Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ገበያውን ለማረጋጋት የመንግስትና የህዝብ ቁርጠኝነት ያስፈልጋል

0 254

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ገበያውን ለማረጋጋት የመንግስትና የህዝብ ቁርጠኝነት ያስፈልጋል

                                                                                   ይልቃል ፍርዱ

በገንዘብ ምንዛሪ መነሻነት በተከሰተው ሁኔታ በመጠቀም የገበያ ሀገራዊ የዋጋ አለመረጋጋት እንዲፈጠር የኢኮኖሚ መዋዠቅ ቀውስ ለመፍጠር፤ በዚህም ሕብረተሰቡን ምሬትና ብሶት ውስጥ ለመክተት እየተሰራ ያለው ኢኮኖሚያው ደባ ሊገታ የሚገባው ነው፡፡

የውጭ ምንዛሪው የጨመረው ሀገራዊ የኢኮኖሚ እድገትን ለማምጣት ታቅዶ በባለሙያዎች ተጠንቶ የተደረገ ሲሆን፤ ይህም በሀገር ውስጥ ተጠቃሚ በሆነው ሕዝብ ላይ ምንም አይነት የዋጋ ጭማሪ እንዳያስከትል አስቀድሞ ዝግጅት ተደርጎበት የተከናወነ ነው። በአሁኑ ሰአት በተጨባጭ በሕብረተሰቡና በነጋዴው መካከል ችግሮች እየተከሰቱ ነው፡፡ የዋጋ ከተጠበቀው በላይ መናርና የሸቀጦች ከገበያ እንዲጠፉ በውድ ዋጋ እንዲሸጡ ማደረግ በተለያዩ ቦታዎች አየተከሰተ የሚገኝ ሲሆን መፍትሔውም የገበያ ማረጋጋት በመሆኑ ይሄው ስራ በመንግስት በኩል እየተሰራ ይገኛል፡፡

ሆኖም ግን ኮሽ ሲል የራሱን ሙዚቃ መጫወት የሚወደው የሀገር ውስጡ በተለያየ ደረጃ የሚገኘው ነጋዴ ባልተጠበቀና በማይገናኝ መልኩ በሕብረተሰቡ መሰረታዊ ፍላጎት አቅርቦቶች ላይ ያልተጠበቀ የዋጋ ጭማሪ ማድረግ ተገቢነት የለውም፡፡ መሰረታዊ ፍላጎቶች  ለምግብ ፍጆታ የሚውሉትንና ሌሎችንም የሸቀጦች ዋጋ ሕብረተሰቡ ሊሸከመው ከሚችለው በላይ እያጎኑት ይገኛሉ፡፡

የጤፍ፣ የጥራጥሬዎች፣ የበርበሬና ሽሮ፣ ምስር፣  ቡናን የመሳሰሉት ጨምሮ ዋጋቸው ወደ ሰማይ እያሻቀበ ሲሆን ነጋዴው ከሕግና ከስርአት በወጣ ለራሱ ያመቸውን እንዳሻው እያደረገ የህዝቡን ምሬት  ማናሩን ተያይዞታል። ይህ የውጭ ምንዛሪው ጨመረ በሚል የሀገር ውሰጥ ምርቶችና ሸቀጦችን ዋጋ መጨመር ሕዝቡን ከማስመረር ተቆጥበው ተገቢ ግልጋሎት እንዲሰጡ ማድረግ ገበያውን የተረጋጋ ያደርገዋል፡፡

የውጭ ምንዛሪን የማይጠይቁ የሀገር ውስጥ ምርቶችን በተለይም ሕዝቡ እለት በእለት የሚጠቀምበትን ሆን ብሎ እንዲጨምሩ ማድረግ ነጋዴው ለራሱ ክብረት ጥሩ አጋጣሚ አድርጎ ቢወስደውም በሰው ቁስል እንጨት ስደድበት አይነት  በሕዝብ መጎዳት ለመክበር የታቀደ በመሆኑ ብዙም አያራምድም፡፡

መንግስት ገበያውን ለማረጋጋት ተከታታይ የሆኑ ስራዎችን በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ ይህንን አይነት ከደምብና ከስርአት ውጪ በሕብረተሰቡ ላይ አላስፈላጊ የሸቀጦች ዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉትን ነጋዴዎች በመንግስት ክትትልም ሆነ በሕብረተሰቡ ጥቆማ ለሕግ የማቅረቡ ስራ እየተሰራ ይገኛል፡፡ ሂደቱ የተሳካ እንዲሆን ሕብረተሰቡ የበለጠ የድርሻውን ሊወጣ ይገባል፡፡

መንግስት እያደረገ ያለውን ሕብረተሰቡን ከሕገወጥ ነጋዴዎች የመከላከል ሰፊ ጥረት   ሕብረተሰቡ ሊደግፈው ይገባል፡፡ በሌላም ወገን ለሕብረተሰቡ አስፈላጊ የሆኑት መሰረታዊ ሸቀጦችና ምርቶች እንዲደርሱት ከነጋዴው ምዝበራና ዘረፋ ሊታደጉት የሚችሉ አሰራሮች በመዘርጋት ላይ ይገኛሉ፡፡

ነጋዴው አጋጣሚዎችን በመጠቀም የደመወዝ ጭማሪና የመሳሰሉት ለውጦች ሲደረጉ እኔስ ለምን አላገኝም በሚል የበቀል በሚመስል ስሜት እየተሞላ የሚፈጽመው ሕገወጥ ድርጊት ሕብረተሰቡን ክፉኛ አስመርሮታል፡፡ እንደዚህም እያደረገ ጥቂት የማይባለው ነጋዴ ግብርና የመሳሰለውን መንግስታዊና ሕዝባዊ ግዴታ ለመወጣት አስር ምክንያት እየፈጠረ  የራሱን ኪስ መሙላትና መክበሩን ብቻ የሚመለከት ኃላፊነትና ግዴታውን በቅጡ ለይቶ የማያውቅ በመሆኑ ሕግን አክብሮ ይሰራ ዘንድ የመንግስትም የሕዝቡም ጫና ሊያርፍበት ይገባል፡፡

ነጋዴው ሕዝብን በመዝረፍ እከብራለሁ ብሎ የሚያስብ ከሆነ ተሳስቶአል፡፡ ይልቁንም ሊያከበረው፣ በአግባቡ ሊይዘው የሚገባው ንጉስ ደንበኛው ነው። ሕዝብ አልገዛም ካለ በስርአቱ የሚገዛበትና የሚገበያይበት ትላልቅ መንግስታዊ ወይም ሕዝባዊ የገበያ ማእከሎች ከተከፈቱ ነጋዴውን ከገበያ በቀይ ካርድ ሊያሰናብተው ይችላል፤ ይህ ይሆን ዘንድ ግን አይፈለግም፡፡

ሕዝቡ በነጋዴው ላይ የያዘው ቅሬታ እስከዚህም ድረስ የዘለቀ ነው፡፡ ሕዝብ አልገዛም ካለ ሸቀጡን እንደታቀፈ አውላላ ሜዳ ላይ ሊያስቀረው ይችላል፡፡ ነጋዴው ትንሽ አጋጣሚ በተፈጠረ ቁጥር በሕዝቡ ላይ የሚፈጽመው ጫና በመንግስት፣ በሕግ እና በገዛ ሀገሩ እስኪማረር ድረስ ያደረሰ ነው፡፡

በየደረጃው ያሉ የክፍለ ከተማና የቀበሌ አመራሮች የሕዝቡን ችግርና ብሶት በአግባቡ በመመልከት በሕገወጥ ነጋዴው ላይ ሕጋዊ እርምጃዎችን አጠናክረው መቀጠል  ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከነጋዴው ጋር እየተመሳጠሩ በሕብረተሰቡ ላይ ቁማር የሚጫወቱትን አመራሮች ሕብረተሰቡ አጋልጦ ማውጣት ይጠበቅበታል፡፡ የምርት እጥረት ሳይኖርና ሳይፈጠር ሆን ተብሎ እንዲፈጠር ነጋዴው በየመጋዘኑ እያከማቸ መልሶ ለሕብረተሰቡ በውድ ዋጋ ከአቅሙ በላይ እንዲገዛ የሚያስገድድበት በሕዝቡ የሚጫወትበት ድራማ ፈጥኖ ማብቃት አለበት፡፡

ስኳር ጠፋ ሲባል ኪሎውን ከአርባ ብር 70 ብር አስገብቶ ሲቸበችብ፤ በሕጻናት ለቅሶ ሲዝናና የራሱን ሀብት ሲያከማች የከረመን ነጋዴ ወገን ነው ብሎ ለመደምደም በእጅጉ ያስቸግራል፡፡ ብዙ መፈተሸም አለበት፡፡ በሕግ ረገድ የሚወሰደውም እርምጃ ለሌላው አስተማሪ መሆንም አለበት።

እንደ ሕዝብ ከሕብረተሰቡ ጋር ችግሩን ሊጋሩ ሲገባቸው ነግደው አትርፈውበታል፤ በችግሩ ተሳልቀዋል፤ ለእነሱ ሰርግና ምላሽ ሆኖአቸዋል። በመሰረቱ ዋናው ችግር የመንግስት አካላት ነው ቢባል ስህተት አይሆንም፡፡ ለዚህም በስርአቱ ቁጥጥር አለማድረግ፣ የሕዝቡን ችግር ለይቶ አፋጣኝ ውሳኔ አለመስጠት፣ ፈጥኖ ችግሩን አለመፍታት ወዘተ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ይሄን ማስተካከል የሚቻለው ደግሞ በየደረጃው የእርምት እርምጃዎች  በመውሰድ  ብቻ ነው፡፡

አንዱም ሕዝባዊ የሆኑ የሕብረት ሱቆችን ቀድሞ ከነበሩት በላይ በስፋትና በተሟላ ሁኔታ በማደራጀት ራሱ ሕብረተሰቡ በመረጣቸውና በየግዜው በሚቀይራቸው አመራሮች  ተፈላጊውን ሸቀጥና ምርት ከገበሬው እየገዙ፣ ከመንግስት ድርጅቶችም እያመጡ ምንም አይነት ችግር ሳይፈጠር፣ የገበያ መናጋትም ሳይኖር እንዲያቀርቡለት ማድረግ ችግሩን በመሰረታዊነት ይፈታዋል፡፡

የሕብረት ሱቅ ማሕበራትን በዘመናዊ መልኩ አደራጅቶ ጤፉን፣ ጥራጥሬውን፣ ዘይቱን፣ ስኳሩን፣ ሳሙናውን፣ ፉርኖ ዱቄቱን፣ ሽሮና በርበሬውን፣ ምስርና አተሩን ወዘተ ለሕብረተሰቡ ካቀረቡለት ያለምንም ውጣ ውረድ የተፈጠረው የገበያ አለመረጋጋት ሰክኖ በመደበኛ ፍሰት መራመድ ይችላል፤ የሕዝቡንም ብሶትና ምሬት ያበርደዋል፡፡

ተገቢውን ቁጥጥር ማድረግ ነጋዴውን ስግብግብና ገደብ የለሽ ትርፍ ፈላጊነቱን እንዲገታና በስርአቱ  በሕጉ መሰረት እንዲሄድ ያደርገዋል፡፡ ግዜ እየጠበቀ በሕዝቡ ላይ የሚፈጥረውን ምዝበራና ብዝበዛ ለማስቆም ፍቱን መፍትሄም ይሆናል፡፡ ለዚህ ነው በየቀበሌው በበቂና በተሟላ በተደራጀ ሁኔታ ሕብረት ሱቆች ዳግም በስራ ላይ መዋል ያለባቸው፡፡

ከተለያዩ አገራት ልምድ መረዳት እንደሚቻለው የሕዝብ ሱቆች ዋናው ምርት ከሚገኝበት ቦታ ድረስ ሄደው በተመጣጣኝ ዋጋ በመግዛት ለሕብረተሰቡ ማቅረብ ይችላሉ፡፡ ይህን በማድረግም ሕብረተሰቡን ከምዝበራና ከችግር ይታደጉታል፡፡

ባጠቃላይ፤ በአሁኑ ሰአት ከገንዘብ ምንዛሪው ማሻቀብ ጋር በተያያዘ የተከሰተው የመሰረታዊ እቃዎችና ሸቀጦች አቅርቦቶች ዋጋ መናር በሕዝቡ ላይ ጫና እያሳደረ በመሆኑ መንግስት ገበያውን ለማረጋጋት የሚወስዳቸውን እርምጃዎች አጠናክሮ በመቀጠል ሕዝቡን ሊታደገው፤ ህዝብም ከመንግስት ጎን ሊቆም ይገባል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy