Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የመድብለ ፓርቲ ሥርዓቱና ጉዟችን

0 299

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የመድብለ ፓርቲ ሥርዓቱና ጉዟችን

ዳዊት ምትኩ

አገራችን እስካሁን በመጣችበት የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ረጅም መንገድ ተጉዛለች። በህገ መንግስቱ መሰረት ፓርቲዎች ሃሳባቸውን በነፃነት የመግለፅና የመደራጀት መብቶችን ተጠቅመው በአገር አቀፍ፣ በአካባቢና በማሟያ ምርጫዎች እየተሳተፉ መጥተዋል። አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአሁኑ ሰዓት ከኢህአዴግ ጋር አንደራደርም ማለታቸው ነው እንጂ፣ ወትሮም ቢሆን የተመቻቸ ሁኔታ እንደነበር መናገር ይቻላል። አሁንም ገዥው ፓርቲና ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች እያደረጉት ያሉት ድርድር የኢትዮጵያን የመድብለ ፓርቲ ስርዓት እመርታ የሚያሳይ ነው።

የአገራችን የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ተቃዋሚ ፓርቲዎች በህጋዊ መንገድ ተንቀሳቅሰውና ሃሳባቸውን በግልጽ አስረድተው በሀገሪቱ ውስጥ በሚደረገው ምርጫ ተወዳድረወ የማሸነፍ ህጋዊ መብት አላቸው፡፡

ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ተቃዋሚዎች በህዝቡ የሚፈለግ አጀንዳን ብቻ ሳይሆን፣ የማይጨበጥና የማይታወቅ ለውጥን እናመጣለን ስለሚሉ ገዥ ፓርቲዎች ያለምንም ተቀናቃኝ በከፍተኛ ድምፅ እየተመረጡ የመንግስት ስልጣን እንዲይዙ ምክንያት ይሆናሉ።

በእኛ አገር ውስጥም ባለፉት አምስት አገራዊ ምርጫዎች ተቃዋሚዎች የማይጨበጥ ነገር ይዘው በመቅረብና የህዝቡ ንብረት የሆነውን ህገ መንግስት በመፃረራቸው አገራችን ውስጥ የአውራ ፓርቲ ሥርዓት እውን ሆኗል።

ይህ የሆነውም ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጠራና የህዝቡን ቀልብ ሊስብ የሚችል ፖሊሲና ስትራቴጂ ባለማቅረባቸው እንዲሁም በህዝቡ ይሁንታ ሳይሆን በውጭ ሃየለሎች ተጽዕኖ ስልጣን ላይ መውጣት በመፈለጋቸው ነው።  

እናም በዚህ አማካኝነት በአገራችን በተካሄዱት አምስት አገር አቀፍ ምርጫዎች ገዥው ፓርቲ በአውራ ፓርቲነት አገሪቱን እየመራ ይገኛል። ይህ የአውራ ፓርቲ ስርዓት በኛ አገር ብቻ የታየ ክስተት አይደለም። እንዲህ ዓይነቱ ሥርዓት እንደ አንድ የፖለቲካ ስርዓት ዓለም አቀፍ ገጽታ ያለው ነው። ሆኖም አሁንም ቢሆን በአገራችን ያለው የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት የፓርቲዎችን የመደራጀት መብት ከመፍቀዱም በላይ ማንኛውም ፓርቲ በሁሉም የምርጫ ሂደቶች እንዲሳተፉ ዕድሎችን የሰጠ ነው።

የኢትዮጵያ ሕዝብ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እንዲጎለብት ባለፋት ጊዜያት የተከናወኑ አምስት አገራዊና ክልላዊ ብሎም የአካባቢና የአዲስ አበባ የምክር ቤቶች የሟሟያ ምርጫዎች የላቀ ሚና ተጫውቷል፡፡

ሕዝቡ በእነዚህ የምርጫ ሂደቶች የሕዝቡ ተሳትፎና ዴሞክራሲውን ወደፊት ለማራመድ የነበረው ሚና ከፍተኛ የሚዘነጋ አይደለም፡፡ የአገሪቱን የፖለቲካ ምህዳር በማስፋት በኩልም የተካሄዱት ምርጫዎች የላቀ ሚና እንደነበራቸውም እንዲሁ ማስታወስ ይቻላል፡፡

ባለፉት አምስት አገራዊ ምርጫዎች የፖለቲካ ፖርቲዎች ከሞላ ጎደል በቁጥር ይሁን በአስተሳሰብ ደረጃ የዴሞክራሲን ምንነት በውል ተረድተው በምርጫ በመሳተፍ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደቱ የነበራቸው ድርሻ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ ነገር ግን በአፈፃፀም ረገድ ችግሮች ነበሩባቸው። ችግሮቻቸውም ቀደም ሲል ከጠቀስኳቸው ሀዝቡንና ህገ መንግስቱን ካለማክበር የመነጩ ይመስሉኛል።

አሁንም አንዳንድ የአገራችን ተቃዋሚዎች ይህን ዕድል በሚገባ እየተጠቀሙበት ነው ማለት አይቻልም። እነዚህ ጥቂት ፓርቲዎች በተለይ በአካባቢና የማሟያ ምርጫዎች ላይ ለመሳተፍ ምንም ዓይነት ፍላጎት የሌላቸው ጭምርም ናቸው። ቀደም ሲል በአገራችን በተካሄዱ የአካባቢና የማሟያ ምርጫዎች ላይ አንሳተፍም ያሉ ጥቂት ፓርቲዎችን እናስታውሳለን።

ነገር ግን የአካባቢና የማሟያ ምርጫዎች የራሳቸው ትልቅ ፋይዳ ያላቸው ነበሩ። እንደሚታወቀው ሁሉ የአካባቢና የሟሟያ ምርጫ ሀገራዊ ምርጫ ከተከናወነ ከሶስት አመታት በኋላ የሚከናወን ነው፡፡ ለምሳሌ አገራዊ ምርጫው በ2007 ዓ.ም ስለተካሄደ በ2010 ዓ.ም የአካባቢና የማሟያ ምርጫ ይካሄዳል ማለት ነው። በዚህ ምርጫ በየአካባቢው የሚገኙ የወረዳ፣ የቀበሌና የከተማ መስተዳደሮች የስራ የጊዜያቸውን አጠናቅቀው ስለሚያበቁ በምትካቸው ፖርቲዎቻቸውን ወክለው አሊያም በግል ተወዳድረው ለምርጫ የሚቀርቡበት ነው፡፡

የአካባቢና የአዲስ አበባ ምክር ቤቶች የሟሟያ ምርጫ ከሀገራዊው ምርጫ ጋር ምንም ግንኙነት የለውም፡፡ በአገራዊ ምርጫ የሚመረጡ አካላት ለሕዝብ ተወካዮች አሊያም ለክልል ምክር ቤት የሚያገለግሉ ሲሆን፤ በዚሁ ምርጫ ተወዳድረው አሸናፊ የሚሆኑት በወረዳ ፣ በቀበሌ እና በከተሞች አስተዳደር በሚገኙ ምክር ቤቶች የሚቀመጡና የሚመሩ ይሆናሉ፡፡

በዚህ ምርጫ ፖርቲያቸውን ወክለው ወይም በግል አሸናፊ ሆነው ወደ ማስተዳደር ስራው የሚመጡ ወገኖች፤ ፊት ለፊት ከሕዝብ ጋር እየተገናኙ ህዝቡ የሰጣቸውን ድምፅ አክብረው በልማቱ ሰፊ እንቅስቃሴ በማድረግ ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ መትጋት የጠበቅባቸዋል፡፡ የሕዝቡን የመልካም አስተዳደራዊ ችግሮች ለማስወገድም ከየአካባቢው ሕዝብ ጋር እየተነጋገሩና እየተወያዩ የተነሱበትን አጀንዳ ማስፈፀም ይጠበቅባቸዋል፡፡

ታዲያ ይህን ወርቃማ እድል ባለመጠቀም ከሕዝቡ ጋር የተራራቁ ፓርቲዎች እንዳሉ ግልጽ ነው፡፡ በእኔ እምነት እነዚህ ፓርቲዎች የመድብለ ፓርቲ ሥርዓቱ ሁሉንም ነገር አመቻችቶላቸው እነርሱ ግን ሊጠቀሙበት ያልቻሉ ናቸው፡፡ ሆኖም ይህ ችግር በያዝነው ዓመት በሚካሄደው የአካባቢና የማሟያ ምርጫ ይስተካከላል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

ያም ሆኖ በአሁኑ ሰዓት አብዛኛዎቹ ፓርቲዎች (በአሁኑ ወቅት ገዥውን ፓርቲ ጨምሮ ድርድር እያደረጉ ያሉ 16 የፖለቲካ ፓርቲዎች) ለመድብለ ፓርቲ ሥርዓቱ እየሰሩ ነው። ይህ ማለት ግን እነዚህ ፓርቲዎች በሁሉም ጉዳዩች ተስማምተዋል ማለት አይቻልም።

ሁሉም ዜጎች አንድ ዓይነት አቋም ይኑራቸው አይባልም። ልዩነት የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ማሳያ ነው። በጠረጴዛ ዙሪያ ለውይይት መቅረብ መቻሉ በራሱ ትልቅ ጉዞ ነው። በድርድር ወቅት ፓርቲዎች ይከራከራሉ፤ ሃሳብ ይለዋወጣሉ።

ጠንካራ ሃሳብ ያለው ለማሳመን ይሞክራል። የሌለው ደግሞ ሃሳቡ ለአገር የሚጠቅም እስከመሰለው ድረስ ይቀበላል። ይህን መሰሉ ዴሞክራሲያዊ ሂደት በአገራችን እየጎለበተ ነው። ረጅም ርቀትም ተጉዘናል። በአሁኑ ሰዓት እየተደራደሩ ያሉት ፓርቲዎች በቀጣይ በሚደረገው አገራዊ ምርጫ አሸናፊው አገር እንዲመራ ተሸናፊው ደግሞ ድምጹ የሚሰማበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ነው። ሌላውን ትተን ይህ ድርድር በራሱ የሚናገረው ነገር አለ። እርሱም የኢትዮጵያ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ምን ያህል ምህዳሩ እየሰፋ መሆኑን የሚያሳይ ነው። ሥርዓቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ የአገሪቱን የፖለቲካ ምህዳር እያሰፋና እያጠለቀ መሄዱን ሂደቱን ከሚከታተል ማንኛውም ዜጋ የሚሰወር አይደለም።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy