Artcles

የዛሬን ልማት በትናንት ቅኝ ገዥ ውሎች ማስተዳደር አይቻልም!

By Admin

November 25, 2017

የዛሬን ልማት በትናንት ቅኝ ገዥ ውሎች ማስተዳደር አይቻልም!

                                                   ዘአማን በላይ

ሰሞኑን ካይሮ ላይ በኢትዮጵያ፣ በሱዳንና በግብፅ የውሃ ሃብት ሚኒስትሮች መካከል በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ውይይት ተካሂዶ ነበር። ይህ ለ17ኛ ጊዜ የተካሄደው የሶስትዮሽ ውይይት እንዲደረግ ካርቱም ላይ የተወሰነው፤ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ተፅዕኖ ግምገማ እንዲሁም የውሃ ሙሌትና አለቃቀቅ በሚሉ ጉዳዩች ላይ ተነጋግሮ የፈረንሳይ ሁለት አጥኚ ኩባንያዎች የሚያካሂዱትን የጥናት መመሪያ ለመወሰን ነበር። ሆኖም በውይይቱ ላይ የግብፅ መንግስት “እ.ኤ.አ የ1929ኙ እና የ1959ኙ የቅኝ ግዛት ውሎች የአጥኚ ቡድኑ መመሪያ ሊሆኑ ይገባል” የሚል አቋም በመያዙ ስምምነት ላይ መድረስ አልተቻለም። ኢትዮጵያና ሱዳን አልተቀበሉትም።

ታዲያ ይህን ሁኔታ ተከትሎ የግብፅ መገናኛ ብዙሃን በህዳሴው ግድብ ዙሪያ እጅግ ከእውነታው ጋር የማይገናኙ ጉዳዩችን ሲያስደምጡን ሰንብተዋል። መገናኛ ብዙሃኑ በቅርቡ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ወደ ኳታር አቅንተው በሁለቱ ሀገራት መካከል ስለሚኖረው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዩች ተነጋግረው መመለሳቸውን በመግለፅ፤ “ኢትዮጵያ ህዳሴውን ግድብ የምትገነባበት ገንዘብ ከኳታር መንግስት አግኝታለች” እስከ ማለት የደረሰ የቅጥፈት ወሬን አናፍሰዋል።

አንዳንድ የግብፅ መንግስት ባለስልጣናትና ተቋማትም በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ብቅ እያሉ የቅኝ ግዛት ውሎችን በማጣቀስ ጉዳዩን የሌላ አጀንዳ ማስቀየሻ አድርገው ሲንቀሳቀሱ ተመልክተናል። ዳሩ ግን ወትሮም የዓባይ ጉዳይ ለግብፅ ቀደምት ፖለቲከኞች የውስጥ ችግር ማስተንፈሻ ሆኖ የሚያገለግል በመሆኑ፤ ዛሬም ታሪክ ራሱን በመድገሙ ምንም የሚደንቅ ነገር የሚኖረው አይመስለኝም።

ያም ሆኖ የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ፤ “የህዳሴ ግድብን በተመለከተ የግብፅ መገናኛ ብዙሃንና የተወሰኑ የመንግስት ተቋማት በኩል እየወጡ ያሉ አፍራሽ መረጃዎች በግንባታው ሂደት ላይ አንዳች ተፅዕኖ አይፈጥርም” ሲል በቃል አቀባዩ አቶ መለስ ዓለም በኩል ገልጿል። የህዳሴው ግድብ ግንባታ የኢትዮጵያዊያን ጉዳይ መሆኑን ኢትዮጵያ የግድቡን ግንባታ ከማፋጠን ጎን ለጎን ከግብፅና ሱዳን ጋር የምታደርገውን ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥልም በመግለጫው ላይ ተመልክቷል።

በእኔ እምነት ይህ መግለጫ ትክክለኛና ወቅቱን የጠበቀ ነው። ለዚህ ደግሞ የራሴ ሁለት ምክንያቶች አሉኝ— የግድቡ ግንባታ ተቀባይነት የሌላቸው የቅኝ አገዛዝ ዘመን ውሎችንና በራሳችን አቅም ከድህነት ለመላቀቅ የምናደርገው ጥረት አካል መሆኑን መግለጫው በግልፅ አመላክቷል ብዬ ስለማስብ ነው።

አንደኛው ምክንያቴ፤ እኛ ኢትዮጵያዊያን እንኳንስ ዛሬ ቀርቶ ትናንትም የቅኝ ገዥዎችን ወረራንና ፍላጎትን ተቀብለን ባለማወቃችን ግብፆችን ጨምሮ የሌሎች አፍሪካዊያን ወንድሞቻችን መኩሪያዎች መሆናችን ነው። ርግጥ ከትናንቱ ሊግ ኦፍ ኔሽን እስከ ዛሬው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ድረስ ቅኝ ገዥዎችንና ሃሳቦቻቸውን ስንቃወም መጥተናል። ቅኝ ገዥዎችንና ፍላጎታቸውን የሚቃወሙ አፍሪካዊያን ወንድሞቻችንንም በሁሉም መስኮች እያገዝን ዛሬ የደረስን ህዝቦች ነን። እናም እኛ ኢትዮጵያዊያን የምናስበው በ21ኛው ክፍለ ዘመን የተፈጥሮ ሃብትን በፍትሐዊት፣ በጋራ ተጠቃሚነትና ሁሉም አሸናፊ በሚሆንበት የሰጥቶ መቀበል ዘመናዊ መርህ እንጂ፤ ሁለት ክፍለ ዘመናትን የኋሊት ተንሸራተን በማሰብ ተስፋፊዎች ለወቅቱ የራሳቸው ፍላጎት ሲሉ ባዘጋጁት የ19ኛው ክፍለ ዘመን ፍርደ-ገምድል ውሎች ልንመራ አንችልም።

ኢትዮጵያዊያን ዛሬ ትናንት አለመሆኑን በሚገባ የምንገነዘብ ህዝቦች ነን። እኛንም ይሁን ሌሎች የተፋሰሱን ሀገራት ወንድሞቻችንን ሊያሰምጥ በሚችለው የትናንቱ ኋላ ቀር ታንኳ ላይ ሆነን ልንቀዝፍ እንደማንችል በሚገባ እናውቃለን። ዛሬ በጠረጴዛ ውይይት ችግሮች መፍትሔ እንደሚያገኙና ኋላ ቀርና ጎታች ህጎች አፍሪካንም ሆነ ዓለምን ሊመሩ ስለማይችሉ፤ በዘመናዊው የሰጥቶ-መቀበል ዘመናዊ መርከብ ላይ መልህቃችንን የጣልን ለሌሎች ወንድሞቻችን የምናስብ ህዝቦች ነን። “በጋራ እንብላ፤ አብረን እንጠጣ” የሚለው ኢትዮጵያዊው ባህላችን፤ ባለንበት ዘመነ-ሉላዊነት (Globalization) ዘመን ውስጥም ቢሆን ከሁሉም አፍሪካዊ ወንድሞቻችን ጋር “ተያይዘን እንደግ” እንድንል ያደረገን ነው። እኛ ኢትዮጵያዊያን ትናንትም ይሁን ዛሬ ለአፍሪካዊያን ወንድሞቻችን መከታ፣ ከለላና ሁለተኛ ሀገራቸው ከመሆን ውጭ የትኛውንም የአንዲት አፍሪካ ልጆችን ጎድተን እንደማናውቅ የታሪክ ድርሳናችንን ማገላበጥ ብቻ በቂ ይመስለኛል። እናም በምናከናውናቸው ማናቸውም ተግባራት የምንጎዳበት አንዳችም ምክንያት የለንም። ሊኖረንም አይችልም። አራት ነጥብ።

ይህ አብረን እንደግ ቁርጠኛ አቋማችንን በሌላኛው ዘውጉ ስንመለከተው፤ በተፈጥሮ ሃብታችን ለመጠቀም ወሳኞቹ እኛ እንጂ የማንንም ፈቃድና ይሁንታ የምንጠብቅ ህዝቦች አለመሆናችን ሊዘነጋ የሚገባ ይመስለኛል። አፍሪካዊያን ወንድሞቻችን ከቅኝ ግዛት ቀንበር እንዲላቀቁ የማንንም ይሁንታ እንዳልጠየቅነው ሁሉ፤ የተፈጥሮ ሃብታችንን በፍትሐዊነትና በጋራ ተጠቃሚነት ለማልማትም የማንንም “አበጀህ!” አሊያም “ተው!” ባይነትንም አናስተናግድም። አንቀበልምም።

እኛ ኢትዮጵያዊያን የትኛውም ዓለም አቀፍ ህግ በተስፋፊዎችና በወራሪ ቅኝ ገዥዎች ውሎች ተመሩ ሊለን እንደማይችልም እናውቃለን። የህዳሴው ግድብ ዓለም አቀፍ ህጎች ጠብቆ በፍትሐዊ የጋራ ተጠቃሚነት ዓለም አቀፍ ህጎችን በማክበር የምንገነባው ስለሆነ የጣስነውና የምንጥሰው ዓለም አቀፍ ድንጋጌም የለም። የትኛውም ህግ ወደ ኋላ ተመልሶ ስለማይሰራ ‘በተፈጥሮ ሃብታችሁ አትጠቀሙ፣ የበይ ተመልካች ሆናችሁ በድህነት አረንቋውስጥ ዳክሩ’ ሊለን እንደማንችል ጠንቅቀን የምናውቅ ህዝቦች ነን።  ያም ሆኖ ግን፤ አፍቃሬ-የቅኝ አገዛዝ መንፈስ ለግብፅ ወንድሞቻችንም ቢሆን የሚጠቅማቸው አይመስለኝም። ምክንያቱም ጉዳዩ ‘ተመልሰን በቅኝ አገዛዝ ስር እንውደቅ’ የማለት ያህል ስለሆነ ነው። ቅኝ አገዛዝ ደግሞ እኛን የማይመለከተን ከመሆኑም በላይ፤ ግብፃዊያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችንም የሚፈልጉት ጉዳይ እንዳልሆነ ግልፅ ይመስለኛል።   

ወደ ሁለተኛው ምክንያቴ ስመለስ ደግሞ፤ ትናንት ከቅኝ ገዥዎችና ከተስፋፊዎች ጋር ተፋልመን ድል እንዳደረግን ሁሉ፤ የህዳሴው ግድብ ዛሬም የዚህ ትውልድ አደጋ የሆነውን ድህነትን ድል መንሳት የምንችልበት የባንዴራ ፕሮጀክታችን ነው። ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መላው ኢትዮጵያ ህዝቦች የራሳቸውን “የውሃ ሃውልት” በገንዘባቸው፣ በጉልበታቸውና በዕውቀታቸው ለ24 ሰዓታት በአንድ ትንፋሽ የሚያካሂዱት የዚህ ትውልድ አሻራ ነው። ሌላ የማንም አይደለም። ሊሆንም አይችልም።

የግድቡ ግንባታ ኢትዮጵያዊያንን እንጂ የትኛውንም ሀገር የሚመለከት አይደለም። እኔ እሰከሚገባኝ ድረስ በህዝቦች አንጡራ ሃብት ተጀምሮ ዜጎች ከዕለት ጉርሳቸው እየቀነሱ ቦንድ በመግዛት፣ ዋንጫው በየክልላቸው ሲዞር የገንዘብ እገዛ በማድረግ ለአፍታ ሳያቋርጡ እንደ ልጅ እየተንከባከቡ ውልደቱ ከ60 በመቶ በላይ እንዲሆን አድርገዋል። ግብፆች ወንድሞቻችን በተፈጥሮ ሃብታችሁ አትጠቀሙ ሊሉን እንደማይችሉ ሁሉ፤ በአሸባሪነትና ድህነትን ለመዋጋት የሚያግዙን ሀገሮችም ቢሆኑ የምናከናውነውን ልማት ‘ይህን ተው፣ ያንን ደግሞ ቀጥሉ’ ሊሉን አይችሉም።

የአንድ ሀገር የመልማት የዜጎቿ ፍላጎት እንጂ የውጭ ሃይሎች ይሁንታና ችሮታ ሊሆን አይችልም። አይገባምም። ምክንያቱም የውጭ ሃይሎች ያቺን ሀገር ‘ይህን አልሚ፣ ያኛውን ደግሞ አታልሚ’ እያሉ የሚያዟት ከሆነ ሉዓላዊነቷ አደጋ ላይ ይወድቃል። በራሷ የምታዘው ነገርም አይኖርም።

እናም ኢትዮጵያ ሉዓላዊት ሀገር እንደመሆኗ መጠን፤ ከየትኛው ሀገር ጋር የሁለትዮሽ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንደምታደርግና ከየትኛው ጋር ደግሞ እንደማታደርግ የምትወስነው እርሷ እንጂ ሌላ ሀገር ሊሆን አይችልም። ካይሮ በዲፕሎማሲው ሜዳ ላይ ከማን ጋር እንደምትውል አዲስ አበባ እንደማትወስን ሁሉ፤ ግብፆችም ‘ኢትዮጵያ ኳታር ሄዳ የግድብ መገንቢያ ብር አገኘች’ በማለት ቅሬታ ሊያቀርቡ የሚችሉበት ምንም ዓይነት መብት ሊኖራቸው አይችልም። እናም የግብፅ ሚዲያዎች ‘ኢትዮጵያ ከኳታር ገንዘብ አገኘች’ የሚል የአጀንዳ ማስቀየሻ ፍፁም ሐሰት ወሬን መንዛት የሚኖርባቸው አይመስለኝም።

በእኔ እምነት፤ የኢትዮጵያ መንግስት ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ እንደመሆኑ መጠን፤ የህዝቡን ከድህነት የመውጣት ጥረትን አንድ ስንዝር ከፍ ከሚያደርግ ማናቸውም ሀገር ጋር ሌሎችን ለመጉዳት ሁኔታ ከመልማት ፖሊሲው አኳያ ብቻ እየመዘነ ግንኙነት መፍጠር ይችላል። ይህን ገለልተኛና ለማንም የማይወግን አካሄዱን ዓለም ሁሉ የመሰከረለት ነው። በሌላ በኩልም ከሀገራት ጋር የሚፈጠረው ግንኙነት በጋራ ተጠቃሚነት እንጂ የ“ጌታ” እና የ“ሎሌ” ዓይነት አሰራርን የማይቀበል መንግስት መሆኑን በተደጋጋሚ ያሳየ ነው። ይህን መንግስት የመረጠው ህዝቡ በመሆኑ ውክልናውም ይሁን ተጠሪነቱ የሀገሪቱ ሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት ለሆነው ህዝብ ብቻ ነው። ሌላ ለማንም አይደለም። አዎ! ለኢፌዴሪ መንግስት “ጌታው” የሀገራችን ህዝቦች ሲሆኑ፣ “ሎሌ” ሆኖ የሚሰራውም ለእነርሱ ብቻ ነው።

ከዚህ አኳያ ይህ መንግስት የሀገራችንን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ፍላጎት በራሱ አቅም ሲያስፈፅም የመጣና ወደፊትም በህዝቡ ይሁንታ ተመራጭ ሲሆን የሚያስፈፅም መሆኑን በርግጠኝነት መናገር የሚቻል ይመስለኛል። የኢትዮጵያ ህዘቦች ፍላጎት ደግሞ የህዳሴውን ግድብ ግንባታ የሚያቆሙት በራሳቸው አቅም ስራው ተጠናቅቆ ሲያልቅ ብቻ ነው። ይህን ፍላጎታቸውን የህዳሴው ግድብ ዋንጫ በየአካባቢው ሲዞር የሌሎችን ጥቅሞች ጉልህ በሆነ ሁኔታ ሳይጎዱ በቁርጠኝት ገልፀዋል።

ልማት የሀገራችን “የሞትና የሽረት” ጉዳይ በመሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደ “ነብር ጭራ” ጥብቅ ተደርጎ የተያዘ ህዝባዊ ውሳኔ ነው። እናም በህዳሴው ግድብ ግንባታ ላይ ወንድሞቻችን ግብፆች ከዚህ “አብረን እንልማ” ባይ ህዝብ ጋር በፍትሐዊ ቢሰሩ ተጠቃሚዎቹ እነርሱ እንደሚሆኑ በግድቡ ፍፃሜ ወቅት የሚገነዘቡት ይመስለኛል። ከዚህ ውጭ፤ ‘ሁለት ክፍለ ዘመናትን ወደ ኋላ በመሄድ በጎታች አስተሳሰቦች ላይ ተፈናጥጠን አብረን እናዝግም’ ማለት በየትኛውም ምድራዊ ህግ ቅቡል ሊሆን አይችልም—ማንንም አይጠቅምምና። የምንነጋገረው በ21ኛው ክፈለ ዘመን ስልጡን እሳቤ እንጂ በ19ኛ ክፈለ ዘመን የቅኝ ገዥዎችና የወራሪዎች አግላይ አስተሳሰብ ሊሆን አይችልምና። ወደፊት እየሰገረ ያለውን ልማታዊ ግልቢያ ልጓሙ የኋሊት ለመያዝ በማሰብ “በገዥዎቻችን ውሎች መጀን!” ብሎ መከራከር፤ እንደ ህዝብ ለኢትዮጵያዊያንም ይሁን ለግብፃዊያን እንዲሁም እንደ አህጉር የቅኝ ገዥዎችን ተግባርና አስተሳሰብ ታግለው ላሸነፉት አፍሪካዊያን ወንድሞቻችን ተቀባይነት የሌለው ነውና። ቸር ያሰንብተን።