Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የተዛነፈን አመለካከት ማቃናት ይገባል

0 390

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የተዛነፈን አመለካከት ማቃናት ይገባል

ሠዒድ ከሊፋ

ጠባብነት/ትምክህተኝነት ሊከስም የሚችለው የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አመለካከትን በማጠናከር ብቻ ነው፡፡ ጠባብነት/ ትምክህተኝነትን በማጋለጥ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አመለካከት እንዲሰርፅና ተቀባይነት እንዲያገኝ በማድረግ ብቻ ነው፡፡ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አስተሳሰብ ጠርቶና ተዘርዝሮ የገዢው ፓርቲ አባላት እና ካድሬዎቹ እንዲያውቁት ሲደረግ ነው፡፡

 

አብዮታዊ ዴሞክራሲን ከጥገኛ አስተሳሰብ በተለይም ከጠባብነት/ ከትምክህተኝነት የሚለየው መሰረታዊ ጉዳይ ጎልቶ እንዲወጣና፣ ጠባብነትን/ትምክህትን በአስተማማኝ ደረጃ እንዲተካ አልተደረገም፡፡ በሙስናና ፀረ ዴሞክራሲ አመለካከቶች ላይ በቂ ሥራ አልተሠራም፡፡ ሙስናና ፀረ ዴሞክራሲ አመለካከት ሲስፋፋ፤ ጥገኝነት እና የዚሁ መለያ የሆነው ጠባብነት/ ትምክህተኝነት መኖናቸው በፍፁም የማይቀር ነው፡፡ ፀረ ዴሞክራሲያዊ አገዛዝ ለመፍጠርና የመንግስት ሥልጣንን እንደ ልብ ለማለብ የሚችሉበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ሲሉ የጠባብነት/ ትምክህተኝነት አመለካከቶችን የሚያሰራጩ ጥገኞችን ከመዋጋት ውጪ ጠባብነት/ ትምክህተኝነት ሊሸነፍ አይችልም፡፡

 

ፀረ ዴሞክራቶችና ሙሰኞች ምንጊዜም ቢሆን መሸፈኛና መደበቅያ የሚሆናቸውን ጠባብነት/ትምክህተኝነት ከማስፋፋት ወደ ኋላ አይሉም፡፡ ስለዚህ ይህን የተገነዘበ እና ያላሰለሰ የፀረ ጠባብነት እና የፀረ ትምክህተኝነት ትግል ሊደረግ ይገባል፡፡ በየጊዜው በሚካዱ ግምገማዎች የሚደረገው ትግል እንደተጠበቀ ሆኖ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ የአመለካከት ጥራት እስካልተፈጠረና በጠባብነት/ ትምክህተኝነትና በአብዮታዊ ዴሞክራሲ መካከል ያለው መሠረታዊ ልዩነት በሚገባ ተሰምሮበት በጥልቀት እንዲጨበጥ እስካልተደረገ ድረስ፤ የፀረ ትምክህት እና የፀረ ጠባብነት ትግሉ ስኬታማ ሊሆን አይችልም፡፡

 

ይሄው ትግል በየቀኑ ጥገኛው የሚያሰራጫቸውን የተውገረገሩ ትንተናዎችና የሃሰት መረጃዎችን በማጋለጥና በአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ትንተናና መረጃ ለመተካት በሚያስችል ትግል እስካልተደገፈ ድረስ፤ ማህበራዊ መሠረቶቻቸውን ከመናድ፣ ሙስናንና ፀረ ዴሞክራሲን ከማጥፋት ትግል ጋር በቅርብ እስካልተቆራኘ ድረስ ውጤታማ የፀረ ጠባብነት/ የፀረ ትምክህተኝነት ትግል ሊሆን አይችልም፡፡

በመሆኑም ነው ውግዘቱና ትግሉ እንደተጠበቀ ሆኖ ውጤቱ ግን የጠባብነትና ትምክህተኝነት ይበልጥ መስፋትና ጥልቀት ማግኘት ሆኖ የቀረው፡፡ ለዚህ ነው ጠባብነት/ትምክህተኝነት የመበስበስ አደጋችን ዋነኛ ፖለቲካዊ መገለጫ መሆኑ በገሃድ የታየው፡፡

 

የመጀመሪያው የተሀድሶ ትግል የተደረገው በገዢው ፓርቲ ውስጥ የመበስበስ አደጋ እየተጠናከረ የመጣው ፀረ ዴሞክራሲና ሙስና እየተስፋፋ በመምጣቱ ነበር፡፡ ሰዎች ይህንኑ ክፍተት  በመጠቀም ራሳቸውን ወደ ጥገኛ ገዥ መደብ ለማሸጋገር በመንቀሳቀሳቸው ነው፡፡ ሙስናና ፀረ ዴሞክራሲ እዚያው እንዳለ ጠባብነት/ትምክህተኝነት በድርጅቱ እንዲስፋፋ ምክንያት ሆኖ ነበር፡፡ በመሆኑም፤ ጥገኞች ጠባብነትን እና ትምክህተኝነትን ለማስፋፋት የሚያሰራጯቸውን የተውገረገሩ ትንተናዎችና የሃሰት መረጃዎች በጠንካራ ያላሰለሰ ዴሞክራሲያዊ ፖለቲካዊ ትግልና ህይወት ከማጋለጥ ውጭ ጠባብነት/ትምክህተኝነትን ማሸነፍና መድፈቅ አይቻልም፡፡

 

የድርጅቱ ዴሞክራሲያዊ ፖለቲካዊ ህይወት እና ትግል በእጅጉ ሲላሸቅ፤ ጥገኞች የሚያሰራጯቸውን ትንተናዎችና መረጃዎች በብቃት ማጋለጥ አይቻልም፡፡ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ትንተናዎችን ትክክለኛ መረጃዎችን በማሰራጨት ረገድ ድክመት ይኖራል፡፡ በሂደትም የራሱ የድርጅቱ ትንተናዎች ጭምር እነዚህን የተዛቡ አስተሳሰቦች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የሚያጠናክሩ እየሆኑ ነው የመጡት፡፡ በቂና ትክክለኛ መረጃ አለመስጠቱ ብቻ ሣይሆን በሂደት የምንሰጣቸው መረጃዎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ጠባብነት/ ትምክህተኝነትን የሚያጠናክሩ እየሆኑ ነው የመጡት፡፡ ይህ ሁኔታ ጠባብነት/ ትምክህተኝነት በድርጅቱ ውስጥ እንዲስፋፋ መስፋፋት ምክንያት ሆኗል፡፡

 

ይሁንና በአንድ በኩል አሁንም ጨርሶ ካልተነቀለው ለኪራይ ሰብሳቢነት የተመቸ የፖለቲካ ኢኮኖሚ፤ በሌላ በኩል በሂደት በገዢው ፓርቲ ውስጥ ቀስ በቀስ እያደገ ከመጣው የአብዮታዊነት መዛነፍና የርዕዮተ አለም ብቃት መጓደል፤ እንዲሁም የውስጠ ድርጅት ትግል መዳከም ጋር ተያይዞ በመጀመሪያው ተሃድሶ ድል የተነሱት የጥፋት አመለካከቶች እንደገና አንሰራርተዋል፡፡ አልፎ አልፎም የፖለቲካ መድረኩን ማዕከላዊ ስፍራ ተቆናጠው ህብረተሰቡን ወደ ፖለቲካዊ ትርምስ ያስገቡበት ሁኔታ ተስተውሏል፡፡ በተለይ ደግሞ ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት የትምክህትና የጠባብነት ኃይሎች በድርጅትና በህብረተሰብ ደረጃ ገዝፈው በመታየት ለከፋ ቀወስ እና ለዜጎች ህይወት መጥፋት ሲዳርጉን አይተናል፡፡ ዜጎች በሰላም ወጥተው የሚገቡበት ዋስትና በማጣታቸው ሐገራችን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር የቆየችበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ገዢው ፓርቲ ድርጅቱን ከዚህ አሳሳቢ ችግር በፍጥነት ማውጣት ካልታለ ሊከተል የሚችለውን ሐገራዊ ቀውስ በመረዳቱ ዳግም በጥልቀት የሚታደስበት መድረክ ከፍቷል፡፡

 

በተሃድሶው ዋናው ችግር የመንግስትና የድርጅት ስልጣንን ለህብረተሰባዊ ለውጥ ሳይሆን ለግል ጥቅም ማስጠበቂያ የማዋል አዝማሚያ እየሰፋ መሄዱ መሆኑን አስቀምጧል፡፡ አመራሩ በተሰጠው ኃላፊነት ውጤታማ ሳይሆን እንኳን በወንበሩ ላይ የመቆየት ፍላጎት ያዳበረው ስልጣንን የኑሮው መሰረት በማድረጉ የተነሳ እንደሆነ የጠቀሰው ገዢው ፓርቲ፤ ከአመራሩ ጀምሮ እስከ አባላት ድረስ የትምክህት/ ጠባብነት አመለካከቶችን እንደ ተሸከመ ገልጧል፡፡

 

ጠባብነትና ትምህተኝነት እንደ አስተሳሰብ ዳግም ጎልተው የወጡበት ዋናው ምክንያት፤ በድርጅቱ ውሰጥ የሚካሄደው የፖለቲካ ትግል እና በዚህ አማካይነት እየዳበረ መሄድ የነበረበት የውስጥ ድርጅት ፖለቲካ ህይወት ስለተዳከመ መሆኑን አውስቷል፡፡ የውስጠ ድርጅት ፖለቲካዊ ህይወት በተቀዛቀዘበትና በተሟሟተበት ሁኔታ አስተሳሰቦቹ ዳግም ማገርሸታቸውንና ለስርአቱ ተጨባጭ አደጋ እስከመሆን የደረሱበትን መኖሩን አስተውሏል። በመሆኑም ‹‹ውስጣዊም ይሁን ውጫዊ ተግዳሮቶች በዋናነት ምንጫቸው የውስጠ ድርጅት ፖለቲካዊ ህይወት መዳከም መሆኑን በመረዳት፤ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ መርህ ላይ ቆመን የውስጠ ድርጅት ትግልን ከማጠናከር ውጭ ሌላ አማራጭ የለንም›› ብሎ፤ በዳግም ተሃድሶ እንቅስቃሴው ራሱን ከችግሮቹ አፅድቶ፤ የበደለውን ህዝብ ለመካስ ቃል ገብቷል፡፡ ገዢው ፓርቲ የገባውን ቃል ሊፈጽም የሚችለው፤ የትምክህት እና የጠባብነት አስተሳሰቦችን ከነመንስዔና የማምከኛ ስልታቸው በመጨበጥ እንደገና በጥብቅ ዲስፕሊን ትግል በማድረግ ነው፡፡ የትምክህት እና የጠባብነት አስተሳሰቦችን ታግሎ በማዳከም ለሐገራችን ሠላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ አደጋ የማይሆኑበት ሁኔታ በመፍጠር ነው፡፡

 

ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝቦች ሠላምን ይሻሉ፡፡ ዴሞክራሲንና ተጠቃሚ የሚሆኑበት ፈጣን ልማትንም ይሻሉ፡፡ ጠባብነትና ትምክህተኝነት በነገሱበት አገር ሠላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ብሎ ማሰብ በፍፁም የማይቻል ነው፡፡ ጠባብነት ሲነግስ ህዝቦች እንዲገነጣጠሉ፣ እንዲናቆሩና በጠላትነት እንዲተያዩ ነው የሚያደርገው፡፡ ትምክህተኝነት ሲነግስ በህዝቦች ላይ የበላይነቱን ለመጫን በሚያደርገው መፍጨርጨር ከፍተኛ የፀረ ጭቆና አመፅን ከዳር ዳር በመቀስቀስ ትርምስ እንዲኖር ነው የሚያደርገው፡፡

 

ጠባብነትና ትምክህተኝነት ሲነግሱ በሠላም ሠርቶ አብሮ መልማት ብቻ ሣይሆን በሠላም መለያየትም የሚቻል አይሆንም፡፡ ይህን ለመገንዘብ ሩቅ መሄድ አያስፈልገንም፡፡ ጠባብነትና ትምክህተኝነት እየተስፋፉ ሲመጡ፤ ኢህአዴግ ገና በስልጣን ላይ እያለ በየአካባቢው ዜጎች የሞቱባቸው መለስተኛና መካከለኛ ግጭቶች አጋጥመዋል፡፡ ጠባብነትና ትምክህተኝነት የበላይነታቸውን አረጋግጠው የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ባላንጣነት እየተጠናከረ ሄዶ ድርጅቱ ከመበታተን ደረጃ ቢደርስ ሐገራችን ከሶሪያም በላይ ለባሰ እልቂት እንደምትዳረግ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡

 

ታዲያ ከዚህ እልቂትና መበታተን ማንም ህዝብ ተጠቃሚ ሊሆን አይችልም፡፡ ህዝቦች ተጠቃሚ የሚሆኑት በሠላም፣ በልማትና በዴሞክራሲ ነው፡፡ ጠባብነትና ትምክህተኝነት እልቂትና የርስ በርስ ፍጅትን ነው የሚያመጡት፡፡ ሰላምን አጥፍተው ልማትና ዴሞክራሲ እንዲቀበሩ ነው የሚያደርጉት፡፡ ሁሉም ሰው ጠባብነት/ ትምክህተኝነትን ሊፋለመው የሚገባው ለዚህ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ የትግራይ፣ የወላይታ፣ የኦሮሞ፣የጉራጌ፣ የአማራ፣ ወዘተ… ህዝብን ምንም ብናደርግ ከእልቂት፣ ከእርስ በርስ መፋጀት፣ በረሃብ ከማለቅ ልናድነው ስለማንችል ነው፡፡ የእያንዳንዱ ብሔር አብዮታዊ ዴሞክራት በአካባቢው ያለውን ጠባብነት/ ትምክህተኝነት የሚፋለመው ለመላው ኢትዮጵያ ህዝብ በማሰብ ብቻ ሳይሆን በዋናነት ቆሜለታለሁ የሚለውን ህዝብ ከጠቅላላ ጥፋት ለማዳን ነው፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy