉድጓድ ውሃን በመጠቀም የወንዝ ውሃን ጠልፎ ጥቅም ላይ በማዋል ብዙ ርቀት ተጉዟል። በመሆኑም አርሶ አደሩ ከራሱ ፍጆታ አልፎ ለከተማው ነዋሪዎች ከፍተኛ ፍላጎት የሆኑትን ምርቶች እያቀረበ ይገኛል።

ከዝናብ ጥገኝነት በተላቀቁ አመራረት የተገኙትን ምርቶች መጠቀምም እየተቻለ ነው። የመስኖ ልማት ሥራው በበጋ የበቆሎ እሸት ተመጋቢዎች እንዲሆን አስችሎናል። ባለፉት ዓመታት ስራው በፍጥነት እያደገ ነው።

ገበያንም ማመቻቸት ተችሏል። አርሶ አደሩ በራሱ ባቋቋማቸው የአርሶ አደሮች የህብረት ስራ ዩኒየኖች አማካኝነት ምርቱን ለገበያ በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረበ ተጠቃሚ መሆን ጀምሯል። ይህም አርሶ አደሩ በየአካባቢው ምርቱን በዘመናዊ መልኩ መከወን ከመቻሉ ጋር የሚያያዝ ይመስለኛል።

የግብርናው ዘርፍም በአስተማማኝ ሁኔታ ገበያው ሳያሳስበው ምርትና ምርታማነቱን በማሳደግ ላይ ብቻ አተኩሮ ለልማት ለውጥ ሽግግሩ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥርበት ደረጃ ላይ ደርሷል ማለት ይቻላል። ይህም ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ በመሆኑ ለምርታማነቱ የላቀ አስተዋፅኦ እንዲያበረክት አድርጎታል።

መንግሥት ባስቀመጣቸው የግብርናው ዘርፍ የልማት ፕሮግራሞች፣ ስትራቴጂዎችና መርሀ ግብሮች በመጠቀም ውጤታማ የሆኑ አርሶ አደሮችን በማበረታታትና በመሸለም በርካታ ውጤታማ አርሶ አደሮችን ለማፍራት ተችሏል። ሽልማቱ ብዙዎችን አነሳስቷል። በአሁኑ ሰዓትም በርካታ ሞዴል አርሶ አደሮች እየተፈጠሩ ነው።

በእኔ እምነት በአሁኑ ወቅት መንግስት ለአርሶ አደሩ የሚያደርገውን ድጋፍ ከፍ ለማድረግ ዘመናዊ የእርሻ መሳሪያዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ መፍቀዱ ተሸላሚ አርሶ አደሮችን አቅም በፈቀደ መጠን ዘመናዊነትን እንዲላበሱ ማትጋት ይገባል።

የሀገራችን ምጣኔ ሃብት ዋነኛ ምንጭ የሆነው የግብርና ስራ አርሶ አደሩ አቅሙን ባገናዘበ ሁኔታ በዘመናዊ የአመራረት ስልት ተጠቅሞ ምርትና ምርታማነትን እንዲያሳድግ በመደረጉ የሞዴል አርሶ አደሮች ምርጫ ከዚህ አኳያ መታየት ይገባዋል እላለሁ። ምክንያቱም እንዲህ ዓይነቱን የማትጊያ መንገድ መጠቀም በአንድ በኩል የአርሶ አደሩ አቅም በፈቀደ መጠን የተያዘውን የማስፋት ስትራቴጂ እውን የሚያደርግ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ ምርትና ምርታማነትን በመጨመር የሀገር ውስጥ ፍጆታን ከመሸፈን ባሻገር በተወዳዳሪነት የውጭ ገበያን መፍጠር ስለሚስችል ነው።