Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

አፈናንና ዴሞክራሲያዊ አንድነትን ለይቶ የሚገነዘብ ህዝብ!

0 377

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

አፈናንና ዴሞክራሲያዊ አንድነትን ለይቶ የሚገነዘብ ህዝብ!

                                                         ደስታ ኃይሉ

በደርግ ሥርዓት ወቅት የኃይል አንድነት ለመፍጠር የተደረገው ሙከራ ያስከተለውን ጉዳትና ከአዲሲቷና ዴሞክራሲያዊ አንድነትን ከምትቀበለው ኢትዮጵያ መፈጠር የተገኘውን ጠቀሜታ ከኢትዮጵያ ህዝብ በላይ እማኝ ሊኖር አይችልም። ጊዜያዊ ግጭቶች ሲከሰቱ ግጭቶቹን የሚያከሸፈው መሳሪያ የታጠቀ ኃይል ሳይሆን ራሱ ህዝቡ መሆኑንና ይኽውም የሰላም እጦት የሚያስከትለውን መዘዝ ስለሚረዳ ነው።

በአፈና ሥርዓት ወቅት የኢትዮጵያ ህዝብ ተገድሏል፣ አካሉ ጎድሏል፣ ተንገላቷል። ወጣት ልጆቹ እየታፈሱ ወደ ግዳጅ ብሄራዊ ውትድርና ተግዘዋል። እንግልትና ስቃይን አይተዋል። በዚህም በጦርነት አበሳ ውስጥ እንዲያልፉ ተደርጓል። ወጣቶች በመማሪያና በመስሪያ አፍላ ጉልበታቸው ወቅት ጠብ-መንጃ ተሸክመው የጥይት አረር ሲሳይ እንዲሆኑ ተደርገዋል።

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ከሀገራቸው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ህይወት ተገልለውና ተረስተው በባይተዋርነት ለመኖር የተገደዱበት አድሎአዊና ፍትህ አልባ ሁኔታ ውስጥ እንዲያልፉ ተደርገዋል።

ዛሬ ግን ይህ ሁኔታ ሙሉ ለሙሉ ተቀይሮ ዴሞክራሲያዊ አንድነት እንዲጎለብት ተደርጓል። በአገሪቱ ተንሰራፍቶ የኖረውን የተዛባ ግንኙነት በመፋቅ አዲስ ኢትዮጵያዊ ማንነት ለመገንባት የሚያስችሉ የማንነቶች እኩልነት ማረጋገጥ፣ ሁሉም ዜጎች ኢትዮጵያን በመገንባት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ማድረግ፣ በአካባቢ ጉዳዮቻቸው ላይ ወሳኝ የሚሆኑበትን የራስ አስተዳደር ማረጋገጥ በአጠቃላይ ከአገሪቱ ልማት ተመጣጣኝ ጥቅም እንዲያገኙ ማድረግ ሕብረ ብሄራዊ ፌዴራል ሥርዓቱ የተነሳበት ዋናው መሠረታዊ አስተሳሰብ ነው፡፡

በመላ ኢትዮጵያ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የተከበሩበት፤ ለዴሞክራሲያዊ አንድነት መሠረት የተጣለበት፤ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ማንነት፤ ውበትና ህብረት የታየበት ብሎም የሥልጣን ባለቤት የተረጋገጠበት፤ የልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ጉዞ የተጀመረበት መሠረቱ ይኸው ህገ መንግሥት ነው፡፡

የህገ መንግሥቱ ድሎችና ውጤቶች ከመቼውም በላይ ተስፋፍተው፤ የዜጎች ማንነትና ባህላዊ እሴቶች ጎልተው ወጥተው፤ መልካም ተሞክሮዎችም ይበልጡን ጎልብተው የአንድነታችንና የጥንካሬያችን መገለጫ ሆነው እንዲቀጥሉ ዜጎች እጅ ለእጅ ተያይዘው ጉዟቸውን ቀጥለዋል፡፡

በእነዚህ ጊዜያት የክልሎችን እኩል ተጠቃሚነት በማረጋገጥ በኩል በተለይም በልማትና ዕድገት አፈጻፀም ረገድ በጎ እርምጃዎች ተወስደው መልካም ውጤቶች ታይተዋል፡፡ በህገ መንግሥት በተደነገገው እኩል የመልማት መብት በመጠቀም በሁሉም ክልሎች በተነፃፃሪ ፈጣን የሚባል ልማትና ዕድገት ተመዝግቧል፡፡

ህብረ ብሔራዊ የፌዴራል ሥርዓት ከአገሪቱ ተጨባጭ ታሪካዊ ሁኔታ በመነሳት በህገ መንግሥቱ ተደንግጎ ተግባራዊ መሆን ጀምሯል፡፡ ህብረ ብሔራዊ የፌዴራል ሥርዓቱ ያለፉት አፋኝ መንግሥታት የቀበሩትን የማንነትና የምጣኔ ሀብት ተጠቃሚነት ጥያቄን በአስተማማኝ ደረጃ መመለስ ችሏል፡፡

በመፈቃቀድና በእኩልነት ላይ የተመሠረተ አንድነትን ለማስቀጠልና ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ቃል ኪዳን ያሰሩበትን አንድ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የመገንባት ጉዳይ በህዳሴው እየተቀላጠፈ ይገኛል፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱ ባልተማከለ አስተዳደር ክልሎች ራሳቸውን በራሳቸው በማስተዳደር ማዕቀፍ ውስጥ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዲኖራቸው አስችሏል፡፡

በዚህም ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊና ማኅበራዊ ተሳትፏቸውና በየደረጃው ተጠቃሚነታቸው ጎልብቷል፡፡ አካባቢያቸውንም በማልማት ለአገር ብልፅግናና እድገት ከፍተኛ ደርሻ እያበረከቱ ይገኛሉ፡፡ የክልሎችን የእኩል ተጠቃሚነት በማረጋገጥ አንፃር ደግሞ የልማትና ዕድገት አፈጻፀም በክልሎች እኩል ተጠቃሚነት እየተፈፀመ መሆኑን የሚያረጋግጥ እውነታ ነው፡፡

የክልሎችን የእኩል ተጠቃሚነት በማረጋገጥ አንፃር ልማታዊው መንግሥት ግልፅ የሆኑ ምጣኔ ሀብታዊ ህጎችን፣ የልማት ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ነድፎ በየአካባቢው ተጨባጭ እቅድ እየተመነዘሩ የሚፈፀሙበትን ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ በአፈጻፀም ሂደት የተገኙ በጎ ልምዶችም እየተቀመሩ በአገሪቱ ሁሉም አካባቢዎችና ለምልዓተ ሕዝቡ የሚደርስበት ስልቶች ተቀይሰዋል፡፡

የልማት ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን በመተግበር ዙሪያ የሚያጋጥሙ ማነቆዎች የሚለዩበትን የአሠራርና የአደረጃጀት ጥያቄዎች ካለፉት ልምዶች በመነሳት እንዲፈተሹና እንዲስተካከሉ በማድረግ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የላቀ ተሳትፎና ተጠቃሚነት እየተረጋገጠ ይገኛል፡፡

ክልሎች በገጠርና ከተማ የልማትና መልካም አስተዳደር ዕቅዶችን በመንደፍና ሕዝቦቻቸውን ዋናው ፈፃሚ አካል በማድረግ ባለፉት ስምንት ዓመታት በአማካይ ለተመዘገበው ከሁለት አኃዝ በላይ እድገት የድርሻቸውን እንዲያበረክቱ አግዟል፡፡

የፌዴራል መንግሥትም ክልሎችን ከክልሎች ብሎም ከአዋሳኝ አገሮች ጋር የሚያገናኙ መንገዶችን በመስራትና ፈጣን የቴሌኮም አገልግሎቶችን በማዳረስ ላይ ይገኛል፡፡ እንዲሁም የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትን በማፋጠን፣ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎትንና የአገር ውስጥና የውጭ አገር የገበያ ትስስርን በመፍጠርና በማጎልበት አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የመገንባቱ ግብ በአስተማማኝ ሁኔታ እየተተገበረ  ይገኛል፡፡

በአገሪቱ ያሉ ክልሎች እርስ በርስ በመደጋገፍና ልምዶችን በመለዋወጥ የሚያደርጉት የጎንዮሽ ይሁን የተዋረድ ግንኙነት ለእኩል ተጠቃሚነትና በተመጣጣኝ ልማትና እድገት ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡

ይህም የልማትና የመልካም አስተዳደር ማነቆዎችን በመፍታትና በጎ ልምዶችን በማስፋፋት ሂደቱን ማስቀጠል ከተቻለ አጭር በሚባል ጊዜ ውስጥ አገሪቱ መካከለኛ ገቢዎች ካላቸው አገራት ተርታ እንድትሰለፍ ማድረግ ይቻላል፡፡

አገሪቱ ከተዘፈቀችበት ድህነትና ኋላ ቀርነት በባሰ ደረጃ ስር ሰዶ የቆየባቸው አካባቢዎችም ነበሩ፡፡ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ ህገ መንግሥት ላይ በግልፅ እንደተደነገገው እነዚህ ክልሎች በአሁኑ ወቅት ፖለቲካዊ መብቶቻቸውን እንደተቀሩት የአገሪቱ ክልሎች አስከብረዋል፡፡

ይህም ራሳቸውን በራሳቸው ከማስተዳደር ጀምሮ አካባቢያቸውን በማልማትና ሕዝቦቻቸውን የሠላም፣ የልማት የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ተጠቃሚዎች ለማድረግ እየተረባረቡ ይገኛሉ፡፡ ማንም ጤነኛ አዕምሮ ያለው ዜጋ በግልጽ አይቶ መፍረድ እንደሚቻለው በእነዚህ ክልሎች ዛሬ ማህበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ተቋማትና የመሠረተ ልማት አውታሮች በሚያስደንቅ ሁኔታ እየተገነቡ ነው፡፡ ይህ የሆነውም እዚህ ገር ውስጥ በተፈጠረው ዴሞክራሲዊ አንድነት ነው፡፡ ዛሬ ዴሞክራሲያዊ አንድነቱን ያላጣጣመ የአገራችን ህዝብ የለም፡፡ ህዝቡ ትላንትን በሚገባ ስለሚያውቅ ዛሬ ያገኘውን ጠቀሜታ ተገንዝቦ አንድነቱን ይበልጥ እያጠናከረ ይገኛል፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy