የኢትዮጵያ ህዝቦች ምርጫ
ደስታ ኃይሉ
አገራችን የምትከተለው የፌዴራሊዝም ሥርዓት የኢትዮጵያ ህዝቦች ምርጫ ነው። የአገራችን ብሔሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ሁሉም ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው በፌዴራላዊ ሥርዓቱ ተከብሮላቸዋል። ከእነዚህም ውስጥ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት፣ ማንኛውም ሰው በህግ ፊት እኩል መሆኑ እንዲሁም ዜጎች ከአገራዊው እድገት ተጠቃሚ እንዲሆኑ መቻላቸው ሥርዓቱ የህዝቦች ምርጫ እንዲሆን አድርጓል።
ለምሳሌ ያህል የራስን እድል በራስ የመወሰን መብትን ብንመለከት፤ ይህ መብት ህገ መንግስታዊ ዋስትና ያለው ነው። በአንቀጽ 39 ስር የተደነገገውና የብሔር፣ ብሔረሰቦችንና ህዝቦችን የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እስከመገንጠል መብትም የሀገራችንን ፌዴራሊዝምን ልዩ ገጽታ የሚያላብሰው የማዕዘን ድንጋይ ነው፡፡
ይህ አንቀፅ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በመፈቃቀድና በአንድነት መኖር የሚያስችላቸውን ዴሞክራሲያዊ የአንድነት ዕድልንም አብሮ ይሰጣል፡፡ ታዲያ ይህን ዴሞክራሲያዊ አንድነት ለመፍጠር ህዝቦች የእኩልነት መብታቸው መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡
በመሆኑም በአንቀጹ አማካኝነት የእኩልነት መብት ማረጋገጫ የሆኑት የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቋንቋዎች፣ ባህሎች፣ ታሪኮች ወዘተ ተከብረዋል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ በፖለቲካዊ አስተዳደር በኩል እኩል የመሳተፍ መብት ያገኙ ሲሆን፤ በልማት ስራው ላይም እኩል ዕድል እዲያገኙና በውጤታቸው መሰረት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ተችሏል፡፡
ታዲያ እነዚህን መብቶች ሁሉ ያረጋገጠ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በምን ምክንያት ሊገነጠሉ ይችላሉ? የመብቶቹ ባለቤት በመሆኑም ጥቅሞቹን እያጣጣመ የፌዴራል ስርዓቱን ያጠናክራሉ እንጂ በምን ዓይነት የሂሳብ ቀመር ሊበታተኑ ይችላሉ?
በመሆኑም አንዳንድ ወገኖች በአንቀጽ 39 ላይ ያላቸው የስጋት ምንጭ ቀዳሚዎቹን አሃዳዊ ስርዓቶች ከመናፈቅ የመጣ አሊያም ህገ -መንግስቱን ቀድዶ ለመጣል ከመፈለግ የመነጨ ከመሆኑ በስተቀር እስካሁን ድረስ ያለው ተጨባጭ እውነታ የመበታተን ስጋትን የሚያመላክት አይደለም፡፡
ይህ የሀገራችን ተጨባጭ ሃቅም በመስኩ ምሁራን የተረጋገጠ ነው፡፡ የፌዴራሊዝም ምሁሩ ጆርጅ አንድርሰን እንደሚናገሩት፤ ምንም እንኳን የመገንጠል ጥያቄ ሊኖር የሚችለው በፌዴራል ስርዓቱ ውስጥ ነው ተብሎ ቢታሰብም እስካሁን ድረስ ያለው ነባራዊ ሁኔታ የሚያመላክተው አብዛኛዎቹ አሃዳዊ መንግስታት መበታተናቸውን ነው፡፡ እናም የራሰን እድል በራስ የመወሰን መብት የህዝቦች ዋስትና ስለሆነ የፌዴራል ሥርዓቱ ተመራጭ እንዲሆን አድርጎታል፡፡
ማንኛውም ሰው በህግ ፊት እኩል መሆኑና ከዚህ አኳያ ዜጎች መብታቸው እንዲጠበቅ መደረጉ ሥርዓቱን ተመራጭ የሚያደርገው ነው፡፡ የኢፌዴሪ ህግ መንግስት የህግ የበላይነትን አረጋግጧል።
በኢፌዴሪ ህገ መንግስት ላይ በግልፅ እንደተደነገገው፤ ማንኛውም ሰው በህግ ፊት እኩል ነው። በመሆኑም ማንኛውም አዋጅ ሲወጣ ሁሉንም ዜጋ ይመለከታል እንጂ ለተለየ የህብረተሰብ ክፍል ተለይቶ አይደለም።
በህግ ካለተደነገገ በስተቀር በየትኛውም ሀገር ውስጥ የሚኖር ዜጋ የህግ የበላይነትን በመፃረር እንዳሻው ሊኖር አይችልም። ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደሞከርኩት የዜጎች ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ በህግና ስርዓት የሚመራ ካልሆነ የትኛውም ወገን የመኖር ዋስትና ሊኖረው አይችልም። በመሆኑም ማንኛውም ዜጋ የሚንቀሳቀሰው ህግ ባለበት ሀገር ውስጥ ነውና ህገ-ወጥ ተግባርን ከከወነ የህግ የበላይነት ተፈፃሚ መሆኑ አይቀርም።
የህግ የበላይነት ከሌለ ሥርዓት አልበኝነትን የሚፈጥር ከመሆኑም ባሻገር፤ ህጎች ለሁሉም ዜጎች እኩል እንዳይሰሩ ያደርጋል። እናም ‘ሁሉም ሰው በህግ ፊት እኩል ነው’ የሚለውን ህገ መንግስታዊ መርህ ገቢራዊ ለማድረግ የህግ የበላይነት በማያሻማ ሁኔታ መረጋገጥ ይኖርበታል።
የህግ የበላይነት መከበር ለሀገር ሰላምና መረጋጋት ብሎም ልማትን ለማሳለጥ ቁልፍ ሚና ይኖረዋል። ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት የህግ የበላይነት ከሌለ ሰላም የሚባልን ነገር ማሰብ አይቻልም። ሰላም ከጠፋ ደግሞ ስለ ልማትና ዴሞክራሲ ማሰብ አይቻልም። ፀረ-ልማትዊነትና ፀረ-ዴሞክራሲያዊነት ቦታውን ይረከባሉ። እናም ማንኛውም ሰው በህግ ፊት እኩል መሆኑና የህግ የበላይነት መረጋገጡ ሥርዓቱ ተመራጭ እንዲሆን አድርጎታል።
ዜጎች ስርዓቱ ከፈጠረው ልማት ፍትሃዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጋቸው ፅርዓቱን ተመራጭ ያደረገው ሌላኛው ጉዳይ ነው። በልማት ወደ ኋላ የቀሩ ክልሎች በመንግሥት ልዩ እገዛ ተደርጐላቸው ጭምር የልማቱ ተጠቃሚነታቸው መረጋገጥ እንዳለበትም ህገ መንግሥቱ በማያሻማ መልኩ ደንግጓል። መንግሥት መሬትንና የተፈጥሮ ሀብቶችን በሕዝብ ስም በይዞታው ስር በማድረግ ለዜጎች የጋራ ጥቅምና እድገት የማዋል ኃላፊነት እንዳለበትም ይገልጻል።
በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ሁሉም ዜጋ በማንኛውም የምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴ ውስጥ የመሰማራትና ለመተዳደሪያው የመረጠውን ሥራ የመከወን መብት እንዲሁም በመንግሥት ገንዘብ የሚካሄዱ ማህበራዊ አገልግሎቶችን በእኩልነት የመጠቀም መብት ተረጋግጦላቸዋል።
በህገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች መሠረትም ሕዝቦች የኑሮ ሁኔታቸው የመሻሻልና የማያቋርጥ እድገት የማግኘት መብት እንዳላቸው በተግባር እየታየ መጥቷል። ዜጐች በብሔራዊ ልማት የመሳተፍ፣ በሚቀረፁ ፖሊሲዎችና ኘሮጀክቶች ላይ አስተያየት የመስጠት መብት እንዳላቸውም በገሃድ እየታየ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ህገ መንግሥት ባለፉት ሥርዓቶች ምጣኔ ሀብታዊና ማህበራዊ ፍትህ ሳያገኙ የቆዩና በዚህም ምክንያት በልማት ወደ ኋላ የቀሩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በመንግሥት ልዩ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ዋስትና ሰጥቷል።
በዚህ መሠረትም የፌዴራል መንግሥት ፍትሃዊ የልማት እንቅስቃሴ ከማረጋገጥ በተጨማሪ፤ በልማት ወደ ኋላ የቀሩ ሕዝቦች መላ አቅማቸውን አሟጠው እንዲጠቀሙ ለማስቻል ልዩ ድጋፍ እየሰጣቸው ይገኛል።
እገዛው በዋናነት የሚያተኩረው በማስፈፀም አቅም ግንባታ ላይ ነው። ዜጐች ንብረት የማፍራት፣ በመረጡት የሥራ መስክ የመሰማራት መብቶች በማረጋገጥ በነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓት የሚመራ ፈጣንና ፍትሀዊ ልማት የማምጣት ጠቀሜታን የሚያመለክቱ ናቸው።
የሕዝቦችን ልማታዊ አቅም ማሳደግና ለአገር ግንባታ ወሣኝ መሆናቸውንም ያሳያሉ። የዜጐችን የልማት ባለቤትነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የልማት እንቅስቃሴዎች ዋና ዓላማ መሆን እንዳለበት የህገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች ያስረዳሉ። እነዚህ ሥርዓቱን ተመራጭ ያደረጉ ሃቆች ወደፊትም ተጠናክረው የሚቀጥሉ ናቸው።