Artcles

የወጣቶች የሥራ ባህል ይደግ

By Admin

November 22, 2017

የወጣቶች የሥራ ባህል ይደግ

ይልቃል ፍርዱ

ወጣቶች የነገ ሀገር ተረካቢዎች ናቸው። ሃገር የነገ እጣ ፈንታ የአንድ  ወጣቶቿ ነው የሚወሰነው በዛሬ ወጣቶች ነው። የነገ ሃገር መሪዎች፣ የሳይንስና ቴክኖሊጂ አመንጪና ፈጣሪዎች የዛሬ ወጣቶች ናቸው። የአንድ ሀገር ትልቁ እምቅ ሀብት ወጣቶች ናቸው። የወጣቱ እውቀት፣ ልቀትና ብቃት የምርምርና የግኘት አቅም ነው። ሀገርን የሚለውጠው ይህ አቅም ነው። አዳዲስ አስተሳሰቦችን መከተል የሕብረተሰቡን ሕይወት የሚለውጡ ምርምሮችን ማካሄድ ከድሕነት መውጫ መንገዱን በሳይንሳዊ ዘዴ ማስላት መስራት ሁሉ የሚጠበቀው የሀገር ሀብት ከሆኑት ወጣቶች ነው።

በተለይ በታዳጊ ሀገራት ውስጥ ወጣቶች አብዛኛውን ስራዎቻቸውን በምርምር ላይ ሲያደርጉ አዲስ ነገር የማግኘትና የመፍጠር ችሎታቸውን ሲጠቀሙ በብዙ መስኮች ለሀገር ልማትና እድገት ይስገኛሉ። ከፍተኛ አስተዋጽኦም ያደርጋሉ። አለምን የለወጡዋት ዛሬ የደረሰችበት ልማትና እድገት የሳይንስና የቴክኒዮሎጂ ምጥቀት ላይ እንድትደርስ  ያደረጓት በወጣጥነታቸው በአግባቡ የሰለጠኑ ተመራማሪዎች ናቸው።

ወጣቱ በሳይንንስና ተክኖሎጂ፣ በግብርና፣ በአቪየሽን፣ በጠፈር ምርምር፣ በወታደራዊ ሳይንስ ዘርፍ በሚያደርገው ምርምር አለምን በለውጥ ምእራፍ ወደፊት እንድትገሰገስ አድርጓል። የትኩስ አእምሮ ባለቤት የሆነው ወጣት የአለም የለውጥ ሂደት መሪና አንቀሳቃሽ ነው። ይህንን እውነት በሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ወደተግባር ለመለወጥ ሰፊ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ይገኛሉ።

የኢፌዴሪ መንግስት ከፍተኛ ትምህርት፣ ለሙያና ቴክኒክ ስልጠና ልዩ ትኩረት በመስጠት  እንዲስፋፉ አድርጓል። ወጣቱ ከቀለም ትምሕርት ባሻገር ለሀገራዊ ልማትና እድገት የሚጠቅሙ የሞያና ቴክኒክ እውቀት እንዲያገኝ በማድረግ በሃገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ውስጥ በመሳተፍ ራሱንና ሀገሩን እንዲጠቅም ለማስቻል ሰፊ ስራዎች ተሰርተዋል። በመሰራትም ላይ  ይገኛሉ።

በአዲስ አበባም ሆነ በክልሎች ቀድሞ ያልነበሩ የቴክኒክ ኮሌጆች፣ የምርምር ማዕከል የሆኑ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እንዲስፋፉ እየተደረገ ነው። ሀገሪቱ ከተያያዘችው አዲስ የሀገር ግንባታ አንጻር የፈጠራ ስራዎች እንዲበረታቱ እንዲጎለብቱ ወጣቱ አዳዲስ የፈጠራ ስራዎች ባለቤት እንዲሆን ለማድረግ ታስቦበት በእቅድ የተሰራ ስራ ነው። እስካሁን ባለው ሂደት ተስፋ ሰጪ ውጤቶች ተገኝተዋል።

ከዚህ ቀደም ከውጭ ሀገራት በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ይገቡ የነበሩ የተለያዩ ማሽኖችን መሳሪያዎችን በቀላል ወጪ በሀገራችን በወጣቶቻችን አማካኝነት መስራትና ማምረት የተጀመረበት ሁኔታ ይታያል። ለዚህም የእርሻ መሳሪያዎችን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል። በሀገር ውስጥ ቀላልና ከባድ መኪናዎችን መገጣጠም ከተጀመረ አመታት ተቆጥረዋል። በሂደትም  መኪና ወደ ማምረት ለመሸጋጋር እየተሰራ ነው።

የወጣቶቹ የስራ ተነሳሽነትና አዳዲስ ነገሮችን በሀገራችን የመፍጠር ስራ በእጅጉ የሚበረታታ ነው። ከሰሞኑ የጣናን ሀይቅ ከወረረው የእምቦጭ አረም ጋር በተያያዘ ከውጭ ሀገር የመጥረጊያ ማሽኖች የሆኑ መኪናዎችን ከማስመጣት ይልቅ የሀገራችን ወጣት ተመራማሪዎች በጎንደርና በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ያመረቷቸውን የፈጠራ ውጤቶች በመጠቀም የእንቦጭ አረምን ለመቆጣጣር ዝግጅት እየተደረገ ነው።

የራሳችንን ማጎልበት እየቻልን የውጭ ሀገራትን ምርትና መሳሪያ ፍለጋ መሄድ አይኖርብንም። ተገቢም አይደለም። መንግስት ለወጣቶች የመደበውን ፈንድ በተመለከተ በሁሉም ክልል ተፈላጊውና ውጤታማ ስራ ተሰርቶአል ለማለት ባያስደፍርም በጅምርም ቢሆን ተስፋ ሰጪ ስራዎች እየተሰሩ ናቸው ማለት ይቻላል።

በኦሮሚያ፣ በትግራይ፣ በአማራና በደቡብ ክልሎች ወጣቶችኑ ውጤታማ ሊሆኑ የሚችልባቸውን የስራ ዘርፎች በመለየት ተደራጅተው ፈንዱን ተጠቅመው ወደስራ እንዲገቡ የማድረግ አበረታች ስራዎች ተሰርተዋል። መንግስት ለወጣቶች የመደበው ገንዘብ ሰርተው አግኝተው መልሰው ወደ መንግስት የሚመልሱት የሕዝብ ገንዘብ ስለሆነ በጥንቃቄና ውጤታማ በሆነ መልኩ ብቻ ሊጠቀሙበት እንደሚገባ መዘንጋት የለበትም።

ክልሎች በድርሻቸው ቀመር መሰረት ማግኘት የሚገባቸውን ፈንድ አግኝተዋል። ወጣቶች ይህን ፈንድ ተጠቅመው በተለያያ የስራ መስክ በመሰማራት የኢኮኖሚ እድገቱ ተሳታፊና የልማቱ ተጠቃሚ መሆን ይጠበቅባቸዋል። የመንግስት የስራ ሃላፊዎችም በዚህ ረገድ ሃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል።

የስኬት ሁሉ ምስጢር ያለው የስራ ባሕል ላይ ነው። አዲሱ ትውልድ መልካም የስራ ባሕልን የእለት ተእለት የሕይወቱ አካል ማድረግ ካልቻለ ትልቅ ለውጥ ለማምጣት አይበቃም። ትልቅ ለውጥ ማለት የራሱን ህይወት ወደተሻለ ደረጃ ማሸጋጋርና ሀገርንም መለወጥ ማለት ነው። ይሄንን ለውጥ ማምጣት የሚያስችል የስራ ባሕል በቤተሰብና በማሕበረሰብ ደረጃ ማጎልበት ያስፈልጋል።