Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የብሔር ብሔረሰቦች በአል የኢትዮጵያዊነት ነፀብራቅ

0 4,991

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የብሔር ብሔረሰቦች በአል የኢትዮጵያዊነት ነፀብራቅ

ስሜነህ

የብሄር ብሄረሰቦች ቀን በዋናነት የብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች መብት የተረጋገጠበትን ህገ መንግስት መሰረት በማድረግ ህገ መንገስቱ በጸደቀበት ህዳር 29 ቀን በየአመቱ የሚከበር ታላቅ በዓል ነው። ይህ ተረክም በጻሉን ታላቅ  ካስባሉት ምክንያቶች መሰረታዊዎቹን እና የመከበሩንም ፋይዳ የሚያወሳ ነው። ሃገራችን ባለፉት 26 ዓመታት በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ በኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት ዘርፍ ላስመዘገበችው ውጤት መሰረቱ የመላው ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ሉዓላዊ መገለጫ የሆነው ህገ መንግስት መሆኑ የመጀመሪያው እና የነገሮች ሁሉ መነሻ ነው። የኢትዮጵያን የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታና ልማታዊ ጉዞ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሥር እየሰደደ እንዲሄድና ፈጣን ወደ ሆነ የልማት ጎዳና እንድትገባ ያደረገው መላው ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ገዢያችን ነው ሲሉ ያጸደቁት ህገ መንግስት ህዝቡን በውስጡ በያዛቸው ድንጋጌዎች  መምራቱ መሆኑም ተያያዥ የሆነው መነሻ ነው። ስለሆነም ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ይበልጥ እንዲተዋወቁ ተሞክሮ እንዲለዋወጡና የለውጣቸውም መሠረት የሆነውን ህገ መንግስት ከማናቸውም አደጋ ለመጠበቅ በጋራ ቃል ኪዳናቸውን ያድሱ ዘንድ የበዓሉ መከበር ዋነኛ ፋይዳ ነው።

ባሳላፍናቸው አመታት በየክልሉ የተከበሩት በዓላት ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች የተጀመረውን ልማት ለማስቀጠል የገቡትን ቃል በመፈጸም ረገድ በየዓመቱ መሻሻሎች ማሳየታቸውና በልዩነት ውስጥ ለምንገነባቸው አንድነትም ሆነ በአንድነት ሆነን ለምንገነባቸው ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶቻችን የሚኖረው ፋይዳ ተነግሮ የማያልቅ መሆኑን አረጋግጠዋል። ሃገሪቱ በመገንባት ላይ የምትገኘው ዴሞክራሲያዊ ስርአት የይስሙላ ሳይሆን ከኖንርበት ከመጣንበትና መሄድ ወደ ምንችልበት የሚያደርስ እንጂ አንዳንዶች እንደሚሉት የውጩን ገልብጦ የሚኮርጅ ወይም ደግሞ ለብተና የሚዳርግ እንዳልሆነም የብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች የሉአላዊነት መገለጫ በሆነው ህገ መንግስትና ህገ መንግስታዊ ስርአቱ ተረጋግጧል። ኢትዮጵያ የምትገነባውን ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መሠረት ማስያዝ ካለባት ብሄር ብሄረሰቦችን መነሻ በማድረግ ብቻ ነው የሚባለውም ስለዚህ ነው። እንደ አንድ ሆነን መሥራት የምንችለው በጅምላ አስገድደን ሳይሆን ልዩነትን ተቀብለንና እኩልነታቸውን አምነን ብቻ መሆኑን ያለፉት የ26 አመታት ጉዟችን በሚገባ አመላክተውናል።

መንግስት ዛሬ ላይ ባሳለፍናቸው 26 ዓመታት አስመዝገብኩ የሚላቸውና እስከነ ችግሮቹም በተግባር ለምናያቸው የልማትና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ውጤቶች ሁሉ ባለቤቶቹ ብሄሮችና ብሄረሰቦች መሆናቸው አያከራክርም። ስለሆነም ብሄሮች ብሄረሰቦችንና ህዝቦችን የዘነጋ ልማት የለም። ሊኖርም አይችልም። ብሄረሰቦችን የዘነጋ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የለም። ሊታሰብም አይችልም። የልማትም ሆነ የዲሞክራሲ መናሻውም ሆነ ግቡ ሃገሬው ነው። ሃገሬው ደግሞ የተለያየ ባህል ቋንቋና ኃይማኖት ያለው በመሆኑ የሁሉንም እኩልነት መሰረት ያደረገ አንድነት ግድ ይለናል ማለት ነው።

የትኛውም አይነት የሃገሪቱ ፖሊሲ መነሻ ብሄሮችና ብሄረሰቦች መሆናቸው እና እነዚህም የሚገለጹትና መልካቸውም ሆነ ልካቸው በደማቁ የሰፈረው በህገመንግስቱ ላይ በመሆኑ እለተ ቀኑን ማክበር የተያዘውን ልማትና የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ለማፍጠንም ሆነ ዘላቂ ለማድረግ ጠቃሚ ይሆናል ማለት ነው።

የኢትዮጵያ ህብረብሄራዊ የፌደራል ስርዓት የተመሰረተበት እና የብሄረሰቦች ቀን የሚከበርበት አንዱና መሰረታዊ የሆነው መነሻ ያለፉት ስርዓቶች የፈጠሯቸውን የተዛቡ ግንኙነቶች ለማስተካከልና ግንዛቤን ለመፍጠር ብሎም ለማሳደግ መሆኑም ሌላኛው መነሻ ነው። ያለፉት ሥርዓቶች የፈጠሯቸውን ግንኙነቶች ማስተካከል ማለት የብሄሮች ብሄረሰቦችና የሃይማኖት እኩልነትን ማረጋገጥ ማለት ነው። እነዚህ ማንነቶች ቋንቋዎቻቸው፣ ባህሎቻቸው፣ ታሪኮቻቸውና ሌሎች የማንነት መገለጫዎቻቸውን እንዲያስፋፉና እንዲያሳድጉ የሚያስችላቸው እኩል እድል መፍጠር ማለት ነው። ያለፉት ስርዓቶች በህዝቦች መካከል የፈጠሩትን ጥርጣሬና መራራቅ በማስወገድ ኢትዮጵያ ሁሉም ማንነቶች እኩል የሚስተናገድባት የብሄር ብረሰቦችና ህዝቦች ቤት እንድትሆን በማድረግ በአይነቱ የተለየ እና አስፈላጊነቱ ጥርጣሬ ላይ የማይወድቅ ግንኙነት እንዲፈጠር ማድረግ ማለት ነው። ስለሆነም የኢትዮጵያ ህዝቦች ከታሪካቸው የወረሱትን በጎ ትስስር በማጎልበት በእኩልነት ላይ የተመሰረተ አዲስ የህዝቦች ግንኙነት መፍጠር ከፌደራላዊ ስርዓቱ መሰረታዊ አስተሳሰቦች ዋናው በመሆኑም ይህ አስተሳሰብ ከገዢ ስርዓቱ ግንዛቤን የማስጨበጥ እጥረትና ያለፉት ስርዓት ናፋቂዎች የእሩምታ ተኩሶች ተፅእኖ አንፃር የተፈለገውን ያህል ባይሆንም እስከነእጥረቱ የማይቀለበስበት ደረጃ ላይ ደርሷል።   

 

የፌደራል ስርዓቱ ልዩ ባህሪያት እንደሆኑ በህገ-መንግስታችን የተመለከቱ ነጥቦችም የመነጩበት የአስተሳሰብ ደርዝ የህዝብ ልእልናን ወይም የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦችን ልዕልና መሰረት ያደረጉ ስለመሆናቸው ህገመንግስቱን ከነባራዊው ሁኔታ ጋር አገናዝቦ በማጤን በመገንዘብ ይቻላል። የኢትዮጵያ ህዝቦች ባለፉት የዘውድና የደርጉ ስርዓቶች በሃገራቸው እንደ ሁለተኛ ዜጋ የተቆጠሩበት ፍፁም ፀረዴሞክራሲያዊ ስርዓቶችን ማሳለፋቸውን መካድ ከእውነታው ጋር መጋጨት ነው። የወቅቱ ገዢዎችና አገልጋዮቻቸው የኢትዮጵያን ህዝብ ዕድል ለመወሰን የተቀመጡ አምባገነኖች እንጂ ህዝብን ሊያገልግሉ የተቀመጡ እንዳልነበረ ግልፅ ነው። ስለሆነም ከአዲሲቷ ኢትዮጵያ የሚጠበቀው አንዱና መሰረታዊ ጉዳይ የጥቂቶቹን ልዕልና ያሰፈነውን ያለፈውን ስርዓትና ለውርሱ የሚተጉ ሃይሎችን በዴሞክራሲያዊ መንገድ በማስወገድ የህዝቦችን ልዕልና ማረጋገጥ እንደሆነ ሳይታለም የተፈታ ነው። ይህም በመሆኑ ሃገሪቱ የምትመራባቸው መሰረታዊ መርሆዎች፣ ፖሊሲዎችና ህጎች የሚመነጩት የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ፍላጎቶችን ለማሟላት ስለሆነ የመንግስትም ሆነ የአጠቃላዩ ዜጎችና ማናቸውም በሃገር ላይ የሚከናወኑ ተግባራቶችና  እንቅስቃሴዎችም ከዚህ አንፃር እንዲቃኙ ግድ ይላል ማለት ነው።   

የኢትዮጵያ ህዝቦች የተነፈጉትን ማንነቶችና መብቶች፣ ታፍኖ የነበረ ታሪካቸውንና፣ ቋንቋቸውን ባህላቸውንና ሌሎች የማንነት መገለጫዎቻቸውን በህገ-መንግስቱ ማረጋገጥ ብቻ ሳይሆን በተግባርም ተፈፃሚ ማድረግ እንዲቻል የፌደራል ስርዓቱ አባል መንግስታት የተደራጁት ወይም የተዋቀሩት በመሰረቱ በብሄር ብሄረሰብ ሆኗል። ይህ የሆነበት ደግሞ ከላይ የተመለከቱት እንደተጠበቁ ሆነው ማንነቶች የተዛባውን ግንኙነት መወገዱን ማረጋገጫ እንደሆኑ ስላመኑበትና በዚህ አወቃቀር አዲስ እኩልነት ግንኙነትና የጋራ ህልውና እንዲመሰረት ስለወሰኑ ነው፡፡ የፌደራል ስርዓቱ ምንጭ የህዝብ ልዕልና ስለመሆኑ ማሳያ የሚሆነን ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት መሆናቸው ነው።

የዚህን የህዝብ ልዕልና መሰረት ያደረገው የህገ መንግስቱ አንቀጽ 8 ድንጋጌ ግልጽ ትርጉምም በመከባበር፤ በመተማመንና በመተባበር በእኩልነት አብሮ የመኖር ስምምነት እንጂ በዚህና በዚያ ቢሉ ያልሰመረላቸው የግዴታ ኢትዮጵያዊነት አቀንቃኞች እንደሚሉት የመገነጣጠል ስምምነት አይደለም።

የሃገራችንን ነባራዊ  ሁኔታ ስንመለከት የብሄር፣ ብሄረሰቦች እስር ቤት ልትሆን የቻለችው የቡድን ማንነቶችን ማፈን ዋነኛ የጭቆና መገለጫ ስለነበር ነው። ይህን ጭቆና በትግል በማስወገድ የራስ አስተዳደር መብትን በማረጋገጥ ብቻ የሚመለስ አልነበረም። ህገ መንግስቱን በማፅደቅ ሂደት ሲነሱ የነበሩ ጥያቄዎችና ክርክሮች ይህንን ግልፅ ያደርጋሉ። የአንዳንድ ብሄሮች የፖለቲካ ድርጅቶች ከጅምሩ የመገንጠል ጥያቄ አንስተዋል፣ አንዳንዶች ደግሞ ነባሩ የተዛባ ግንኙነት በፈጠረባቸው ስነ ልቦናዊ ጫና ምክንያት በሰንደቅ ዓላማ ቀለማት አመራረጥ ሳይቀር በስፋት መከራከራቸው ይታወሳል። ይህ የሚያመለክተው ከመገንጠል በመለስ ያለውን የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ማረጋገጥ ለብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በእርግጥ የሚያረካ እንዳልነበረ ነው። ካለፉት 26 ዓመታት ተጨባጭ ተሞክሮ የምንረዳው ጉዳይ የመገንጠል መብት የብሄርና ተጓዳኝ ጭቆናዎችን ለማስወገድ ዋስትና ተደርጎ እንደታየ፣ እንዲሁም ይህ መብት በህገ መንግስት ከተደነገገ በኋላ ጥያቄውን ሲያነሱ የነበሩ ሃይሎች በህብረቱ መቀጠል መቻላቸውን ነው።

በኢትዮጵያ የሚገኙ ሃይማኖቶች በተለያዩ ወቅቶች ከውጭ የገቡ እንደሆነ ይታወቃል። እነዚህ ሃይማኖቶች ተቻችለውና ተከባብረው ለመኖር የነበራቸውን ፍላጎት ብዙ ፈተና ሲገጥመው የነበረ መሆኑም ይታወሳል። በተለያዩ ወቅቶች የነበሩ ነገስታትና ሱልጣኖች አንዱ በሌላው የበላይነት ለመቀዳጀት በእምነቶች መካከል ግጭቶችና ጦርነቶችን ይቀሰቅሱ እንደነበርም የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ። በዚህ ምክንያት በርካታ አብያተ ክርስቲያናትና መስኪዶች ወድመዋል። ብዙ አማኞች ህይወታቸውን አጥተዋል፣ በተለይ በዘውድ አገዛዝ ዘመን አንድ ሃይማኖት በሕገ መንግስት የተደገፈ የበላይነት እንዲኖረው ተደርጓል። ሌሎች አማኞች ተገድደው እምነታቸውን እንዲለውጡ ተሞክሯል። በደርግ ጊዜም ሁሉም ሃይማኖቶች እምነታቸውን በነፃነት እንዳያራምዱ ታፍነዋል።   

መንግስት ሁሉም ዜጎች የሃገሪቱን  የተጠራቀመ እውቀትና ሃብት በፍትሃዊነት ይጠቀሙ ዘንዳ እንዲሰራ የተሰጠው ሃላፊነት መነሻው የብሄር ብሄረሰቦች ኢኮኖሚያዊ እኩልነት ነው። ይህ ደግሞ ለቀድሞዋ እና ደሃይቱ ኢትዮጵያ ሁነኛ ምክንያት የነበረ መሆኑ በተግባር የተረጋገጠ እና ይህንንም ለማስወገድ የሃገሪቱ ባለቤት የሆኑት ብሄር ብሄረሰቦችን ኢኮኖሚያዊ እኩልነት በማረጋገጥ ማስወገድ እንደሚቻል ስለታመነበት በህገ መንግስቱ አንቀጽ 89 አግኝቷል። ስለሆነም ይህን ቀን መዘከር ከላይ የተመለከቱ ጥቅሞችን እና ህልውናዎችን ማስቀጠል፤ ከማይቀለበስበት ደረጃ ላይ ማድረስና አዲሲቱ ኢትዮጵያ የምትንፀባረቅበትን መደላድል ማመቻቸት ይሆናል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy