Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የሰርጎ ገቦችን የሽብር ጥቃት በንቃት እንከላከል

0 437

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የሰርጎ ገቦችን የሽብር ጥቃት በንቃት እንከላከል

ብ. ነጋሽ

የኤርትራ መንግስት ሃገሪቱ ነጻነቷን ካወጀች በኋላ ባሉት ዓመታት ከምስራቅ አፍሪካ አጎራባች ሃገራት ጋር ሰላማዊ ግንኙነት መመስረት አልቻለችም። ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ጋር መቀላቀል አልቻለም። የአንድ ግለሰብ አምባገነንነት የሰፈነበት የኤርትራ የመንግስት በይፋ የሃገሪቱን ነጻነት አውጆ አምስት ዓመት እንኳን ሳይሞላው ነበር በሉዓላዊ ሃገራት ላይ ጦርነት ማወጅ የጀመረው። በመጀመሪያ በ1988 ዓ/ም የሃኒሽ ደሴቶች ይገባኛል በሚል ከቀይ ባህር ማዶ የለችው የመን ላይ ወረራ ፈጸመ። በዚህ አላበቃም፤ በስተምእራብ አቅጣጫ ከሱዳን ጋርም ግጭቶችን ቀስቅሷል። በሃገሪቱ በስተደቡብ ምስራቅ የምትገኘውን ጅቡቲንም ሲተነኳኩስ ቆይቷል። በኋላም ሰኔ 2000 ዓ/ም ላይ ጅቡቲ ላይ ግልጽ ወረራ ፈጽሟል።

የኤርትራ መንግስት የየመን ሃኒሽ ደሴቶች ላይ በፈጸመው ወረራ ደሴቶችን ተቆጣጥሮ ቢቆይም፣ በዓለም አቀፍ አስታራቂ ፍርድ ቤት (intrernational court of arbitration) ደሴቶቹ የየመን መሆናቸው ተወስኖ የኤርትራ ሰራዊት ስፍራውን ለቅቆ እንዲወጣ ተደርጓል። የኤርትራ መንግስት በዚሁ ከየመን የሃኒሽ ደደሴቶች እንዲወጣ በተደረገበት ዓመት፣ ማለትም 1990 ዓ/ም ግንቦት ወር ላይ ፊቱን ወደደቡብ በማዞር  ኢትዮጵያ ላይ ወረራ ፈጸመ።

ኢትዮጵያ በ1992 ዓ/ም በአንድ ሰው በሚመራው የኤርትራ መንግስት የተሰነዘረባትን ወረራ ቀልበሳ በአካባቢው የነበረውን ሁኔታ ከወረራ በፊት ወደነበረበት እንዲመለስ ማድረጓ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው። ከዚህ በኋላ በሁለቱ ሃገራት ድንበር ላይ በተለይ ወረራውን ፈጽሞ በነበረው የኤርትራ መንግስት ወሰን ውስጥ 25 ኪሎ ሜትር የተባበሩት መንግስታት ሰላም አስከባሪ ልዑክ እንዲሰፍር ተወሰነ። የሁለቱ  ሃገራት የድንበር ጉዳይ በአልጀርሱ ስምመነት መሰረት በዓለም ፍርድ ቤት እንዲወሰን ተደረገ።

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ያሳለፈውን ውሳኔ ተቀብላ ወሰኑን መሬት ላይ የማካለል ስራ ግን በሁለቱ መንግስታት ውይይት እንዲከናወን የሚል አቋም ይዛለች። ይህ ተገቢ አቋም ነው። ተገቢ የሚያደርገው በፍርድ ቤቱ ውሳኔ ላይ የተገለጸው ድንበር ሃሳባዊ በመሆኑ፣ ይህን መሬት ላይ ካለው እውነታ ጋር በማጣጣም መካለል ያለበት መሆኑ ነው። ሃሳባዊ የድንበር ወሰን አንድ ቤተሰብን ሁለት ቦታ ቆርጦ ሊያለያይ የሚችል መሆኑን ልብ ይሏል።

ይሁን እንጂ፤ የኤርትራ መንግስት በውይይት መሬት ላይ ወሰን የማካለሉን የኢትዮጰያ ሃሳብ ሳይቀበል ይቀራል። በመቀጠል ሁለቱ ሃገራት የገቡትን የተኩስ አቁም ስምምነት በማስከበር ወሰን የማካለሉን ስራ ለማከናወን የሚያግዝ ሁኔታን ለመፍጠር ሰፍሮ የነበረውን የተባበሩት መንግስታት የሰላም አስከባሪ ልኡክ  እንቅስቃሴ ገደበ። በዚህም ምክንያት የሰላም አሰከባሪ ልኡኩ በ2000 ዓ/ም በኤርትራ መንግስት ምክንያት ሃላፊነቱን መወጣት አለመቻሉን አስታውቆ ተልዕኮውን በይፋ አቋረጠ።

ከዚህም በኋላ የኤርትራ መንግስት ቀጠናውን የማተራመስ ተግባሩን ቀጥሎበታል። በተለይ በ1998 ዓ/ም መንግስት አልባ በነበረችው ሶማሊያ አልሸባብ ይፋ የወጣ ሃይል ሆኖ ኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ሲያወጅ፣ የኤርትራ መንግስት ሰራዊት በማሰልጠንና መሳሪያ አጓጉዞ በማስታጠቅ አሸባሪ ሃይሉን ደግፏል። ከዚህ በተጨማሪ የኢፌዴሪን ህገመንግስታዊ ስርአት በሽብር ጥቃት ለማፍረስ የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ ቡድኖችን፤ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)፣ የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻነት ግንባር (ኦብነግ)፣ ግንቦት 7 እና ለሌሎች ጥቃቅን ቡድኖች ከለላ በመስጠት፣ በማደራጀት፣ ወታደራዊና የሽብር ጥቃት ስልት ስልጠና በመስጠት ኢትዮጵያን በእጅ አዙር ለማተራመስ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል። አሁንም በዚህ ድርጊቱ እንደቀጠለ ነው።

የኤርትራ መንግስት በተመሳሳይ በጅቡቲ ላይ ቀጥታ ወረራ ከመፈጸም ባሻገር፣ ልክ ኢትዮጵያ ላይ እንደሚያደርገው በእጅ አዙር የሽብር ጥቃት ሃገሪቱን የሚያተራምሱ ቡድኖችን አደራጅቶ ተልዕኮ እየሰጠ ያሰማራል።

ይህ የኤርትራ መንግስት የምስራቅ አፍሪካን ቀጠና የማተራመስ ተግባር በህቡዕ የሚከናወን ቢሆንም፣ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ መሰወር አልቻለም። በተለይ የዓለም አቀፉ አሸባሪ አልቃይዳ የአፍሪካ ክንፍ ለሆነው አልሸባብ የሚያደርገው ወታደራዊ ድጋፍ ከቀጠናውም አልፎ ዓለም አቀፍ ስጋት መሆኑ ከግንዛቤ ተወስዷል። እናም በ2002 ዓ/ም የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት የሶማሊያና የኤርትራ ክትትል ቡድን አቋቁሞ የኤርትራን መንግስት እንቅሰቀሴ እንዲያጠና ተደርጓል። የክትትል ቡድኑ በሚያቀርበው  ሪፖርት ላይ በመመስረት የኤርትራ መንግስት ላይ የመሳሪያ ግዢ፣ የተወሰኑ ምርቶች የወጪ ንግድ እና በውጭ ሃገራት ከሚኖሩ ዜጎቹና ተወላጆቹ በግዳጅ የሚሰበስበው ገቢ፣ እንዲሁም የተወሰኑ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች እንቅስቃሴ ላይ ማዕቀብ ተጣለ።

የጸጥታው ምክር ቤት የሰየመው የኤርትራና የሶማሊያ የክትትል ቡድን እስካሁን ስራውን እያከናወነ ይገኛል። ቡድኑ ከ2002 ዓ/ም ጀምሮ በየዓመቱ በሚያቀርበው የክትትል ሪፖርት መሰረት የኤርተራ መንግስት ላይ ማዕቀቡ ሲጸና መቆየቱ ይታወቃል። ዘንድሮም ይሄው ማዕቀብ እንዲጸና የጸጥታው ምክር ቤት በ11 የድጋፍ ድምጽ በ4 ድምጸ ተዐቅቦ ውሳኔ አሳልፏል፤ ከአስር ቀን በፊት ህዳር 5፣ 2010 ዓ/ም።

የክትትል ቡድኑ በኤርትራ ላይ ማዕቀቡ ለአንድ ዓመት እንዲራዘም ሲጠይቅ ባቀረበው ሪፖርት፣ የኤርትራ መንግስት ኢትዮጵያንና ጅቡቲን ለማተራመስ ዓላማ ለታጣቂ ቡድኖች ድጋፍ በመስጠት ተግባሩ መቀጠሉን ያስረዳል። የኤርትራ መንግስት የኢትዮጵያ ታጣቂ ተቃዋሚ የሆኑትን አርበኞች ግንቦት 7፣ የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄና የቤኒሻንጉል ህዝቦች የነጻነት ንቅናቄ ለተሰኙ ቡድኖች ወታደራዊ ስልጠና በመስጠት ወደኢትዮጵያ ሰርገው እንዲገቡ ሲያደርግ መቆየቱንም ይገልጻል። እነዚህ ቡድኖች ለኢትዮጵያ አስጊ አለመሆናቸውን የሚያመለክተው የክትትል ቡድኑ ሪፖርት፣ ይሁን እንጂ የኤርትራ መንግስት ለቡድኖቹ የሚያደርገው ድጋፍ በአካባቢው የሰላም ችግር እንዲኖር ያደርጋል፣ እንዲሁም በቀጠናው ሃገራት መሃከል ሊኖር ለሚገባው መልካም ግንኙነት ዋጋ የማይሰጥ ነው ይላል።

የኤርትራ መንግስት ላይ ለአንድ ዓመት ማዕቀቡ እንዲጸና የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት የወሰነው ከላይ የተገለጸውን የክትትል ቡድን ሪፖርት መነሻ በማድረግ ነው።

እንግዲህ፤ የክትትል ቡድኑ ሪፖርት የኤርትራ መንግስት ባለፉት 7 ዓመታት በማዕቀብ ስር ቢቆይም አሁንም ኢትዮጵያን ብሎም የምስራቅ አፍሪካን ቀጠና ከማተራመስ ድርጊቱ ያልተቆጠበ መሆኑን ያመለክታል። ይህ ደግሞ የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት በየዓመቱ እያጸና  ላለፉት 7 ዓመታት በኤርትራ ላይ እንዲቆይ ያደረገውን ማዕቀብ ቆንጣጭነት ጥያቄ ላይ የሚጥል ነው፤ በተለይ የኤርትራ መንግስት የትርምስ ስትራቴጂ ማስፈጸሚያ የሆነው የሽብር ጥቃት ዒላማ በሁኑት ኢትዮጵያውያን ዘንድ።

ኢትዮጵያውያን ከኤርትራ መንግስት የትርምስ ስትራቴጂ ቀጣይነት ጋር በተያያዘ የሚጠረጥሩት ነገር አለ። ይህም የኤርትራ መንግስት በተለይ ኢትዮጵያ ላይ የሚከተለውን የትርምስ ስትራቴጂ በስውር የሚደግፉ መንግስታት የመኖራቸው ጉዳይ ነው። የኤርትራ መንግስት ኢትዮጵያን በማተራመስ ዓላማው እስከጸና ደረስ ድጋፍ የሚያደርጉለት መንግስታት መኖራቸውን የሚያመለክቱ መረጃዎች አሉ። እናም ከከጸጥታው ምክር ቤት ማዕቀብ ቁንጠጣ ይልቅ ኢትዮጵያን ለማተራመስ በሚከተለው ስትራቴጂ የሚያገኘው ድጋፍ አይሎስ እንደሆነ? የክትትል ቡድኑ ይህንንም ቢቃኝ መልካም ነው።

ም ሆያነ ይህ፣ የኤርትራ መንግስት ኢትዮጵያን ለማተራመስ አደራጅቶ፣ አሰልጥኖና አስታጥቆ ያዘጋጃቸው ቡድኖች ኢትዮጵያን የሚያክል ግዙፍ ሃገር ላይ ጉዳት ማደረስ የማይችሉ ሚጢጢዎች ናቸው። ይህን የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት የሰየመው የክትትል ቡድንም በሪፖርቱ ላይ በግልጽ አስቀምጦታል። ይሁን እንጂ የሽብር ጥቃት በባህሪው በመንግስት የደህንነት ሃይሎች አቅም ብቻ መከላከል አይቻልም። ይህ በትላልቆቹ የአውሮፓ ሃገራት በአሜሪካም ጭምር በተግባር የታየ ነው።

በመሆኑም፣ የኤርትራ መንግስት አሰልጥኖና ፈንጂ አስታጥቆ የሚልካቸው አሸባሪዎች ንጹሃን ኢትዮጵያውያንን ዒላማ ያደረገ የሽብር ጥቃት ሊፈጽሙ የሚችሉበት እድል ሊኖር እንደሚችል መጠርጠር ብልህነት ነው። የመንግስት የደህንነት አካላት የዚህ አይነት ስጋቶችን ሙሉ በሙሉ ለማስቀረት የህዝቡን ድጋፍ ይፈልጋሉ። እናም የኢትዮጵያ ህዝብ፣ የኤርትራ መንግስት አሁንም የሽብር ጥቃት ዒላማ ያደረገው መሆኑን በማስታወስ፣ ከደህነነት አካላት ጋር በመተባበር የሰርጎ ገብ አሸባሪዎችን እንቅስቃሴ በመቆጣጠሩ ሂደት ሃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል።

  

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy