Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ድርድሩ የሥርዓቱ ውጤት ነው!

0 487

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ድርድሩ የሥርዓቱ ውጤት ነው!

                                              ታዬ ከበደ

በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ ማንኛውም ቡድን ሆነ ግለሰብ ሰላማዊ በሆነ መንገድ የፈለገውን ሃሳብ ማራመድ ይችላል። የሚያግደው ነገር የለም። ሁሉም ዜጋ በህገ መንግስቱ ላይ የተቀመጠውን ሃሳብ የመያዝና የመግለጽ መብት በመጠቀም ያሻውን አቋም መያዝ ይችላል።

በማንኛውም ሕገ መንግስታዊ ሥርዓት ውስጥ መስማማት አሊያም አለመግባባት ሊኖር ይችላል። ይህ ነባራዊ ሁኔታ ነው። ሆኖም በአሁኑ ወቅት ሁሉም ዜጋ ሃሳቡን ባሻው መንገድ የሚገልጽበት ሁኔታ ይበልጥ ተመቻችቷል። የዚህ መገለጫና የሥርዓቱ ውጤት የሆነው በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል እየተደረገ ያለው ድርድር አንዱ ማስረጃ ነው።

እንደሚታወቀው ሁሉ ገዥው ፓርቲና ተቃዋሚዎች በበርካታ ጉዳዩች ዙሪያ ለወራት ሲደራደሩ ቆይተው ድርድራቸውን በመነጋገር እየፈፀሙ ነው። የዴሞክራሲያችን ማደግም መገለጫ ነው።

እርግጥ ዴሞክራሲ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበተ የሚመጣ የሂደት ውጤት ነው። የመራጩ ህዝብ አስተሳሰብ፣ በጊዜ ሂደት ለምርጫ የሚሰጠው ትርጉም የሚያድግና የሀገሪቱ የፖለቲካ ምህዳር እንዲሁም እየሰፋ የሚመጣ ብሎም ተወዳዳሪ ፓርቲዎች በምርጫ የሚኖራቸው ተሳትፎ እየጎለበተ የሚሄድበት አውድ ነው።

ይህ ተጨባጭ ሁኔታም በጅምር ላይ ያለ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እና ረዥም ዕድሜን ያስቆጠረ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ በምንም መልኩ አንድ ሊሆን እንደማይችሉ የሚያመላክት ነው። ዴሞክራሲ በአንዴ የሚገነባ ሳይሆን በጊዜ ዑደት ውስጥ ከህዝቡ አስተሳሰብ ደረጃ ጋር እያደር አብሮ የሚራመድ ሂደት ነው የሚባለው ለዚሁ ይመስለኛል።

ከዚህ አኳያ የአገራችን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ስንመለከተው ሂደቱ 26 ዓመታትን የተሻገረ ነው። በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ የተሟላ ነው ለባል አይችልም። በመሆኑም ምንም ዓይነት ተግዳሮቶች የሉበትም ለማለት አይቻልም። አሁን በምንገኝበት ደረጃ የህዝብ አስተሳሰብ አድጓል፣ የአገሪቱ የፖለቲካ ምህዳርም በሚፈለገው መጠን ሰፍቷል ለማለት አይቻልም። ይሁን እንጂ ረጅም ርቀት መጓዛችን ከማንም የሚሰወር አይደለም።

በገዥው ፓርቲ ኢህአዴግና በሀገር ውስጥ በሰላማዊ መንገድ በሚንቀሳቀሱ 15 ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ክርክርና ድርድር አካሂደው በበርካታ ጉዳዩች ላይ እየተስማሙና ሰጥቶ በመቀበል መርህ ድርድራቸውን እያካሄዱ መሆኑ ተዘግቧል። ዴሞክራሲን ከማስፋትና ጥልቀት እንዲኖረው ከማድረግ አኳያ ይህ በገዥው ፓርቲ አማካኝነት ተጠርቶ እየተደረገ ያለው የድርድር መድረክ ሊመሰገን የሚገባው ተግባር ነው።

እንዲህ ዓይነት መድረኮች በበዙና በተበራከቱ ቁጥር የአገራችን ዴሞክራሲ ይበልጥ አሳታፊ፣ ግልፅነት የተሞላበትና ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች በበቂ ሁኔታ ሊያሳትፍ የሚችል ይሆናል። ታዲያ በገዥው ፓርቲና በተቃዋሚዎች መካከል የሚካሄደው ክርክርና ድርድር የሥርዓቱ ውጤት መሆኑን መዘንጋት አይገባም።

እርግጥ የሀገራችን የህዳሴ ጉዞ ሊረጋገጥ የሚችለው በመጎልበት ላይ የሚገኘው የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባህል ግንባታችን ያለ አንዳች እንቅፋት ሳይሸራረፍ ሲቀጥል ነው፡፡ እናም ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታችን መጠናከርና ማበብ ጤናማ እና ገንቢ ሚና የሚጫወቱ የፖለቲካ ፖርቲዎች መኖር አለባቸው፡፡

መንግስት በአገሪቱ ዴሞክራሲን የሚያጠናክሩ ፖርቲዎች መኖር እንዳለባቸው ያምናል፡፡ ተደጋግሞ እንደሚነገረውም የመንግስት ፍላጐት የሀገራችን የመድብለ ፖርቲ ስርዓት ዳብሮ እና ጐልብቶ ማየት የዘወትር ፍላጐቱ መሆኑ ነው፡፡ ሁሉንም የሀገራችንን ህዝቦች የሚወክሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ድምፃቸው እንዲሰማ ጥረት እያደረገ ነው፡፡

የሀገራችን የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባህል ግንባታ ጤናማነቱ ተጠብቆ ሊጓዝ የሚችለው ጤናማ እና ገንቢ ሚና የሚጫወቱ የፖለቲካ ፖርቲዎች ተሳትፎ እየጐለበተ ሲመጣ ነው፡፡ በመሆኑም በተለይም ተቃዋሚ ፓርቲዎች ራሳቸውን በማብቃትና ከጅምላዊ አካሄድ በመታቀብ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ ማበብ ሀገራዊ ግዴታ ያለባቸው ይመስለኛል፡፡

እንደሚታወቀው ሁሉ በየትኛውም ዴሞክራሲያዊ ሀገር ውስጥ አንድ በህዝብ የተመረጠ ፓርቲ የሚያከናውናቸው ማናቸውም ተግባር የህዝብን ውክልና መሰረት ባደረገ መልኩ ነው። ህዝቡ የሚፈልገውን ለማስፈፀም እንጂ እርሱ የሚፈልገውን ነገር በህዝቡ ላይ ለመጫን አይደለም።

አገራችን ለዴሞክራሲ ገና አዲስ ናት። በዚህም ሳቢያ ስለ ዴሞክራሲ ፅንሰ ሃሳቦች የሚነሱ ጉዳዩች በሁሉም ወኖች በኩል ህፀፆችን መፍጠራቸው አይቀርም። በዚህም ግልፅነትና ተጠያቂነት ብሎም መቻቻልን የመሳሰሉ የዴሞክራሲ እሴቶችን በተገቢውና በፈጠነ ሁኔታ ገቢራዊ ማድረግ ያስቸግር ይሆናል። ፅንሰ ሃሳቦች አዲስ በመሆናቸውም በአስተማማኝ ሁኔታ ይተገበሩ ዘንድ ጊዜን ምርኩዝ ያደርጋሉ። ብዥታምን ሊፈጥሩ ይችላሉ። ሆኖም ለተግባራዊነታቸው ከሂደት መማር ይቻላል።

በሌላ በኩልም ያለፉት ስርዓቶች በሀገራችን ህዝቦች መካከል ፈጥረውት ያለፉት ፀረ-ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰቦች በቀላሉ የሚሽሩ አይደሉም። ፀረ-ዴሞክራሲያዊ እሳቤዎችን በዴሞክራሲያዊነት ለመቀየርም አስተሳሰብንና ስለ ዴሞክራሲ ያለንን አመለካከት መለወጥ ይገባል። በህዝቦች ውስጥ ለዘመናት ሲፈጠሩ የነበሩትን የተዛቡ ግንኙነቶች በጥቂት ዓመታት ውስጥ መቀየርም አይቻልም።

ዴሞክራሲውን ይበልጥ ለማስፋት የህዝቡ ወኪሎች የሆኑት ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ሊያበረክቱ ይገባል። የህዝብ ወኪል የሆነ ፓርቲ ምንግዜም ማሰብ ያለበት ህዝቡን ነው። ሌላ ማንንም አይደለም። ህዝቡን ወክሎ ሲወያይም ዴሞክራሲው እንዲጎለብት የበኩሉን ሚና እየተጫወተ ነው።

በአሁኑ ወቅት የአገራችንን ዴሞክራሲ ለማጐልበት የተለየ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው። ከዚህ አኳያ አንዱ ቀዳሚ ስራ በገዥው ፓርቲና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል በሚደረግ ድርድር የምርጫ ህጉን የማሻሻል ጉዳይ ነው።

መንግስት ይህን ለመተግበር ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ድርድርና ውይይት እያካሄደ ነው። ድርድሩና ውይይቱ ሰጥቶ በመቀበል መርህ ተግባራዊ በመደረግ ላይ ይገኛል።

እየተካሄደ ያለው ድርድር መደማመጥን፣ ለዴሞክራሲው መጎልበት ሲባል ከግማሽ በላይ ርቀት ሄዶ የሌላውብ ሃሳብ መጋራትን አሊያም በመስማማት አለመስማማት ገቢራዊ እየሆነበት ነው። የዴሞክራሲ ባህላችን ካለፉት ጊዜያት ስር እየሰደደ ይበልጥ እያደገ ሚሄድ ሆኗል። በድርድሩ የተገኘው ይህ ከፍታ የሥርዓቱ ውጤት ነው።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy