Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የጸረ ሽብር እና ሽናርተኝነት ትግል

0 437

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የጸረ ሽብር እና ሽናርተኝነት ትግል

                                                                                          ይልቃል ፍርዱ

ቀድሞ ከአፍጋኒስታን በኋላም ወደ መንግስት አልባዋ ሶማሊያ አምርቶ የነበረው የአለም አቀፉ አሸባሪ ድርጅት መሪው ኦሳማ ቢን ላደን መንግስት፣ ሕግ እና ስርአት ባልነበራት፤ በማይከበርባት፤ የጎሳ የጦር አለቆች በሚፈነጩባት ሶማሊያ 17 የአሸባሪዎች ማሰልጠኛ ጣቢያዎችን አቋቁሞ መጠነ-ሰፊ ስልጠናዎችን ሰጥቶአል፤ ኢትዮጵያ አንደኛዋ የቅርብ ኢላማቸውም ነበረች፡፡

በሶማሊያ መኖሩ ቆይቶ ሲደረሰበት ወደ ሱዳን በማቅናት አልቃይዳን ለማስፋፋት ብዙ ሰርቶአል፡፡ እዛም፣ ከዶ/ር ሀሰን አልቱራቢ ጋር በመሆን በምስጢር ተግባሩን ሲያስፋፋና መዋቅሩንም መንግስታዊ ያልሆኑ እስላማዊ የእርዳታ ድርጅቶችን በመመስረት ሽፋን ሲዘረጋ ነበር፡፡ ቢን ላደንም ሆነ ሀሰን አልቱራቢ ኢትዮጵያ ኢላማቸው የነበረች ቢሆንም በአሰቡት መጠን ለመግፋት አልቻሉም፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት በወቅቱ መንግስታዊ ባልሆኑ አለም አቀፍ እስላማዊ ድርጅቶችና በእርዳታ ስም በሀገር ውስጥ ገብተው ሕጋዊ ፈቃድ ወስደው ሲንቀሳቀሱ የነበሩትን ድርጅቶች ስውር ስራ በተጨባጭ ተከታትሎ ስለደረሰበት  በአስቸኳይ ከሀገር ለቀው እንዲወጡ በማድረጉ ለረዥም ግዜ አቅደውት የነበረው ሴራና መዋቅራቸው ፈራርሶአል፡፡ በሀገር ውስጥ የተመለመሉት ወኪሎቻቸው የተወሰነ ርቀት ለመንቀሳቀስ ሞክረው ነበር፤ እሱም አልተሳካም፡፡

ቢን ላደን የሱዳን ቆይታው አደጋ ላይ መውደቁን ሲረዳ ቀጣዩን ጉዞ አፍጋኒስታን አድርጎ ከታሊባኑ መሪ ኦማር ሙላህ ጋር በመሆን የአልቃይዳን ማሰልጠኛ በስፋት ማስፋፋት አክራሪ እስላማዊነትንም በጥልቀት ማራመድ ችሎ ነበር፡፡ አሜሪካ የመስከረም አንዱን በትዊንስ ታወር ላይ የተደረገ የአሸባሪዎች ጥቃት ተከትላ ልዩ ኃይልዋን በአፍጋኒስታን ላይ ስታዘምት ቢን ላደን ከኦማር ሙላህ ጋር አፍጋኒስታን ውስጥ ይገኝ ነበር፡፡ በተለይም በውል ተለይቶ በሚታወቀው ቶራ ቦራ ተራራ አካባቢ፡፡

ኢትዮጵያን በተመለከተ ትልቁ ትግላቸው የነበረው የሀገሪቱን ከፍተኛውን እስላማዊ ምክርቤት ምርጫ ከስር ጀምሮ በመቆጣጠር ከቀበሌ እስከ ላይ ድረስ በሙሉ በመያዝ የራሳቸውን ሰዎች በማስመረጥ በሕጋዊ መንገድ ወንበር ይዘው የዋሀቢ አክራሪ እስላማዊ እምነትን በመላው ኢትዮጵያ ከዳር እስከዳር ለማስፋፋት ነበር፡፡

በውስጡ አደገኛ ብሔራዊ አደጋን በሽፋን ጠቅልሎ የያዘው የምርጫ ትግል መሸፈኛ ያደረገው የኃይማኖታዊ ነጻነት መብትን መከበር ቢሆንም ምስጥሩ በሽፋን አክራሪና አሸባሪ የሆነውን የዋሀቢ እምነትን በማስፋፋት ሀገሪቱን የአክራሪ አሸባሪዎች መናሀሪያ ለማድረግ ነበር፡፡ ከዚህ ጀርባ ዋናዋ ፋይናንሰር ሳኡዲ አረቢያ ነበረች፡፡

ድርጅቶቹ በኢትዮጵያ በነበራቸው የተወሰነ ግዜ ቆይታ ወጣት ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችን በመመልመል በሱዳንና በሌሎች አክራሪ እምነትን በሚከተሉ ሀገራት እንዲማሩ እስኮላርሺፕ እየሰጡ ልከዋል፡፡ ይሄም ይታወቃል፡፡ በሀገር ውስጥ በተለያየ ግዜ ሲከሰቱ የነበሩት አመጾችም የጀርባ ገፊ ኃይላቸው ይሄው አክራሪ እስላማዊ ኃይል ነበር፡፡

ሶማሊያ ላይ የነበረው የአልቃይዳ አሸባሪ ኃይል አልኢትሀድ አልኢስላሚያን በማደራጀትና በማስታጠቅ በኢትዮጵያ ላይ አዝምቶ የነበረ ቢሆንም በኢትዮጵያ የመከላከያ ኃይል ኦጋዴን ላይ ተደምስሶአል፡፡ ይሄው ኃይል በሌሎችም አረብ ሀገራት ኤርትራንም ጨምሮ ይረዳና ይታገዝ የነበረ ነው፡፡ ከኦጋዴኑ ነጻ አውጪ ግንባር (ኦብነግ) ጋርም ጥብቅ ትስስርና ግንኙነትም ነበረው፡፡

ለዚህ ነው የአክራሪና የአሸባሪዎች አደጋ እየገፋ ወደ ሀገር ውስጥ ከመግባቱና ከመስፋፋቱ በፊት ኢትዮጵያ በሶማሊያ የመሸገውን አክራሪና አሸባሪ የአልቃዳ አጋርና ክንፍ የሆነውን አልሻባብ ሶማሊያ መሬት ውስጥ በመግባት መዋጋት የጀመረችው፡፡ በዚህም በተለያዩ የሶማሊያ ግዛቶች ውስጥ ሰፊ መሬት ይዞ የነበረውን ከሌሎች አለማት ጭምር አሸባሪዎችን ያካተተውን ኃይል በተደጋጋሚ በከባድ ውጊያዎች መደምሰስ ችላለች፡፡

የኢትዮጵያ በሶማሊያ መሬት ገብቶ ከአሸባሪዎች ጋር መዋጋት የማንንም የውጭ ሀገር ጉዳይ ለመፈጸም አይደለም፡፡ የራሳችንን ብሔራዊ ጥቅምና ሰላም ለመጠበቅና ለመከላከል የተደረገ ነው፡፡ በተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክርቤት ውሳኔ በኃላም በአፍሪካ ሰላም አስከባሪ ኃይል ጥያቄ የኢትዮጵያ ሠራዊት በተደጋጋሚ በሶማሊያ ምድር እንዲገባ ተጠይቆ ከአክራሪ አሸባሪ እስላማዊ ኃይሎች ጋር ከባድ ውጊያዎችን በማድረግ ይዘውት የነበረውን መሬት በተደጋጋሚ ለማስለቀቅ ችሎአል፡፡ የእኛ ሠራዊት አካባቢውን ለሌሎች ሰላም አስከባሪ ኃይሎች ለቆና አስረክቦ ሲወጣ አልሻባብ በፍጥነት ጦርነት በማድረግ መልሶ እየተቆጣጠረው ተመልሶ አደጋ የሚሆንበት ሁኔታ በተደጋጋሚ ግዜ ተፈጥሮአል፡፡

በተለይ በአሁኑ ሰአት በሶርያ ምድር በከባድ ሁኔታ በሕብረ-ብሔሩ የምእራባውያን ወታደራዊ ዘመቻ የተመታው አይሲስ (እስላሚክ ሌቫንት) ኃይል ቀሪና ተራፊ አክራሪ አሸባሪዎች ጓዛቸውን ጠቅለው የገቡት ሶማሊያ ውስጥ ነው፡፡ አለም አቀፉ መረጃ ይህንን ያመለክታል፡፡ በቅርቡ ሶማሊያ ከዚህ ቀደም ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ ሁኔታ ሶስት የእግር ኳስ ሜዳ በሚያህል ስፍራ ያውም በዋናው ከተማ መቋዲሾ ውስጥ የተፈጸመው የአሸባሪዎች የፈንጂ ጥቃት ከ300 በላይ ሰዎች ገድሎአል፡፡ በዚህ መጠንና ደረጃ በሶማሊያ ምድር ውስጥ ከቀድሞ ጀምሮ የተካሄደ የአሸባሪዎች ጥቃት አልነበረም፡፡

ይህ የሚያሳየው አልሻባብ እንደገና ለሶማሊያ ብቻ ሳይሆን እኛን ጨምሮ ለቀጠናው ትልቅ አደጋ መደቀኑንና ከአለም አቀፍ አሸባሪዎች እነ አይሲስ ጋር ያለው ቁርኝት በከፍተኛ ደረጃ እያደገ መምጣቱን ነው፡፡ አልሻባብ ከቅርብ ግዜ ወዲህ ይዞታዎቹን፤ በተለይም እጅግ አስቸጋሪ በሆኑ የመሬት ገጽታዎች አካባቢ ያሉትን፣ እያሰፋ በመሄድ ላይ መሆኑን የሚጠቁሙ መረጃዎች አሉ፡፡

የአልሻባብ የአልቃይዳ የአይሲስ አለምአቀፍ አሸባሪ ኃይሎች የወጠኑት አደጋን በተመለከተ በእስላማዊ ስቴት ስር የሚካተቱ ሀገራት ብለው ባወጡት ካርታ ውስጥ ኢትዮጵያም ትገኛለች፡፡ አደጋው በከፋ ሁኔታ ለእኛም ይተርፋል፤ ከወዲሁ መከላከል መሰረታዊ የስትራቴጂክ ግብ የሚሆነውም ለዚህ ነው፡፡

ሠራዊታችን ዳግም በሶማሊያ መሬት ገብቶ አክራሪው እስላማዊ ኃይል ይዞታውንና የጥፋት እቅዱን ወደእኛም መሬት ከማስፋፋቱ በፊት ባለበት አካባቢ በመዋጋት ሊያመክነው ይገባ ዘንድ የግድ በመሆኑ ነው ተመልሶ ወደ ሶማሊያ መሬት የገባው፡፡ የአሁኑን የሶማሊያ ወቅታዊ ሁኔታ የሚለየው በሶርያ መሬት በከባድ ውጊያ ኃይሉ የተመናመነውና የተደመሰሰው አይሲስ የተረፉት ወታደራዊ አዛዦችና ኮማንደሮች ሌላ መግቢያ ስለሌላቸው በሙሉ የገቡት ሶማሊያ ምድር ለመሆኑ የሚገልጹ መረጃዎች መኖራቸው ነው፡፡

ይህ ማለት አክራሪና አሸባሪ የሆነው እስላማዊ ኃይል እኛን በተመለከተ እጅግ ብዙ የተለያዩ ሀገራዊ አደጋዎች ፈተናዎችን ሊደቅንብን እንደሚችል በእርግጠኝነት በውል መታወቅ አለበት፡፡ የአጥቶ ጠፊዎች ተልእኮ በቅርቡ የጀመሩት በመኪና ማንኛውንም ሰላማዊ ሰው በተሰበሰበበት መዝናኛ ቦታ፣ ትምህርት ቤት ይሁን ኮሌጅ፤ የትም ይሁን የትም አንድ ግለሰብ መኪናን በጦር መሳሪያነት ተጠቅሞ አደጋ የማድረስ፣ ከዚያም በኋላ መኪናው አልሄድ ካለ በእግር ወርዶ እስከቻለው ድረስ በስለት በመውጋት የመግደል አዲስ ሰልትን ሁሉ እስከመከተል ደርሰዋል፡፡ በዚሁ ስልት በመጠቀምም በምእራቡ አለም ተከታታይ አደጋዎችን አድርሰዋል፡፡ እናም፣ ሁላችንም ይህን የሽብር ተግባር በመዋጋት፤ የጸረ ሽብር እና ሽብርተኝነት ትግላችንን በማጠናከር ድርጊቱን ከወዲሁ መከላከል ግድ ይለናል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy