Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የአገልግሎት አሰጣጦች እየተሻሻሉ ነው!

0 396

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የአገልግሎት አሰጣጦች እየተሻሻሉ ነው!

                                                  ደስታ ኃይሉ

መልካም አስተዳደርን አንድ ዴሞክራሲያዊ ማህበረሰብ ሊያገኘው የሚገባው ጉዳይ ነው። የዴሞክራሲም መገለጫ ነው። በአሁኑ ሰዓት ቀደም ሲል በህዝቡ ይነሱ የነበሩት የመልካም አስተዳደር ችግሮች በሂደት እየተፈቱ ናቸው።

በተለይም ዋና ዋና የአገልግሎት አሰጣጦችን እየተሻሻሉ መጥተዋል። የመብራት አገልግሎት፣ የንፁህ ውሃ አቅርቦት፣ የመንገድ መሰረተ ልማት ዝርጋታና ሌሎች የመሰረታዊ የአገልግሎት አሰጣጦች መሻሻሎችን እያሳዩ ነው። ይህ ሁኔታም መንግስት በጥልቅ ተሃድሶው መጀመሪያ ላይ ለህዝቡ የገባውን ቃል ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን የሚያረጋግጥ ይመስለኛል።

በመንግስት ስልጣን የመገልገል ፍላጎት ያላቸው አንዳንድ የመንግስት ስራ አስፈፃሚዎች ለመልካም አስተዳደር ችግር መፈጠር ምክንያት እንደነበሩ አይዘነጋም። መንግስትም ይህን የብልሹ አሰራር ሁኔታ በማመን በጥልቅ ተሃድሶው መጀመሪያ ላይ ችግሩን ከህዝቡ ጋር በመሆን እንደሚፈታው ቃል ገብቶ ነበር። በገባው ቃል መሰረትም በሂደት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በሂደት እየፈታ ነው።

ይሁን እንጂ በአንዳንድ ተቃዋሚዎች በኩል የሚነሳው ትችት መንግስት በዚህ ረገድ ምንም ነገር እንዳልሰራ ለመገምገም የሚሞክር ነው። ይህ ግምገማም በአስፈፃሚው አካል ላይ ካላቸው የደፈና ጥላቻ የመነጨ ይመስለኛል። በተለይም በሀገራችን የህግ አስፈፃሚ አካላት ላይ የሚያነሷቸው ትችቶች አሉባልታን መሰረት መሰረት ያደረጉ በመሆናቸው ችግሩን ለመቅረፍ የመፍትሔው አካል ሲሆኑ አይታዩም።

ዳሩ ግን የሀገራችን የህግ አስፈፃሚ አካላት ተቃዋሚዎቹ እንደሚያስደምጡን በጥላቻና በአሉባልታ ላይ የተመሰረተ ህፀፅ ማውጣት ሳይሆን፤ ይህ አካል በህግና በህግ ማዕቀፍ ውስጥ ብቻ የሚመራና የሚሰራ ነው። በመሆኑም አባሎቻቸው በወንጀል ተጠርጥረው በህግ ጥላ ስር ሲውሉ “የህግ የበላይነት የለም” እያሉ ትችት የሚያቀርቡት ተቃዋሚዎች ይህን ሃቅ ሊረዱት የሚገባ ይመስለኛል። ምክንያቱም በህግ ጥላ ሰር የሚገኝ ማንኛውም ታራሚ ህጉ የሚፈቅድለትን ነገሮች ሁሉ ከማከናወን የሚያግደው አንዳችም ነገር ስለሌለ ነው። ይህም የመልካም አስተዳደር ቁልፍ መርህ የሆነው የህግ የበላይነት ያለምንም መሸራረፍ ገቢራዊ ለማድረግ ታስቦ የሚከናወን መሆኑ ግልፅ ሊሆን ይገባል።

እናም ተቃዋሚዎች አመራሮቻቸው ወይም አባሎቻቸው በህጉ መሰረት በህግ ጥላ ስር ሲውሉ ዕውነታውን እዚህ ሀገር ውስጥ ዕውን መሆን ካለበት ከህግ የበላይነት አኳያ መታየት ይኖርበታል።

በመሆኑም የተቃውሞው ጎራ አመራሮች የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ሲባል ህግ በቁጥጥሩ ስር ሲያውላቸው ለእነርሱ ተብሎ የሚቀለበስ ወይም እነርሱን ለመጉዳት ተብሎ የሚፈፀም የህግ አግባብ አለመኖሩን መገንዘብ ያለባቸው ይመስለኛል።

እንደሚታወቀው በፍርድ ቤት በተያዘ ጉዳይ አስፈፃሚው አካል በማንኛውም መስፈርት ጣልቃ የሚገባበት ሁኔታ የለም። ምናልባትም እንዲህ ዓይነቱ ጣልቃ ገብነት ተቃዋሚዎቹ በሚያራምዱት ፀረ-ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ውስጥ ገቢራዊ ሊሆን ይችላል። በህግ ልዕልና እና ሁሉንም ጉዳዩች በህግ ማዕቀፍ ውስጥ ብቻ ለሚመለከት አካል ግን ምንም ዓይነት ቦታ ሊኖረው የሚችል አይመስለኝም።

ወደ ተነሳሁበት ነጥብ ልመለስና መንግስት በጥልቅ ተሃድሶው ዋዜማ ወቅት በገባው ቃል መሰረት ከህዝቡ ጋር በመሆን የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ለውጥ እያመጣ ነው። በዚህም በተለይ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የያዛቸውን ውጥኖች ለማሳካት እየጣረ ይገኛል።

መንግስት የአገራችን ህዳሴ እንቅፋት ይሆናል ተብሎ የሚታሰበውን ሙስናንና ኪራይ ሰብሳቢነትን አስተሳሰብና ድርጊት ከምንጩ ለማድረቅ ሲባል የራሱን ከፍተኛ ባለስልጣናት ሳይቀር በህግ ፊት በማቅረብ ቁርጠኝነቱን አሳይቷል። በዚህም አስተማሪ በሆነ መንገድ ትምህርት ለመስጠት ሞክሯል።

ምንም እንኳን የሙስና እና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር በአጭር ጊዜ በቁጥጥር ስር ሊውል የሚችል ባይሆንም፣ ድርጊቱን በሂደት የመቅረፍ ስራዎች ተከናውነዋል። “በሁለተኛው ዕትዕ” ወቅት በዘርፉ ዙሪያ የሚከናወነው ተግባርም በቀዳሚው የዕቅድ ዘመን የተካሄደውን ሁሉን አቀፍ ክንዋኔዎች የሚያጠናክርና አዳዲስ አሰራሮችን የሚከተል ነው።

እስቲ በቅድሚያ “ዕትዕ ሁለትን” ጥቅል እሳቤዎችን በአጭሩ እንመልከትና የልማት ዕቅዱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ከመፍታት አኳያ ሊጫወት የሚችለውን ለመመልከት እንሞክር።

ሁለተኛው የአምስት ዓመት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በሀገራችን የተጀመረውን የትራንስፎርሜሽንና የህዳሴ ጉዞ በማፋጠን በ2017 ዓ.ም ኢትዮጵያን የመጀመሪያ ደረጃ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለማሳለፍ በሚደረገው ጥረት ወሣኙን ምዕራፍ የያዘ ነው። የዜጐችን እኩል የልማት ተሳታፊነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና ልማታዊ የፖለቲካ ኢኮኖሚ እና አንድ የጋራ ማህበረሰብ ለመገንባት የላቀ አስተዋፅኦ ያለው ዕቅድ ነው፡፡

ስለሆነም የዕቅዱ ዋና መነሻ በ2017 ዓ.ም ኢትዮጵያን የመጀመሪያ ረድፍ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች ተርታ የማሰለፍ ሀገራዊ ራዕይን የነገበ ነው ማለት ይቻላል፡፡ እናም በቀጣዩ የአምስት ዓመት ዕቅድ እስከ 2012 ዓ.ም ድረስ የሚከናወኑ የልማት ተግባራት በጥቅሉ ሲታዩ፣ ወደዚሁ ሀገራዊ ራዕይ እንዲያደርሱን ሆነው የተቀረፁ መሆናቸውን መገንዘብ ያሻል፡፡

ሁለተኛው የልማት ዕቅድ ሀገራዊ የሴክተር ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችንም በመነሻነት የያዘ ነው። እንደሚታወቀው ሁሉ በአገራችን ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገትንና ትራንስፎርሜሽንን ለማረጋገጥ እንዲሁም በየደረጃው የሕዝቡን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ዕውን ለማድረግ ብሎም የዴሞክራሲ ሥርዓታችንን ለመገንባት በሚገባ የተዘረዘሩ አገራዊ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ተዘጋጅተው በመተግበር ላይ ናቸው።

መንግስት እያከናወነ ባለው ስራ የፖለቲካ ኢኮኖሚው ኪራይ ሰብሳቢነት የበላይነት ከያዘበት ወደ ልማታዊነት የበላይነት ወደ ያዘበት መሸጋገሩ የሚቀር አይደለም። በመሆኑም በአንድ ወገን ልማታዊነትን የሚያጐለብቱ ድጋፎችን በጥራት በማቅረብ፣ በሌላ በኩል የኪራይ ሰብሳቢነት ዋነኛ ምንጭ ሆነው የተለዩትን ጉዳዮች በልዩ ትኩረት በማድረቅ ኪራይ ሰብሳቢነት፣ ሙስናና ብልሹ አሠራሮችን በቁጥጥር ሥር በማዋል ልማታዊነት የበለጠ እንዲጐመራና የአንበሳውን ድርሻ እንዲይዝ ማድረግ እንደሚቻል በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። ይህም መልካም አስተዳደርን ዕውን ከማድረግና በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ እጅግ ወሳኝ ድርሻ ይኖረዋል።

ከተሃድሶው በአሁኑ ሰዓት የመብራት መቆራረጥ ቀንሷል፣ የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግርም እየተቃለለ ነው። የመንገድ መሰረተ ልማት ዝርጋታም እየተሳለጠ ነው። ሌሎችም የአገልግሎት አሰጣጦች እየተሻሻሉ ናቸው። ውጤቶቹ የተገኙት መንግስት ከህዝቡ ጋር በመሆን ያደረገው ጥረት ነው። እነዚህ ጥረቶች ወደፊትም በተጠናከረ ሁኔታ ከቀጠሉ ህዳሴያችንን ቅርብ የሚያደርጉ ናቸው።

 

  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy