Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የኦሮሚያው ግጭት ተራ ሽፍትነት ነው!

0 247

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የኦሮሚያው ግጭት ተራ ሽፍትነት ነው!

ዳዊት ምትኩ

በቅርቡ በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠረው ግጭት የጥበትና የትምክህት ሃይሎች የፈጠሩት ነው። ድርጊቱ የተራ ሽፍትነት ወይም የወንበዴነት ተግባር መሆኑ ከማንም የተሰወረ አይደለም። ሆኖም መንግስት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታትና በአካባቢው አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን ከፍተኛ ጥረት በማድረጉ በአሁኑ ወቅት ችግሩን በቁጥጥር ስር ለማዋል ችሏል። በአሁኑ ወቅት ህብረተሰቡ በግጭቱ ሳቢያ ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ በማድረጉ ተፈናቃዩች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ማድረግ ተችሏል።

ሆኖም አሁንም ቢሆን የትምክህትና የጥበት አስተሳሰቦች እስካልተቀረፉ እንዲሁም ኪራይ ሰብሳቢዎችና ኮንትሮባንዲስቶችን መቆጣጠር እስካልተቻለ ድረስ ችግሩን መፍታት አዳጋች መሆኑ አይቀርም።

በትምክህትና ጠባብነት አስተሳሰብ የተጠመቁ ኃይሎች ከሁሉ በላይ የቋንቋ፣ የባህልና የማንነት ብዝሃነትን አጥብቀው ይጠላሉ፡፡ የትምክህት ኃይሉ የእኔ ብሄር ብቻ ልዕለ ኃያል የሆነ፣ ቋንቋዬ፣ ባህሌና ማንነቴ ከሌላው የሚበልጥና የተለየ፣ ሁሌም ለመግዛት የተፈጠርኩ ነኝ ብሎ ያምናል፡፡

ከዚህ ጐን ለጐንም ሌላውን ብሔርና ዜጋ ተራና ርካሽ፣ ለመመራት እንጂ ለመምራት ያልተፈጠረ ቋንቋው፣ ባህሉና ማንነቱ የወረደ አድርጐ ይቆጥረዋል፡፡ የህዝብ ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤትነትንም አይቀበልም። ስለሆነም ብዝሃነትን ደፍጥጦ የራሱን አስተሳ ሰብ፣ ቋንቋና ባህል በሌላው ላይ ለመጫን የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም፡፡

ይህ ካልሆነ ሀገር ትጥፋ ህዝብም ይለቅ የሚል ህሳቤም የተጠናወተው ነው። ዴሞክራሲያዊ አንድነትና ብሔርተኝነትን የማይቀበል፣ የህዝቦች አንድነት ሳይሆን የግዛት አንድነት የሚያሳስበው ኃይል ነው። ከህዝብ ይልቅ ተራራና ወንዝ የሚናፍቅ ፀረ ህዝብ አመለካከት የተጠናወተውም ነው፡፡ የዚህ አስተሳሰብ ተቃራኒ የሆነው ጠባብነትን የተላበሰ ኃይል ደግሞ ሁሉንም ለእኔ እና ለእኔ ብቻ ብሎ የሚያስብ ነገሮችን ሁሉ በጠባብነት መነፅር የሚመዝን የዚህ ዓለም ዕውነታ የሆነውን ብዘሃነትን ተቀብሎና ተቻችሎ መኖር የእሬት ያህል የሚጎመዝዘው ኋላ ቀር አሳቢ ነው። በጠባብነት ድንበር የታጠረ እንደመሆኑ መጠንም ከሱ ብሔር ውጪ ያለ ህዝብ በአካባቢው እንዳይኖር ሌላ ቋንቋ እንዳይነገር ይሰብካል፡፡ ያስባል፡፡ ያልማል፡፡

ይህ የጥበት ሃይል በመስበክ ብቻ ራሱን አያቅብም፡፡ የብሔሩ አባል ሌላውን በጥላቻና በጥርጣሬ እንዲመለከተው ዕድሉ ሲመቻችለትም እንዲያጠቃና እንዲያጠፋው ተግቶ ይሠራል፡፡ በአኩልነት ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ አንድነትን አይቀበልም። የዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ፀር በመሆንም ሌላውን ዜጋ ለመጨፍለቅ ይሞክራል—ቢሳካለትም ባይሳካለትም፡፡

ታዲያ የዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ፅኑ ጠላት የሆኑትና እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የሃይማኖት፣ የብሔር፣ የቋንቋና የባህል ብዝሃነት ባለባቸው ሃገሮች ፈጽሞ ሊሠሩ የማይችሉት እነዚህ ሁለት አስተሳሰቦች፤ በአሁኑ ወቅት በሰላማችንና በልማታችን ላይ የተደቀኑ እንቅፋትና ጋሬጣዎች መሆናችው ፍንትው ብሎ እየታየ ነው፡፡ እናም የእነዚህ የጥፋት አስተሳሰብ በሮች ሊከረቸሙ የሚገባቸው ይመስለኛል፡፡

የትምክህት ኃይሉ በግንቦት ሰባት፣ ጠባብ ኃይሉ ደግሞ በኦነግ ፊታውራሪነት ለራሱ እንኳ መሆን ባልቻለውና ማተራመስና ሽብርን የዕለት እንጀራው ባደረገው የኤርትራ መንግሥት አይዞህ ባይነት ኢትዮጵያን የማፈራረስና ከፈጣን ልማቷ የማደናቀፍ ተልዕኮ ተቀብለው ላለፉት ዓመታት የሽብርና የጥፋት ተግባርን ያለመታከት በመፈጸም ላይ ይገኛሉ፡፡ ምንም እንኳን በመላ ኢትዮጵያውያንና በጀግናው የመከላከያ ሠራዊታችን ጽናት የጥፋት ተልዕኳቸውን መፈፀም ባይችሉም፡፡

ራሱን ግንቦት ሰባት ብሎ የሚጠራው የሽብርና የብዝሃነት ጠላት የሆነ የትምክህት ኃይል በኢትዮጵያ የሰፈነው የብሄር ብሔረሰቦች የማንነት፣ የቋንቋና የሃይማኖት እኩልነትን ፈጽሞ የማይቀበል፣ በአንድን ብሔር ስም የሚነግድና በተግባር እንደታየው የሁሉም ብሔሮችና ብሔረሰቦች ደመኛ ጠላት ነው፡፡

የትምክህት ሱሱን መወጣትና የአስመራውን ከፍ ሲልም የአንዳንድ ኢትዮጵያ እንዳታድግ የሚሹ ሃይሎችን ተልዕኮ በመያዝ የቀን ቅዠት ሰንቆ ሽብርና ትርምስ ለመፍጠር አቅዶ ይሰራል፤ የቀቢፀ ተስፋ ምኞቱ ባይሳካለትም፡፡

በሌላ ዘውጉም ከዚህ ቡድን በዓላማም ሆነ በአስተሳሰብ ተቃራኒ የሆነው የጠባብ ኃይልም በኦሮሞ ህዝቦች ደም ሲነግድ በኖረው ኦነግ የተባለ አሸባሪ ድርጅት የሚመራና የኤርትራ መንግሥት የጡት አባቱ የሆነለት የጥፋት ቡድን ነው፡፡ ቡድኑ ‘የኦሮሞን ህዝብ ከተቀረው የኢትዮጵያ ብሔር ገንጥዬ ኦሮሚያ የምትባል ሀገር እፈጥራለሁ’ በሚል የቀን ህልም ውስጥ የተዘፈቀ የሽብርተኞች ስብስብም ነው፡፡

የትላንት ገዥ መደቦች በህዝቦች ላይ የፈፀሙትን በደል ሁሉ የአንድ ብሔረሰብ አባላት እንደፈፀሙት አድርጐ የጥላቻ መርዝ መርጨትና አንዱ ብሔር በሌላኛው ላይ ተነሳስቶ እልቂት ሲፈጥር ማየትም የማይለወጥ ራዕዩ ነው፡፡ ለዚህም ነው— ‘እገሌ የተባለውን ብሔረሰብ አባል ከክልልህ አባረው ወይም አጥፋው’ በማለት የማያቋርጥ ስብከቱን ሲያሰማ የሚኖረው፡፡

በጥበት ሃይልነት የሚነሳው ሌላው አካል ጃዋር መሃመድ የተሰኘው የእነ ግብፅ መንግስት ተቋማት ተላላኪ ነው፡፡ የጃዋር የጥበት መጠን ‘አንገቱን በሜጫ’ እስከሚል አስገራሚ ዲስኩር የሚዘልቅ ነው፡፡

ይህ ግለሰብ በፀረ ኢትዮጵያ ሃይሎች ዳረጎት ሰጪነት ያቋቋመውን “ኦኤምኤን” የተሰኘን ጣቢያ በማቋቋም ሀገራችን ውስጥ ብጥብጥ ለመፍጠር ተሯሩጧል። በርካታዎች ደማቸው ደመ ከልብ ሆኖ እንዲቀር አድርጓል። በድሃው የኦሮሞ ልጅ እጅ ፍም እሳትን በመያዝ ወጣቶችን ባልተገባ መንገድ መርቶ ብጥብጥ ፈጥሯል። “አኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” የሚል ብሂልን በመከተል በሌላኛው ላይ እሳትን ለመለኮስ ጥረት አድርጓል፡፡

እንግዲህ ከላይ አጠር ባለ መልኩ ልዩነታቸውን የተመለከትናቸው የትምክህትና የጥበት ኃይሎች በቅርቡ በጥብቅ የሚያቆራኛቸውን ነገር አግኝተው ፍቅራቸው ጣራ መንካቱን እናስታውሳለን፡፡

ይሁንና ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ትምክህትና ጥበት አምሳያዎች ቢሆኑም በአንድነት መስራት ስለማይችሉ አንደኛው ራሱን የበላይ በማድረግ መብት ለሌላኛው ለመስጠት ይሞክራል፡፡ ሌላኛው ደግሞ የእገሌ ብሔር ምሁራን እያለ ስም በማውጣት በማንነት ጥያቄዎች ላይ ላይ ያላቸውን አስተሳሰብ ጥንብ እርኩሱን ሲያወጣ ይስተዋላል። ሆኖም አንዱ ሌላውን ከመንቀፍ የሚቦዝንበት ቀን የለም።

ከእነዚህ ትምክህተኞችና ጠባቦች ባልተናነሰም እዚህ አገር ውስጥ ኪራይ በመሰብሰብ ኑሯቸውን ያደላደሉ ኮንትሮባንዲስቶችም የሁከት አጋፋሪዎች ናቸው። እነዚህ ሃይሎች የኪራይ ሰብሳቢነትን ፖለቲካል ኢኮኖሚ ለመድፈቅ በሚደረገው ትግል ምክንያት በማኩረፍ ህዝብን ከህዝብ ለማባላት የተሰለፉ ናቸው።

ኪራይ ሰብሳቢነታቸው እስከተነካ ድረስ የወንበዴነት ወይም የተራ ሽፈትነት ስራዎችን በህዝቡ ላይ ከመፈፀም ወደ ኋላ አይሉም። በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል በዜጎች ላይ እንዲፈፀም ያደረጉት ነገር የዚህ ተግባራቸው መገለጫ ነው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy