Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የኢንዱስትሪ ፓርኮች መስፋፋት

0 460

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የኢንዱስትሪ ፓርኮች መስፋፋት

ዳዊት ምትኩ

ኢትዮጵያ በሁሉም የአገራችን አካባቢዎች በሚያስብል መልኩ እየገነባች ያለችውን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ተስፋ ሰጪ ነው። ሰሞኑን በመላ ሀገሪቱ የሚገነቡት የተለያዩ የኢንዱስትሪ ፓርኮች እየተስፋፉ መምጣታቸውን የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል። ይህም ለአገራችን ለኢንቨስትመንት መስፋፋትና ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለምናደርገው ሽግግር ምቹ ሁኔታ የሚፈጥና ለዘላቂ ዕድገታችን መሰረት የሚጥል ነው። እናም ይህን ጉዳይ ሰፋ አድርጎ መመልከት ያስፈልጋል።

እንደሚታወቀው ሁሉ መንግስት ፓርኮቹን የሚገነባው የሀገር ውስጥም ይሁን የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ነው። ፓርኮቹ አስፈላጊው የመሰረተ ልማት ተሟልቶላቸው የሚገነቡ በመሆናቸው ባለሃብቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ስራ እንዲገቡ የሚያደርጓቸው ናቸው።

በመልማት ላይ የሚገኙት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ዓለም የደረሰበትን የግንባታ ሂደት ተከትለው የሚገነቡ በመሆናቸው ከአካባቢ ብክለት ነፃ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ  በምርት ወቅት ተረፈ ምርታቸውን እንደገና መጠቀም በሚያስችል ሁኔታ የተገነቡ በመሆናቸው የሃብት ብክነትን ማስወገድ ይችላሉ። ይህም ፓርኮቹ በምርትም ይሁን በተረፈ ምርት ውጤታማ መሆን የሚያስችሉ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ማንኛውም ሀገር በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በፖለቲካ መስኮች ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ ተጠቃሚ ያደርጋል። ልማቱ እንደ ጨርቃጨርቅ በመሳሰሉ ቀላል የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በርካታ የስራ ዕድል የሚፈጠር እና የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትንም በስፋት መሳብ የሚችል ነው። ይህም የህዝቦችን ተጠቃሚነት ከፍ የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ፤ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ረገድም የራሱን ሚና ይጫወታል። ከዚህ ጎን ለጎንም የቀላል ማኑፋክቸሪንግ ልማቱን ያፋጥናል፤ ከተሞችን ወደ ላቀ የዕድገት ደረጃ የማሸጋገር ብሎም አዳዲስ ከተሞች እንዲፈጠሩና በዚያኑ ልክም የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲቀረፉ የራሱን አዎንታዊ ሚና ይጫወታል።

እነዚህን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን ለማግኘትም በመንግስት በተቀመጠው ዕቅድ መሰረት ስራውን ከጀመረው ከሃዋሳው የኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት በተጨማሪ የመቀሌና ኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ግንባታ እውን መሆናቸውን መረጃዎች ያስረዳሉ። በሌሎች የአገራችን አካባቢዎችም መሰል ግንባታዎች እየተከናወኑ ናቸው።

በአገራችን የተተለመው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ፕሮግራም መሬትን ውጤታማ በሆነ መልኩ ለልማት ስራ ብቻ እንዲውል የሚያደርግና የኪራይ ሰብሳቢነት በር የሚዘጋ መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ይመስለኛል።

እርግጥም ልማቱ ለመሰረተ ልማት ግንባታ የሚወጣውን ወጪ በተቀናጀ መልኩ መጠቀም የሚያስችልና ለአካባቢ ጥበቃ ሥራ ትኩረት የሚሰጥ በመሆኑ ኢንዱስትሪዎችን በእሴት ሰንሰለት እርስ በርስ ስለሚያስተሳስር ብክነትን የሚቀንስና የኪራይ ሰብሳቢነትን በመዋጋት ረገድ ሚናው የጎላ ነው።

በውጭ አገር ባለሙያዎች የሚከናወኑ ስራዎችን በሂደት በሀገር ውስጥ የሙያው ባለቤቶችና በሀገር በቀል ተቋማት አማካኝነት እንዲከናወኑ መሰረት ይጥላል። ይህም የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲረጋገጥ ሰፊ ዕድልን ይፈጥራል።

የኢንዱስትሪውን በተለይም የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ኢንዱስትሪውን ለማዘመን በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ላይ ውጥኖች ተይዘው እየተተገበሩ ነው። በዕቅዱ ላይ በዘርፉ የተጠቀሱትን ስኬቶች እውን ለማድረግ በሁለት ዘርፎች ትልሞች ተይዘው ተግባራዊ እየሆኑ ነው። በጥቃቅንና አነስተኛና መካከለኛ እንዲሁም ለከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ትኩረት ተሰጥቶም እየተሰራባቸው ናቸው።

ይህ ሁኔታም በሁለቱም ዘርፎች ውስጥ ኤክስፖርት መር የኢንዱስትሪ አቅጣጫን ለመከተልና ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶችን ለመቀነስ በሚደረገው ሽግግር ውሰጥ የራሱን ሚና ይጫወታል።  

እንደሚታወቀው ሁሉ በሀገራችን ውስጥ ያለው የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ መሰረቱ ይህን ያህል የሚያስመካ አይደለም—ጠባብ ነው። ያም ሆኖ ግን ሀገራችን በዘርፉ ለውጥ እንድታመጣ በዋነኛነት ኢንቨስትመንትን ማስፋፋት ይኖርባታል። በተለይም በማደግ ላይ የሚገኘው የሀገራችን ባለሃብት የለውጡ ተሳታፊ እንዲሆን እንዲሁም በተመረጡ የቀጥታ ኢንቨስትመንት ዘርፎች ተግባሩ እንዲከናወን ማድረግ ያስፈልጋል።

እናም ከሀገር ውስጡ ባለሃብት በተጨማሪ የውጭ ባለሃብቶች በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚኖራቸው የቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ተሳታፊነት የማይናቅ ቦታ ይኖረዋል። ይህም የዘርፉን ዕድገት ለማፋጠን ጉልህ ሚና አለው።

ይህን መሰረታዊ ዕውነታ በመመርኮዝም በዕቅድ ዘመኑ በሁሉም ዘርፎች ጥንቃቄ በተሞላው ሁኔታ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ብርቱ ጥረት ይደረጋል። በተለይም  ከፍተኛ አቅምና ፍላጎት እንዲሁም በአፈፃፀማቸው ጥሩ ስምና ዝና ያላቸውን የውጭ ኩባንያዎች በመመልመልና የማግባባት ስራ በማከናወን የዘርፉን ዕድገት እንዲያሳድጉት ለማድረግ እየተሰራ ነው። ባለሃብቶቹን ኤክስፖርት ተኮር በሆኑ የማኑፋክቸሪንግ ውጤቶች ላይ በማሰማራት ሀገራችን ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ ለማድረግ ውጥን ተይዟል።

እርግጥ ሀገራችን የውጭ ባለሃብቶች ኤክስፖርት ተኮር በሆኑ ዘርፎች ውስጥ እንዲካተቱ ስታደርግ ለሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ምንም ዓይነት ቦታ ሳትሰጥ ነው ማለት አይደለም። የሀገር ውስጥ ባለሃብቶችም መዋዕለ ንዋያቸውን በዘርፉ እንዲያፈሱ ይደረጋል።

በተለይም በማደግ ላይ የሚገኙት የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ ተመልምለው በቂ ድጋፍ እንደሚሰጣቸውና በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ገቢ ምርቶችን በሚተኩ ዘርፎች ጭምር እንዲሳተፉ እንደሚደረግ ዕቅዱ ያብራራል።

የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዕድገት ሊረጋገጥ የሚችለው ከኢንቨስትመንት መስፋፋት ጋር ተያይዞ እንጂ ለብቻው ተፈፃሚ እንዲሆን ብቻ አይደለም። የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ኢንቨስትመንትን ዕውን ከማድረግ አኳያ መቆራኘት እንደሚኖርበት ታምኖ እየተተገበረ ነው።

እርግጥ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ለአገራችን ህዳሴ ወሳኝ ትርጉም አለው። በመፈጠር ላይ ያለው ቀጣይና ተከታታይ ዕድገት ዘላቂ እንዲሆንና የህዳሴ ጉዟችንን መደላድል ለማስፋት በዕቅዱ ዓመታት የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዕድገት ማስመዝገብ ይኖርበታል።

ይህም ለኢኮኖሚው መዋቅራዊ ለውጥ ጉልህ ሚና ይኖረዋል። የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥን ዕውን ለማድረግ የሚከናወነው ስራም ሀገራችን ለነደፈችው ራዕይ የሚጫወተው ሚና ሊተካ አይችልም። እንዲያውም የሞት ሽረት ጉዳይ ነው ማለት ይቻላል። እናም ኢንዱስትሪው ይበልጥ እንዲስፋፋ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy