Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

አንዱ ላጠፋው ሌላው ተጠያቂ ሊሆን አይችልም!

0 379

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

አንዱ ላጠፋው ሌላው ተጠያቂ ሊሆን አይችልም!

ዳዊት ምትኩ

የአገራችን ህገ መንግስት አንቀፅ 51 እና 52 ላይ የፌዴራልና የክልል መንግስታት ስልጣንና ተግባር በግልፅ ተብራርቶ ተቀምጧል። በዚህም መሰረት የፌዴራል መንግስት ከክልሎች በተሰጠው ሰልጣን መሰረት ተግባርና ሃላፊነቱን ይወጣል። ፌዴራል መንግስቱ ያለው የስልጣን ወሰን ተለይቶ ተቀምጧል። ይህ ስልጣን በአብዛኛው በአገር አቀፍ ደረጃ እውን የሚሆን ነው።

ህገ መንግስቱ ለፌዴራል መንግስት የሰጠው ስልጣን በክልሎች መከበር እንዳለበት፣ የክልሎችም ስልጣን በፌዴራል መንግስቱ መከበር እንዳለበት ደንግጓል። ለምሳሌ በአንቀፅ 52 (ሀ) ላይ ራስን በራስ ማስተዳደርን ዓላማ ያደረገ ክልላዊ መስተዳደር እንደሚያዋቅር፤ የህግ የበላይነት የሰፈነበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንደሚገነባ፤ ህገ መንግሥቱን እንደሚጠብቅና እንደሚከላከል በግልፅ አስቀምጧል።

የፌዴራል መንግስት ችግሮች ሲፈጠሩ ክልሎች ከአቅማቸው በላይ ሆኖ እገዛ ካልጠየቁት በእነርሱ የስልጣን ተዋረድ ውስጥ ጣልቃ ሊገባ አይችልም። ይህም ህገ መንግስቱ መብት ብቻ ሳይሆን ተጠያቂነትን አብሮ የሰጠ መሆኑን ያሳያል።

ፌዴራል መንግስቱ በአገር አቀፍ ደረጃ በህገ መንግስቱ መሰረት የተሰጠውን ስልጣን በተገቢው ሁኔታ ተፈፃሚ ካላደረገ እንደሚጠየቀው ሁሉ፤ የክልል መንግስታትም በክልላቸው ውስጥ ለሚከናወኑ ችግሮች ተጠያቂ መሆናቸው አይቀርም። እናም አንዱ ለሚያጠፋው ሌላው ተጠያቂ ሊሆን አይችልም። በመሆኑም የፌዴራል መንግስቱ ላጠፋው ክልሎች፣ ክልሎች ላጠፉት ደግሞ የፌዴራል መንገስ ተጠያቂ የሚሆንበት አሰራር የለም።

በፌዴራል ደረጃ የሚከሰቱ የህግ የበላይነት የማስከበር ሂደት በክልሎች ሊተገበር አይችልም—ፌዴራል መንግስቱ በህገ መንግስቱ ላይ እንደተጠቀሰው በውክልና እንዲያስፈፅሙ ካልጠየቃቸው በስተቀር። የክልሎችም ጉዳይ እንዲሁ።

እናም ህገ መንገስቱ ሁሉም በልኬታው የሚጠየቅበትን አሰራር የዘረጋ መሆኑን መገንዘብ የሚገባ ይመስለኛል። እንደሚታወቀው የህግ የበላይነትና የተጠያቂነት አሰራር በደዴሞክራሲያዊ አገር ውስጥ የግድ የሚሉ አሰራሮች ናቸው። እነዚህ አሰራሮች ደግሞ በፌዴራሉም ይሁን በክልል መንግስታት ላይ ተፈፃሚ የሚሆኑ ናቸው። አንዱ የሚፈፅመው ሌላው የሚተዋቸው አይደሉም።

እንደሚታወቀው በፌዴራልም ይሁን በክልል ደረጃ የመንግስት ግልፅነትና ተጠያቂነት ይበልጥ መስፈን ይኖርበታል። የሁሉም መንግስታት አሰራሮች ግልፅነትና ተጠያቂነት ባለው መንፈስ እውን መሆን አለበት። ይህ ግልፅነትና ተጠያቂነት የሀገሪቱ ህዝቦች መንገስት እንደያከናውነው የሚፈልጉት ጉዳይ ነው።

እናም መንግስት ሁሌም በአሰራሮቹ ላይ ግልፅነትንና ተጠያቂነትን በማስፈን የህዝቦችን ህገ መንግስታዊ ፍላጎት እውን ማድረግ ይጠበቅበታል። ይህም በመሆኑ በየጊዜው ለህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት የየወራት ስራዎቹን ያቀርባል። ያስገመግማል። መጠንከርና መሻሻል በሚገባቸው ጉዳዩች ላይ የሚሰጡትን አስተያየቶችንም ይቀበላል።

የመንግስት የተጠያቂነት አሰራር የዴሞክራሲ አንዱ መገለጫ ነው። በዴሞክራሲ ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤት የሆነው ህዝብ አስተሳሰብ፣ በጊዜ ሂደት ለምርጫ የሚሰጠው ትርጉም የሚያድግና የሀገሪቱ የፖለቲካ ምህዳር እንዲሁም እየሰፋ የሚመጣ ብሎም ተወዳዳሪ ፓርቲዎች በምርጫ የሚኖራቸው ተሳትፎ እየጎለበተ የሚሄድበት አውድ ነው።

ይህ ተጨባጭ ሁኔታም በጅምር ላይ ያለ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እና ረዥም ዕድሜን ያስቆጠረ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ በምንም መልኩ አንድ ሊሆን እንደማይችሉ የሚያመላክት ነው።

እናም የሀገራችን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ስንመለከተው ሂደቱ 26 ዓመታትን ብቻ ያስቆጠረ ጅምር በመሆኑ ምንም ዓይነት ተግዳሮቶች የሉበትም ለማለት የሚያስደፍር አይመስለኝም። አሁን የምንገኝበት ደረጃ የህዝብ አስተሳሰብ አድጓል፣ የሀገሪቱ የፖለቲካ ምህዳርም በሚፈለገው መጠን ሰፍቷል ለማለት አይቻልም።

እናም ሀገሪቱን በመምራት ላይ የሚገኘው ፌዴራል መንግስትም ይሁን ክልሎች የህዝቦች የዘመናት ጥያቄ የሆነውን ዴሞክራሲ በጥልቀት ማስፋትና ማጎልበት ይጠበቅባቸዋል። የአሰራሩን ተጠያቂነትና ግልፅነት በዚያኑ ልክ ለህዝቡ ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል። ከዚህ አኳያ ክልሎችም በክልል ደረጃ ፌዴራል መንግስትም በፌዴራል ደረጃ ለሚያከናውኗቸው ስራዎች ተጠያቂነት አብሮት ያለ መሆኑን ሊገነዘቡ ይገባል።

በተለይ በአሁኑ ወቅት በየክልሉ ለሚታየው የፀጥታ መደፍረስ ችግር ሁሉም በህገ መንግስቱ መሰረት ሃላፊነት ወስደው መስራት ይሞርባቸዋል። የህግ የበላይነት ካልተከበረ እዚህ ሀገር ውስጥ የሚካሄዱትና ተጨባጭ ውጤት እያስገኙ ያሉት ተግባሮች እንቅፋት ይገጥማቸዋል።

በህግ ካለተደነገገ በስተቀር በየትኛውም ሀገር ውስጥ የሚኖር ዜጋ የህግ የበላይነትን በመፃረር እንዳሻው ሊኖር አይችልም። ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደሞከርኩት የዜጎች ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ በህግና ስርዓት የሚመራ ካልሆነ የትኛውም ወገን የመኖር ዋስትና ሊኖረው አይችልም። በመሆኑም ማንኛውም ድርጅት፣ አመራር ወይም ዜጋ የሚንቀሳቀሰው ህግ ባለበት ሀገር ውስጥ በመሆኑ ህገ-ወጥ ተግባርን ከከወነ የህግ የበላይነት ተፈፃሚ እንደሚሆንበት ማወቁ ያስፈልጋል።

በፌዴራል ደረጃም ይሁን በክልሎች ውስጥ የህግ የበላይነት ሊጠበቅ ይገባል። የህግ የበላይነት ልዕልና ካልተጠበቀ በሀገሪቱ የሚረቀቁ ማናቸውም ህጎች በሚፈለገው መጠን ገቢራዊ ሊሆኑ አይችሉም። ህጎች በሚፈለገው መጠን ገቢራዊ ካልሆኑና በቸልታ የሚታለፉ ከሆኑ የዜጎች መብቶች ሊሸራረፉ ይችላሉ።

የመብት መሸራረፎች ደግሞ አንዱ እንዳሻው እንዲፈነጭ የሚያደርገው ሲሆን፤ ሌላው ደግሞ ህግና ስርዓትን አክብሮ እንዲንቀሳቀስ ያደርገዋል። ይህም ህግና ስርዓትን የሚያከብረው ዜጋ ሌላውን በመመልከት ወደ ተሳሳተ መንገድ ሊያመራ ይችላል። በመሆኑም ይህን ችግር ለመቅረፍም የህግ የበላይነት ልዕልና ገቢራዊ መሆን አለበት። ለዚህ ደግሞ ማናቸውም ግለሰብ ይሁን ቡድን የህግ የበላይነትን ተላልፎ ለፈፀመው ተግባር ተጠያቂ እንዲሆን ማድረግ ይገባል።

ስለሆነም በክልሎች ውስጥ የሚታዩ ሁከቶች የመቆጣጠር ሃላፊነት የክልሎች ነው። በክልሎች ውስጥ ለሚከናወኑ የህግ ጥሰቶች፣ የሰው ህይወት መጥፋትና የንብረት መውደም ሁኔታዎች ተለይተው መታወቅ ይኖርባቸዋል። ለሁከቶቹ መፈጠር የትኛው አመራር፣ ቡድን ወይም ዜጋ ተሳታፊ ሁኖ አሉታዊ ሚና እንደተጫወተም በዝርዝር ይዞ የተጠያቂነት አሰራር እውን መሆን አለበት። አንዱ በሌላኛው ላይ ጣቱን እየቀሰረ የዜጎች ህይወት ሲቀጠፍና ንብረታቸው ሲወድም ዝም ተብሎ መታየት የለበትም። እናም ተገቢውን የህግ የበላይነት የማስከበር ስራ በማከናወን የተጠያቂነት አሰራርን እውን ማድረግ ይገባል እላለሁ።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy