Artcles

ያለ ሰላምና መረጋጋት ልማትን ማረጋገጥ አይቻልም!

By Admin

November 29, 2017

ያለ ሰላምና መረጋጋት ልማትን ማረጋገጥ አይቻልም!

                                                       ታዬ ከበደ

በአገራችን እጅግ ጥቂት አካባቢዎች ተፈጥሮ የነበረው ግጭት በአሁኑ ወቅት በህዝቡ፣ በፌዴራልና በክልል መንግስታት የጥምረት ስራዎች  በአንፃራዊነት  በቁጥጥር ስር ውሏል። አሁንም የሚቀሩ ስራዎች ቢኖሩም፤ የህግ የበላይነትም እየተከበረ ነው።

ህዝብና መንግስት ይህን ተግባር እያከናወኑ ያሉት ሰላምና መረጋጋት ለአንድ አገር ልማት ያላቸውን ትልቅ ፋይዳ ስለሚገነዘቡ ነው። በመሆኑም ሁሉም ክልሎች ሰላማቸውንና መረጋጋታቸውን አሁን ካለው በላይ ይበልጥ አስተማማኝ በማድረግ ለአገራቸው ልማት ቀጣይነት የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት ይኖርባቸዋል።

ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ የማይነጣጠሉ ጉዳዩች ናቸው። ሰላም ከሌለ ስለ ልማትና ዴሞክራሲ ማሰብ ዋጋ የሌለው ይሆናል። እንደ ኢትዮጵያ ያለች ከድህነት ለመውጣት የምትታትር አገር ሰላምና መረጋጋቷን ማስጠበቅ ወሳኝ ተግባሯ ነው።

እንደሚታወቀው ሁሉ የአገራችን ህዝቦች አሁን የተገኘውን ሰላም ለማምጣት በአያሌው ታግለዋል። ሰላምን ጨምሮ የዘመናት ጥያቄያቸው የነበሩትን ልማትና ዴሞክራሲን ዕውን ለማድረግ በርካታ መስዋዕትነቶችን ከፍለዋል። በቀደምት ስርዓቶች በርካታ ግፎች ቢደርስባቸውም፤ በመስዕዋትነታቸው በደላቸውን መሻር ችለዋል።

እናም በሰላምና መረጋጋት እጦት ይህ ትግላቸው እንዲቀለበስባቸው አይፈልጉም። መላው የሀገራችን ህዝቦች በተለይም ያለፈው አምባገነናዊና ‘የሁሉም ችግሮች መፍትሔ ጦርነት ነው’ የሚለው ስርዓት የፈጠረውን እልቂት በሚገባ ስለሚገነዘቡ የሰላምን ዋጋ ያውቃሉ። የትላንት የጦርነት ሰቆቃን ስለሚያውቁ ነው።

የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዛሬ እንደ ትናንቱ ጦርነት ያንዣበበትን የሰቆቃ ህይወት አይመሩም። በጆሯቸው ላይ የጥይት አረሮች አይጮሁም። ለአቅመ-አዳም የደረሱ ልጆቻቸው በግዳጅ ብሔራዊ ውትድርና ወደ ጦርነት አይላኩም። እነዚህ ከዛሬ 26 ዓመታት በፊት የነበሩት ትውስታዎቻቸው በሰላም ትሩፋቶች ተሞልተዋል። ይህ አስተማማኝ የሰላም ምህዳርም የኋሊት እንዲቀለበስባቸው አይፈልጉም። እናም በልማትና በዴሞክራሲ ባህል ግንባታቸው ላይ አተኩረዋል።

በተገኘው አስማማኝና ዘላቂ የሰላም ቁመና ታጅበውም ህዳሴያቸውን ዕውን ለማድረግ እጅ ለእጅ ተያይዘው ቆመዋል። በሰላማቸውና በመረጋጋታቸው ከፍታቸውን ለማረጋገጥ ዝግጁ ሆነዋል። እናም እዚህም ሆነ እዚያ ይህን የሰላምና የመረጋጋት መንገድ ለመዝጋት የሚፈልጉ የውስጥም ይሁን የውጭ ሃይሎችን አይታገሱም።

በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋሉትን የሰላምና የመረጋጋት ችግሮችን በዘላቂነት ለመቅረፍ ከፀጥታ ሃይሎች ጋር ተባብረው በመስራት ላይ ይገኛሉ። እርግጥ በየትኛውም ሀገር ውስጥ እውን እንዲሆን የሚፈለግ ሰላም ያለ ህዝቡ ተሳትፎ ምንም ዓይነት ውጤት ሊያመጣ አይችልም። የሰላም ዋጋን ዋነኛ መዛኙ ኃይል ህዝብ ነው። ህዝብ ጥቅሙን የማያውቀው ሰላም ዕውን ሊሆን አይችልም።

እርግጥም ለአንድ ሀገር ልማትና ዕድገት ሰላም ከምንም በላይ የገዘፈ ዋጋ ያለው መሆኑ አያጠያይቅም። እንደ እውነቱ ከሆነ የሰላም ዋጋ በምንም አይነት ምድራዊ ዋጋ ሊለካ የሚችል አይመስለኝም።

ሰላም የሚተመንበት አሊያም የሚሰፈርበት ልኬት አለው ሊባል የሚችልም አይመስለኝም። ከግለሰብ የነገ ማንነት ህልም ጀምሮ እስከ የሀገር ህዳሴ ዕውን መሆን ድረስ ሰላም ዋጋው እጅግ የገዘፈ ነው። አዎ! የአንድ ሀገር ሰላም የህዝቧቿ ሰላም ነው።

በመሆኑም ዜጎች መብትና ግዴታዎቻቸውን ሲያውቁና ሌላውን ለማስተማር ሲነሳሱ የሀገር ሰላም ይረጋገጣል። ልማትና ዕድገትም ይደረጃሉ፤ ዴሞክራሲያዊ እሴቶችም በዚያው መጠን እያበቡ ይሄዳሉ።

እርግጥ የአገርን ሰላምና ደህንነት መጠበቅ የመንግስት ብቻ አይደለም—ዋነኛው ተዋናይ የሆነው የሀገራችን ህዝብ ጭምር እንጂ። ህዝቡ በያለበት ሆኖ ሰላሙን ከጠበቀ ሰላምን ለማደፍረስ የሚሮጥ የትኛውም ሃይል አቅም ሊኖረው አይችልም።

የሰላምን ምንነት የሚገነዘብ ህዝብ ውስጥ ፀረ ሰላምነትን ማንገስ አይቻልምና። እናም ህዝብ የሚጠቀምባቸውን ማንኛውንም ዓይነት ንብረቶችንና የግለሰቦችን ሃብት ለማውደም አይበቃም— ይጠብቃቸዋል እንጂ። ለፀረ ሰላም ሃይሎች ፕሮፖጋንዳ የማይፈታ የትኛውም የህብረተሰብ ክፍል የዜጎች ንብረት በምንም ዓይነት መንገድ እንዲወድም አይሻም።

ወጣቶች እንደ ማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ መሆን ይሻሉ። ተጠቃሚነታቸውን ግን ማሳካት ያለባቸው በህጋዊና ህጋዊ መንገድ ብቻ መሆኑን ተጠርጣሪዎቹ ወደ ህብረተሰቡ ሲቀላቀሉ ማስተማር ይኖርባቸዋል።

አገራችን ውስጥ ከተገኙት የልማት ውጤቶች አቅም በፈቀደ መጠን ተጠቃሚ መሆን አለባቸው። ይሁን እንጂ ተጠቃሚነታቸው ሊረጋገጥ የሚችለው በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ እንጂ ከሁከትና ከብጥብጥ አለመሆኑን ማወቅ ይኖርባቸዋል።

ሰላም ከሌለ ምንም ነገር ስለማይኖር በሰላም ጉዳይ መደራደር እንደማያስፈልግ ማሳወቅም ከተጠርጣሪ ወጣቶቹ የሚጠበቅ ተግባር ይመስለኛል። ሰላም ከሌለ የትኛውም የህብረተሰብ ክፍል የሚመኘውን ተጠቃሚነት ዕውን ማድረግ አይቻልም። ሰላም ከሌለ ልማትንም ይሁን ዴሞክራሲን ማስፋትና ማረጋገጥ አይቻልም። ሰላም በሌለበት ሁኔታ ከእነዚህ መሰረታዊ መብቶች ባሻገር ዋነኛውና በህይወት የመኖር ዋስትና ሊኖር አይችልም።

የሰው ልጅ በህይወት መኖር ካልቻለ ደግሞ ስለ ሌላው መሰረታዊ መብቶች ማሰብ ከጉንጭ አልፋነት የዘለለ ሚና ይኖረዋል ተብሎ አይታሰብም። እናም ሁሉም ዜጋ ስለ አገሩ ሰላም ይበልጥ ማሰብና መጨነቅ ይገባዋል።  

እርግጥ ለዴሞክራሲ ግንባታም ሆነ ለልማት መጠናከር ወሳኝ የሆነውን ሰላምን በጋራ ለማቆም መንግስትን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሰላማዊ የውይይት ባህልን እየገነቡ መሄድም ያስፈልጋል።

እርግጥ ሰላምና ልማት ወዳዱ የአገራችን ህዝብ የእነዚህን አሸባሪዎችና ፀረ-ሰላም ኃይሎች እኩይ ሴራን ጠንቅቆ ያውቃል። ከዚህ በፊትም ሰላሙን ለማናጋትና በሀገሪቱ እየተመዘገበ ካለው ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት በየደረጃው ተጠቃሚ እንዳይሆን የሚሹ አካላትን አይፈልግም።

ሰላምን ተጻረረው በአገራች ላይ ችግር ለመፍጠር የሚከጅሉ ሃይሎች ፍላጎታቸው የሰላም ሳይሆን የብጥብጥና የሁከት፣ የመብት ተጠቃሚነት ሳይሆን የመብት አዋኪነትና የኪራይ ሰብሳቢነት፣ ሁሉም በየደረጃው የሚጠቀምበት ሳይሆን የዜሮ ድምር ፖለቲካ መጫወትን፣ የመከባበርና የመቻቻል ሳይሆን የጠባብነትና የትምክህተኝነት እንዲሁም የነጻነት መንገድ ሳይሆን የባርነት ቀንበር መሆኑን ከአገራችን ህዝብ የሚሰወር አይደለም። በመሆኑም አሁን የተገኘው ልማት በሰላምና መረጋጋት የመጣ መሆኑን ይበልጥ በማወቅ ለዚሁ የሰላም አውድ መትጋት ይገባል።