Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የኤርትራን አፍራሽ ድርጊት ያረጋገጠ ውሳኔ!

0 297

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የኤርትራን አፍራሽ ድርጊት ያረጋገጠ ውሳኔ!

ዳዊት ምትኩ

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በቅርቡ የኤርትራንና የሶማሊያን ጉዳይ በሚያጠናው አጣሪ ቡድን አማካኝነት የቀረበለትን ሪፖርት ተመርኩዞ በኤርትራ ላይ የጣለው ማዕቀብ በአንድ ዓመት እንዲራዘም ወስኗል። ይህ ውሳኔ የኤርትራ መንግስት በምስራቅ አፍሪካ አገሮች ላይ የሚያካሂደውን አፍራሽ ድርጊት የሚያረጋግጥ ነው።

የኤርትራ መንግስት የአገራችንን ሰላም ለማወክና ልማታችንን በተላላኪዎቹ አማካኝነት ለማደናቀፍ የቆመ ነው። ምንም እንኳን ይህ ባህሪው ሰላም ወዳዱ የአገራችን ህዝብና በፀጥታ ሃይሎች የጋራ ርብርብ በየጊዜው እየከሸፈበት ቢሆንም ዛሬም አሸባሪዎችንና ፀረ ሰላም ኃይሎችን እየደገፈ በመሆኑ ህብረተሰቡ ሰላሙን በመጠበቅ የተለመደ ጥንቃቄውን ማድረግ ይኖርበታል።

የኤርትራ መንግስት በእነዚህ ጥሰቶቹ የኤርትራ መንግስት ለየትኛውም ቀጣናዊም ይሁን አህጉራዊ ብሎም ዓለም አቀፋዊ ህግ የማይገዛ መሆኑን ነው። የአስመራው መንግስት ለቀጣናው ፀረ-ሰላም ሃይሎችና አሸባሪዎች የሚያደርገው ድጋፍ፤ ከብሔራዊ የደህንነት ፅህፈት ቤት፣ ከኤርትራ ወታደራዊና ከህግደፍ (ህዝባዊ ግንባር ለዴሞክራሲና ለፍትህ) አመራሮች በተውጣጡ አነስተኛና ከፍተኛ መኮንኖች በተመሰረተ ቡድን የሚመራ መሆኑን አጣሪ ቡድኑ አስታውቆ እንደነበር አይዘነጋም። ዛሬም ምንም ለውጥ የለም። ይህም ሻዕቢያ ምስራቅ አፍሪካን ለማተራመስ ፀረ-ሰላም ሃይሎችንና አሸባሪዎችን በሁሉም መስኮች በመደገፍ የቀጣናውን ሀገራት ለማተራመስ በመንግስት ደረጃ ምን ያህል ተደራጅቶ እንደሚሰራ የሚያሳይ ነው።

በተለይም ከኢትዮጵያ ጋር በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት በግንባር ላይ የፊት ለፊት ውጊያ የተጎነጨው የሽንፈት ፅዋ ሁሌም እያንገበገበው በሀገራችን ላይ ለባዕዳን ያደሩ ፀረ ሰላም ሃይሎችንና አሸባሪዎችን እያደራጀ፣ እያሰለጠነና አስርጎ ለማስገባት እየሞከረ ሰላማችንን ለማወክ ያልጣረው ነገር የለም—ከንቱ ጥረቱ በሀገራችን ሰላም ወዳድ ህዝብና በመንግስት የተቀናጀ ጥረት ሊሳካ አልቻለም እንጂ።

ከዚህ አኳያ የኤርትራ መንግስት ራሳቸውን “ግንቦት ሰባት” እና “ኦነግ” በማለት የሚጠሩ አሸባሪዎችን እንዲሁም አንድም ሆነ ሁለት አባላት ያሏቸው ፀረ-ሰላም ሃይሎችን በራሱ ወጪ አደራጅቶ የኢትዮጵያንና የህዝቦቿን ሰላም ለማወክ ያደረገውንና እያደረገ ያለውን ጥረት ማስታወስ የሚቻል ይመስለኛል።

ታዲያ ይህን መሰሉ የኤርትራ መንግስት የጠብ አጫሪነት ተግባር የሚሰምርለት አይመስልም። በሻዕቢያ የተደራጁ ፀረ ሰላም ኃይሎችና አሸባሪዎች በተለያዩ ወቅቶች የኤርትራን መንግስት ተልዕኮ በመተው በሰላም ወደ ሀገራቸው እየተመለሱ ነው። በአቶ ሞገስ አስገዶም ይመራ የነበረው “ደምሕት” እንዲሁም ራሱን “የቤኒሻንጉል ነፃነት ንቅናቄ” (ቤነን) እያለ የሚጠራው ቡድን አብነቶች ናቸው።

እነዚህ ቡድኖች እንዲህ ዓይነቱ የፀረ-ሰላም ኃይሎችና የአሸባሪዎች በሰላም ወደ ሀገራቸው መጥተው ከህዝባቸው ጋር በመቀላቀል የልማቱ ተቋዳሽ መሆን መቻላቸው ለኤርትራ መንግስት ጥሩ ምልክት ነው ማለት ይቻላል። ይህ ማለት ግን አሁንም ቢሆን የኤርትራ መንግስት ችግር ሊፈጥር አይችልም እያልኩ አይደለም። የተመቻቸ ቦታ ካገኘ ችግር መፍጠሩ አይቀርም።

እውነታውን ለመገንዘብ በስሩ ስለሚተዳደሩት ጥቂት ጠባቦችና ትምክህተኞች ላንሳ። እንደሚታወቀው ራሳቸውን “ኦነግ” እና “ኦብነግ” እያሉ የሚጠሩት ጠባብ የሽብር ቡድኖች ዓላማቸውን በሰላማዊ መንገድ ማራመድ እየቻሉ፤ ነገር ግን በህዝቡ የተተፉ ፀረ – ሠላም ኃይሎች መሆናቸውን በመገንዘባቸው ሳቢያ የሻዕቢያ “ተወርዋሪ ድንጋይ” መሆንን የመረጡ ሃይሎች ናቸው፡፡

አሸባሪዎቹ እናራምደዋለን የሚሉትን “የመገንጠል ዓላማ” በህገ መንግሰታዊ ስርአቱ ውስጥ ባለው የምርጫ ፉክክር ህዝባቸውን አሳምነው ሳይሆን፤ ለኢሳያስ አፈወርቂ ተላላኪ በመሆን የሚሳካላቸው የሚመስላቸው የጎጠኞች ስብስብ ናቸው፡፡

በኤርትራ መንግሰት እምነት መሰረትም ‘ምናልባት እነዚህ ኃይሎች በለስ ቀንቷቸው ቢሳካላቸው ኢትዮጵያ ትፈረካከስና እኔም የአካባቢው “አውራ” የመሆን ህልሜን እንዲለመልም ያደረጉታል’ ብሎ ያስባል፡፡ የኤርትራ መንግስት በባህሪው ጦረኛ በመሆኑና ለቀጠናው ሰላም መፋለስ የሚሰራ በመሆኑ የአውራነት ህልሙን እውን ሊያደርግ አይችልም፡፡

በምርጫ 97 ወቅት በተፈጠረው የቅንጅት ነውጠኛ አመራሮችና በደርግ ቅሪቶች የተመሰረተውና የራሱን “ግንቦት ሰባት” እያለ የሚጠራው የትምክህተኞች ጥርቅምቃሚ የሽብር ቡድንም፤ ሌላው ቀርቶ የኤርትራን ነጻነት የማይቀበል መሆኑ ለኢሳያስ አፈወርቂና ለተከታዮቻቸው ግልጽ ነው፡፡ ይሁንና የኤርትራ መንግስት ሀገራችንን ለመበታተን ያሉትን አማራጮች ሁሉ አሟጦ የሚጠቀም የአሸባሪዎች አጋፋሪ በመሆኑ፤ የእነዚህን ኃይሎች ማንነት እያወቀ እንኳን ምንም ሊያደርገው አልቻለም። እንዲያውም አልሳካለት ብሎ እንጂ ያላደረገለት ነገር የለም።

ኤርትራ ውስጥ የተጠለሉ የአሸባሪዎችና ፀረ ሰላም ሃይሎች የኤርትራ መንግስት ኢትዮጵያን ለመበታተን ይጠቅመኛል ብሎ እስካሰበ ድረስ ጠባቡንም ይሁን ትምክተኛውን የሽብር ኃይል አንድ ላይ አሰማርቶ ከማተራመስ የማይመለስ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው፡፡

ምንም እንኳን እነዚህ የከሰሩ አሸባሪዎችና ፀረ ሰላም ሃይሎች በአንድነት አስመራ ውስጥ ተሰባስበው በአጭር ጊዜ ኢትዮጵያን ይበታትናሉ የሚል የቀን ቅዥት ህልም የአስመራ መሪዎች ቢኖራቸውም፤ አሸባሪዎቹና ጸረ ሰላም ሃይሎቹ በአሁኑ ወቅት ይህ ነው የሚባል ተጨባጭ ውጤት ያመጡና የሚያመጡ አይደሉም። ይህንንም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አጣሪ ቡድን በሪፖርቱ ላይ ገልፆታል።

የኤርትራ መንግሰት የኢትዮጵያን ፈጣን ልማት ካሰናከሉ፣ ግጭት እንዲፈጠር ካደረጉና በዚህም የአገሪቱን ገጽታ ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ተቀባይነት ካበላሹ እንዲሁም የሚፈሰውን ኢንቨስትመንት እንዲቋረጥ ወይም እንዲቀንስ ካደረጉ በቂዬ ብሎ የሚያምን ነው። እናም አሸባሪዎቹንና ፀረ ሰላም ሃይሎቹን የሽብር መረቡ አስፈጻሚ አካላት አድርጓቸው መንቀሳቀስን በአማራጭነት የወሰደ ሃይል ነው።

በመሆኑም ዛሬም ድረስ አሸባሪ የሆኑትና ራሳቸውን “ኦነግ”፣ ኦብነግ” እና ግንቦት ሰባት” እያሉ የሚጠሩት የክህደት ቡድኖችን ብሎም እዚህ ግባ የሚባል አቅም የሌላቸውን ጸረ ሰላም ሃይሎችን እየደገፈ ይገኛል። የምስራቅ አፍሪካዊቷን ጂቡቲን ሰላምም እያናጋ ይገኛል—ለአገሪቱን ተቃዋሚ ሃይል ድጋፍ በማድረግ።

እናም የኤርትራ መንግስት በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ አገራችን ተዳክማ ማየት የረጅም ጊዜ ህልሙ በመሆኑ የትርምስ ሴራውን አይተውም። ይህ ሁኔታ ደግሞ በተለይ ከሻዕቢያ ጋር ተጎራባች ለሆኑ የሰሜን አገራችን ህዝቦች ከፍተኛ ስቃይ መሆኑ ይታወቃል። ይሁንና ያ የሰሜን ህዝብ ትናንት ሻዕቢያን በሚኒሻው ጭምር የመከተ ህዝብ በመሆኑ ዛሬም እንደ ተለመደው ፀጉረ ልውጦችን በመከታተል ተላላኪዎቹን ማምካን አለበት።

በአጠቃላይ ሁሉም የአገራችን ህዝቦች የኤርትራ መንግስት የኢትዮጵያን ሰላምና መረጋጋት ለማደፍረስ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ከተባበሩት መንግስታት ደርጅት ውሳኔ በመገንዘብ በያለበት ቦታ ሁሉ የኤርትራን መንግስት እኩይ ምግባር በንቃት እየተከታተለ ማምከን ይኖርበታል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy