የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ዋስትና
ዳዊት ምትኩ
በፌዴራላዊ ሥርዓታችን የተጎናፀፍናቸውን ስኬቶች በርካታ ናቸው። ፌዴራላዊው ስርዓታችን የሰላማችን፣ የልማታችን፣ የዴሞክራሲ ሥርዓታች እንዲሁም አንድ የጋራ ማኅበረሰብ የመፍጠር ዓላማችን መሳካት ዋስትና መሆኑ ባለፉት 26 ዓመታት ታይቷል። አገራችን የምትከተለው ሥርዓት በሁሉም መስኮች አንገታችንን ቀና አድርገን አንድንሄድ ያደረገን፣ ለሌሎች ምሳሌ እንድንሆን ያስቻለንና ዋስትናቸውም አድርገውን እንዲመለከቱን ያደረገ ነው።
ፌዴራላዊ ሥርዓቱ እውን የሆነበት የኢፌዴሪ ህገ መንግስት ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ እውን እንዲሆን መሰረት ጥሏል። ዴሞክራሲያዊ አንድነታችን እንዲጎለብትና ህዳሴያችን እውን እንዲሆን እንድንተጋ እያደረገን ነው።
እንደሚታወቀው ሁሉ ላለፉት 27 ዓመታት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ጥቅሞቻቸውን በማጎልበት አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመገንባት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በአንድነት ተነሳስተዋል፡፡ በብዝኃነት ላይ መሠረቱን የጣለው አንድነት ለህዳሴውም ስኬት መገለጫ ነውና የዜጎች ሁሉ የበላይ የሆነውን ህገ መንግሥት ጠብቆ ለማቆየት ሁሉም በፅናት ቆሟል፡፡
በመላ ኢትዮጵያ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የተከበሩበት፤ ለዴሞክራሲያዊ አንድነት መሠረት የተጣለበት፤ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ማንነት፤ ውበትና ህብረት የታየበት ብሎም የሥልጣን ባለቤት የተረጋገጠበት፤ የልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ጉዞ የተጀመረበት መሠረቱ ይኸው ህገ መንግሥት ነው፡፡
የህገ መንግሥቱ ድሎችና ውጤቶች ከመቼውም በላይ ተስፋፍተው፤ የዜጎች ማንነትና ባህላዊ እሴቶች ጎልተው ወጥተው፤ መልካም ተሞክሮዎችም ይበልጡን ጎልብተው የአንድነታችንና የጥንካሬያችን መገለጫ ሆነው እንዲቀጥሉ ዜጎች እጅ ለእጅ ተያይዘው ጉዟቸውን ቀጥለዋል፡፡
በአሁኑ ሰዓት በህገ መንግሥቱ በተደነገገው እኩል የመልማት መብት በመጠቀም በሁሉም ክልሎች በተነፃፃሪ ፈጣን የሚባል ልማትና ዕድገት ተመዝግቧል፡፡ ህብረ ብሄራዊ የፌዴራል ሥርዓት ከአገሪቱ ተጨባጭ ታሪካዊ ሁኔታ በመነሳት በህገ መንግሥቱ ተደንግጎ ተግባራዊ መሆን ጀምሯል፡፡ ሕብረ ብሄራዊ የፌዴራል ሥርዓቱ ያለፉት አፋኝ መንግሥታት የቀበሩትን የማንነትና የምጣኔ ሃብት ተጠቃሚነት ጥያቄን በአስተማማኝ ደረጃ መመለስ ችሏል፡፡
በመፈቃቀድና በእኩልነት ላይ የተመሠረተ አንድነትን ለማስቀጠልና ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ቃል ኪዳን ያሰሩበትን አንድ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የመገንባት ጉዳይ በህዳሴው እየተቀላጠፈ ይገኛል፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱ ባልተማከለ አስተዳደር ክልሎች ራሳቸውን በራሳቸው በማስተዳደር ማዕቀፍ ውስጥ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዲኖራቸው አስችሏል፡፡
በዚህም ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊና ማኅበራዊ ተሳትፏቸውና በየደረጃው ተጠቃሚነታቸው ጎልብቷል፡፡ አካባቢያቸውንም በማልማት ለአገር ብልፅግናና እድገት ከፍተኛ ደርሻ እያበረከቱ ይገኛሉ፡፡ የክልሎችን የእኩል ተጠቃሚነት በማረጋገጥ አኳያ ደግሞ የልማትና ዕድገት አፈጻፀም በክልሎች እኩል ተጠቃሚነት እየተፈፀመ መሆኑን የሚያረጋግጥ እውነታ ነው፡፡ የክልሎችን የእኩል ተጠቃሚነት በማረጋገጥ አንፃር ልማታዊው መንግሥት ግልፅ የሆኑ ምጣኔ ሀብታዊ ህጎችን፣ የልማት ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ነድፎ በየአካባቢው ተጨባጭ እቅድ እየተመነዘሩ የሚፈፀሙበትን ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ በአፈጻፀም ሂደት የተገኙ በጎ ልምዶችም እየተቀመሩ በአገሪቱ ሁሉም አካባቢዎችና ለምልዓተ ሕዝቡ የሚደርስበት ስልቶች ተቀይሰዋል፡፡
የልማት ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን በመተግበር ዙሪያ የሚያጋጥሙ ማነቆዎች የሚለዩበትን የአሠራርና የአደረጃጀት ጥያቄዎች ካለፉት ልምዶች በመነሳት እንዲፈተሹና እንዲስተካከሉ በማድረግ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የላቀ ተሳትፎና ተጠቃሚነት እየተረጋገጠ ይገኛል፡፡
ክልሎች በገጠርና ከተማ የልማትና መልካም አስተዳደር ዕቅዶችን በመንደፍና ሕዝቦቻቸውን ዋናው ፈፃሚ አካል በማድረግ ባለፉት ስምንት ዓመታት በአማካይ ለተመዘገበው ከሁለት አኃዝ በላይ እድገት የድርሻቸውን እንዲያበረክቱ አግዟል፡፡
የፌዴራል መንግሥትም ክልሎችን ከክልሎች ብሎም ከአዋሳኝ አገሮች ጋር የሚያገናኙ መንገዶችን በመስራትና ፈጣን የቴሌኮም አገልግሎቶችን በማዳረስ ላይ ይገኛል፡፡ እንዲሁም የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትን በማፋጠን፣ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎትንና የአገር ውስጥና የውጭ አገር የገበያ ትስስርን በመፍጠርና በማጎልበት አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የመገንባቱ ግብ በአስተማማኝ ሁኔታ እየተተገበረ ይገኛል፡፡
በአገሪቱ ያሉ ክልሎች እርስ በርስ በመደጋገፍና ልምዶችን በመለዋወጥ የሚያደርጉት የጎንዮሽ ይሁን የተዋረድ ግንኙነት ለእኩል ተጠቃሚነትና በተመጣጣኝ ልማትና እድገት ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡
በመሆኑም የልማትና የመልካም አስተዳደር ማነቆዎችን በመፍታትና በጎ ልምዶችን በማስፋፋት ሂደቱን ማስቀጠል ከተቻለ አጭር በሚባል ጊዜ ውስጥ አገሪቱ መካከለኛ ገቢዎች ካላቸው አገራት ተርታ የማትሰለፍበት አንዳች ምክንያት የሚኖር አይመስለኝም፡፡
በሀገሪቱ ያሉ ክልሎች እርስ በርስ በመደጋገፍና ልምዶችን በመለዋወጥ የሚያደርጉት የጎንዮሽ ይሁን የተዋረድ ግንኙነት ለእኩል ተጠቃሚነትና በተመጣጣኝ ልማትና እድገት ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡
ይህም የልማትና የመልካም አስተዳደር ማነቆዎችን በመፍታትና በጎ ልምዶችን በማስፋፋት ሂደቱን ማስቀጠል ከተቻለ አጭር በሚባል ጊዜ ውስጥ አገሪቱ መካከለኛ ገቢዎች ካላቸው አገራት ተርታ የማትሰለፍበት አንዳች ምክንያት የሌለ መሆኑን የሚያመላክት ይመስለኛል፡፡
ዛሬ ዜጎች ለአዲስ ህይወት ማበብ ተስፋ ሰንቀው፣ በፀና ህብረት ላይ ቆመው፣ እጅ ለእጅ ተያይዘው ኑሮን ማጣጣም ጀምረዋል፡፡ ንፁህ አየር መማግ፣ በሠላም ገብቶ መውጣት፣ በነፃነት መንቀሳቀስን ችለውበታል፡፡
ለዚህ መብቃት የተቻለው ደግሞ ሺህዎች በከፈሉት የህይወት መስዋዕትነት ነው፡፡ በውጤቱም በመላ አገሪቱ ሠላም ተገኝቷል፤ የልማት መስመር ተይዟል፤ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ በፅኑ መሠረት ላይ ቆሟል፡፡
ያለፉት ዘመናት አስከፊ የህይወት ጉዞዎች ተገትተዋል፤ ዛሬ የመንግሥት ሥልጣን በሠላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ ብቻ የሚረከቡባት ሀገር መፍጠር ተችሏል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የተጎናፀፉትን ሠላምና ዴሞክራሲ መሠረት በማድረግ ከልማቱ በፍትሃዊነትና እኩልነት ተጠቃሚ ይሆኑ ዘንድ የፀና እምነት ይዘው አገራቸውን እያለሙ ነው፡፡ ይህም ሥርዓቱ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ዋስትና መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡