Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የዴሞክራሲ ባህላችን እያደገ ነው!

0 418

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የዴሞክራሲ ባህላችን እያደገ ነው!

                                                   ዘአማን በላይ

ዛሬ የሀገራችን የመድብለ ፓርቲ ስርዓት እየጎለበተ ነው። በአሁኑ ወቅት በሀገር አቀፍ የፖለቲካ ድርጅቶች የጋራ መድረክ አማካኝነት የፖለቲካ ፓርቲዎች እያካሄዱት ያለው ውይይትና ድርድር ለዚህ አባባሌ ማሳያ ነው። ውይይቱና ድርድሩ የዴሞክራሲ ባህላችን እያደገ መምጣቱን እንዲሁም ሰለጠነ ሁኔታ የሰጥቶ መቀበል መርህ እየጎለበተ መሄዱን የሚያረጋግጥ ነው። ይህ የሆነውም ሀገራችን የምትከተለው የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ይበልጥ እየጎለበተ በመሄዱ የዴሞክራሲ ባህላችን እያደገ ስለሆነ ነው።

ምንም እንኳን ዴሞክራሲን ከራስ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር እያቆራኙ ማሳደግ ቀላል ባይሆንም፤ ለሀገራችን ህዝቦች ግን ዴሞክራሲን ማጎልበትና ማጥለቅ የሞት ሽረት ጉዳይ መሆኑ መዘንጋት የለበትም።

ዴሞክራሲን በማጎልበትና በማጥለቅ ረገድ የህዝቡ ተሳትፎና ዴሞክራሲውን ወደፊት ለማራመድ የነበረው ሚና ከፍተኛ ነበር፤ ነውም። የሀገሪቱን የፖለቲካ ምህዳር በማስፋት ረገድም የህዝቡ ተሳትፎ የላቀ የላቀ እንደነበር ግልፅ ነው።

የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን የፖለቲካ ፖርቲዎችም ቢሆኑ በቁጥር ይሁን በአስተሳሰብ ደረጃ የዴሞክራሲን ምንነት በውል ተረድተው ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደቱ የነበራቸው ድርሻ በቀላሉ የሚታይ አይመስለኝም።

ግና እዚህ ላይ ሳልጠቅስ የማላልፈው ዋነኛ ጉዳይ፤ የሀገራችን የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታ ገና 26 ዓመታትን ብቻ እልፍ ያለ ለጋ መሆኑን ነው። ምንም እንኳን ሂደቱ ሙሉ ለሙሉ የተሟላ ነው ብሎ መናገር ባይቻልም፤ ገዥውም ይሁን በህጋዊ መንገድ ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የዴሞክራሲያዊ ባህል ግንባታ ሂደቱ ስር እንዲሰድ የተቻላቸውን ያህል ጥረት ማድረጋቸው የሚያስመሰግናቸው ነው።

ታዲያ ገዥውም ይሁን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ካለፈው ዓመት ጀምሮ በምርጫ ህጉና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዩች ዙሪያ እያካሄዱት ያሉት ድርድርና ውይይት የዚህ ጥረታቸው አካል ነው ብሎ በርግጠኝነት መናገር የሚቻል ይመስለኛል። ይህም ለመድብለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታው የበኩሉን አስተዋፅኦ ማበርከቱ አይካድም።

በዴሞክራሲ ጎዳና እየተራመደች ያለችው አዲሲቷ ኢትዮጵያ፤ ባለፋት ዓመታት የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታን በሂደት እየገነባች መጥታለች። ድህነትን ለማሸነፍ ባደረገችው ርብርብ አንፀባራቂ ሊባል የሚችል ውጤት የማግኘቷን ያህል፣ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታን ከራሷ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በማጣጣም ረጅም ርቀት መጓዝ ችላለች።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ድርድርና ውይይት የዚህ ርቀት ማንፀሪያ ነው ማለት ይቻላል። እናም ሁሉም ፓርቲዎች ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ ወሳኝ የህልውና ጉዳይ መሆኑን የተገነዘቡ ይመስላሉ።

እዚህ ላይ አንድ እውነታን ማንሳት ይገባል። እርሱም ዴሞክራሲ የተኛውም አካል ስለፈለገ ለዜጎች የሚሰጠው፣ ሳይፈልግ ደግሞ የሚነፍገው ጉዳይ አለመሆኑ ነው። የሀገሪቱ ብሔራዊ ደህንነት አደጋ ላይ እስካልወደቀ ድረስ ዴሞክራሲ የሚነፈግ መብት አይደለም። እንዲያም ሆኖ ቢነፈግ እንኳን በከፊል እንጂ ሙሉ ለሙሉ አይገደብም፤ በአጭር ጊዜ ውስጥም ወደ ነበረበት ሁኔታ እንዲመለስ ይደረጋል። ይህ በየትኛውም ሀገር የሚሰራበት እውነታ ነው።

እንደ እውነቱ ከሆነ በሀገሪቱ ውስጥ የተካሄደው ረጅም ጦርነት መነሻው የዴሞክራሲያዊ መብቶች አለመከበር በመሆኑና ይህ የሀገራችን ህዝቦች የዘመናት ጥያቄ በአሁኑ ወቅት በቂ ምላሽ እንዲያገኝ ተደርጓል።

እናም መብቱ በሀገራችን ህገ መንግስት ላይ በግልፅ የተመለከተና በተግባር እየተተረጎመ የሚገኝ መሆኑን መገንዘብ ይገባል። በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ ያለውና በአብዛኛዎቹ ጉዳዩች መግባባት ላይ እየተደረሰባቸው የሚገኘው የፖለቲካ ፓርቲዎች ድርድርና ውይይት የዚህ አባባል ማረጋገጫ ነው።

እንደሚታወቀው የሀገራችን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በህዝቡ ፍትሐዊ ድምጽ የተመሰረተ ነው። የስርዓቱ ምሶሶ የሆነው ህገ መንግስታችን ደግሞ በሁሉም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ፍላጎትና እምነት ፀድቆ ስራ ላይ የዋለ ሰነድ ነው።

ስለሆነም እያንዳንዱ ዜጋ ለዚህ ሰነድ ጥብቅና ይቆማል። ከሰነዱ ጋር መጋጨትም በቀጥታ ከድምጽ ሰጪው ህዝብ ጋር መላተም ይመስለኛል። እናም ስለ ዴሞክራሲ ማበብና መጎልበት ስንናገር ይህን ወሳኝ አካል መዘንጋት የለብንም።  

ርግጥ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ከነባራዊ ሁኔታ ጋር አብሮ የሚሄድ እንጂ እንደ ቁሳቁስ ከውጭ በቀጥታ ከውጭ የሚገባ አይደለም። እናም ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገነባው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ህዝቡ በሚሰጠው ድምጽ ላይ የተመሰረተ እንጂ፤ በውጭ ኃይሎች በሚሰጥ ዳኝነት የተመረኮዘ አለመሆኑን መረዳት ያስፈልጋል።

ስለሆነም የሀገራችንን ዴሞክራሲ ዳኝቶ ውሳኔ የሚሰጠው ፍትሐዊው የሀገራችን ህዝብ እንጂ አንዳንድ ፅንፈኛ ሃይሎች እንደሚያልሙት የውጭ ሃይሎች አይደሉም። ሊሆኑም አይችሉም። እንዲህ ማሰብ ህዝብን መናቅ ብቻ ነው የሚሆነው።  

ያም ሆኖ ላለፉት 26 ዓመታት የዴሞክራሲ ባህል ግንበታችን እየጎለበተ መጥቷል። ቀደም ሲል እንዳልኩት ሌላውን ትተን ገዥው ፓርቲ ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የሚያደርገው ድርድርና ውይይት የዚህ እውነታ ማሳያ ነው።

ፓርቲዎቹ ከመድብለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታው ጋር ተያይዞ መንግስት ያለበትን ችግሮች ነቅሶ በማውጣት ህፀፆቹን በግልፅ እንዲያይ ያደርጉታል። መንግስትም አግባብና ትክክለኛነት ያላቸውን አስተያየቶች በመቀበል ለስራው እንደ አንድ ድጋፍ እንዲጠቀምባቸው የመነሻ ሃሳቦች ሊሆኑት ይችላሉ።

ይህ ሁኔታም በአንድ በኩል ዴሞክራሲውን ለማስፋትና የህዝቦችን ተደማጭነት ከፍ የሚያደርግ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ የተቃዋሚ ፓርቲዎች የተሰሚነት ድምፅ እንዲጨምር ዕድል ይሰጣል።

በፓርላማ ደረጃ የሚኖረው የአሳታፊነት ዴሞክራሲ መንፈስና ተግባርም ይጎለብታል። ይነስም ይብዛም ተቃዋሚዎችን የሚወክሉ ህዝቦች ድምፅ ይሰማል። መድብለ ፓርቲ ስርዓቱም እንዲያድግ ያደርጋል። ይህ ከሆነም ስርዓቱ በቁርጠኝነት የያዘው የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የተፈለገው ደረጃ ይደርሳል።

በአሁኑ ወቅት ኢህአዴግ እና 15 ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በቅርቡ በቅይጥ የምርጫ ስርዓት የአብላጫና ተመጣጣኝ ድምፅ የመቶኛ ድርሻ ላይ ተስማምተዋል። በዚህም 80 በመቶ በአብላጫ ድምፅ፣ 20 በመቶ ደግሞ በተመጣጣኝ ድምፅ የፓርላማ ወንበር የሚያዝበትን የመጨረሻ ውሳኔያቸውን አሳውቀዋል። ሁለቱ ወገኖች በምርጫ ስርዓት ማሻሻያው ላይ ወራትን የፈጀ ክርክር አካሂደው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሁን ያለው 550 ወንበር በ20 በመቶ እንደሚጨምር ለማድረግ  ተስማምተዋል።

ይህም ድርድሩና ውይይቱ ሰጥቶ በመቀበል መርህ እየተከናወነ መሆኑን የሚያዳይ ከመሆኑም በላይ፤ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ዴሞክራሲን ለማጎልበት የያዘችውን ዕቅድ የሚያሳካ ነው። ሃሳቦች በበላይነት መንፈስ ሳይሆን ሁሉም እኩል ድምጹን የሚሰጥበት፣ እኔን ብቻ ስሚኝ ማለት ተወግዶ አንደኛው የሌላኛውን ሃሳብ እየተቀበለና የራሱንም እየሰጠ የሚካሄዱ ድርድሮችና ውይይቶች የዴሞክራሲ ባህላችን ከትላንት ዛሬ መሻሉንና መጎልበቱን የሚያመላክት በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል እላለሁ።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy