Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

“የትንሿ ኢትዮጵያ” መገለጫዎች

0 435

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

“የትንሿ ኢትዮጵያ” መገለጫዎች

                                                  ቶሎሳ ኡርጌሳ

የኢፌዴሪ ህገ መንግስት አንቀፅ 32 (1) ማንኛውም ዜጋ ወይም በህጋዊ መንገድ በሀገሪቱ ውስጥ የሚኖር የውጭ ዜጋ በመረጠው የሀገሪቱ አካባቢ የመዘዋወርና የመኖሪያ ቦታ የመመስረት እንዲሁም ከሀገር የመውጣት መብት እንዳለው ይደነግጋል። ይህ ድንጋጌ ዜጎች ማናቸውን ተግባራት በየትኛውም የሀገሪቱ አካባቢዎች ተዘዋውረው የመስራት፣ የመማርና ኑሮ የመመስረት መብት ያላቸው መሆኑን የሚያሳይ ነው። ለምሳሌ ያህል አንድ የባህር ዳር ነጋዴ ወይም ተማሪ ወደ አዳማ ወይም ጅግጅጋ ሄዶ ንግድ ሊያካሂድ አሊያም ሊማር ይችላል። ይህም በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ህብረ-ብሔራዊ ቀለምና አንድነት እንዲደምቅ ያደርጋል። በተለይ ዩኒቨርስቲዎች ይህን በመተግበር ቁልፍ ሚና አላቸው።

እንደሚታወቀው ዛሬ ዩኒቨርስቲዎች ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ ተማሪዎች ባህላዊ ትውፊቶቻቸውን የሚያስተዋውቁበት ቦታዎች ሆነዋል። “የትንሿ ኢትዮጵያ” መገለጫዎች ተብለውም እየተጠሩ ነው። እናም ተቋማቱ የትውውቅ መድረክ ፈጣሪዎች በመሆናቸው የተማሪዎቹ ስብጥር ሊጠበቅ ይገባል።

ግና በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ ዩኒቨስርቲዎች በተፈጠረ ሁከት ምክንያት ተማሪዎችን ከቦታ ቦታ ለማዘዋወር እየተደረገ ያለው ጥረት መፍትሔ ያመጣል ተብሎ የሚገመት አይመስለኝም። አንድነትንም ያጠናክራል ብዬም አላስብም። ከዚህ ይልቅ ችግሩ ባለባቸው አንዳንድ ዩኒቨርስዎች የህግ የበላይነት ማረጋገጥ ተገቢ ይመስለኛል።

በህገ መንግስቱ መሰረትም የዘጎችን የመንቀሳቀስ መብት መገደብ ነው። ርግጥ መብቶች በተለያዩ ሁኔታዎች ሊገደቡ ይችላሉ። ዳሩ ግን አብዛኛውን ጊዜ እንደ መፍትሔ ተደርገው ሊወሰዱ አይችሉም። ስለሆነም መብትን ከመገደብ ይልቅ በየከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ያለውን የህግ የበላይነት ማስከበር፣ ሁከት ፈጣሪዎችን ተጠያቂ ማድረግ ተገቢነቱ አያጠያይቅም።  

ማንኛውም የዚህ ፅሑፍ አንባቢ እንደሚገነዘበው፤ የህግ የበላይነት ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት ቁልፍ መሳሪያ ነው። ህገ መንግስቱም ለህግ የበላይነት ቅድሚያ በመስጠት በአንቀፅ ዘጠኝ ላይ እንዲደነገግ አድርጓል። ይህም በፌዴራላዊ ስርዓት ውስጥ የህግ የበላይነት ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን የሚያመላክት ነው።

ሁላችንም እንደምናውቀው ህገ መንግስቱ የህግ የበላይነትን ለማስጠበቅ ሲል ከህግ አግባብ ውጪ ስልጣን መያዝ የተከለከለ መሆኑን ደንግጓል። ይህም በህገ መንግስቱ ላይ በሚገባ ተገልጿል። የትኛውም አካል ህገ መንግስቱ ላይ ከተደነገገው ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ውጪ ነፍጥ አንግቦ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለመጣል የሚያደርጋቸው ማናቸውም ተግባራት ህገ ወጥ ናቸው። እናም በዚህ ተግባር ላይ የተሰለፉ ማናቸውም የፖለቲካ አሊያም የሽብር ድርጅቶች ህገ ወጥ ስለሆኑ ተጠያቂነትንም ያስከትላሉ።

ከእነዚህ የሽብር ቡድኖች ጋር የሚደረግ ማናቸውም ግንኙነት ወይም የእነርሱን አጀንዳ በማራመድ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ለመናድ የሚደረጉ ጥረቶች የህግ የበላይነትን መፃረር ነው። ምክንያቱም እነዚህ ሃይሎች ከህግ የበላይነት ጋር ሆድና ጀርባ ሆነው ሀገርን ለማወክ የተሰለፉ በመሆናቸው ነው። ዩኒቨርስቲዎች ደግሞ ይህን በማስከበር ረገድ ግንባር ቀደም ተቋማት ይሆናሉ ተብሎ ይታሰባል።

ርግጥ በዩኒቨርስቲዎችም ይሁን በማናቸውም ቦታ የህግ የበላይነት ልዕልና ካልተጠበቀ በሀገሪቱ የሚረቀቁ ማናቸውም ህጎች በሚፈለገው መጠን ገቢራዊ ሊሆኑ አይችሉም። ህጎች በሚፈለገው መጠን ገቢራዊ ካልሆኑና በቸልታ የሚታለፉ ከሆኑ የዜጎች መብቶች ሊሸራረፉ ይችላሉ። የመብት መሸራረፎች ደግሞ አንዱ እንዳሻው እንዲፈነጭ፤ ሌላው ደግሞ ህግና ስርዓትን አክብሮ እንዲንቀሳቀስ በማድረግ ሚዛኑን ያዛባዋል።

በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍሎች ውስጥ የህግ የበላይነትን አለማረጋገጥ ህገ መንግስቱን መፃረር ነው። “ለምን?” ከተባለ፤ ህገ መንግስቱ የህጎች ሁሉ የበላይ እንደመሆኑ መጠን፤ እርሱን ተከትለው የሚወጡ አዋጆችን ተፈፃሚ አለማድረግ መልሶ ህገ መንግስቱን መቃወም ስለሆነ ነው። የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲሁ ለይስሙላ የተደነገጉ አይደሉም። ዜጎች ሰዎች በመሆናቸው ሳቢያ የተጎናፀፏቸው መብቶች ናቸው።

እናም ማንኛውም አካል የህግ የበላይነት እንዳይሸረሸር መፍቀድ ያለበት አይኖርበትም። እንዲህ ዓይነት ዝንባሌ በሌላኛው እሳቤ የህግ የበላይነት ዕውን እንዳይሆን መፍቀድ በመሆኑ ነው። የህግ የበላይነትን መፃረር ስርዓት አልበኝነትን የሚፈጥር ከመሆኑም ባሻገር፤ ህጎች ለሁሉም ዜጎች እኩል እንዳይሰሩ ያደርጋል። ይህም ‘ሁሉም ሰው በህግ ፊት እኩል ነው’ የሚለውን ህገ መንግስታዊ መርህ ይጥሳል። እናም በየዩኒቨርስቲዎቹ ለሚፈጠሩት ሁከቶች የህግ የበላይነትን ማስከበር ቁልፍ ተግባር ሊሆን ይገባል።

የህግ የበላይነት ከሌለ ሰላም የሚባልን ነገር ማሰብ አይቻልም። ሰላም ከጠፋ ደግሞ ስለ ልማትና ዴሞክራሲ ማሰብ አይቻልም። ፀረ-ልማትዊነትና ፀረ-ዴሞክራሲያዊነት ቦታውን ይረከባሉ። ይህ ሁኔታ ደግሞ እንደ እኛ ሰላምን፣ ልማትንና ዴሞክራሲን የህልውናው ጉዳይ ላደረገ ሀገር አሜኬላ እሾህ መሆኑ አያጠያይቅም። እናም በየበዩኒቨርስቲዎቹ የህግ የበላይነት ሊተገበሩ ይገባል።

ሀገራችን የጀመረችው የዕድገትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ባህል ግንባታ ሂደት ስኬታማ ሆኖ እንዲቀጥል፤ አስተማማኝ ሰላም የሰፈነበት ምህዳርን መፍጠር የግድ ነው። ምክንያቱም ሀገራችን ፈጣን ልማትን ማምጣትና ከተመፅዋችነት መላቀቅ ብሎም ዴሞክራሲን መገንባት ወሳኝ ጉዳይ ስለሚሆንባት ነው። ሰላምን በማረጋገጥ ሂደት ውስጥ ለብሔራዊ ደህንነቷ ስጋት የሆኑ እንቅስቃሴዎችን መከላከልና መቆጣጠር ያስችላት ዘንድ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ይኖርባታል። ከዚህ አኳያ የሀገራችን ዩኒቨርስቲዎች የህግ የበላይነት ማሳያ ሊሆኑ ይገባል።

ተማሪዎች ያለ ሰላም ትምህርታቸውን ሊከታተሉ አይችሉም። በሰላም ውስጥ ሆነው ነገ ተምረውና ተመራምረው ሀገርን ሊጠቅሙ የሚችሉት። ያለ ሰላም በብጥብጥ ውስጥ የሚዳክር የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተማሪ ምንም ዓይነት ሀገራዊ ትሩፋት ሊያስገኝ አይችልም። እናም ዩኒቨርስቲዎች ይህን እውነታ ለተማሪዎቻቸው በማስረዳት የሰላምንና የህግ የበላይነት ዋጋን ግልፅ ሊያደርጉ የሚገባ ይመስለኛል።  

ከሁሉም በላይ ፌዴራላዊ ስርዓቱ የህግ የበላይነትን በሚገባ የሚያስከብር ነው። የህግ የበላይነትን ተላልፎ የሚገኝ ማንኛውም ዜጋ ተጠያቂ ይሆናል። ሁሉም ሰው በህግ ፊት እኩል እንደመሆኑ መጠን፤ በመረጃና በማስረጃ በተረጋገጠበት ጥፋት ልክ ተጠያቂ መሆኑ አይቀርም። ይህ አሰራር በማንኛውም ዜጋ ወይም አካል ላይ ገቢራዊ የሚሆን ነው።

አንዱን ዜጋ ከሌላው በማበላለጥ የሚከናወን የህግ አሰራር በፌዴራላዊ ስርዓቱ ውስጥ ፈፅሞ ሊኖር አይችልም፤ መቼም ቢሆን። እናም የህግ የበላይነትን ኢትዮጵያ ውስጥ ማስከበር ማለት የህገ መንግስቱን መንፈስ በሁሉም መስኮች ማስፈፀም ማለት መሆኑን የትኛውም ዜጋ ግንዛቤ መያዝ ይኖርበታል።

ርግጥ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ በነበርንበት ወቅት እንኳን የህግ የበላይነትን ለማስከበር ሲባል የዜጎች ሰብዓዊ መብት እንዳይነካ ከፍተኛ ጥንቃቄ ተደርጓል። ይህ ጥንቃቄ የተደረገው ህገ መንግስታዊው ፌዴራላዊ ስርዓት ለሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ጥንቃቄ ስለሚያደርግ ነው። የቱንም ወገን ለማስደሰት አሊያም ለማስከፋት ሲባል የሚከናወን የሰብዓዊ መብት ጥበቃ የለም። እናም ይህ ዓይነቱ የዜጎች መብት ጥበቃ በዩኒቨርስቲዎች ውስጥም አውን መሆን አለበት።

ዩኒቨርስቲዎች “የትንሿ ኢትዮጵያ” መገለጫዎች ናቸው። የዚህኛው አሊያም የዚያኛው ብሔር አሊያም ወገን መቆራቆሻ ቦታዎች አይደሉም። የህብረ-ብሔራዊነታችን ማሳያ መድረኮች ናቸው። በመሆኑም ተቋማቱ ለህግ የበላይነት ቅድሚያ በመስጠት ህዝብና መንግስት የጣሉባቸውን አስተምሮና ተምሮ ሀገርን የማነፅ ተግባራቸውን ሊወጡ ይገባል እላለሁ።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy