Artcles

ኢህአዴግ ሆይ ወዴት ነህ?

By Admin

November 25, 2017

ኢህአዴግ ሆይ ወዴት ነህ? አባ መላኩ ጭፍን ተቃውሞ ወይም ድጋፍ ለአገራችንም ይሁን ለህዝባችን የሚበጅ የፖለቲካ አካሄድ አይደለም። ሁሉም በልክ ብልክ ብናደርገው መንግስት በአግባብ ራሱን እንዲያይና ለአገርም ሆነ ለህዝብ የተሻለ ተግባራትን እንዲያከናውን ያስችለዋል። ኢህአዴግ ባለፉት 26 ዓመታት በአገራችን ዘርፈ ብዙ ስኬቶችን ማስመዝገብ እንደቻለ ሁሉ የፈጸማቸውም ስህተቶችም እንዳሉ አሌ አይባልም። ኢህአዴግ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የከፍታ መንገድን አስጨብጧል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢህአዴግ በሚፈጽማቸው አንዳንድ ተራ ስህተቶች አንድ ሺህ ስኬቶቹ በነጠላ ስህተቱ ሲጣፋበት እየተመለከትን ነው። እውነት እንነጋገር ከተባለ ኢህአዴግ ከነድክመቱም ቢሆን የአገራችን የስኬት ምንጭ ነው።

ኢህአዴግ ባከናወናቸው ድንቅ ተግባራት ሳቢያ አገራችን በታሪኳ አይታው ወደማታውቀው አዲስ የከፍታ ዘመን በመውጣት ላይ ነች። ይሁንና ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ኢህአዴግ የቀድሞው ጥንካሬው እየከዳው ለውጡን በአግባብ መምራት እየተሳነው ይመስላል። በዚህም በአገራችን ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ በርካቶች ህይወታቸውን እያጡ፣ ሚሊየኖች እየተፈናቀሉ፣ ንብረታቸውን እየተዘረፉ ያለበት ሁኔታ እየተከሰተ ነው።

ኢህአዴግ ባለፉት 27 ዓመታት ኢትዮጵያን በስኬት ጎዳና መርቷታል። አዲሲቷ ኢትዮጵያ ህገመንግስታዊና ጠንካራ መንግስት እንዲኖራት አድርጓል፤ የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ በማድረግ ነጻነትና እኩልነታቸው እንዲረጋገጥ አድርጓል፤ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በመገንባት በአገራችን ዘላቂ ሰላም አረጋግጧል፣ በዚህም ሳቢያ ልማት በመፋጠኑ በተከታታይ ለ15 ዓመታት ባለሁለት አሃዝ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በማስመዝገብ ሁሉም በየደረጃው ፍትሃዊ ተጠቃሚ የሚሆንበት ሁኔታ አመቻችቷል፤ በዚህም ድህነትን ከግማሽ በላይ መቀነስ ችሏል፤ በዲፕሎማሲው ረገድም ስኬታማ ተግባራትን ማከናወን በመቻሉ አገራችን በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም ዓቀፍ ደረጃም ተሰሚነቷ እጅጉን አድጓል።

ኢህአዴግን ከትጥቅ ትግሉ ጀምሮ እስከ አገርና ህዝብ መምራት ደረጃ ውጤታማ እንዲሆን ካደረጉት አበይት ምክንያቶች አንዱና ቀዳሚው ነገር የድርጅቱ መርህ መሰረት የሚያደርገው የህዝብ ፍላጎትንና የህዝብ ድጋፍ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ መሰረቱ የኢህአዴግ የቆየ ጠንካራ የግምገማ ባህሉ ነው፡፡ የድርጅተቱ ጠንካራ የግምገማ ባህል አባላቱ ጥሩ ስነ ምግባር እንዲላበሱ፣ ተጠያቂነትን እንዲያውቁና የተጣለባቸው ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ ከሚያደርጋቸው ምክንያቶች ቀዳሚውና ዋንኛው ጉዳይ ይመስለኛል፡፡ የድርጅቱ ውስጠ ዴሞክራሲያዊነት የሰፈነበት፤ የብዙሃን ድምጽ ተቀባይነት ያለበት ድርጅት ነው። በፓርቲው የውስጥ አሰራር የግለሰቦች ሃሳብ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የሚንሸራሸርበት ሃሳብ በነፃነት የሚፋጭበት፤ ይሁንና መቼም ቢሆን የብዙሃኑ ድምጽ የበላይነት የነገሰበት ፓርቲ ነው፡፡ ይሁንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጠንካራው የኢህአዴግ ቤት አዳዲስ ነገሮች (ጠቃሚ ያልሆኑ) እየተመለከትን ነው። ለማንም የማይበጁ አንዳንድ መደበላለቆች በፓርቲው ቤት እያስተዋልን ነው።

በአገራችን በበርካታ አካባቢዎች መሰረታዊ እሴቶቻችን እየተሸረሸሩ፤ በአንጻሩ ደግሞ የጥበትና ትምክህት አስተሳሰቦችና ተግባሮች እየነገሱ ናቸው። ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት የኢህአዴግ መሰረታዊ መለያው ከህዝባዊ አመለካከቱና ህዝባዊ ወገንተኝነቱ ነው። ኢህአዴግን እዚህ ያደረሰው ለህዝብ ፍላጎት ተገዢ መሆኑና ለህዝብ ጥቅም ቅድምያ መስጠቱ ናቸው። ባለፉት 26 ዓመታት በአገራችን በየዘርፉ አንጸባራቂ ድሎች ተመዝግበዋል። የህዝቦችን ሰብዓዊ መብቶች ሙሉ ለሙሉ በሚባል መልኩ ተረጋግጠዋል፣ ከነእጥረታቸውም ቢሆን ዴሞክራሲያዊ መብቶች ተረጋግጠዋል፣ ዓለምን ያስደመመ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት በመመዝገቡም ፍትሃዊ ተጠቃሚነት በመረጋገጥ ላይ ሲሆን፤ መሕብራዊ መገልገያዎችም ለአብነት መንገድ፣ መብራት፣ ጤና፣ ትምህርት፣ ቴሌ፣ እጅግ በከፍተኛ ሁኔታ ተስፋፍተዋል። በዚህም አገራችን ተስፋ ሰጪ የማንንም ቀልብ ሊስብ የሚችል አገር በመሆን ላይ ነች። ከዚሁ ጎን ለጎንም አንዳንድ ግድፈቶች ብቅ ብቅ በማለት ላይ ናቸው።

በዴሞክራሲያዊ መዓከላዊነት የሚታወቀው ኢህአዴግ፣ የስኬት ምንጭ የሆነው ኢህአዴግ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በምናስተውለው ነገር ብዥ እያለብን ነው። በእህትማማች ድርጅቶች መካከል መደማመጥና መከባበር ችላ ተብሎ፤ እርስ በርስ የመጠራጠር፣ በጋራ ለተደረሰባቸው ውሳኔዎች ተግባራዊነት መንሸራተት፣ አባላቱ ብቻ ሳይሆን አንዳንድ ከፍተኛ አመራሮች አገርንና ህዝብን የሚጠቅም ተግባር ከማከናወን ይልቅ ለርካሽ ተወዳጅነት መሯሯጥ እንዲሁም ቁጥራቸው ቀላል የማይባል አመራሮች ጠበው ጠበው በክልሎቻቸው ጉዳይ ብቻ ላይ መጠመድ ሳይሆን አልፎ አልፎም፤ በየጎጦቻቸው ጉዳይ ተሸጉጠው ተመልክተናል።

አንዳንድ የድርጅቱ አመራሮችና አባላት ደገሞ ራሳቸውን ከህዝብ በላይ አድርገው በመመልከት በግል ጥቅም ናወዘው ይህን ጥፋታቸውን ለመደበቅ ሲሉ በብሄርና ሃይማኖት ካባ በመጀቦን ከተጠያቂነት ለማምለጥ ሲሯሯጡ እየተመለከትን ነው። የድርጅቱ መሰረት የሆነው አብዮታዊ ዴሞክራሲ አስተሳሰብ በአዳዲስ አባላት እንዲሰርጽ ከማድረግ ይልቅ የራስን ጥቅም ለማረጋገጥ መሯሯጥ በኢህአዴግ ቤት እየተመለከትን ነው። ኢህአዴግ ሆይ የሚያስችል ኔትዎርክ ለመገንባት ጥረት በመደረግ ላይ ነው።

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ለጥበትና ትምክህት ሃይሉ መጠቀሚያ የሚሆኑ የመልካም አስተዳደር ክፍተቶች እያስተዋልን ነው። ህዝባዊነት እየተሸረሸረ ህዝበኝነት (ርካሽ ተወዳጅነት) እየገነገነ እንደመጣ በርካታ አስረጂ ማቅረብ ቢቻልም ኢህአዴግ ራሱ “በተሃድሶ” መድረክ የነገረንን ሂሶች ማስታወስ በቂ ይመስለኛል። ለአብነት በድርጅቱ አመራርና አባላት ዘንድ በአቋራጭ የመበልጸግ ስሜትና ተግባር መታየት፣ ቡድንተኝነት፣ ዘረኝነት፣ አድሏዊነት፣ ጎጠኝነት፣ ጥበትና ትምክህት ተግባርና አስተሳሰብ መገንገን፣ ከህግ የበላይ የመሆን አካሄዶች ወዘተ በእነዚህ ሳቢያ ህብረተሰቡ በመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲማረር ሆኗል ሲል ራሱ ኢህአዴግ ነግሮናል።

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ አንዳንድ ሁኔታዎች መልካቸውን በፍጥነት እየቀየሩ መምጣት ጀምረዋል። የትምክህትና ጠባብነት አስተሳሰቦችና ተግባሮች በድርጅት አባላት ብቻ ሳይሆን በከፍተኛ አመራሩ በራሱ መታየቱ ሁኔታዎችን የከፉ እያደረጋቸው ነው። የህግ የበላይነት በተረጋገጠባት አገር፣ ከእኛ አልፎ ለምስራቅ አፍሪካ መከታ ይሆናል የምንለው ጠንካራ ሰራዊት ባለባት አገር ሰዎች በዘራቸው ብቻ በተደራጁ ሃይሎች በጠራራ ጸሃይ የሚገደሉበት፣ የሚደበደቡበት፣ የሚዘረፉባት፣ አሊያም ታስረው የሚሰቃዩበትን ሁኔታዎች እየተመለከትን ነው። እንዲህ ያለ መረን የጣ ድርጊት የተፈጸመው በሩዋንዳ፣ ብሩንዲ ወይም ሶማሊያ ሳይሆን ጠንካራውና ስኬታማው ኢህአዴግ ገዢ ፓርቲ ሆኖ በሚያስተዳድራት አገር ኢትዮጵያ ነው። ይህን ስመለከት ኢህአዴግ ሆይ ወዴት ነህ ለማለት ወደድኩ? አዎ ኢህአዴግ ሆይ ወዴት ነህ?