Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የዜጎች መብት፤ ጥቅም እና ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል የአዋጁ ምሰሶዎች መሆናቸውን ማረጋገጥ ይገባል

0 495

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የዜጎች መብት፤ ጥቅም እና ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል የአዋጁ ምሰሶዎች መሆናቸውን ማረጋገጥ ይገባል

ስሜነህ

በነጻ ኢኮኖሚ ስርአት ውስጥ የግል ባለሃብቱ ዋነኛ የኢንዱስትሪ ልማቱ አንቀሳቃሽ ሞተር ተደርጎ ዛሬ በርካታ አሰሪዎች የተፈጠሩባት ለስራና ለኑሮ አመቺ የሆነች ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እየተገነባች መሆኑ ይታወቃል። በዚህም ለአሠሪና ሠራተኛ ግንኙነት ምቹ መደላድል የፈጠረ የልማትና የዲሞክራሲ ሥርዓት በመምጣቱ የልማት ኃይሎቹ በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ ተመስርተው መብትና ጥቅማቸውን በእኩልነት ለማስከበር፣ ኃላፊነትና ግዴታቸውን ለመወጣትና እንደ ሃገር ከድህነት ለመላቀቅ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የኢንዱስትሪ ሰላም ለሰፈነበት ድባብ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል።

አሠሪና ሠራተኛ በሥራ ቦታ የሚያደርጉት ማህበራዊ ምክክር ባህል እየሆነ እንዲቀጥል  ማህበራቱ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ ሊጫወቱ የሚገባ መሆኑ አያከራክርም። ባለፉት አመታት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሠራተኞችን ያቀፉ በሺዎች የሚቆጠሩ ነፃ የሠራተኛ ማህበራት ተደራጅተው በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኙ መሆኑም ይታወቃል። በተመሳሳይ መልኩ በክልልና በአገር አቀፍ ደረጃ የአሠሪዎች ማህበራት ተደራጅተው በብሔራዊ፣ አህጉራዊና ዓለም  አቀፋዊ  መድረኮች ላይ በመሳተፍ የአሠሪውን ድምፅ ለማሰማት የቻሉበትን መብት ተጎናጽፈዋል። ሃገራችን ፈጣን ልማት በማስመዝገብ፣ በቀጣናው የተረጋጋና ሰላማዊ ሁኔታ እንዲፈጠር ገንቢ ሚና መጫወት በመጀመሯ በርካታ የውጭ ኢንቨስተሮች የሚሰማሩባት ለስራ እና ለኑሮ የተመቸች ሃገር ለመሆን በቅታለች።    

የመንግሥት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትናን በተመለከተ በ1983 ዓ.ም የአንድ ጡረተኛ ወርሃዊ ክፍያ ብር 5ዐ ከነበረበት ዝቅተኛ ደረጃ ተነስቶ ዛሬ ብር5ዐ3 ላይ ደርሷል፡፡ ዓመታዊ የጡረታ መዋጮ ብር63.93 ሚሊዮን ብቻ የነበረው አሁን ከ12 ቢሊየን ብር በላይ ዓመታዊ መዋጮ በመሰብሰብ ለአገራዊው ኢኮኖሚ የበኩሉን ድርሻ በመወጣት ላይ ይገኛል።

የግል ድርጅቶች ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትናን ለማረጋገጥ በ2ዐዐ3 ዓ.ም በአዋጅ የተመሠረተው ተቋም ከ12ዐ,ዐዐዐ በላይ ድርጅቶችን የጡረታ አቅድ ተጠቃሚ የማድረግ ስኬት አስመዝግቧል። ከ9ዐዐ,ዐዐ0 በላይ ሠራተኞች በመብቱ ታቅፈዋል። ከሠራተኞችና ድርጅቶች 9.6 ቢሊየን ብር ተሰብስቧል። ሰራተኛው በነጻ ፍላጎቱ የመደራጀት ነጻነቱን በመጠቀም ከልማቱ ፍትሃዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ የኢንዱስትሪ ሰላም እንዲሰፍን፣ ምርትና ምርታማነት እንዲጎለብት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል። የተረጋጋ፣ሰላማዊ የፖለቲካ ስርአት መፈጠሩ፣ ሊያሰራ የሚችል የኢንዱስትሪ ፖሊሲ መነደፉ አገራችን የውጭ ኢንቨስትመንት ምቹ መዳረሻ እንድትሆን ማድረግ ተችሏል።ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ወቅቱንና የሃገሪቱን የእድገት ደረጃ ታሳቢ ያደረገ ነው የተባለ አዲስ ረቂቅ አዋጅ በመንግስትና በሰራተኞች ማህበራት በኩል ሰሞንኛ ውዝግብን ፈጥሯልና አጀንዳውን ማንሳታችን ተገቢ ይሆናል።

ከላይ በተመለከተው መልኩ የተደራጀው የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ጠቅላይ ምክር ቤት እንደ አዲስ ተረቅቆ የተዘጋጀውን የአሠሪና ሠራተኛ ረቂቅ አዋጅ ፈፅሞ እንደማይቀበለው፣ ረቂቁ እንዲሻሻል በተደጋጋሚ ያቀረበው ጥያቄ ምላሽ ካላገኘ የሠራተኛውን መብትና ጥቅም ለማስከበር በአገር አቀፍ ደረጃ እስከ ሥራ ማቆም አድማ የሚደርስ ዕርምጃ ለመውሰድ ውሳኔ ማሳለፉን የተመለከቱ ዘገባዎች ወጥተዋል።

በረቂቁ ላይ ለዓመታት በሦስትዮሽ መድረክ ጭምር ድርድር ሲያደርግ መቆየቱን የሚጠቁመው የአሠማኮ ጠቅላይ ምክር ቤት የአቋም መግለጫ፣ ከዚህ ቀደም እንዲካተቱ ስምምነት ተደርሶባቸው የነበሩ አንቀጾች ተለውጠው እንደ አዲስ ተዘጋጅቶ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ  የሠራተኛውን መብት ፈፅሞ የማያስከብር እንደሆነ ይገልጻል።  

“አዋጅ 337/96 ማሻሻያ ላይ ያለንን ልዩነት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ለሁሉም ሚኒስትሮች ያቀረብን ቢሆንም፣ አንዳችም ምላሽ ስላልተሰጠን መንግሥት ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በጥሞና እንዲያይልን በአክብሮት እንጠይቃለን” በሚል የወጣውና ይፋ የሆነው የአቋም መግለጫ፣ ረቂቁ አሠሪዎችን የሚደግፍና ሠራተኞችን ያላገናዘበ በመሆኑ የጠቅላይ ምክር ቤቱ አባላት ረቁቂን ለማስለወጥ ተከታታይ ዕርምጃዎችን ለመውሰድ ውሳኔ ላይ መድረሳቸውንም ያመለክታል።

የረቂቅ አዋጁን አንዳንድ አንቀጾች በጥብቅ የሚቃወሙ መሆኑንና መንግሥት እንዲያስተካክል በአፅንኦት በጠየቀበት የአቋም መግለጫ፣ ይህ ሳይሆን ቀርቶ መንግሥት አዋጁን ሕግ አድርጎ ለማውጣት እንቅስቃሴ በሚጀመርበት ወቅት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 42 መሠረት ዕርምጃ ለመውሰድ መወሰኑንም አመልክቷል፡፡ በዚህም መሠረት ዕርምጃውን የሚጀምረው በኢሠማኮ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አስተባባሪነት፣ በአገር አቀፍ ደረጃ መላውን ሠራተኛ ያቀፈ የተቃውሞ ሰላማዊ ሠልፍ እንዲጠራ በማድረግ እንደሆነ የሚገልጸው መግለጫ፤  የጠቅላይ ምክር ቤቱ ተሳታፊዎች በአገር አቀፍ ደረጃ ሰላማዊ ሠልፍ ተደርጎ ምላሽ የማይሰጥ ከሆነ ደግሞ፣ በማናቸውም ጊዜ በህገ መንግሥቱ አንቀጽ 42 (ለ) መሠረት በመላው አገሪቱ የሥራ ማቆም ዕርምጃ እንዲወሰድ የሚል ውሳኔ ማሳለፉን እና ስለዚህም ጉዳይ የኢሠማኮ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ ሠራተኞችን አንድነት እንዲያስተባብርና እንዲያስፈጽም ሙሉ ውክልና እንደሰጡት፣ የጠቅላይ ምክር ቤቱ አባላት በአቋም መግለጫቸው ላይ ማስፈራቸው ተመልክቷል።

እዚህ ውሳኔ ላይ ለመድረሱ ምክንያቴ ናቸው ሲል ከጠቀሳቸው መካከልም ረቂቁ የጋራ ውይይት ተደርጎበታል ይባል እንጂ የአገሪቱን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያና ማኅበራዊ ፖሊሲዎችና ተጨባጭ ሁኔታ ያላገናዘበ፣ እንዲሁም ኢትዮጵያ ከፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ጋር የማይጣጣም የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ መቅረቡን የተመለከቱት ይገኙበታል።

በረቂቅ ሕጉ ምክክር ላይ በሶስትዮሽ ተሳታፊ የነበረው የአሠሪዎች ፌዴሬሽን በበኩሉ “ሕጉ ከዚህ ቀደም ከነበረው የተሻለ ቢሆንም፣ እንደ አሠሪዎች ፌዴሬሽን ያቀረብናቸው ማሻሻዎች ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት አግኝተዋል ማለት አይደለም” ይልና በተቻለ መጠን ሰጥቶ መቀበል የሚለውን መርህ በመከተል፣ ለሁሉም የሚጠቅም ሕግ እንዲወጣ መሥራቱን ይገልጻል። የትኛው ነው ሚዛን የሚደፋው የሚለውን ለመለየት አብነቶች መጥቀስ መንግስትን ወደትክክለኛው አቅጣጫ ይወስደው ይሆናልና አብነቶች እናንሳ።

አንዱና መሰረታዊ ነው ሊባል የሚችለው አብነት ሠራተኞችን ለተለያዩ ኩባንያዎች በሚያስቀጥሩ ወኪሎች የሚፈጸሙ የሥራ ውሎች እያደረሱ ያለው ችግር ነው።በአሁኑ ወቅት ቁጥራቸው እየተበራከቱ የመጡ ኤጀንሲዎች፣ የሠራተኞችን መብት እየገፈፉ እንደሆነ በርካቶች እየገለጹ ነው። ነዚህ ኤጀንሲዎች የሠራተኛውን ጉልበት እየበዘበዙ እንደሚገኙ በመጥቀስ፣ ከዚህ ቀደም በፅዳትና በጥበቃ ሠራተኞች ላይ አነጣጥሮ የነበረው የኤጀንሲዎች አድራጎት በአሁኑ ወቅት ወደ ተለያዩ የሥራ መደቦች እየሰፋ በመሄድ አሳሳቢ የመብት ጥሰት እንዲፈጸም እንዲያደርጉ ያስቻላቸው እንደሆነም ብዙዎች ይመሰክራሉ።ዛሬ የባንክና የኢንሹራንስ እንዲሁም የትራንስፖርት ኩባንያዎች ከኤጀንሲዎች ሠራተኛ መቀበል ጸሃይ የሞቀው ሃቅ ነው።በዚህ ረገድ ያለውን የተወሳሰበ የመብት ጥሰት በማስረጃ አስደግፈን ማቅረብ እንችላለን የሚሉት የሰራተኛ ማህበራት  አንድ የሥራ አገናኝ ኤጀንሲ አምስት ሺሕ ብር የሚቀበልበት፣ የሠራተኛው ደመወዝ ግን አንድ ሺሕ ብር ብቻ መሆኑ፣ ኤጀንሲዎችና የኢንሹራንስ ኩባንያዎቹ ስምምነት ሠራተኛው ተገቢውን ጥቅም እንዳያገኝ እንቅፋት እንደሆነም ይገልጻሉ። በኤጀንሲዎች በኩል የሚቀጠሩ ሠራተኞች ኤጀንሲዎቹ የሚያሳድሩባቸውን ተፅዕኖ በመቋቋም መብቶቻቸውን ለማስከበር የማይችሉበት ደረጃ ላይ መደረሳቸውንም በኤጀንሲ በኩል ስራ የያዙ ቤተሰብ ያላቸው ወገኖች የሚያውቁት ይሆናል።

የሠራተኞቹን መብት ለማስጠበቅ ሲባል የተደረጉ ጥረቶች ሊሳኩ አልቻሉም የሚለው ኢሠማኮ “በኤጀንሲ በኩል የተቀጠሩ ሠራተኞች ወደሚገኙበት ኩባንያ ሲኬድ ኤጀንሲውን አነጋግሩ፣ ኤጀንሲውን ስናነጋግር ኩባንያውን አነጋግሩ እየተባልን ግራ የሚያጋባ ነገር በመፈጠሩ ስለሠራተኛው ጉዳይ ማንን እንደምናነጋግር ተቸግረናል፣ መብቶቻቸውንም ለማስከበር እንቅፋት ሆኖብናል፤” ይላል። የኤጀንሲዎች ጉዳይ በሕግ የተደገፈ አሠራር እንዲኖረው ታኅሳስ 26 ቀን 2006 ዓ.ም. ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በመነጋገር ሕጋዊ መስመር ይይዛል መባሉን ታሳቢ ያደረገ ሚዛን ላይ ጉዳዩን ስናስቀምጥ እና፤ የተባለውን ተከትሎ እንዲያስፈጽም ኃላፊነት የተሰጠው የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር  ምንም አለማድረጉ ችግሩን እንዳወሳሰበው ማመን በመንግስት በኩል የሚጠበቅና ክርክርም የማያሻው ይሆናል።

በጠቅላይ ምክር ቤቱ ስብሰባ ወቅት ሊፈታ ያልቻለ ችግር ሆኖ የቀረበ መሆኑን እና አቋም የተወሰደበት ነጥብ ነው ተብሎ በተለያዩ ዘገባዎች ይፋ የሆነው ጉዳይ ኢትዮጵያውያን ሊሠሯቸው በሚችሉ ሥራዎች ላይ የውጭ ዜጎችን ቀጥረው የሚያሠሩ ኩባንያዎች ጉዳይ ሲሆን፣ መንግሥትም ዕርምጃ ሊወስድ አለመቻሉን የተመለከተው ነው።

ድንበር ዘለል ኩባንያዎች ኢትዮጵያውያን በቀላሉ ሊሠሯቸው የሚችሉ ሥራዎችን በከፍተኛ ደመወዝ ጭምር የውጭ ዜጎችን እየቀጠሩ ማሠራታቸውን መግታት አለመቻሉ፣ ለዚህም ሕግ ይወጣል ተብሎ እየተባለ ሳይወጣ መቆየቱ አግባብ እንዳልሆነ የተመለከተ ሲሆን፤ ይህ ጉዳይ የ አራት አመት ግድም ዛሬ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በተደረገው ውይይት ወቅት መፍትሔ እንዲሰጥበት መመርያ ቢተላለፍም፣ እስካሁን ወደ ተግባር ሊለወጥ አለመቻሉም የሰራተኞቹን ጩኸት ምክንያታዊ ያደርገዋል። 

የሥራ ላይ አደጋ የሚያስከትለው ጦስም የሠራተኛው ጥያቄ ነው፡፡ በአደጋ መከላከያ አልባሳትና ቁሳቁሶች ዕጦት ምክንያት የተጎዱ ሠራተኞችን ምሥል በማደገፍ ለሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃው ቢቀርብለትም ዕርምጃ ሊወስድ አለመቻሉ በዋቢነት ቀርቧል፡፡

የሠራተኞች የመደራጀት መብትን በተመለከተ ከዚህ ቀደም ጥያቄዎች ሲቀርቡ ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ይህንን ችግር በተመለከተ “ሕገ መንግሥቱ የሰጠውን የመደራጀት መብት ማንም አካል ሊደራደርበት አይገባም። የመደራጀት መብት የሕገ መንግሥቱ ምሰሶ ነው፡፡ ይህን መብት መጣስ ከሕገ መንግሥቱ ጋር እንደመላተም የሚቆጠር ነው፤” በማለት ገልጸው የነበረ መሆኑና ከላይ በመግቢያው የተመለከተው የሰራተኛና አሰሪን የተመለከተ ሃገራዊ አቅጣጫ ከግምት ሲገባ የሰራተኞቹ ጩኸት ተገቢ ይሆናል።  

ስለሆነም በዚሁ አቅጣጫ መሰረት የአሠሪና ሠራተኛ ግንኙነት የሰመረ እንዲሆን ለማስቻል መንግሥት ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያማከለ ሕግ እንዲያወጣ ይጠበቅበታል።   የኢትዮጵያ ህገ መንግሥት በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅና አገሪቱ በፈረመቻቸውና ባፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች  የሠራተኛው የመደራጀትና የመደራደር መብት ተረጋግጧል ይላል።  ከመንግስት የሚጠበቀውም ያለአንዳች መሸራረፍ ይህንን በተግባር መፈጸም ነው።  

እንደምንም ተቸግረው የተደራጁ የሠራተኛ ማኅበራት መሪዎችና አባላት የሥራ ዋስትና ማጣት፣ በረሃብና በችግር ውስጥ መውደቅና በየፍርድ ቤቱ መንገላታት የሠራተኛው ዕጣ ፈንታ መሆኑን የሚገልጹ ሰራተኞች፤ ለዚህም የሌሎች አገሮች ተሞክሮዎችን በዋቢነት ጠቅሰው ይሞግታሉ።  

የሌሎች አገሮች ተሞክሮ እንደሚያሳየው በሥራ ላይ የነበረ ሠራተኛ በአጋጣሚ የሥራ ውሉ ቢቋረጥ ገቢ የሚያስገኝ ሌላ ሥራ ላይ እስኪሰማራ የሚያገኘው ክፍያ ስለሚኖረው፣ በልቶ ማደር ጥያቄ ውስጥ አይገባም። በአገራችን የሥራ ውል የተቋረጠበት ሠራተኛ ግን እንኳንስ ይህ መብት ሊኖረው ቀርቶ፣ የተቋረጠበት ደመወዝ በአብዛኛው የዕለት ጉርሱን በሚሸፍንበት ሁኔታ ላይ አይገኝም ሲሉ ይህ  እየታወቀ ረቂቅ ሕጉን ማፅደቅ ተገቢ አይደለም ሲሉ ይወቅሳሉ።  

ስለሆነም፣ ከላይ በተመለከተው አግባብ የጉዳዩ መፍትሄ ሊሆን የሚችለው የመንግሥት ዋነኛው ዓላማ የዜጎችን መብትና ጥቅም ማስከበርና ፍትሐዊ ሀብት ክፍፍል እንዲፈጠር መሥራት የመሆኑን ግልጽ አላማ ታሳቢ ያደረገ ውሳኔ ብቻ ነው። አዋጁን ለማሻሻል የገቡት አንቀጾችም ይህንኑ እና ይህንኑ ዓላማ ታሳቢ ያደረጉ መሆናቸውን ማረጋገጥ ከመንግስት የሚጠበቅና ሁነኛው የመፍትሄ አቅጣጫ ነው። ረቂቁ የኢንዱስትሪ ሰላምን የማያሰፍንና ምርትና ምርታማነት የሚያሳድግ መሆኑን ማረጋገጥ ሌላኛው የመንግስት ቁልፍ ተግባርና የመፍትሄው ዋነኛ አካል ነው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy