Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የግብርና ስራችን ስኬቶች

0 356

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የግብርና ስራችን ስኬቶች

                                                 ደስታ ኃይሉ

በግብርናው ዘርፍ የተገኘውን የመኸር ምርት ለአገራችን ትልቅ ትርጉም ያለው ነው። ይህ ሁኔታ አገራችን በግብርናው ዘርፍ የተከተለችው ፖሊሲ ትክክለኛ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው። ታዲያ በዚህ ድል ሳቢያ በየክልሉ በርካታ ሞዴል አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች እየተፈጠሩ ነው።

አብዛኛዎቹ ወጣቶች ሲሆኑ ወደ ኢንቨስትመንትም በመግባት ላይ ይገኛሉ። ለዚህ አብነት ይሆን ዘንድ የአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች እያንዳንዳቸው ከሚሊዮን በላይ ሞዴሎችን ማፍራታቸውን መጥቀስ ይቻላል። በሌሎች ክልሎችም የማይናቅ ውጤት ተገኝቷል። ይህም የአገራችንን ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ነው።

ግብርና አሁኑ ሰዓት የአገራችን ኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ሞተር ነው። ቀኝ እጃችን ነው። መንግሥት ግብርናውን ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር አማራጭ የሌለው መፍትሔ መሆኑን ተገንዝቦ ሲሰራ ቆይቷል። በያዝነው ሁለተኛው የልማት ዕቅድ ላይም ቀደም ባሉት የልማት ዓመታት የተገኘውን አመርቂ ውጤት ይበልጥ አጎልብቶ ለመቀጠል እየተሰራ መሆኑን መረጃዎች ያስረዳሉ።

እንደሚታወቀው ሁሉ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ለእርሻ ሊውል የሚችል ሰፊና ለም መሬት እንዲሁም የአርሶ አደሩ ጉልበት አለ። በአገሪቱ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ታዲያ ይህ ግብርናው ውጭ ከፍተኛ እምቅ ሃብት ነው። ይህ ሃብት ለዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል እየፈጠረ ሲሆን፤ ገና ምንም ያልተነካ እምቅ በመሆኑም ውጤት ሊያመጣ የሚችል ነው። ሀገሪቱን ለመለወጥ ወሳኙ ሃብት ተደርጎ መወሰዱም እንዲሁ።

በያዝነው አምስት ዓመታት የግብርና ዘርፍ በየዓመቱ ቢያንስ በአማካይ የስምንት በመቶ ዕድገት እንዲያስመዘግብ ተደርጎ ውጤት ተገኝቶበታል። ምርጥ ተሞክሮ ያላቸውን አርሶ አደሮች ውጤት ወደ ሌሎች አርሶ አደሮች በማስፋፋት የዋና ዋና ሰብሎችን ምርት በእጥፍ ለማሳደግ እየተሰራ ነው። በዚህም መሠረት የግብርናን ዘርፍ አማካይ ዓመታዊ ዕድገት በመሠረታዊ አማራጭ ከነበረው ስምንት በመቶ ወደ 11 በመቶ ከፍ እንዲያደርገው ዕቅድ ተይዟል። ይህ ዕቅድ ይሳካ ዘንድም በዋናነት አስተዋፅኦ የሚያደርጉት ዋነኛ የሰብል ምርቶች በ16 በመቶ እንዲያድጉ ወሳኝ ስራዎች እየተከናወኑ ነው።

የዋነኛ የሰብል ምርቶች ከጠቅላላው የግብርና ምርት ተጨማሪ እሴት ያላቸው ድርሻ በአማካይ 40 በመቶ ነው። በዚህ ምክንያት ይህ የዕድገት ጭማሬ በሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች ዕድገት ላይ ሊኖረው የሚችለው ግብረ መልስ ሳይካተት በግብርና ዕድገት ምክንያት ብቻ በዕቅዱ ዘመን አማካይ አጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕድገት በከፍተኛ የዕድገት አማራጭ 12 ነጥብ ሁለት በመቶ ያደርሰዋል ተብሎ ይታመናል። ይሁንና በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመንም ግብርና በጥቅሉ ዋነኛው የዕድገት ምንጭ ሆኖ መቀጠሉ ይቀጥላል።

ይህን ለመከወንም መንግሥት ለዘመናዊ ግብርና ያልተደፈረውን የአገሪቱን አርሶ አደር የአስተራረስ ዘይቤ የመለወጥን አስፈላጊነት ተገንዝቦ በቀየሰው መስመር እነሆ የሚታየ ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ ነው። አርሶ አደሩ በድርቅ በቀላሉ መጠቃት ምክንያቱም ደግሞ የዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴ አለመኖር እንደሆነ ተረጋግጧል።

በአሁኑ ወቅት አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ኑሮው እንዲሻሻል ተገቢ ትኩረት አግኝቷል። ለዚህም በቂ ማሳያዎችንም ማቅረብ ይቻላል። መንግሥት የዘመናት ቁጭቱን አገራዊ መሠረት ባላቸው አቅጣጫዎች የመፍታት ትግሉን እያካሄደ ነው። አርሶ አደሩ ከራሱ ተርፎ ለገበያ በማምረት ተጠቃሚ የሚሆንበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ፣ ሀገሪቱም ከግብርናው ዘርፍ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ ለማድረግ የሚያስችል የለውጥ ጎዳና ላይ መሆኗን አረጋግጧል።

በአርሶ አደሩ እጅ እንዳለ የሚታሰበው መሬት አነስተኛ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ካለችው መሬት የሚያገኘው ምርት ዝቅተኛ ነው። ይህን መንግሥት በሚገባ በመገንዘቡ ዘርፈ ብዙ የማሻሻል ጥረቶች አድርጓል። በውጤቱም አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮችን ይዞ ለውጥ  ማምጣት አይቻልም የሚለውን አስተሳሰብ መስበር ችሏል።

አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮች ትኩረት ከመስጠት ይልቅ ለሰፋፊ እርሻዎች ትኩረት መስጠትና ለውጥ ማምጣትን የሚሰብኩ ወገኖች እንዳሉ ግልጽ ነው። እነዚህ ወገኖች የሚሰብኩት በግብርናው ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች ትኩረት የመስጠትን አስፈላጊነት የሚሰብክ ነበር። ይህ ደግሞ ሀገራዊና ህዝባዊ ጥቅም የሚመጣበትን ምስጢር ካለመረዳት ወይም ለመረዳት ካለመፈለግ የመጣ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል።

መንግሥት አነስተኛ ይዞታ ላላቸው አርሶ አደሮች ምን ያህል ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ በተደጋጋሚ ገልጿል። ይህን የመንግሥትን ፖሊሲ ትክክለኛነት ለማረጋገጥም ተችሏል። የሚታይና አሳማኝ ውጤት ማምጣትም እንደተቻለም ከአርሶ አደሩ በላይ ምስክር የሚያሻው አይመስለኝም።

ምንም እንኳን ለውጡን የማይፈልጉ ኃይሎች ስህተት ፈላጊ ሆነው ቢቀጥሉም፤ በግብርናው ዘርፍ ባመጣነው ለውጥ ብዙዎች በመስማማት ላይ ይገኛሉ። ኢትዮጵያ የአርሶ አደሩን ምርታማነት በማሳደግ፣ ለምርቱ ገበያ በማመቻቸትና ከግሉ ዘርፍ ጋር ትስስር በመፍጠር ምርትና ምርታማነትን አሳድጋ ተጠቃሚ በመሆን ላይ ትገኛለች።

አርሶ አደሩ የለውጥ መስመሩን ተረድቶ በእምነት ወደ ሥራው በመግባቱ በዓመት ሁለቴና ከዚያም በላይ ለማምረት ችሏል። እንዲሁም በከርሰ ምድርና በገጸ -ምድር ያለውን የውኃ ሃብት የመጠቀም ሰፊ ተግባር አከናውኗል።

በውኃ ማሰባሰብና ማቆር፣ የጉድጓድ ውኃን በመጠቀም የወንዝ ውኃን ጠልፎ ጥቅም ላይ በማዋል ብዙ ርቀት ተጉዟል። በመሆኑም አርሶ አደሩ ከራሱ ፍጆታ አልፎ ለከተማው ነዋሪዎች ከፍተኛ ፍላጎት የሆኑትን ምርቶች ማቅረብ ችሏል። ከነዚህ ውስጥ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች በግንባር ቀደምነት ተጠቃሽ ናቸው።

ከዝናብ ጥገኝነት በተላቀቁ አመራረት የተገኙትን ምርቶች መጠቀምም እየተቻለ ነው። የመስኖ ልማት ሥራው በበጋ የበቆሎ እሸት ተመጋቢዎች እንዲሆን አስችሎናል። ባለፉት ሁለት ዓመታት ደግሞ ሥራው ከሁለት እጥፍ በላይ አድጓል።

ለአርሶ አደሩም በዚያው ልክ ገበያው ተመቻችቷል። አርሶ አደሩ በራሱ ባቋቋማቸው የአርሶ አደሮች የህብረት ሥራ አማካይነት ምርቱን ለገበያ በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረበ ተጠቃሚ መሆን ጀምሯል። በዚህም ተጠቃሚነቱን እያረጋገጠ ነው።

የግብርናው ዘርፍም በአስተማማኝ ሁኔታ ገበያው ሳያሳስበው ምርትና ምርታማነቱን በማሳደግ ላይ ብቻ አተኩሮ ለልማት ለውጥ ሽግግሩ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥርበት ደረጃ ላይ ደርሷል ማለት ይቻላል።

አርሶ አደሩን በማህበር የማደራጀት ሥራ በተናጠል ሊፈቱ ያልቻሉ ችግሮች በጋራ እንዲፈታ አስችሎታል። መንግሥት ያቋቋመው የምርት ገበያም በተለይ ቡና፣ ሰሊጥ፣ በቆሎና ቦሎቄ በዘመናዊ ግብይት ውስጥ እንዲያልፉ በማድረግ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት አረጋግጧል።

እነዚህ የመንግስት ጥረቶችና የአርሶ አደሩ ጠንካራ ሰራተኛነት በአሁኑ ወቅት ለተገኙት ለውጦች ምክንያቶች ናቸው። የግብርናው ዘርፍ በዚህ ሁኔታ ካደረ የኢኮኖሚውን የመሪነት ሚና ይዞ ይቀጥልና ወደፊት ሚናውን ለኢንዱስትሪው ዘርፍ ሲያስረክብ ጠንካራ ግብዓት ሆኖ መቀጠሉ አይቀርም።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy