ከመበተን ያዳነን ፌዴራላዊ ስርዓት
ዘአማን በላይ
አዲሲቷ ኢትዮጵያ እየተከተለች ያለችው ፌዴራላዊ ስርዓት እንኳንስ አሁን ቀርቶ ያኔ በደርግ ስርዓት መገርሰስ መባቻ ላይ በብሔር የተደራጁና የታጠቁ ኃይሎች በነበሩበት ወቅት እንኳን ሀገሪቱን ከብተና ያዳነ ነው። ያኔ አንዳንድ ሟርተኞችና የውጭ መገናኛ ብዙሃን “ኢትዮጵያ ተበታተነች፣ በቃ አለቀላት!” እያሉ ቢያሟርቱም፤ ስርዓቱ በወቅቱ የነበረውን አደጋ ህዝቡን ከጎኑ በማሰለፍ ተቋቁሞት አልፏል።
ዛሬም እየተፈቱ የሚገኙና ሊፈቱ የሚገባቸው ተግዳሮቶች ሀገራችን ውስጥ ቢኖሩም ቅሉ፤ እነዚህን ተግዳሮቶች ፌዴራላዊ ስርዓቱ ያልፈጠራቸው በመሆናቸው ልክ እንደ ያኔው ከህዝቡ ጋር ሆኖ እየፈታቸው ነው። ያልተፈቱ ጉዳዩች ካሉም አሁንም ከህዝቡ ጋር በመሆን እንደሚፈታቸው በርግጠኝነት መናገር የሚቻል ይመስለኛል። ምክንያቱም ሀገራችን እየተከተለችው ያለችው ፌዴራላዊ ስርዓት ማናቸውንም ጉዳዩች ከህዝቡ ጋር መክሮና ዘክሮ የመፍታት የካበተ ባህልን ያዳበረ በመሆኑ ነው።
እንደሚታወቀው ወታደራዊው የደርግ ስርዓት በወደቀ ማግሥት ሟርተኞች ስለኢትዮጵያ መጻዒ ሁኔታ ሲተነብዩ ያላሉት ነገር አልነበረም። ‘ኢትዮጵያ የሶማሊያና የዩጎዝላቪያ ዕጣ ፋንታ ይገጥማታል፤ መበታተኗም አይቀሬ ይሆናል’ ሲሉም ተንብየዋል። እውነታው ግን የተገላቢጦሽ ነው የሆነው። በወቅቱ ኢሕአዴግና የሽግግር መንግስቱ በያዙት የተጠና መስመር አገሪቱን ከብተና ታድገዋታል። ይህ ተግባራቸውም ዛሬ ኢትዮጵያ በዓለም ላይ የልማት ለውጥ አብነት እንድትሆን መሠረት ጥለውላታል። ትናንት ከህዝብ ጋር ሆነው በቀየሱት መንገድ ተመርተው ዛሬ ለሁለንተናዊ ለውጥ እንዳበቁን ሁሉ፤ ነገም በአሁኑ በአገራችን አንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋሉት ተግዳሮቶች ነገ ደግሞ እነዚህ ተግዳሮቶች ተፈትተው ለህዳሴያችን አበቁን ማለታችነ የሚቀር አይመስለኝም።
ሀገራችን ላለፉት 26 ዓመታት በሰላም፣ በልማትና በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሂደት ከፍተኛ እመርታ ማስመዝገቧ አያከራክርም። ለዚህም የምትመራበት የፖለቲካ መስመር ትክክለኛነት ተጠቃሽ ነው። ይህ ብቻ አይደለም! በህገ መንግስቱ ውስጥ የሰፈሩት የዴሞክራሲና የልማት ድንጋጌዎች ጭምር እንደሆነም ይታመናል። በቅድሚያ ህገ መንግሥቱ በሰፊው የሕዝብ ተሳትፎ የተዘጋጀ ነው። በህገ መንግሥቱ ውስጥ የሰፈሩት ድንጋጌዎችም በጋራ ጉዳዩች ዙሪያ መግባባት እንዲመጣ ጉልህ ሚና ነበራቸው።
በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሥር እየሰደደ እንዲሄድ ብሎም አገሪቱ ፈጣን ወደሆነ የልማት ጐዳና እንድትገባ ለዴሞክራሲና ልማት ድንጋጌዎች ተግባራዊነት ቁርጠኛ መንግሥት መኖር ውጤቱን አፋጥኖታል። የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት አገሪቱ ፍትሃዊ የምጣኔ ሀብት ዓላማዎችን ማራመድ እንዳለባት በግልጽ ይደነግጋል።
ይህን ዓላማ ለማረጋገጥ መንግሥት ዜጎች በአገሪቱ የሚገኘውን ሀብት በፍትሃዊነት ተጠቃሚ የሚሆኑበትን አሰራር ቀይሶ ተፈጻሚ እያደረገ ይገኛል። በልማት ወደ ኋላ የቀሩ ክልሎች በመንግሥት ልዩ እገዛ ተደርጐላቸው ጭምር የልማቱ ተጠቃሚነታቸው እየተረጋገጠ መጥቷል። ህገ መንግሥቱም በግልጽ ለነዚህ መብቶች ዋስትና ሰጥቷል። መንግሥት መሬትንና የተፈጥሮ ሃብቶችን በህዝብ ስም በይዞታው ሥር በማድረግ ለዜጎች የጋራ ጥቅምና ዕድገት የማዋል ኃላፊነትን ተቀብሎ ውጤት ማምጣት ችሏል።
በደርግ ሥርዓት ማንኛውም ዜጋ ተገፍፎ የነበረውን የግል ንብረት ባለቤት የመሆን መብት ጠብቆ ሁሉም ዜጋ የግል ንብረት ባለቤትነት መብቱ በህገ መንግሥቱ እንዲከበር አድርጓል። ከሁሉም በላይ ህገ መንግሥቱ የገጠርም ሆነ የከተማ መሬት የማይሸጥ የኢትዮጵያ ህዝቦች የጋራ ንብረት እንደሆነ በግልፅ አስፍሯል። በመሬት ጉዳይ የህዝቦችን የጋራ ተጠቃሚነት በጽኑ መሠረት ላይ ጥሏል። እናም የተፈጥሮ ሃብት ባለቤትነት መብት የመንግስትና የህዝብ ብቻ እንዲሆን አድርጓል። የኢትዮጵያ አርሶና አርብቶ አደሮች መሬትን በነፃ የማግኘት፣ በመሬታቸው የመጠቀምና ከመሬታቸው ያለ መፈናቀል መብታቸው ህገ መንግሥታዊ ዋስትና አግኝቷል።
የፌዴራል መንግሥት ፍትሃዊ የልማት እንቅስቃሴ ከማረጋገጥ ባሻገር፤ በልማት ወደ ኋላ የቀሩ ህዝቦች መላ አቅማቸውን አሟጠው እንዲጠቀሙ ለማስቻል ልዩ ድጋፍ እየሰጣቸው ነው። እገዛው በዋናነት የሚያተኩረው በማስፈፀም አቅም ግንባታ ላይ ነው። የመንግሥት አስተዳደርን የመገንባት፣ ቀልጣፋ አሰራርንና አደረጃጀት የመፍጠር እንዲሁም የሰው ኃይል አቅም ማጎልበትን በአቅም ግንባታ ስር ተካትተው እገዛ እየተደረገ ነው። ክልሎች ከፌዴራል መንግስቱ በሚያገኙት ድጋፍ ተመርኩዘው ክልሎቻቸውን የተረጋጉ፣ ፀጥታ የሰፈነባቸውና ለልማት ምቹ እንዲሆኑ በማድተግ ላይ ይገኛሉ—በአንዳንድ አካባቢዎች ‘ብልጭ ድርግም’ የሚል የፀጥታ መደፍረስ ጉዳይ ቢኖርም።
የሀገራችን ፌዴራላዊ ስርዓት በነፃ ፍላጐት፣ በህግ የበላይነት፣ በእኩልነት፣ በጋራ ጥቅምና በራስ ፈቃድ ላይ የተመሠረተ አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ በጋራ መገንባትን እውን ለማድረግ የሚያስችል ነው። በፌዴራላዊ ስርዓቱ ውስጥ ማንኛውም ዜጋ ንብረት የማፍራት፣ በመረጠው የስራ መስክ የመሰማራት መብቶች አሉት። እነዚህ ህገ መንግስታዊ መብቶች የህዝቦች ይሁንታ ስለሆኑ ማንም ሊሽራቸው አይችልም። እነዚህ ጉዳዩች በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ለመሻር መሞከር ሀገራችን የምትመራበትን የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ስርዓት አለመቀበል አሊያም ፈጣንና ፍትሃዊ ልማት የማምጣት ርምጃን መፃረር ይመስለኛል። እንዲሁም የዜጐችን የልማት ባለቤትነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ሁለንተናዊ ጥረት ላይ “ውሃ የመቸለስ” ያህል መስሎ ይሰማኛል።
ርግጥ የዜጎችን ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስንና በማንኛውም የሀገሪቱ ክልል ውስጥ ሃብት የማፍራት መብቶችን መገደብ አይቻልም። ይሁንና በኪራይ ሰብሳቢዎችና በኮንትሮባንዲስቶች እንዲሁም ከእነርሱ ጋር ትስስር ባላቸው አንዳንድ የመንግስት ስራ አስፈፃሚዎች ህገ መንግስታዊ ስርዓቱንና ህገ መንግስቱን የሚፃረሩ ተግባራት ተፈፅመዋል። ይህም የክልሎችን እኩል የመልማት ዕድል ከመጋፋት ባሻገር በነፃ ፍለጐት ላይ የተመሠረተ አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመገንባት የሚደረገውን ርብርብ እንደሚያደናቅፍ ይታወቃል።
ክልሎች ከፌዴራል መንግስቱ ከሚያገኙት ድጋፍ ባሻገር በራስ አቅምና በራስ ፍላጐት ነፃ አገራዊ ኢኮኖሚ ለመገንባት የመኪያደርጉትን ጥረቶች ይገድብባቸዋል። ለአገሪቱ ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ የሚያደርጉትን ጥረትንም መና የሚያስቀርባቸው ይመስኛል። የልማት እንቅስቃሴ ዋና ዓላማም የዜጐችን የኑሮ ደረጃ ማሻሻል በመሆኑ የእነዚህ ተፈናቃይ ዜጎች ኑሮን ከማሻሻል መንግስታዊ ስራዎች ተቋዳሽ አለመሆን ክልሎች በሀገር አቀፋዊ አስተዋፅኦዋቸው ላይ ጥላ እንዲያጠላበት ያደርጋል።
ርግጥ በአሁኑ ወቅት የልማት ስራ ለሀገራችን ምን ያህል የሞት ሽረት ጉዳይ እንደሆነ ይታወቃል። ሆኖም ከላይ የጠቀስኳቸው ተግዳሮቶች መጠናቸው አነስተኛ ቢሆንም በሞት ሽረት ጉዳይ ላይ ያነጣጠሩ በመሆናቸው የፌደራላዊ ስርዓቱ ተግዳሮቶች ተደርገው የሚወሰዱ ይመስለኛል። ለነገሩ በኮንትሮባንዲስቶችና በኪራይ ሰብሳቢዎች እንዲሁም ከእነዚህ አካላት ጋር ግንኙነትን በመፍጠር የመንግስትን ስልጣን ለራሳቸው በማዋል ላይ በሚገኙ ጥቂት የፖለቲካ አመራሮች ሳቢያ ዜጎችን የማፈናቀል፣ ለዘመናት ተቻችሎ በኖረው ህዝብ ውስጥ ጥርጣሬ እንዲፈጠር በማድረግ፣ ህይወት በማጥፋትና ንብረት በማውደም የሚሳተፉ ሃይሎችን ከህዝቡ ጋር በመሆን የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ እየተሰራ ነው።
ፌዴራላዊ ስርዓቱ ከተቋቋመት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ ህዝቡን ባማከለ ሁኔታ የህግ የበላይነትን የማስከበር ልምድ ያለው ነው። ሰሞኑን የመንገስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዩች ፅህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ዶክተር ነገሪ ሌንጮ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች በድንበር ውዝግብ ሳቢያ ለተፈጠረው ችግር ሰዎች እንዲገሉ፣ ንብረታቸው እንዲወድምና ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ ያደረጉ በርካታ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን መግለፃቸው የዚህ እውነታ ገላጭ ነው። ምክንያቱም ህዝብ የተሳተፈበት ማናቸውም ተግባሮች ውጤታማ መሆናቸው ስለሚታወቅ ነው።
ስርዓቱ በህዝቦች ፍላጎት የተገነባና በህዝብ ጠባቂነት ዛሬ ድረስ የዘለቀ ነው። ባለቤትነቱ የህዝብ የሆነው ይህ ስርዓት የሚያጋጥሙትን ተግዳሮቶች ሁሉ እየፈታ የመጣ ነው። ህዝቡም ዋነኛ ተዋናይ ሆኖ የገነባውን ስርዓት ሲጠብቅ ኖሯል። ይህ አሰራር የስርዓቱ መገለጫ ሆኗል ማለት ይቻላል። እናም ዛሬም የተፈጠሩ ችግሮችን በመፍታት ላይ ይገኛል። ያልተፈቱ ጉዳዩችንም በሰከነ ሁኔታ ህዝቡን ይዞ ነገም ይሁን ከነገ በስቲያ በዘላቂነት ማሰሪያ እንደሚያበጅላቸው በርግጠኝነት መናገር ይቻላል። ‘እንዴት?’ ከተባለ፤ ትናንት ከትልቁ የመበተን አደጋ ያዳነን ስርዓት ዛሬም ተግዳሮቶቸን የመፍታት ብቃትና አቅም ያዳበረ የህዝብ ስርዓት ስለሆነ ነው።