የምንዛሬ ማሻሻያው ላልገባቸው ሁሉ
ስሜነህ
የንግድ አሠራሩን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ በማድረግ በመላ ሀገሪቱ የሸቀጦችና የጉልበት ነፃ ዝውውር እንዲኖርና የሸቀጦች ዋጋ በአቅርቦትና ፍላጎት ህግጋት መሠረት በውድድር እንዲመራ ማድረግ የሚያስችል ስርአት መዘርጋቱ ይታወቃል። ይህ ስርአት የኑሮ ውድነቱ በህብረተሰቡ ላይ የሚያሳድረውን ጫና ለመቀነስ መሰረታዊ ሸቀጦችን በድጎማ ለህብረተሰቡ በማቅረብና በማሰራጨት እንዲሁም በጅምላ ንግድ ስርአቱ ውስጥ የሚታየውን የገበያ ክፍተት ለመሸፈን የሚያስችል መሆኑም በመንግስት በተደጋጋሚ በኩል ተገልጿል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ እየተዳከመ የመጣውን የወጪ ንግድ ለማበረታታት ሲባል የኢትዮጵያ ብር ከሌሎች የውጭ ገንዘቦች በ15 በመቶ ቀንሶ ግብይት እንዲፈጸምበትና ባንኮች ለተቀማጭ ገንዘብ የሚከፍሉት የወለድ መጠን ወደ ሰባት በመቶ ከፍ እንዲል ተደርጓል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አዲሱን የምንዛሪ ለውጥ አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው፤
“ ለወጪ ንግዱ መቀዛቀዝ እንደ አንድ ምክንያት የሚጠቀሰው ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የአገሪቱ ምርቶች በዓለም ገበያ ዋጋቸው እየቀነሰ መምጣቱ ነው፡፡ በተለይ በወጪና በገቢ ንግድ መካከል ያለውን ክፍተት ለማጥበብ የግድ የወጪ ንግዱን ማሳደግ ስለሚገባ”
ዕርምጃው መወሰዱን አመልክቷል፡፡
ያም ሆኖ ግን እንዲህ ዓይነት የገንዘብ ምንዛሪ ለውጥ ለወጪ ንግዱ ሊሰጥ ከሚችለው ጠቀሜታ ባሻገር አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚኖረው የዘርፉ ጠበብቶች ይመሰክራሉ ። ይህም ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ዋጋ ላይ ጭማሪ የሚያስከትል መሆኑ ነው፡፡በእርግጥም እርምጃው ከተወሰደ በኋላ ቢያንስ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪው ሊከሰት የሚችለው ከሁለት ወራት በኋላ ሊሆን እንደሚችል ቢገመትም አስቀድመው በነበረው ዋጋ በገቡት የውጭ ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሬው ወዲያውኑ ተከስቷል። በተለይ በኮንስትራክሽን እና ኤሌክትሮኒክስ እቃዎች ላይ የታየው ጭማሪ በአስተሳሰብ ደረጃ በአቋራጭ የመበልጸግ ፍላጎት ከንግዱ ማህበረሰብ ውስጥ እንዳልተቀረፈ የሚያመላክት ነው።
በዚህ ሳያበቃ ደግሞ የሃገር ውስጥ ምርትን ለማበረታታት ይጠቅማል የተባለው ክለሳ ተቀልብሶ በሃገር ውስጥ ምርቶች ላይ ይልቁንም ከዋጋ ጭማሬው ጋር ምንም ተያያዥነት በሌላቸው ምርቶችና አገልግሎቶች ላይ ጭማሬው ታይቷል። መንግስት ሰው ሰራሽ የሆነ የኑሮ ውድነት በሚፈጥሩ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ እየወሰደ ቢሆንም አንዳንዶቹ የመንግስት ድርጅቶች መሆናቸው ጉዳዩን የበለጠ ግራ ገብ ያደርገዋል።
የመንግስት በሆኑ ስኳር ድርጅቶች ተመርቶ የሚወጣ ስኳር እስከ 80 ብር፤ ከውጭ ምንዛሬ ጋር ምንም ዝምድና በሌለው የቄራዎች ድርጅት የእርድ አገልግሎት ላይ ክፍያውን በማናር ስጋን ማስወደድ፤ ወዘተ ሊታዩና ለፈተሹ ከሚገባቸው የምንዛሬ ለውጡን ዓላማ ከሚያስቱ ማሳያዎች መካከል ለጠቀሱ የሚገባቸው ናቸው። የግብርና ምርቶች ላይ እየታየ ያለው ደግሞ አሰቃቂ እና የነገሩን መድረሻ ግራ በማጋባት ወደየት እየሄድን እንደሆነ የሚያሳስብ ነው
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ሐሙስ ጥቅምት 16 ቀን 2010 ዓ.ም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት፤ በዚህ የብር የመግዛት አቅም መዳከም የተነሳ የኑሮ ውድነት እንዳይከሰትና ዝቅተኛ ገቢ ያለው የኅብረተሰብ ክፍልና የመንግሥት ሠራተኛ ላይ የኑሮ ውድነት እንዳይኖር፣ እንዴት መከላከል እንደሚቻል የተቀመጠ መፍትሔ ካለ እንዲያብራሩ ጥያቄ ቀርቦላቸው የነበረ መሆኑ ይታወሳል።
ለጥያቄው ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚነስትር ኃይለ ማርያም፣ የብር የመግዛት አቅም እንዲዳከም የተደረገው የአገሪቱን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ውጤታማ ለማድረግ ነው። የአገሪቱ የግብርና ምርቶች ኤክስፖርት በመጠንም በገቢም እንደሚጨምር ለማበረታታት፣ እንዲሁም ተስፋ መቁረጥ የታየበትን የኤክስፖርት ምርቶች አምራች የሆነውን ገበሬ ለማበረታታት የምንዛሪ ለውጡ ተደርጓል። በተጨማሪም የአገሪቱን ኢኮኖሚ ዕድገትና ልማት ከዚህ በኋላ ማስቀጠል የሚቻለው በኤክስፖርት ተኮር ኢንዱስትሪ (ማኑፋክቸሪንግ) በመሆኑ፣ ቀድሞ በነበረው የብር ዶላርን የመግዛት ጠንካራ አቅም ዘርፉ እንዳይዳከም መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በዚህ ምክንያት የብር ምንዛሪ ተመን ለውጥ ሲደረግ ከውጭ በዶላር ተገዝተው የሚገቡ የፍጆታ ዕቃዎች ዋጋ ማኅበረሰቡን እንዳይጎዳ ጥንቃቄ መደረጉን የተናገሩት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ ከተወሰዱት ጥንቃቄዎች መካከል ከትራንስፖርት ጋር በዋናነት የሚያያይዘው የአገር ውስጥ የነዳጅ መሸጫ ዋጋ በመሆኑ፣ ብር ላይ በተደረገው የምንዛሪ ለውጥ ምክንያት በአገር ውስጥ የነዳጅ ዋጋ ላይ አንድም ሳንቲም እንዳይጨመር መወሰኑን ተናግረዋል፡፡ በዚህ ምክንያት በኢትዮጵያ የነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ላይ የሚመጣውን ጫና መንግሥት በድጎማ የሚሸፍነው ይሆናል፡፡ ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ የሚስያረዳው የብር የመግዛት አቅም እንዲዳከም በመደረጉ፣ በዶላር ተገዝቶ ለአገር ውስጥ የሚቀርበው የነዳጅ መሸጫ ዋጋ በምንዛሪ ተመኑ መሠረት እንዳይጨመር መወሰኑን ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከነዳጅ ውጪ እንደ ስኳር፣ ዘይት፣ ስንዴና የመሳሰሉ የፍጆታ ዕቃዎችን መንግሥት እያስገባ ማከፋፈሉን እንደሚቀጥልም ተናግረዋል፡፡ የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት ሲባል የተቋቋመው “አለ በጅምላ” መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎችን አቅርቦትና ሥርጭት በማሻሻል የብር ምንዛሪ ተመን ለውጡ ማኅበረሰቡ ላይ ጫና እንዳይፈጥር እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡ እርሳቸው ይህን ይበሉ እንጂ ይህ ጸሃፊ ጉዳዩን አስመልክቶ በአንድ የሃገር ውስጥ ሬዲዮ ባደረገው የቀጥታ ስልክ ውይይት ገበያው ከተፈራውም በላይ እየከበደና ለዚህም ተጠያቂው ነጋዴው ብቻ ሳይሆን ህብረተሰቡና መንግስት መሆኑን አረጋግጧል።
በገበያ ውስጥ ብረትና እንጨትን ጨምሮ በተለያዩ የካፒታል ዕቃዎች፣ በተሽከርካሪዎች፣ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በጥራጥሬና በቅባት እህሎችና በመሠረታዊ አቅርቦቶች ላይ የዋጋ ጭማሬው ከሁለትና ሶስት ወራት በኋላ የሚጠበቅ ቢሆንም ከአሁኑ እየታየ ያለው የዋጋ ጭማሪ ግን ከሁለት ወር በኋላ ምን ሊሆን እንደሚችል የሚያመላክትና ህዝቡን ስጋት ላይ የጣለ ነው፡፡
የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን፣ የውጭ ምንዛሪ ተመን ለውጥ ይፋ በተደረገ በማግሥቱ ከጥቅምት 1 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ እየተደረገ መሆኑን መረጃዎች እንደደረሱት በውይይቱ ላይ በተገኙት ተወካዩ በኩል አረጋግጦ፤ በምንዛሪ ለውጡ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ሸቀጦችን የሚደብቁና የሚያከማቹ ሕገወጥ ነጋዴዎች መኖራቸውን ከደረሰው ጥቆማና ከዚህ ቀደም ከነበሩ ልምዶች መረዳቱን አስታውቋል፡፡
በተለይ የውጭ ምንዛሪ ተመኑ ይፋ ከመደረጉ በፊት አገር ውስጥ በገቡ ምርቶችና አገር ውስጥ በተመረቱ ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ መደረጉ ምንም ዓይነት ኢኮኖሚያዊ ምክንያት የሌለውና ሕገወጥ በመሆኑ፣ መንግሥት የማስተካከያ ሕጋዊ ዕርምጃ ይወስዳል ብሏል፡፡ ከወራት በኋላ ወደ አገር በሚገቡ ምርቶች ላይ ሊኖር የሚችለውን የዋጋ ጭማሪ ከወዲሁ እየተጨመረ መሆኑ ከፍተኛ ሥጋት መፍጠሩን ብዙዎቹ አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል፡፡
ቢያንስ በሚቀጥሉት ሦስት ወራት ሊኖር የሚችለውን ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ አሁን እያደረጉ በሚገኙ፣ ምርቶችን በሚሰውሩና በሚያከማቹ ነጋዴዎች ላይ ዕርምጃ ለመውሰድ በፌዴራል ደረጃ ግብረ ኃይል መቋቋሙ ተገልጿል፡፡ ግብረ ኃይሉም ሆነ ባለሥልጣኑ ጥፋተኛ ሆነው በተገኙት ላይ የንግድ ፈቃድ ከማገድ እስከ ንግድ መደብር የማሸግ አስተዳደራዊ ዕርምጃዎች፣ እንዲሁም በሕግ እስከ መጠየቅ የሚደርስ ዕርምጃ እንደሚወስድ የገለጸ ቢሆንም ግብረ ሃይሉም ከኪራይ ሰብሳቢ ሃይሎች ጋር ተመሳጥሮ የህዝብን ጥቆማዎች መሰረት ያደረገ ክትትል እያደረገ አለመሆኑን የውይይቱ ተሳታፊ የነበሩ ዜጎች መስክረዋል፡፡ የባለሥልጣኑ ተወካይ በአቋራጭ አላስፈላጊ ትርፍ ለማግበስበስ ከሚደረግ ጥረት ነጋዴው በመቆጠብ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ሲያሳስቡ፤ህዝቡና ህጋዊ ነጋዴዎች በአጠገባቸው የሚገኙ ህገወጦችን በይሉኝታ ታስረው እሹሩሩ ከማለት ተቆጥበው ማጋለጥ የሚገባቸው እንደሆነም አመልክቷል፡፡ ከሁሉ በላይ ግን የትኛውም ነጋዴ በሌላ መልክ ሸማች መሆኑን አውቆ በራሱ ላይ ሲደርስ ከማማረር አስቀድሞ እራሱን በማረም ህጋዊ ወደሆነው መስመር የመመለስ ሞራላዊ ጥያቄውን ሊመልስ ይገባል።
የውጭ ምንዛሪ ተመን ላይ የተደረገው ማሻሻያ በጥናት ላይ ተመሥርቶ የተፈጸመ መሆኑን መንግስት አመልክቷል፡፡ የወጪ ንግድን በማሳደግ የውጭ ምንዛሪ ገቢን ለማሳደግ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም በአገር ውስጥ ምርትና በውጭ ምርቶች ላይ በአሁኑ ጊዜ የዋጋ ጭማሪ ሊያስከትል የሚችል ምንም ዓይነት ኢኮኖሚያዊ ምክንያት የሌለ መሆኑ ታውቆ፣ ማንኛውም በድርጊቱ የሚሳተፍ በአቋራጭ ትርፍ ለማግበስበስ ከሚደረግ ጥረት በመቆጠብ ከሞያና ማኅበራዊ ኃላፊነት አንፃር ኅብረተሰቡን ሊያገለግል ይገባል።