Artcles

የአባይ ጉዳይ ከግብፅ የአቋም መዋዥቅ አንፃር

By Admin

November 30, 2017

የአባይ ጉዳይ ከግብፅ የአቋም መዋዥቅ አንፃር

                                                                                           ይልቃል ፍርዱ

ሰሞኑን የግብጽ ሚዲያዎች ከቀድሞው ምን የተለየ ነገር እንዳገኙ ባይታወቅም ቀደም ሲል ቦስስትዮሽ የግንኙነቱ መድረክ ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን ከስምምነት ደርሰው ብዙ ርቀት ሄደው እየሰሩ የነበሩበትን ሁኔታ በማፋለስ የአባይ ውሀ ጉዳይ ለግብጽ የሞት የሽረት ጉዳይ ነው ሲሉ ፕሬዚደንት አልሲሲ መናገራቸውን የተለያዩ ሚዲያዎች በስፋት እያስተጋቡት ይገኛሉ፡፡ ግብጽ ተኮር ማሕበራዊ ሚዲያዎችም በዚሁ ዜና ተጠምደው ከርመዋል፡፡

ምናልባት በውስጥ በእስላማዊ አክራሪ ኃይሎች በሕዝቡ ውስጥ የተከሰተባቸውን ውጥረት ለማስተንፈስ አቅጣጫ ለማስቀየር የሕዝብ ቁጣ እንዳይቀሰቀስባቸው ከመስጋት የመነጨ ሊሆን እንደሚችል የሚደመጡ አስተያየቶች አሉ፡፡ ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ተዳድራ የማታውቅ በቅኝገዢዎች ስርም ያልነበረች ነጻነትዋን አስከብራ የኖረች ሀገር እንደመሆንዋ መጠን በማታውቀው፣ ባልተገኘችበት፣ ባልፈረመችው የቅኝ ግዛት ውል የምትገዛ ሀገር አይደለችም፡፡

በቀድሞዎቹ ውሳኔዎች የአባይ ውሀ ዋነኛ ባለቤትና 85 በመቶ የውሀው ምንጭ የሆነችው ኢትዮጵያ ተጠቃሚ አልነበረችም፡፡ ገና አሁን አቅም አግኝታ በአባይ ወንዝ ላይ ግድብ ለመስራት ስትነሳ፤ ምንም አይነት አለም አቀፍ የገንዘብ ብድርና እርዳታ እንዳታገኝ ከፍተኛ ተጽእኖና ጫና ስታሳድር የኖረችው ግብፅ፤ ኢትዮጵያ ግድብ ብትሰራ ወታደራዊ እርምጃ እወስዳለሁ በሚል ከጥንት እስከ ሕዳሴው ግድብ መጀመር ድረስ ስትዝት ቖይታለች፤ የሰማት የለም፤ ወደስራም ተገባ፡፡

የትላንትም ሆኑ የዛሬዎቹ በሚገባ ሊያውቁት የሚገባው ጉዳይ ኢትዮጵያ በግብጽ መሪዎች በየዘመኑ ሲሸረብባት የኖረውን የተሰራባትን ሴራና ደባ እያንዳንዱን ጠንቅቃ ታውቃለች፡፡ ለዚህም በየትውልዱ ፈረቃ ብዙ ማስረጃዎች አሏት፡፡ ኢትዮጵይ አልፋ ሄዳ ግብጽን የተተናኮለችበት ግዜ ድሮም ዘንድሮም የለም፡፡ ኢትዮጵያ የአባይ ውሀ ተፈጥሮ በጋራ እንድንጠቀምበት የሰጠን በመሆኑ የግብጽ ወንድምና ወዳጅ ሕዝብ ውሀ እንዲያጣ የምትፈልግ ሀገር አይደለችም፡፡ ይህንኑ ለዘመናት ስትገልጽና በተግባርም ስታሳይ ኖራለች፡፡

የተፈጥሮ አየር ንብረት በሚለወጥበትና ከፍተኛ ሙቀትና በረሀማነት ሲፈጠር ውሀው በትነት ይቀንሳል፡፡ አንዳንድ ዘመንም ዝናብ ሲጠፋ የአባይ ውሀ ሙላት ዝቅ ይላል፡፡ የውሀው መጠን የሚቀንሰው ለኢትዮጵያም ጭምር ነው፡፡ ይሄንን ክስተት ለበርካታ ሺህ ዘመናት እኛም፣ ሱዳንም፣ ግብጽም ኖረንበታል፡፡ ከፍተኛ ዝናብ ሲዘንብ ደግሞ ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ተራሮችና ሸለቆዎች አስገምግሞ የሚወርደው የአባይ ገባር ወንዞች ውሀ የሚፈጥረው ሙላትና መጥለቅለቅ ከኢትዮጰያ አልፎ ሱዳንን አቋርጦ ግብጽን እንደሚያጥለቀልቅ ይታወቃል፡፡

ኢትዮጵያ የአባይ ወንዝ ባለቤትነትዋን ያህል ብዙ መስራትና ማድረግ ስትችል ሳትጠቀምበት ኖራለች፡፡ ግብጾች ከእኛ የሚሄደውን የአባይን ወንዝ ውሀ በመጠቀም የአስዋን ግድብንና የናስር ሀይቅን ገንብተዋል፡፡ በእኛው ውሀ ታላላቅ ለአለም አቀፍ ገበያ የሚቀርቡ የብርቱካንና የሙዝ እርሻ የአሳ ማምረቻ ሰው ሰራሽ ሀይቅ ባለቤቶች ወዘተ ሆነዋል፡፡ ይሄ ሁሉ ውሀ የሚገኘው ከአባይ ወንዝ ውሀ ነው፡፡

ከዚህ አንፃር ኢትዮጰያን በፍቅርና በአክብሮት ነበር ሊመለከቱ የሚገባቸው፡፡ ዘመን ወደማይሽረው ጠላትነት የለወጣቸው እኛ ብቻ በአባይ ወንዝ ውሀ መጠቀም አለብን የሚለው ለራሳቸው ብቻ የማሰብ ስግብግብ ፍላጎታቸው ነው፡፡ ዛሬም እንደፈርኦኖች ከማሰብ አልወጡም፡፡ ይህ ደግሞ በምንም መንገድ በየትኛውም መስፈርት ለዚህ ለምንኖርበት የ20ኛው ክፍለ-ዘመን አይመጥንም፡፡ ተቀባይነት የለውም፡፡

የግብጹ ፕሬዚደንት አልሲሲ ዋነኛዋ የውሀው ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ የራስዋን መብት በመጠቀም በአባይ ወንዝ ውሀ ግድብ መስራት አትችልም፤ ግድብ ከሰራች የእኛ የውሀ ድርሻ መጠን ይቀንሳል፤ ስለዚህም የውሀው ጉዳይ ለግብጽ የሞት የሽረት ጉዳይ ነው ሲሉ መናገራቸው በራሱ ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ግድፈት ነው፡፡

ኢትዮጵያ በግልጽነት የታላቁን ሕዳሴ ግድብ ግንባታና ሂደት በተመለከተ ማንንም እንደማይጎዳ ይልቁንም ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ስታስረዳ ኖራለች፡፡ ግድቡ ውሀ እንዲሞላ በሚያጠራቅምበት ወቅትም ደግማ ደጋግማ ውሀ እንደሚለቀቅ፤ የግድቡ ውሀ ዋናው ስራም ኃይል ማመንጨት እንጂ ውሀውን በዘላቂነት ማጠራቀም እንዳልሆነ እንዲያውም የግድቡ መሰራት የአካባቢውን ሀገራት በኢኮኖሚ እንደሚያስተሳስር ያላትን ሃሳብ በተደጋጋሚ አጋርታለች፡፡

ኢትዮጵያ የግብጽ ሕዝብ በውሀ እጦትና እጥረት እንዲጎዳ አትፈልግም፡፡ የራስዋን የመጠቀም ሉአላዊ መብትም ለድርድር አሳልፋ የምትሰጥ ሀገርም አይደለችም፡፡ የአባይ ወንዝና የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ለኢትዮጵያና ለሕዝብዋ የሞትና የሽረት ጉዳይ ነው፡፡ የግድቡ ባለቤትም የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው፡፡ ግብጾች ኢትዮጵያ አለም አቀፍ የገንዘብ እርዳታ አግኝታ በአባይ ወንዝ ውሀ ላይ ግድብ እንዳትሰራ ሲያደርጉ የነበረውን ዘመናት ያስቆጠረ ሴራ በጣጥሶ የታላቁን ሕዳሴ ግድብ በራሱ ገንዘብ መስራት የጀመረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው፡፡

የግብጽ ሚዲያዎች ኢትዮጵያ በድርቅና በረሀብ ስትጠቃ የኖረች ድሀ ሀገር ነች፤ እንዴት አድርጋ ነው ትልቅ ግድብ በአባይ ወንዝ ላይ ልትገነባ የምትችለው በሚል ሲሳለቁ እንደነበር እናውቃለን፡፡ ያልተረዱት ነገር እነሱን ወደ ሀብትና ክብረት ማማ ያወጣቸው፤ አርሰው እንዲበሉ፣ ጠግበው እንዲያድሩ፣ ግድብና የአታክልት እርሻ፣ የሰው ሰራሽ ኃይቅ ባለቤት ያደረጋቸው፤ ድሀ ከሚልዋት ሀገር ማህጸን እየፈለቀ ወደ እነሱ የሚፈሰው የአባይ ወንዝ ነው፡፡

ግብጾች ይህንን እኛ ብቻ ጠግበን በልተን እንሙት የሚለውን ነውረኛ፣ ግለኛና ለሌላው ሕዝብ ከበሬታና ሀዘኔታ የሌለውን እጅግ ኋላቀር አስተሳሰባቸውን ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ ሊለውጡት፣ ሊቀይሩት ይገባቸዋል፡፡ የሚበጀው ተከባብሮ ተደማምጦ ተፈጥሮ በጋራ የሰጠችንን ከእኛም አልፎ ለእነሱ የተረፈውን የአባይን ወንዝ ውሀ በጋራ መጠቀሙ ብቻ ነው፡፡ ሱዳን የሕዳሴው ግድብ ውሀ ማቆር ሲጀምር እስከዛሬ ለግብጽ አሳልፌ ሳልጠቀምበት ስሰጥ የነበረውን የውሀ ድርሻዬን መጠቀም እጀምራለሁ ማለትዋ የማናውቀውና አዲስ የተገለጸ ምስጢር ቢሆንም እነሱ በራሳቸው ቋንቋ መወያየት መደራደር ይችላሉ፡፡

ሆኖም ግን በአባይ ወንዝ ውሀ እንደባለቤትነታችን የሌሎችን የመጠቀም መብት ሳንነካ በሙሉ ነጻነት የመጠቀም መብታችን በየትኛውም መልኩ ለድርድር አይቀርብም፡፡ ቅኝ ገዢዎች ኢትዮጵያ በሌለችበት የባለቤትነት መብትዋን ተዳፍረውና ረግጠው ያከፋፈሉት የውሀ ድርሻና መጠን ተቀባይት የለውም፡፡ እኛ ነጻነታችንን አስከብረን የኖርን እንደመሆኑ መጠን በቅኝ ግዛት ውልና ድርድር አንገዛም፡፡ አንተዳደርም፡፡

ይሄም ብቻ አይደለም ግብጾች ከአንዴም ሁለት ግዜ በቀድሞ ዘመናት ኢትዮጵያን ለመውረር ሞክረው ጦር አዝምተው ጉራና ጉንደት ላይ ተደምስሰው የቀሩት ሸሽተው መመለሳቸው በታሪካችን ተመዝግቦ ይገኛል፡፡ አሁንም ሰክኖ ማሰብ፣ አርቆ ማየት የሚጠቅመው ለግብጽ መሪዎች ነው፡፡ ማርሻል አልሲሲ ለምን በተለይ ይሄንን ግዜ መርጠው የአባይ ውሀ ጉዳይ ለግብጽ የሞት የሽረት ጉዳይ ነው ማለትን መረጡ የሚለውም ጉዳይ የተለየ ምስጢር የለውም፡፡ ማርሻል አልሲሲ ለኢትዮጵያ ቅርብ አጎራባች በሆኑ ሀገሮች ዙሪያ ጅቡቲ የመን ኤርትራ ሶማሊያ ሱዳን ውስጥ የግብጽን ጦር ሰፈር ለመገንባትና ሠራዊታቸውን ለማስፈር ብሎም ለግብጽ ተዋጊ ጀቶች ማረፊያና መነሻ የሆኑ ቦታዎችን ለማግኘት ያቀረቡት ጥያቄ በአንዳንዶቹ መንግስታት ውድቅ ቢደረግም በኤርትራ በኩል ቦታ አግኝተው ኃይላቸውን አስፍረዋል፡፡

ከኤርትራ አቅጣጫ ኢትዮጵያን ለማጥቃት የሚደረግ ማንኛውም የአየርም ሆነ የምድር ሙከራ ከጀርባው የግብጽ ሠራዊት እንደሚኖርበት ኢትዮጵያም አሜሪካም ሩሲያም ቻይናም እንግሊዝም ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ የገልፉ ሀገራት በሳኡዲ አረቢያ መሪነት በየመን ላይ ለሚያደርጉት ጦርነት ከኤርትራ የአሰብን ወደብ በሊዝ ገዝተው ሠራዊታቸውንና የጦር ጀቶቻቸውን አስፍረዋል፡፡ ከዚህም በመነሳት ነው የመንን የሚደበድቡት፡፡

ይህ ቀጣናውን በበላይነት ለመቆጣጠር የሚደረገው እሽቅድምድም ወደየት ያመራል? በዚህ ቁልፍ ስትራቴጂካዊ የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ያለችው ኢትዮጵያስ ይህን ሁኔታ እንዴት ታየዋለች? የሚለውን ጉዳይ ግዜ የሚመልሰው ይሆናል፡፡ ግብጽ በኢትዮጵያ ውስጥ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር የተለያዩ ተቃዋሚዎችን በገንዘብና በስልጠናና በትጥቅ እየደገፈች የታላቁን ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ለማሰናከል ትላንትም ዛሬም እየሰራች መሆኑን እናውቃለን፡፡ ስለምናውቅም አልተዘናጋንም፤ አንዘናጋምም። አባይ ይገደባል፤ እንደጀመርነው እንጨርሰዋለን!!!!!!