Artcles

የፌደራል ስርአቱ ለኛ የህልውና ጉዳይ ነው

By Admin

November 28, 2017

የፌደራል ስርአቱ ለኛ የህልውና ጉዳይ ነው

ስሜነህ

ህገ መንግስታዊ ስርአቱ መሬት ከመርገጡ አስቀድሞ በነበረው የሽግግር ዘመኑ ወቅት የነበረው  ሀገራዊ ገፅታ የተለያዩ ፈተናዎችን ይዞ የቀረበ የነበር መሆኑ አይዘነጋም። የመጀመሪያው ፈተና ከዓለማቀፍ ገፅታ ጋር የሚወራረሰውና የአፈናው አገዛዝ ሲገረሰስ በእመቃ ስር የነበሩ ሕዝቦችን በፈቃዳቸው በአንድነት የማስቀጠሉ ፈተና የነበረ መሆኑ የመጀመሪያው ነው።ተፈርቶና ብዙ ተሟርቶበት የነበረው የኢትዮ ኤርትራ ጉዳይ እንደ ቼኮዝሎቫኪያ የኃይል አገዛዙ ሲወገድ ቼክ እና ዩጎዝላቪያ ሁለት ሀገራት ሆነው ለመቀጠል ሰላማዊ የመለያየት ሂደት እንዳከናወኑት ሁሉ የደርግ አገዛዝ ሲገረሰስ ኢትዮጵያና ኤርትራ በሰላም ተለያየተው ሁለት ሀገራት ሆነው የሚቀጥሉበት ዕድል የተሟረተውን ያህል አይደለም ኢምንት ፈተና ሳይገጥመው በሰላም የተጠናቀቀ መሆኑም ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር አብረው የመቀጠላቸው ሁኔታ ግን የዩጎዝላቪያ ዕጣ ሊገጥመው የሚያስችል ፈተናዎች ተደቅነውበት የነበረ መሆኑ አይተባበልም።ደርግ በመጨረሻዎቹ የስልጣን ጊዜያቱ የእስትንፋሱ ማስቀጠያ አድርጎ የወሰደው “የኢትዮጵያ አንድነት” አጀንዳ የትምክህት ሀይሎችን በዙሪያው ያሰለፈለት መሆኑ የማይዘነጋ ሁነት ነው። እነዚህ ኃይሎች ከደርግ ውድቀት በኋላም የአፈና አንድነትን ማስቀጠልን መሰብሰቢያ አድርገው የሚያካሂዱት እርኩቻ በአንድ ወገን፣ የጠባብ ኃይሎች አንዲትም ቀን በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር ላለማሰለፍ የተያያዙት ዘመቻ በሌላ ወገን ሀገሪቱን አፋፍ ላይ አስቀምጠዋት የነበር መሆኑም የቅርብ የነበረ ታሪካችን ነው።ስለሆነም ሁለቱ ጥጎች የመጨረሻውን ጫፍ ይዘው ሊሰነዝሩ የተዘጋጁት መባላት ብዙዎች የኢትዮጵያ እጣ ዩጎዝላቪያን ያጋጠማት እልቂትና መበታተን እንደሚሆን እንዲገምቱ ያስቻላቸው መሆኑ የማይገርም እና በወቅቱ የነበረውን አሰላለፍ መነሻ ያደረገ እውነታ ነው።

የሰርብ ትምክህተኞች በአንድ በኩል፣ የየአካባቢው ብሄረተኞችና ጠባቦች በሌላ በኩል ከመፋጠጥ አልፈው የገቡበት መተላለቅ ዩጎዝላቪያን እስከ ወዲያኛው በታትኗትና የአካባቢውን ኢኮኖሚ አድቅቆ እንዳለፈ ሁሉ ኢትዮጵያም ከዚህ በባሰ ደረጃ የእልቂት ምድር እንደምትሆን ብዙዎች መገመታቸውም ሃገራቸው ነውና ተገቢ ነው።የገዥው ፓርቲ ድርጅታዊ ሰነዶችም የነዚህን ወገኖች  ግምት ክፉ ምኞት ወይም ሟርት እንዳልሆነ ገልጾ በተጨባጭ መረጃ ላይ የተመሰረተ ትንታኔም መሆኑን ማመላከታቸውም ስለዚሁ ነው።

ይህንን አፍጥጦ የመጣ አደጋ ለመቀልበስ የቻለው ትምክህትንም ጥበትንም እኩል ታግሎ ያስታገሰውና ህዝባዊነትን ዓይነተኛ ኃይል ያደረገው የሃገራችንን ተጨባጭ ሁኔታ መሰረት አድርጎ የተመሰረተው ፌደራላዊ ስርአት ነው።  

አንዳንዶቹ ከዚህ በኋላ በኢትዮጵያዊነት መቀጠል ራስን ለባርነት ዳግም አሳልፎ መስጠት ነው ብለው ያምኑ የነበረ ሲሆን፤ የትምክህት ኃይሉ በጦር ሜዳ ቢሸነፍም ያለ የሌለ ኃይሉን በዴሞክራሲያዊ መድረክ በማሰለፍና በማጯጯህ “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” አይነት ኃላፊነት የጎደለው እልቂትን እየለፈፈ ባለበት ሁኔታ በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ አንድነትን በህዝቦች ይሁንታ በተመሰረተው የፌደራላዊ ስርአት ማስቀጠል ተችሏል።

ለዚህ ሁሉ መሰረቱ ደግሞ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ተሁኖም ከሞላ ጎደል በሀገሪቱ የነበሩትን ሁሉንም የፖለቲካ ኃይሎች ያሳተፈ የሽግግር መንግስት እንዲመሰረት መደረጉ ነው። ጥሪው ለሁሉም እና ግልፅ ነበር። ይህንኑ በመጠቀም እንኳን አብሮ መቀመጥ በአንድ መንገድ ላይ መተላለፍ የማይችሉ ፅንፈኞች ከየጥጉ መጥተው በምስረታው ላይ ተሳታፊ መሆን መቻላቸው የፌደራላዊ ስርአቱ የመሰረት ድንጋይ ሆኖ ይቆጠራል ።  

ለሽግግሩ መድረክ የተዘጋጀውና የፀደቀው ቻርተር ሁለት ታሪካዊ ዕውነታዎችን አረጋግጦ ያለፈ ነው፡፡ በተለያዩ ጠርዘኛ አመላከቶችና ፅንፈኛ ሀይሎች መካከልም ኢህአዴግ ለዓመታት የታገለላቸውን መሰረታዊ የዴሞክራሲያዊ የዕኩልነት መብቶችን የጋራ አቋም አድርጎ መውጣቱ አንዱ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ኢህአዴግ መሰረታዊ መርሆዎች የነበሩት የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት እስከ መገንጠል እና የመሬት ይዞታ ጉዳይ ዕልባት ሳያገኙ በነበሩበት እንዲቀጥሉ ያደረገ ቻርተር መሆኑ ሁለተኛውና የመሰረት ድንጋዩ አካል ነው።  

የሽግግሩ ዘመን በርካታ አወንታዊ ተግባራት የተከናወኑበት ቢሆንም ከሁሉም ልቆ የሚጠቀሰው የፈደራላዊ ስርአቱ የማእዘን ድንጋይ የሆነውን ታላቁን የኢትዮጵያ ሕገ-መንግስት የማርቀቅና የማፅደቅ ተግባር የተፈፀመበት ጊዜ ነው።የሽግግሩ ሂደት የተለያዩ አመለካከትና የፖለቲካ አቋም የነበራቸውን በርካታ ወገኖች ያሳተፈ እንደመሆኑ፣ ሕገ-መንግስትን የማርቀቁና የማፅደቁ ሂደትም በዚሁ መድረክ የተመራና ያለፈ የነበር መሆኑ ይታወሳል። አብዛኛዎቹ የሕገ-መንግስት ክፍሎች /ለምሳሌ፡- በዴሞክራሲያዊ መርሆዎች፣ ፌዴራላዊና ፓርላማዊ የመንግስት አደረጃጀቶች/ ላይ ያለብዙ ልዩነት ስምምነት ላይ የተደረሰ ቢሆንም የሕገ-መንግስቱ መለያ ማዕዘናት በሆኑት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ግን ከፍ ያለ ትግል ስለመደረጉ የሽግግር ዘመኑን የሚያስታውሱ ሰነዶች ያረጋግጣሉ።ከእነዚህ መካከልም የመሬት ጥያቄ ፣የብሄር ብሄረሰቦች መብት /የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት እስከ መገንጠል/ የሕገ-መንግስት አተረጓጎም፣ የፌዴሬሽን ም/ቤት ባህርይ ውክልና፣ ስልጣንና አወቃቀር ዋና ዋናዎቹ የረዘመ እና ሰፊ ጊዜን የወሰደ ትግል የተደረገባቸው አጀንዳዎች ናቸው፡፡  

የወቅቱ የኃይል አሰላለፍ ዓይነተኛ መክፈያ የነበረው እና ዋነኛ መፋለሚያ የነበረው  የብሄር ብሄረሰቦች መብት ጥያቄ ነው። በተለይ የእስከ መገንጠል መብት ዓይነተኛ የፍልሚያ ርዕስ እንደነበር የሚያወሱት ድርጅታዊ ሰነዶች፤ ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያዊነት ፈቅደውና ወደው የሚጎናፀፉት የኢትዮጵያ አንድነትም በህዝቦቿ መፈቃቀድና መልካም ፈቃድ ላይ የሚመሰረት እንጂ በኃይልና በግዴታ የሚጫን መሆን የለበትም የሚለው አዲስ አስተሳሰብ የበላይነት መያዙ የፌደራላዊ ስርአቱን እውን መሆን ያበሰረና መጀመሪያ የታለፈው ፈተና ነው።  

“የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች በተራዘመ ትግል ዕውን ባደረጉት ዴሞክራሲያዊ መድረክ እየተረቀቀ ያለውን ሕገ-መንግስት የመተርጎም ስልጣን የራሳቸው የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች እንጂ ለማንም የሚተውት ጉዳይ አይደለም” የሚለውም አቋም ለፌደራላዊ ስርአቱ እውንነት መገዳደር የገጠመው ጉዳይ ነበር። “ሕገ-መንግስቱን የመተርጎም ስልጣን ኒዮ ሊበራሎቹ ለዳኞች መተው አለበት” ብለው ሞግተዋል።አሁንም እየሞገቱ መሆኑ ይታወቃል። ጥያቄው የሕግ ጉዳይ ሳይሆን የአትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች አብረው ለመኖር የገቡት ቃል ኪዳን፣ እምነትና ፖለቲካዊ ጉዳይ በመሆኑ እዚህም ላይ ከላይ የተመለከተው አቋም አራማጆች አሸናፊ ሆኖ መውጣታቸው ከብተና ለታደገን ፌደራላዊ ስርአት እውንነት የመጨረሻው ምእራፍ ሆኖ ፋይሉ ተዘግቷል።

በሕገ-መንግስቱ መግቢያ እንደተገለፀው የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች በሀገራቸው ዘላቂ ሰላም፣ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲሰፍን፣ ማህበራዊ ዕድገታቸው እንዲፋጠን፣ የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን መብታቸውን ተጠቅመው በነፃ ፍላጎታቸው በሕግ የበላይነት እና በራሳቸው ፈቃድ ላይ የተመሰረተ አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ ለመገንባት ቁርጠኝነታቸውንና መተማመናቸውን የገለፁበት የቃል ኪዳናቸው ሰነድ ሆኖ ፀድቋል።

የማፅደቁ ሂደት በምልዓተ-ሕዝቡ ሰፊ ውይይትና ተሳትፎ ያለፈ በየደረጃው ከፍ ያለ ትግል የተካሄደበትና ዴሞክራሲያዊ የነበረ መሆኑንም የህገ መንግስቱ ባለቤት የሆነው ህዝብ አረጋግጧል። መሰረታዊ አቋሞቻቸው ተቀባይነት ያላገኘው ወገኖች የመጨረሻ ምሬታቸውን በሂደቱ ዴሞክራሲያዊነት ላይ ለማሳበብ ቢኖክሩም እዚህም ላይ ተሸንፈው ወድቀዋል። በ1987 ዓ.ም የተካሄደው የመጀመሪያው  ሀገራዊ ምርጫ ውጤትም ይህንኑ አረጋግጧል። የሕገ-መንግስቱን መፅደቅ ተከትሎ በተካሄደው የመጀመሪያው ምርጫ በአብላጫ ድምፅ ማሸነፍ የቻሉት ኢህአዴግና አጋሮቹ የመጀመሪያውን የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት በመመስረት ከብተና ያዳነንን የፌደራላዊ ስርአት መሬት ማስነከስ ችለዋል።  

በዚሁ መሰረት የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የሀገራቸው ሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት መሆናቸውና እኩልነታቸው መረጋጡ እንኳንስ ለመበታተን በመላ ሀገሪቱ ዳር እስከ ዳር ሰላምን ከማስፈኑም ባሻገር ለአዲስ ኢትዮጵያዊነት ግንባታ መሰረት ጥሏል። ከመንግስት ምስረታ በኋላ የትምክህትና የጥበት ኃይሎች የፅንፈኝነት አጀንዳቸውን ቢያራግቡም የሚቃጠል ነገር ማግኘት አልተቻለም።ወደፊትም የማይቻል መሆኑን በሚያረጋግጥ አግባብ ስርአቱ አሁን በጽኑ መሰረት ላይ ተገንብቷል።

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ አስቀድሞም የተፈጠረና ለፌደራላዊ ስርአቱ አደጋ የሚሆኑ ስጋቶች አሁንም እያጋጠሙ መሆኑ ግን ሊተባበል የማይችል ነው።በዚሁ ስርአት የተገኘው ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም የአርሶ አደሩ ዕርካታ የመንግስት ስልጣን የተቆጣጠረው መሪ ድርጅት ባለበት እንዲያንጎላጅ ምቹ ሁኔታን ፈጥሮለት እስካሁንም ቀስቃሹ ቢበዛም እያንቀላፋ ለመሆኑ በርካታ አስረጂዎች መጥቀስ ይቻላል።ብዙዎቹን መጥቀስ ሳያስፈልግ በፌደራላዊ ስርአቱ ታሪክ ሃገሪቱን ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያበቃ ሁኔታ የተፈጠረው መሪ ድርጅቱ እና የመንግስትን ስልጣን የተቆጣጠሩ ሃይሎች ከእንቅልፋቸው ባለመነሳታቸው ነው።  እንደ ትጥቅ ትግሉ ጊዜ በእሳት የተፈተነ ብቻ ሳይሆን የኪራይ ሰብሳቢነት ፍርፋሪ ለቃሚ የሆኑ አባላት ጭምር ወደ ድርጅቱ የሚቀላቀሉበት መንገድ ስለሰፋ ችግሩን አባብሰው አንዳንድ ነባር አመራሮች ዘንድ የታየው ዝቅጠት በተፈጠረለት ምቹ ሁኔታ መገዛት በመቻሉ ችግሩ ፈታኝ የሆነበት ደረጃ ደርሶ የነበረ እና በተሃድሶ ሊፈታ የቻለ ቢሆንም ይህ አደጋ አሁንም ተመልሶ መጥቷል። በጥልቅ ተሃድሶ ቢሞከርም የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካል ኢኮኖሚ አሁንም የበላይነትን በያዘበት ሃገር ላይ እንድንገኝ ግድ ሆኗል።ከብተና ያዳነን ፌደራላዊ ስርአትን ዘላለማዊነት ማረጋገጥ ካስፈለገ ደግሞ ወገቤን ሳይባል በዚህና ህዝብን የልማቱ ተጠቃሚ እንዳይሆን በማድረግ ባይተዋር ያደረጉ ኪራይ ሰብሳቢ ሃይሎችን መፋለም እና በአደባባይ መቅጣት ተገቢና ወቅቱ የግድ የሚለን አጀንዳ ነው።