Artcles

የሥርዓቱ ባለቤትም ሆነ ጠባቂ ህዝቡ ነው!

By Admin

November 08, 2017

የሥርዓቱ ባለቤትም ሆነ ጠባቂ ህዝቡ ነው!

                                                         ደስታ ኃይሉ

አዲሲቷ ኢትዮጵያ የምትከተለው ፌዴራላዊ ሥርዓት እንዲፈጠር ያደረጉት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ናቸው፡፡ ሥርዓቱ አንዳች ችግር ቢደርስበትም የሚጠብቀው ህዝቡ ነው፡፡ ሥርዓቱ በዚህች አገር ውስጥ እንዲረጋገጥ የህይወት፣ የአካልና የንብረት መስዋዕትነት የከፈለው ህዝቡ በመሆኑ በተለያዩ ወቅቶች ሥርዓቱ ያጋጠሙን ችግሮች በመፍታት ዛሬ ላይ እንዱደርስ ያደረገውም እርሱ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች የቃል ኪዳን ማሰሪያ ሰነድ የሆነው የኢፌዴሪ ህገ -መንግስት ጸድቆ በስራ ላይ ከዋለ ወዲህ ሀገራችን ትክክለኛ የዕድገት አቅጣጫ ይዛ በአዲስ የታሪክ ምዕራፍ ላይ በድል ለመረማመድ በቅታለች፡፡ የብሔሮችና ብሔረሰቦች እስር ቤት እስከመባል ደርሳ የነበረችው ሀገራችን፤ የህዝቦቿ መብት የተረጋገጠባት፣ የዕድገትና ልማት ብሩህ ተስፋን የሰነቀች፣ የእኩልነትና የፍትህ አምባ ለመሆን ችላለች፡፡

በመሆኑም የአፈና አገዛዝ፣ የግፍ ቀንበር ተጭኖት የኋላቀርነትና የበታችነት ተምሳሌት ተደርጎ ይታይ የነበረው የብሔር ብሔረሰቦቿ ባህል፣ ታሪክና ቋንቋ የህዝቦቿ መኩሪያና መከበሪያ፣ የሀገራችን መድመቂያ ጌጥና የመልካም ገጽታዋ መገለጫ ወደ መሆን ተሸጋግሯል፡፡

የተለያየ እምነትና የአኗኗር ዘይቤን የሚከተሉ የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በመግባባትና በመረዳዳት መንፈስ አብሮ በመኖር በዓለም የሚታወቁበት የመቻቻል ባህልም ከመቼውም በላቀ ሁኔታ በመዳበር ላይ ይገኛል፡፡

እነዚህ ታሪካዊ፣ ባህላዊና መንፈሳዊ የጋራ እሴቶቻችን ለሀገራችን ተጨማሪ ክብርና ሞገስ ከማላበስ አልፎ ለፈጣን ልማት ስራዎቻችን የበኩላቸውን ድርሻ ማበርከት ወደ ሚችሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል፡፡

ከሁሉም በላይ ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ከሀገራቸው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ህይወት ተገልለውና ተረስተው በባይተዋርነት ለመኖር የተገደዱበት አድሎአዊና ፍትህ አልባ ሁኔታ ሙሉ ለሙሉ ተቀይሮ፤ ዜጎች በማንኛውም ሀገራዊ ጉዳይ ውስጥ እኩል ተሳታፊ የመሆን ዕድል አግኝተዋል፡፡

ይህንንም በተጨባጭ ስራ ላይ በማዋል የሀገራችንና የህዝባችን የማደግና የመበልጸግ ተስፋን በእጅጉ ለማለምለም ችለዋል፡፡ መላው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በመብቶቻቸው እየተገለገሉና ዘላቂ ጥቅሞቻቸውን እያስከበሩ በፈጣን ልማትና በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አቅጣጫ ላይ የተያያዙት ፈጣን የዕድገት ጉዞም የፌዴራላዊ ሥርዓቱ ተጨባጭ ፍሬ ነው፡፡

በሀገራችን እውን የሆነው ፌዴራላዊ ሥርዓት ለሀገራችንና ለህዝባችን አንድነት፣ ሠላምና ዕድገት መጠናከር ወሳኝ አስተዋጽኦ ያበረከተ ነው፤ በማበርከት ላይም ይገኛል። የዚህ አዲስ ሥርዓት ግንባታ ሂደት በተጨባጭ ተፈትኖ ፍቱንነቱ የተረጋገጠ ነው፡፡ የተገነባው ፌዴራላዊ ሥርዓት በሀገራችን ላይ አንዣቦ የነበረውን የመበታተን አደጋ ያስወገደና በእኩልነትና በመፈቃቀድ ላይ ለተመሰረተ ከብረት የጠነከረ የህዝቦች አንድነት ዘላቂ ዋስትናን ያሰገኘ ነው፡፡

በዚህም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ረጅሙንና አስቸጋሪውን የትግል ምዕራፍ በድል አድራጊነት በቋጩ ማግስት በጋራ ተወያይተውና አምነው ያጸደቁት ህገ – መንግስት የዘመናት ጥያቄዎቻቸውን ሙሉ ለሙሉ የመለሰ ከመሆኑም ባሻገር፤ በቀጣይ ለሚያካሄዷቸው የጋራ አጀንዳዎች ዘላቂነትና ውጤታማነት ዋስትና የሰጠ ነው፡፡

በመሆኑም የመላው ህዝባችንን ጥያቄዎች የፈታውና ለዘላቂ ሠላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ዋስትና የሰጠው የኢፌዴሪ ህገ – መንግስት የፀደቀበት ዕለት በታላቅ ድምቀትና በልዩ ሁኔታ በየዓመቱ እየተከበረ ይገኛል፡፡

እርግጥ የሀገራችን ህዝቦች ከህገ – መንግስቱ ጋር በብዙ መልኩ እጅግ የጠበቀ ቁርኝት አላቸው፡፡ አዎ! የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የህገ – መንግስቱ ባለቤቶች ናቸው፡፡ ህዝቡ ህገ- መንግስቱን ያቋቋመና የመንግስትንም አወቃቀር በፈቃዱ የነደፈ ነው። ይህም በህገ – መንግስቱ ላይ በግልጽ እንደሰፍር አድርገዋል፡፡

እንደሚታወሰው ያለፉት ሥርዓቶች የራሳቸው ህገ-መንግስት  የነበሯቸው ቢሆንም፤ ህዝባዊ መሰረት ግን አልነበራቸውም፡፡ ይህ የሆነው ባለፉት ሥርዓቶች በሀገራችን ህገ-መንግሥት የማይታወቅ በመሆኑ አልነበረም፡፡ እስከ ደርግ ውድቀት ድረስ በሀገራችን ሦስት የተጻፉ ህገ-መንግሥቶች እንደነበሩ ይታወሳል፡፡

ይሁን እንጂ በንጉሱ የአገዛዝ ዘመን የነበሩት ሁለት ህገ መንግሥቶችም ሆኑ በደርግ ህገ መንግሥት ወቅት ዘግይቶ የተረቀቀው ህገ-መንግስት የየሥርዓቶቹን ፊውዳላዊና አምባገነናዊ ሥልጣን ማስጠበቂያ ብቻ ናቸው፡፡ ዋነኛ ዓላማቸው የገዢዎችን ሥልጣን ማራዘምና ሥርዓታቸውን ዘለዓለማዊ ማድረግ ነው፡፡

ያለፉት ሥርዓቶች ህዝባዊ አለመሆን በህገ-መንግሥታቸው ካሰፈሯቸው እውነታዎች በግልጽ መገንዘብ ይቻላል፡፡ በህገ-መንግሥቶቹ ላይ ለህዝብ የሚጠቅሙ መሠረታዊ ጉዳዮች ካለመስፈራቸውም ባሻገር፤ የሰፈሩትም ቢሆን ለይስሙላ ካልሆነ በስተቀር ተፈጻሚ የሆኑ አልነበሩም፡፡

በመሆኑም ህዝቡ ገዢዎች የራሳቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ ህገ-መንግስቱን እንደ መጠቀሚያ ከመጠቀም ባለፈ፤ ተጨባጭ ተልዕኮው ምን እንደሆነ የሚያውቀው ጉዳይ አልነበረውም፡፡

በሀገራችን አዲስ ሥርዓት ዕውን ከሆነ በኋላ ህገ – መንግስቱ ጸድቆ በስራ ላይ ከዋለ ጀምሮ ሀገራችንና ህዝቦቿ በተለያዩ መስኮች እጅግ ውጤታማ  ተግባር አከናውነዋል፡፡ እነዚህን ውጤቶች አቅቦ ከመጓዝና ለአዳዲስ ድሎች ከመብቃት አኳያም፤ በአሁኑ ሰዓት መንግስትና መላው ህዝብ በላቀ ቁርጠኝነት እየተረባረቡ ይገኛሉ፡፡ ይህም የሀገራችን የድህነትና ኋላቀርነት ገጽታ በአጭር ጊዜ ውስጥ በመለወጥ ላይ ይገኛል፤ ሂደቱም እጅግ በተጋጋለ ሁኔታ ቀጥሏል፡፡

እርግጥ እዚህ ላይ በአገራችን በሁሉም ዘርፎች የሚመዘገበው ዕድገት ህዝቡን በየደረጃው ተጠቃሚ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ የህዝቡን ተጠቃሚነት ደግሞ የአገራችንን ዕድገት የሚያፋጥን ሆኗል፡፡ ይህ ተጠቃሚነት አራማጅነቱም የአገራችንን ፌዴራሊዝም እንደ ጀማሪነቱ እንዲታይ ያደረገው አይደለም፡፡

ይህ ሥርዓት የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የእኩልነትና የነጻነት ጥያቄዎች ምላሽ ሊሰጥ የቻለው ለነፃነት በተደረገው ትግል ነው፡፡ ከጅምሩ እስካሁን ድረስ ሁሉም የአገራችን ህዝቦች እኩል ሥርዓቱን እያራመዱት ነው፡፡ ችግር ቢኖርም የሚፈቱት እነርሱው ናቸው፡፡ እነርሱ የሥርዓቱ ባለቤትም ሆነ ጠባቂዎች መሆናቸውን መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡