Artcles

የከፍተኛ ትምህርት እድል ለተሰጣቸው 253 ኤርትራዊያን ስደተኞች አሸኛኘት ተደረገ

By Admin

November 30, 2017

ሽሬ እንዳስላሴ ህዳር 21/2010 የኢትዮጰያ መንግስት በዘንድሮው የትምህርት ዘመን የከፍተኛ ትምህርት እድል ለሰጣቸው 253 ኤርትራዊያን ስደተኞች ትናንት በሽሬ እንዳስላሴ ከተማ አሸኛኘት ተደረገላቸው፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ለኤርትራውያን ስድተኞች እያደረገው ካለው ሁንተናዊ ድጋፍ አንዱ የትምህርት እድል እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታን መፍጠር መሆኑን የኢትዮጵያ የስድተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ አስተዳደር የሰሜን ኢትዮጵያ የኤርትራ ስደተኞች ማስተባበርያ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተክኤ ገብረእየሱስ በሽኝት ኘሮግራሙ ላይ ገልፀዋል፡፡

“በተያዘው የትምህርት ዘመን ለስምንተኛ ጊዜ የከፍተኛ ትምህርት እድል ከተሰጣቸው ኤርትራውያን ስደተኞች መካከል 17ቱ ሴቶች ናቸው” ብለዋል፡፡

እንደ ሀላፊው ገለፃ ለስደተኞቹ የትምህርት እድል የተሰጣቸው በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ነው።

የእድሉ ተጠቃሚ የሆኑ እነዚህ ኤርትራውያን ስድተኞች ትምህርታቸውን በሚገባ ተከታትለው እስኪያጠናቅቁ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግላቸው ኃላፊው ተናግረዋል።

በተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (UNHCR) ተወካይ ሚስቴር ሻጊ ሚና በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግስት ስደተኞችን በፀጋ ከመቀበል በተጨማሪ የትምህርት እድል እንዲያገኙ እያደረገ ነው።

”የአውሮፓ ህብረት ሃገራት ስድተኞች ወደየሃገሮቻቸው እንዳይገቡ በራቸውን እየዘጉ ባሉበት በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ መንግስት ይህን የመሰለ ሰብአዊ ተግባር መፈፀሙ ታላቅ ምስጋና ይገባዋል” ብለዋል።

የከፍተኛ ትምህርት እድል ተጠቃሚ ከሆኑት ኤርትራውያን ስደተኞች መካከል ተማሪ ይካአሎ ተስፋህይወት እንዳለው፣ “የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ በፀጋ ተቀብሎ ከማስተናገዱ በተጨማሪ በአገራችን የተነፈገንን የትምህርት እድል እንድናገኝ መደረጉ ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶኛል” ብሏል።

ሌላዋ የትምህርት እድሉ ተጠቃሚ ተማሪ ራሄል ገብረእየሱስ በበኩሏ ”የኢትዮጵያ መንግስት የሰጠን የትምህርት እድል መነሻው የሚከተለው የተቃና ፖሊሲና ውጤት ነው” ብላለች።

በትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን በሚገኙ በማይ ዓይኒ፣ አዲሃሩሽ፣ ህፃፅና ሺመልባ መጠለያ ጣቢያዎች ለሚገኙ ከ2 ሺህ በላይ ኤርትራዊያን ስደተኞች ባለፉት ሰባት ዓመታት የከፍተኛ ትምህርት እድል ተጠቃሚ መሆናቸው ታውቋል፡፡

በአሁኑ ጊዜም ከአንደኛ ደረጃ እስከ መሰናዶ ትምህርት 10 ሺህ 300 ስደተኞች ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ መሆናቸውን ከዞኑ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ አስተዳደር ጽህፈት ቤት የተገኘ መረጃ ያመለክታል።