Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የአየር ንብረት ለውጥና ኢትዮጵያ  

0 326

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የአየር ንብረት ለውጥና ኢትዮጵያ                                                         አባ መላኩ

አረንጓዴ ኢኮኖሚ ያለው ጠቀሜታ ከብክለት ነፃ የሆነ ከባቢን ለመፍጠር ግቡ ያደረገ ነው። በየጊዜው የሚከሰተውን የድርቅ አደጋ በዘላቂነት ለመቋቋም ያለው ጠቀሜታም ከፍተኛ ነው። ኢትዮጵያም የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂን በመከተል ቀዳሚውን ሥፍራ ይዛ ትገኛለች።

መንግሥት ባለፉት ዓመታት በተፈጥሮ የአየር ንብረት ምክንያት የሚከሰተውን የድርቅ አደጋ ለመከላከልና በዜጎች ህይወት ላይ አንዳች ጉዳት እንዳይደርስ ብርቱ ጥረቶችን ከውኗል። መንግሥት የሚከውነው ህዝባዊ ወገንተኝነት እንደተጠበቀ ሆኖ፤ የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂን ቀርጾ ድርቅን በዘላቂነት ለመከላከል አገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ግዴታውን በመወጣት ላይ ይገኛል።

እየተተገበረ በሚገኘው በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን የዕቅድ ትግበራ ዘመን በሁሉም መስኮች አበረታች ሥራዎች በመከናወን ላይ ናቸው። በዕቅድ ተይዞ የሚከናወኑ ተግባሮች ውጤታማነታቸውም አበረታች ነው። የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ጠቀሜታን በተመለከተ ለአየር ንብረት ለውጥ በዋና ችግርነት የሚቀርቡት ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቁ የበካይ ጋዞች ልቅት መጨመርና የደን ሀብት እየተመናመነ መምጣት ነው። ይህንንም የዘርፉ ምሁራን በተደጋጋሚ ሲገልጹ ይሰማል።  

እነዚህን ችግሮች በዘላቂነት ለመቅረፍ የበካይ ጋዝ ልቀትን መቀነስና የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂን መከተል ይገባል። ከዚህም ጋር የተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤን ማጎልበትና በደን ልማት ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ተመራጭ መፍትሄ ነው። እነዚህም ዓለም ከስምምነት የደረሰባቸው እውነታዎች ናቸው። በግብርና ምርታማነት ላይ መሠረቱን ለጣለ ኢኮኖሚ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖው ከፍተኛ መሆኑ ሳይዘነጋ ማለት ነው፡፡

መንግሥት እነዚህን ችግሮች ለይቶ በማውጣት በርካታ ተግባራትን አከናውኗል፡፡ ለዚህ ተግባር ተስማሚ የሆነ፣ የሥራ ዕድልን የሚፈጥር፣ ምርትንና ምርታማነትን የሚያሳድግ፣ የአካባቢ መራቆት ሂደትን የሚከላከል፣ አካባቢውን ለልማት የሚያውል አገልግሎት የማቅረብ እንዲሁም ቀጣይ አቅምን የሚያጎለብት፣ በጎ ተሞክሮን እና ቴክኖሎጂን በማሰስ በርካታ ክንዋኔዎች ገቢራዊ አድርጓል፡፡

በዚህ መሠረት የአካባቢ አንክብካቤን መነሻ ያደረገ የእፅዋትና የፍራፍሬ ልማት ቴክኖሎጂን ወደአገሪቱ በማስገባት ተግባራዊ ማድረግ ተችሏል፡፡ ቴክኖሎጂው ተራራማና ደጋማ በሆኑ ሥፍራዎች በዓመታዊ ሰብሎች አመራረት ምክንያት የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ የዕፅዋትና የፍራፍሬ ልማት ብሎም የአፈርና ውኃ እቀባ ሥራዎችን በማቀናጀት የሚተገበር ነው፡፡

ይህ ሁኔታም የኅብረተሰቡን ገቢ በማሻሻል በተለይም ወጣቶችን እንደ ደን ቆረጣ ካሉ አካባቢን ከሚጎዱ የገቢ ማስገኛ መስኮች በማላቀቅ አማራጭ ወደሆኑ የገቢ ማስገኛ መስኮች ትኩረታቸውን እንዲያደርጉ የሚያግዝ ነው።  

ከዚህ ሌላ በእርሻ ላይ የተመሠረተው ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ ለሚደረገው ሽግግር አጋዥ ይሆናል። ቴክኖሎጂው ከፍተኛ ዋጋ የሚያውጡ የሰብል፣ የዛፍ፣ የፍራፍሬና አትክልት ዝርያዎችን፣ የእንስሳት እርባታና ድለባን፣ የንብ ማነብ ሥራዎችን አቀናጅቶ በማልማት የገቢ ምንጭን ያሳድጋል።  

ትግበራው በምጣኔ ሀብቱ ከሚያሳርፈው አዎንታዊ ተፅዕኖ ባሻገር፤ በተፈጥሮ ሀብት ላይ የሚያደርሰውን ጫና በመቀነስ ጉልህ ሚናን ይጫወታል፡፡ ፊዚካላዊና ሥነ ህይወታዊ የአካባቢ ሥራዎችን በመከወን የተጎዱ ሥፍራዎች መልሰው እንዲያገግሙ በማድረግና የአፈር መሸርሸርን በመከላከል የአፈር ለምነትን ለመጨመር እገዛ እያደረገ ይገኛል።  

ከዚህ በተጓዳኝ ቴክኖሎጂው የእፀዋት እና እንስሳት ዓይነቶች እንዲበራከቱ ድርሻ አለው።  አካባቢውም በተለያዩ እፀዋቶች ሲሸፈን የአካባቢው ውበት ስለሚያምር ለኅብረተሰቡ የመዝናኛ ቦታን ያበረክታል፤ ንፁህ ከባቢን ለመፍጠር የሚደረገውን ርብርብም ያግዛል። ፡

የአካባቢ ጥበቃን መሠረት አድርገው እየተተገበሩ ካሉ ቴክኖሎጂዎች መካከል፤ የተጎዱ መሬቶችን ከእንስሳትና ከሰው ንክኪ ነፃ ሆነው እንዲያገግሙ የማድረግ ቴክኖሎጂ ቀዳሚው ነው፡፡ ቴክኖሎጂው በእፀዋት ሽፋን መሳሳትና በአፈር ለምነት መቀነስ ምክንያት የተጎዱና ምርታማነታቸው የተቋረጡ መሬቶች መልሰው እንዲያገግሙ በማድረጉ ረገድ የበኩሉ አስተዋጽኦ አለው።  

ቴክኖሎጂው የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ እንዲያገግሙ ለማድረግ በየአካባቢው መልክዓ ምድር ሊተገበር ይችላል። ለአካባቢው አየር ፀባይ ተስማሚ የእፀዋት ዝርያ በመምረጥ፣ ተስማሚ የእርከን ዓይነቶችን በመለየት እና የገቢ ምንጭ ሊያስገኙ የሚችሉ ሥራዎች ተቀናጅተው የሚሰሩበት ሁኔታ በማጤን ኅብረተሰቡ የሚጠቀምበትን መንገድ ለማሳየት በርካታ ተግባሮች እንዲከናወኑ አስችሏል፡፡

ኅብረተሰቡም የተጎዱ ቦታዎችን መልሶ እንዲያገግሙ የማልማት ብሎም እውቀትና ክህሎት እንዲዳብር አጋዥ ሆኗል። የመሬት ጥበቃ ችግርን በሰበብነት በመጥቀስ ዜጎች ከአካባቢያቸው እንዳይሰደዱ አስተዋጽኦ አበርክቷል።  

ከዚህ በተጨማሪ የጓሮ አትክልቶችንና ፍራፍሬዎችን አልምቶ ራስንና ቤተሰብን ለመመገብ ብሎም ጤናው እንዲሻሻል በማድረግ ረገድ መንግሥት አስቀድሞ በሽታን ለመከላከል ለያዘው ዕቅድ የራሱ ሚና ተጫውቷል።  

በዚህ ምክንያት በየአካባቢው ጠፍተው የነበሩ የእፀዋትና የእንስሳት ዝርያዎች በመመለስ ላይ ይገኛሉ፡፡ ቴክኖሎጂው ለአካባቢ ጥበቃ ከሚያደርገው ጉልህ ድርሻ ባሻገር፤ ከግብዓት አቅራቢዎች ጋር የአቅርቦት ትስስር በመፍጠር በማኅበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው አድርጓል፡፡ ምጣኔ ሀብታዊ ጠቀሜታው አስተማማኝ በመሆኑም ለቴክኖሎጂ ዘላቂነት  ሚናውን እየተጫወተ ይገኛል፡፡

የተጎዱ መሬቶችን መልሶ እንዲያገግሙ ለማድረግ የተለያዩ አገር በቀል ዛፎችን መትከል ሌላው ዋነኛ አማራጭ ነው፡፡ ለዚህ ስኬታማነት ደግሞ በርካታ የችግኝ ማፍያ ጣቢዎችን በስፋት መጠቀም ተገቢነት ይኖረዋል። በዘርፉ ለተሰማሩ ባለሃብቶችም ከፍተኛ ዋጋ ያላቸውን የዛፍ፣ የፍራፍሬና የአትክልት ችግኞችን ለገበያ በማቅረብ የሥራ መስክ በመፍጠር በኩል ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል፡፡

በአነስተኛ እና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች ለተደራጁ ዜጎች የሰብል ፍርፍሬና፣ አትክልት የዛፍ ችግኞችን አቀናጅቶ በማምረት የገቢ ምንጫቸውን ማሳደግ ተችሏል፡፡ እነዚህ ጥቅል የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ምጣኔ ሀብታዊ ጠቀሜታዎች ለኢትዮጵያ ብሎም ለአፍሪካ እንዲሁም ለዓለማችን ወሣኝነታቸው አያጠያይቅም። ዜጎች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች በግልና በጋራ ችግኞችን በመትከል፣ ከፀደቁ በኋላም በመንከባከብ የድርሻቸውን ሊወጡ  ይገባል።  

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy