Artcles

ዘግይቷል፣ ዕውቅና መሰጠቱ ግን መልካም ነው!

By Admin

November 21, 2017

ዘግይቷል፣ ዕውቅና መሰጠቱ ግን መልካም ነው!

ወንድይራድ ኃብተየስ

ብአዴን የተመሰረተበትን 37 ዓመት በማክበር ላይ ነው። ኢህአዴግን ከመሰረቱት አራት እህት ድርጅቶች መካከል አንዱ የቀድሞው ኢህዴን የአሁኑ  ብአዴን  ነው።  ብአዴን 37ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን የሚያከብረው ለቀድሞ ታጋዮቹ ዕውቅና በመስጠት መሆኑ መልካም ነገር ይመስለኛል። ብአዴን ለታጋዮቹ  የሰጠው ዕውቅና የዘገየ ነው ቢባልም  ድርጅቱ ለታጋዮቹ  ያለውን ፍቅርና  አጋርነት  ያሳየበት ነገር  በመሆኑ መልካም ጅምር  ነው።

  

ብአዴን/ ኢህአዴግ ጠንካራ ውስጠ ዴሞክራሲያዊ አሰራር የነገሰበት፣ በሃሳብ ልዕልና የሚያምን፣ የቡድን አሰራር የበላይነት አሰራርን  የሚከተል፣ ጠንካራ የግምገማ ስርዓት ያለው ፓርቲ  በመሆኑ እስካሁን  በስኬት  ላይ መረማመድ አስችሎታል።   በድርጅቱ መርህና  አሰራር  መሰረት አባላት ወደውና ፈቅደው  ወደ ድርጅት  የሚቀላቀሉበት   እንዲሁም  በፈቀዱና  በመረጡት  ወቅት ድርጅቱን  የሚሰናበቱበት ዴሞክራሲያዊ   መብቶቻቸው  የተጠበቁበት   አሰራር የነገሰበት ነው ፓርቲ ነው።  እስካሁን የድርጅቱ መስራቾችን ጨምሮ  በርካታ  አባላት  በማንኛውም ወቅት በፍቃደኝነት አሊያም በግድ  ከድርጅቱ ሲሰናበቱ ተመልክተናል። ይሁንና  ብአዴን/ ኢህአዴግ  ማንም ከድርጅቱ ቢለቅ ወይም  ማንም ወደ ድርጅቱ  ቢመጣ   ከድርጅቱ መርህ ውጭ  ነገሮች  አይፈጸሙም።  የድርጅቱ  መዓከላዊ ዴሞክራሲያዊ አሰራሩ  ፓርቲውን  በስኬት ጎዳና  እንዲጓዝ ያደረገው።  ከላይ ለማንሳት እንደሞከርኩት  ብአዴን/ ኢህአዴግ  የቡድን አሰራር የነገሰበት ፓርቲ በመሆኑ  በጥቂት ግለሰቦች የሚዘወር ፓርቲ አይደለም። ሰሞኑን አንዳንድ መስራች የፓርቲው አመራሮች ከድርጅቱ በመሰናበታቸው   ብአዴን/ ኢህአዴግ  ላይ የሚያመጣው ለውጥ አይኖርም።

 

ኢህዴን/ ብአዴን የትግል መሰረቱ የአማራ ክልል ነው። በፀረ ደርግ ትግል ብአዴን ያታገለው ለአማራ ህዝብ እንዲሁም ለመላው ጭቁን ህዝቦች  ነጻነት ነው። የአማራ ህዝብ ከማንም በላይ ኢህዴን/ ብአዴንን ያውቀዋል፤ እንዲሁም ኢህዴን/ብአዴንም  የአማራን ህዝብ ከማንም በላይ ያውቀዋል። የቀድሞው  ኢህዴን ከአፈጣጠሩ ህብረ ብሄራዊ ድርጅት የነበረ ቢሆንም፣ ንቅናቄው በዴሞክራሲያዊ ብሄረተኝነት ላይ ካለው መርህ ተከል አቋም በመነሳት የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) እና በኋላም የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄን ሲመሰረቱ  ድርጅቱ  በሂደት የአማራ ህዝበ ተወካይ ድርጅት ለመሆን በቅቷል። ይሁን እንጂ በተለይ የአማራ ህዝብን ብሄራዊ መብትና ነፃነት ለማሰከበር እንዲሁም የአማራን ህዝብ የመልማት መብት እውን  ያደረገው ብአዴን/ ኢህዴን ነው። ዛሬ በአማራ ክልል እንዲሁም በመላ አገሪቱ ለተመዘገቡ ስኬቶች   ብአዴን/ ኢህአዴግ   ትልቅ ሚና አለው። ህዝባዊነቱንም በተግባር ያስመሰከረ  ድርጅት  ነው።

 

ብአዴን/ ኢህአዴግ   ከአማራው ክልል ስኬት ባሻገር ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታና ፈጣን ልማት፣ የህዝቦች መፈቃቀድና አብሮነት እንዲሁም የአገሪቱ አንድነት በጠንካራ መሰረት ላይ እንዲመሰረት ትልቅ ድርሻ አበርክቷል። በማበርከትም ላይ ነው። ይህ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል። የኢህአዴግ እህት ፓርቲዎች  ግንኙነታቸውን የበለጠ ማጠናከር ይኖርባቸዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚስተዋሉ አንዳንድ ችግሮች ምንጮቻቸው ሊደርቁ የሚችሉት እህት ፓርቲዎች ግንኙነታቸውን የበለጠ ማስተሳሰር ሲችሉ ነው። በኢህአዴግ  ውስጥ የሚኖር ጠንካራ የግምገማ ባህል፣ የሂስና ግለሂስ መድረኮች  ለአገራችን የህልውና መሰረቶች በመሆናቸው ፓርቲው ይህን የጥንካሬው ምንጭ የሆነውን ጠንካራ የመገማገም ባህል ሊያጎለብተውና ወደላቀ ደረጃ ሊያሳድገው ይገባል።

 

ብአዴን/ኢህአዴግ አገራችን የመድብለ ፓርቲ ስርዓትን እንድትተገብርና የህዝቦች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲረጋገጡ፤ አዲሲቷ ኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ስርዓት እንድትከተል  በማድረግ  ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ፣ ባህላቸውንና ቋንቋቸውን እንዲያጎለብቱ የበኩሉን አስተዋጽዖ በማበርከት ላይ ነው።  ብአዴን/ኢህአዴግ  በድህነትና ጦርነት ትታወቅ የነበረችን  አገርን በዓለም ፈጣን የኤኮኖሚ ዕድገት የምታስመዘግብ  እንዲሁም  ፍትሃዊ ተጠቃሚነት በህዝቦች መካከል   እንዲሰፍን  የበኩሉን ድርሻ  በመወጣት ላይ ነው።  ባለፉት  27 ዓመታት በተለይ ደግሞ  ባለፉት 15 ዓመታት  አገራችን  ፈጣን ልማት  እንድታስመዘግብ  ብአዴን/ ኢህአዴ  ትልቅ ሚና ነበረው።ይህ መልካም ጅምር ቀጣይነት እንዲኖረው ለስርዓታችን አደጋ የሆኑትን የጥበትና ትምክህት አስተሳሰቦችና ተግባራቶች  ብአዴን/ኢህአዴግ እንደቀድሞው ሁሉ ሊታገላቸው ይገባል። ጥበትና ትምክህት ለአገራችን ሰላም፣ ልማትና ዕድገት ጠንቅ ናቸው። በመሆኑም ብአዴን/ኢህአዴግ አባላቱን ብቻ ሳይሆን አመራሩንም ሊፈትሸው ይገባል።

 

የአገራችንን  ሰላም ከማረጋገጥ ባሻገር  ልማቱም እንዲጠናከርና የህዝቦች ተጠቃሚነት የበለጠ እንዲጎለብት  ብአዴን/ኢህአዴግ ከቀድሞው በበለጠ  መረባረብ ይኖርበታል። አገራችን  የተከተለችው  የግብርና መር ኢኮኖሚ  ህዝቦች ፍትሃዊ   ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። የግብርና መር ኢኮኖሚ የአገሪቱ  እድገት ፈጣንና ቀጣይነት እንዲኖርው ያስቻለው ድርጅቱ ለአርሶና አርብቶ አደሩ ካለው ቀረቤታ ነው።   

 

በመጀመሪያው ይዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ማብቂያ ላይ አገራችን  በምግብ ሰብል  ራሷን ችላለች። ይህ ለአገራችን ትልቅ ስኬት ነው።  በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ይህን ተሞክሮ በቤተሰብ ደረጃ  ለማረጋገጥ ብአዴን/ ኢህአዴግ  ጠንክሮ በመስራት ላይ ነው።  በግብርናው ዘርፍ  ላይ ባደረገው ርብርብ   በዘንድሮው የመኸር ምርት ዘመን በአማራ ክልል ብቻ በዋና ዋና ሰብሎች 120  ሚሊዮን ኩንታል በላይ ሰብል  ሊሰበሰብ እንደሚችል ቅድመ ትንበያ ያመላክታል። ይህ አሃዝ ከ10 ዓመት በፊት የአገራችን ዓመታዊ  አጠቃላይ የሰብል  ምርት  ውጤት ነበር። ዛሬ በአገር ደረጃ በዋና ዋና ሰብሎች ብቻ  ከ345 ሚሊዮን ኩንታል በላይ  የመኸር ምርት እንደሚሰበሰብ ትንበያዎች ያመላክታሉ። ይህ ምርት የሚሰበሰበው አገራችን በ50 ዓመታት ጊዜ ውስጥ በድርቅ  በተመታችበት ማግስት መሆኑ የግብርናው  ዘርፍ ድርቅን መቋቋም መጀመሩን ያሳያል።

 

ብአዴን/ኢህአዴግ  ህዝባዊ ድርጅት ነው።  ይህ አንጋፋ ድርጅት ባለፉት 37 የትግል ዓመታት በርካታ ነገሮችን ማሳካት ቢችልም፤ አሁንም የክልሉና የኢትዮጵያ ህዝቦች ከብአዴን/ኢህአዴግ ተጨማሪ  በርካታ ስኬቶችን  ይጠብቃሉ። ብአዴን/ ኢህአዴግ እንደቀድሞው ሁሉ የህዝብ አደራን ለማሳካት በሚያስችለው አቋሙ ላይ  ነው ብዬ አምናለሁ። በመሆኑም  ብአዴን/ ኢህአዴግ  እስካሁን ባስመዘገባቸው  ድሎች ሳይረካና ሳይመካ   ለተጨማሪ ስኬቶችን በማስመዝገብ  የአገራችንን ህዳሴ ለማረጋገጥ መትጋት ይኖርበታል። ዛሬም በርካታ አባላቶቹ የተሰውለት ዓላማ ከዳር አልደረሰም። በርካቶች ዜጎች  በከፋ ድህነት ውስጥ ናቸው። የዴሞክራሲ ስርዓታችን ገና ብዙ የሚቀረው ጅምር ነው። በመሆኑም ፓርቲው እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ህብረተሰቡን ማንቀሳቀስ ይኖርባታል።

 

ብአዴን/ኢህአዴግ  እንደትላንቱ ሁሉ  ለችግሮች መፍትሄ ማፈላለግ ላይ  መፍጠን መቻል ይኖርበታል። ለችግሮች  መፍትሄ መስጠት ማለት  ሁሌም  አዎንታዊ  መልስ ይዞ መገኘት ማለት አይደለም። ምክንያታዊ የሆነ “አይሆንም”  በራሱ መልስ ነው። የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በቅርበት በመከታተል መፍታት  ብአዴን/ኢህአዴግ የቀድሞ ባህሉነና ጥንካሬው  ነው። በቅርብ እንደተመለከትነው ለህዝብ ጥያቄዎች  አፋጣኝ ምላሽ  ያለመስጠት ትልቅ ዋጋ አስከፍሎናል፤  በርካታ ህይወት ጠፍቷል፣ አካል ጎድሏል፣ ንብረት ወድሟል፤ የአገራችንም ገጽታ ላይ አሉታዊ ነገር ፈጥሯል።   ጥያቄዎች በህጋዊ መንገድ ምላሽ ሲነፈጋቸው  ለጸረሰላም ሃይሎች  መጠቀሚያ  መሆናቸው ያማይቀር  መሆኑን ተመልክተናል።  በመሆኑም   ብአዴን/ኢህአዴግ እንደቀድሞው ሁሉ ህዝባዊ ጥያቄዎችን  በወቅቱ ምላሽ ቢሰጥባቸው መልካም ነው። ብአዴን/ኢህአዴግ  በህዝብ ፍላጎት ላይ መሰረት ያደረጉ  የልማት ስራዎችን  በህብረተሰቡ ተሳትፎ  እንዲታጀቡ  ከቀድሞው በላቀ መልኩ ሊሰራ ይገባል።