Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የማህበራዊ ልማት እድገት ለመሰረታዊ ኢኮኖሚያዊ ለውጥና ቀጣይነት

0 400

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የማህበራዊ ልማት እድገት ለመሰረታዊ ኢኮኖሚያዊ ለውጥና ቀጣይነት

ስሜነህ

በተሃድሶው መስመርና የኢትዮጵያ ህዳሴ ሰነድ በትክክል እንደተቀመጠው የአገራችን ህዳሴ በትክክለኛው አቅጣጫ ተመርቶ በ40 እና 50 አመታት ጊዜ ውስጥ የበለጸጉት አገሮች ተረታ መሰለፍ የሚቻለው የኢኮኖሚ ለውጥና ቀጣይነት በየምእራፉ በትክክለኛው መንገድ መፈጸም ሲቻል ብቻ እንደሆነ ነው። የኢኮኖሚ ለውጥ ቀጣይነት ደግሞ ከሁሉ በፊት የልማታዊ መንግስት ቀጣይነትን የማረጋገጥና መንግስት የገበያ ጉድለቱን በተመረጠ አኳኋን ጣልቃ እየገባ በማስተካከል የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካል ኢኮኖሚን በልማታዊነት እንዲለወጥ በማደረግ እንደሆነም በነዚሁ ሰነዶች ተመልክቷል። የኢኮኖሚ ለውጥ ቀጣይነት የቴክኖሎጂ እድገት ቀጣይነት፣ የመሰረተ ልማት እድገት ቀጣይነት ማረጋገጥና ለቀጣይ ለውጥ ምቹ ሁኔታዎችን የመፈጠር ጉዳይ ነው። ይልቁንም በማህበራዊ ልማት ዘርፍ የሚደረግ ለውጥ አጠቃላይ ለሚሆነው የኢኮኖሚ ለውጥ ቁልፍና ወሳኝ ጉዳይ ነው።  

በኢትዮጵያ የእድገት መገታት ሰፍኖ በቆየባቸው ዘመናት ማህበራዊ ልማትም አብሮ የቀጨጨበት ሁኔታ እንደነበር ለማረጋገጥ አይከብድም፡፡ በአንድ በኩል ቀደምት መንግስታት ማህበራዊ ልማትን የማፋጠንና የማስፋፋት ፍላጎትና ግብ፣ በሌላ በኩል ደግሞ አቅሙ ስላልነበራቸው ኢትዮጵያ በማህበራዊ መስኮች እጅግ ወደ ኋላ የቀረች አገር የነበረች መሆኑም እሙን ነው፡፡

ዘመናዊ ትምህርት ዘግይቶ የጀመረባት ብቻ ሳትሆን በቅጡ ያልተስፋፋባት አገር የነበረች መሆኑም ይታወቃል፡፡ አገሪቱ ይህ ነው የሚባል የሙያ ማሰልጠኛና ለህዝቧ ቁጥር የሚመጥን ብዛት ያለው የከፍተኛ ትምህርት ተቋም አልነበራትም፡፡ አንድ ዩኒቨርሲቲና ጥቂት ኮሌጆች ብቻ የነበሯት አገር ነበረች፡፡ ደርግ ሲወድቅ ከ60 ሚሊዮን ያህል ህዝብ በመደበኛ ትምህርት ቤት ውስጥ የነበረው 2.1 ሚሊዮን ብቻ የነበረ ስለመሆኑ የማእከላዊ ስታትስቲክስ ሰነዶች ያመለክታሉ፡፡ በዚህ የተነሳ እስከ ደርግ ውድቀት ድረስ በነበሩት አመታት የመማር እድል ያገኘው ከህብረተሰቡ ከ4 በመቶ አይበልጥም ፡፡

ከባለፉት ሃያ ዓመታት ወዲህ የተማሪው ቁጥር ከ2.1 ሚሊየን ተነስቶ 28 ሚሊዮን መድረሱን የሚያመለክቱት መረጃዎች፤ ሌላው ቀርቶ ትርጉም ባለው መጠን ፊደል የቆጠረ ሰው ለማግኘት የማይቻልባቸው በነበሩ የአርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር ማህበረሰቦች ሳይቀር እስከ ዩኒቨርሲቲ የዘለቀ ትምህርት መስፋፋቱን ይጠቁማሉ፡፡ ይህም በእያንዳንዱ ዓመት ከአንድ ሚሊዮን የማያንሱ ተጨማሪ ህፃናት የመማር እድል ያገኙ መሆኑን የሚያጠይቅ ነው። ስለአጠቃላዩ ኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ለውጥ  ዛሬ ከአገራችን ህዝብ እስከ 30 በመቶ የሚሆነው በትምህርት ገበታ ላይ ይገኛል፡፡ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ኮሌጆችና የቴክኒክ ማሰልጠኛ ተቋማት፣ እንዲሁም የ41 ዩኒቨርሲቲዎች ባለቤት ሆነናል። ይህ ደግሞ ወደ ኢንዱስትራላይዜሽን እየተደረገ ለሚደረገው ሽግግር ቅድመ ሁኔታና መሰረታዊ የሚሆነው መደላድል ነው። በተለይ ተገንብተው የተጠናቀቁትን ጨምሮ በመገንባት ላይ የሚገኙትን እና በሚሊዮን የሚቀጠር የተማረ ሃይል የሚፈልጉትን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ከግምት ውስጥ ከተን ነገሩን ስንመዝነው ቁጥር ብቻ ሲሉ ተደራሽነትን የሚያጣጥሉ አካሎች ምን እያሉን እንደነበር ግልጽ ይሆናል።

አገራችን ትምህርት የልማት መሳሪያና የእድገትና ፍትሃዊነት ማረጋገጫ ግብም እንደሆነ በመቀበል በማህበራዊ ልማት ዘርፍ በተቀረጸው ፖሊሲ ተመርታ በትምህርት መስክ የምዕተ ዓመቱን ግቦች ለማረጋገጥ ችላለች፡፡ ስለሆነም በማያቋርጥ መልክ  የዘለቀው እድገት አንዱ ተጨማሪ ማረጋገጫ አገራዊ የትምህርት ስኬታችን ነው ብሎ መውሰድ ተገቢ ይሆናል፡፡

ልክ እንደ ትምህርቱ ሁሉ በጤናውም መስክ የተመዘገበው ለውጥ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ የተማረውም ሆነ ያልተማረው ሃይል እንደድርሻው አምራች መሆን የሚችለው ጤናው ሲጠበቅ ብቻ ነው። መከላከልን ማዕከል ባደረገውና ከዚህ በተጨማሪ በህክምና የሚፈወሱ በሽታዎችን ለማከም የሚያግዙ የተለያዩ የጤና ተቋማትን በማስፋፋት ላይ ያነጣጠረው የጤና ልማት ፖሊሲ የምዕተ ዓመቱን ግቦች ከማሳካትም በላይ የህዝቡን መሰረተ ሰፊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ሆኖ የተቀረጸውም ስለዚህና ዘላቂ ስለሆነው እድገት ነው፡፡

አገራችን ለረጅም ዘመናት በቀላሉ ሊፈወሱ ይችሉ በነበሩ በሽታዎች ስትጠቃ የቆየች አገር የነበረች መሆኑ ይታወቃል፡፡ የዚህ ጥቃት ዋነኛ ሰለባዎች ደግሞ አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ እንዲሁም የከተማው ሰፊ ህዝብ ነበሩ፡፡ በተለይ አርሶ አደሩ በነዚህ በሽታዎች መነሾ ከማሳው ተነጥሎ የሚቆይባቸው ቀናት በወራት የሚቆጠሩ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የኢኮኖሚያችን መዘውር የሆነው ግብርና የተሽመደመደ የነበረ መሆኑም ይታወሳል። እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች የኢኮኖሚ አቅማቸው ዝቅተኛ ከመሆኑም በላይ በሳይንሳዊ አኳኋን በመመራት ሊወገዱ ይችሉ በነበሩ ተዛማች በሽታዎች የሚጠቁ ስለነበሩ ከጤና እክል ጀምሮ እስከ ኢኮኖሚያዊ ጉስቁልና ድረስ ለሚዘልቅ ጉዳት ሲዳረጉ ኖረዋል፡፡

ይህ ሂደት መቋረጥ የጀመረው  መንግስት መከላከልን ማዕከል ያደረገ የጤና ፖሊሲ ቀርፆ ተግባራዊ ማድረግ ከጀመረ በኋላ ነው፡፡ በዋነኛነት የመከላከል ትምህርትን እያስፋፋ ከዚህ ጎን ለጎንና በተደራቢነት ደግሞ የጤና ተቋማትን እየገነባ ባደረገው ርብርብ በአገራችን በገዳይነታቸው የሚታወቁ አብዛኞቹ በሽታዎች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ለማድረግ ተችሏል፡፡ ከወባ እስከ ተስቦ፣ ከሳንባ ነቀርሳ እስከ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ድረስ ያሉ በሽታዎች መንግስትና ህዝብ ባደረጉት ርብርብ የመስፋፋት መጠናቸው በእጅጉ ቀንሷል፡፡

ለዚህ ሥራ ልዩ ትኩረት የሰጠው መንግስት ከኤክስቴንሽን ሙያተኞች ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ሀኪሞች በማሰልጠንና በማሰማራት በልዩ ሁኔታ በመረባረቡ፣ የህክምና ተቋማት ግንባታና የመድሃኒት አቅርቦት እንዲስፋፋ በማድረጉ በጤናው መስክ የምዕተ ዓመቱን ግቦች ከማሳካት አልፈን መሰረተ ሰፊ የህዝብ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ አስችሎናል፡፡ እናቶችና ህፃናት በአጠቃላይ ደግሞ ለጥቃቱ ተጋላጭ የነበሩ ብዙሃኑ ኢትዮጵያውያን ከመቼውም ጊዜ የተሻለ የጤና ልማት ተጠቃሚ እስከመሆን ደርሰዋል፡፡  

ዘርፉን የተመለከቱ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት የአገራችን ህዝቦች በ1982 ዓ.ም ከነበሩበት በህይወት የመቆየት አማካይ የ45 ዓመት እድሜ ተነስተው ከላይ በተመለከተው መልኩ በተሰራው አግባብ አሁን በአማካይ የ65 ዓመታት ዕድሜ የመኖር ፀጋን ተጎናፅፈዋል፡፡   ሁሉም ዜጋ በአማካይ የሦስት ዓመት ከስምንት ወር ዕድሜ እንዲቀጥል ለማድረግ የተቻለበት ይህ ሂደት፣ በርግጥም የኢትዮጵያ ህዳሴ የተበሰረበት ከመሆን ሌላ ምንም ሊሆን አይችልም፡፡

በባለፉት ሃያ የሚደርሱ ዓመታት በማህበራዊ ልማት ዘርፍ ይልቁንም በትምህርትና በጤናው መስክ የተመዘገበው እድገት ኢትዮጵያን አጠቃላይ ለሆነ የማህበረ ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ያበቃና ወደ ህዳሴዋ እያደረገች ያለውን ጉዞ እያፋጠነላት ለመሆኑ እኛ ብቻ ሳንሆን አለምም እየመሰከረ ነው። ይህ ማለት ግን ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ ነው ማለት አይደለም። ከዚህ ለበለጠ ፈጣን የህዳሴ ጉዞ ሁለቱንም ዘርፎች ከኪራይ ሰብሳቢ ሃይሎች ማጽዳትና ጥራታቸውን ማረጋገጥ ተገቢና ጊዜው የሚጠይቀን ቁልፍ ተግባር ይሆናል።  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy