Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ጠንካራው የህዝቦች ትስስር አይላላም!

0 274

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ጠንካራው የህዝቦች ትስስር አይላላም!

ዳዊት ምትኩ

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የትስስር ገመድን ማንም ሊያፈርሰው አይችልም። የአገራችን ህዝቦች የሚከተሉት ፌዴራላዊ ሥርዓት  የቡድንና የግለሰቦችን መብቶች ማስከበር የቻለ ነው፡፡ ይህም በህዝቦች መካከል ጠንካራ ትስስር እንዲኖር አድርጓል። ላለፉት ዓመታትም በዚህ ትስሰር አማካኝነት ሁለንተናዊ ተጨባጭ ውጤቶችን ማስመዝገብ ተችሏል። ህዝቡም በየደረጃው ተጠቃሚ ሆኗል። ይህም የህዝቦችን የጋራ አንድነት እንዲጠናከርና እንዳይላላ ያደረገው ነው።

በአሁኑ ሰዓት የህገ መንግሥቱ ድሎችና ውጤቶች ከመቼውም በላይ ተስፋፍተው፤ የዜጎች ማንነትና ባህላዊ እሴቶች ጎልተው ወጥተው፤ መልካም ተሞክሮዎችም ይበልጡን ጎልብተው የአንድነታችንና የጥንካሬያችን መገለጫ ሆነው እንዲቀጥሉ ዜጎች እጅ ለእጅ ተያይዘው ጉዟቸውን ቀጥለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መርጠው በላኳቸው ወኪሎቻቸው አማካይነት ህገ መንግሥቱ ፀድቆ ሥራ ላይ ከዋለ 23 ዓመታት እየሆኑት ነው፡፡

በእነዚህ ወቅቶች የክልሎችን እኩል ተጠቃሚነት በማረጋገጥ በኩል በተለይም በልማትና ዕድገት አፈጻፀም ረገድ በጎ እርምጃዎች ተወስደው መልካም ውጤቶች ታይተዋል፡፡ በህገ መንግሥት በተደነገገው እኩል የመልማት መብት በመጠቀም በሁሉም ክልሎች በተነፃፃሪ ፈጣን የሚባል ልማትና ዕድገት ተመዝግቧል፡፡

ህብረ ብሄራዊ የፌዴራል ሥርዓት ከአገሪቱ ተጨባጭ ታሪካዊ ሁኔታ በመነሳት በህገ መንግሥቱ ተደንግጎ ተግባራዊ መሆን ጀምሯል፡፡ ሕብረ ብሄራዊ የፌዴራል ሥርዓቱ ያለፉት አፋኝ መንግሥታት የቀበሩትን የማንነትና የምጣኔ ሀብት ተጠቃሚነት ጥያቄን በአስተማማኝ ደረጃ መመለስ ችሏል፡፡

በመፈቃቀድና በእኩልነት ላይ የተመሠረተ አንድነትን ለማስቀጠልና ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ቃል ኪዳን ያሰሩበትን አንድ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የመገንባት ጉዳይ በህዳሴው እየተቀላጠፈ ይገኛል፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱ ባልተማከለ አስተዳደር ክልሎች ራሳቸውን በራሳቸው በማስተዳደር ማዕቀፍ ውስጥ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዲኖራቸው አስችሏል፡፡

በዚህም ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊና ማኅበራዊ ተሳትፏቸውና በየደረጃው ተጠቃሚነታቸው ጎልብቷል፡፡ አካባቢያቸውንም በማልማት ለአገር ብልፅግናና እድገት ከፍተኛ ደርሻ እያበረከቱ ይገኛሉ፡፡ የክልሎችን የእኩል ተጠቃሚነት በማረጋገጥ አንፃር ደግሞ የልማትና ዕድገት አፈጻፀም በክልሎች እኩል ተጠቃሚነት እየተፈፀመ መሆኑን የሚያረጋግጥ እውነታ ነው፡፡

የክልሎችን የእኩል ተጠቃሚነት በማረጋገጥ አንፃር ልማታዊው መንግሥት ግልፅ የሆኑ ምጣኔ ሀብታዊ ህጎችን፣ የልማት ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ነድፎ በየአካባቢው ተጨባጭ እቅድ እየተመነዘሩ የሚፈፀሙበትን ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ በአፈጻፀም ሂደት የተገኙ በጎ ልምዶችም እየተቀመሩ በአገሪቱ ሁሉም አካባቢዎችና ለምልዓተ ሕዝቡ የሚደርስበት ስልቶች ተቀይሰዋል፡፡

የልማት ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን በመተግበር ዙሪያ የሚያጋጥሙ ማነቆዎች የሚለዩበትን የአሠራርና የአደረጃጀት ጥያቄዎች ካለፉት ልምዶች በመነሳት እንዲፈተሹና እንዲስተካከሉ በማድረግ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የላቀ ተሳትፎና ተጠቃሚነት እየተረጋገጠ ይገኛል፡፡

በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ሁሉም ዜጋ በማንኛውም የምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴ ውስጥ የመሰማራትና ለመተዳደሪያው የመረጠውን ሥራ የመከወን መብት እንዲሁም በመንግሥት ገንዘብ የሚካሄዱ ማህበራዊ አገልግሎቶችን በእኩልነት የመጠቀም መብት ተረጋግጦላቸዋል።

በህገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች መሠረትም ሕዝቦች የኑሮ ሁኔታቸው የመሻሻልና የማያቋርጥ እድገት የማግኘት መብት እንዳላቸው በተግባር እየታየ መጥቷል። ዜጐች በብሔራዊ ልማት የመሳተፍ፣ በሚቀረፁ ፖሊሲዎችና ኘሮጀክቶች ላይ አስተያየት የመስጠት መብት እንዳላቸውም በገሃድ እየታየ ይገኛል።

የልማት እንቅስቃሴው ዋና ዓላማም የዜጐችን እድገትና መሠረታዊ ፍላጐቶችን ማሟላት በመሆኑ መንግሥት የሚያወጣቸው ፖሊሲዎችና የሚያደርጋቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የአገሪቱን ሕዝቦች ተጠቃሚነት መብት የሚያስከብሩ ስለመሆናቸው ከጋራ መግባባት ላይ  ተደርሷል። ዜጐች በመንግሥት ገንዘብ በሚካሄዱ አገልግሎቶች በእኩልነት የመጠቀም መብት አላቸው።

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ህገ መንግሥት ባለፉት ሥርዓቶች ምጣኔ ሀብታዊና ማህበራዊ ፍትህ ሳያገኙ የቆዩና በዚህም ምክንያት በልማት ወደ ኋላ የቀሩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝ}ቦች በመንግሥት ልዩ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ዋስትና ሰጥቷል።

በዚህ መሠረትም የፌዴራል መንግሥት ፍትሃዊ የልማት እንቅስቃሴ ከማረጋገጥ በተጨማሪ፤ በልማት ወደ ኋላ የቀሩ ሕዝቦች መላ አቅማቸውን አሟጠው እንዲጠቀሙ ለማስቻል ልዩ ድጋፍ እየሰጣቸው ይገኛል።

እገዛው በዋናነት የሚያተኩረው በማስፈፀም አቅም ግንባታ ላይ ነው። የመንግሥት አስተዳደርን የመገንባት፣ ቀልጣፋ አሰራርንና አደረጃጀት የመፍጠርና የሰው ኃይል አቅም ማጎልበትንም ይጨምራል።

የግንቦት ትሩፋቶች የሆኑት የህገ መንግሥቱ ምጣኔ ሀብታዊና ማህበራዊ ድንጋጌዎች ተጠቃለው ሲታዩ በነጻ ፍላጐት፣ በህግ የበላይነት፣ በእኩልነት፣ በጋራ ጥቅምና በራስ ፈቃድ ላይ የተመሰረተ አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ በጋራ የመገንባት ወሣኝነትን የሚያመለክቱ ናቸው።

ከዚህ በተጨማሪ ዜጐች ንብረት የማፍራት፣ በመረጡት የሥራ መስክ የመሰማራት መብቶች በማረጋገጥ በነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓት የሚመራ ፈጣንና ፍትሀዊ ልማት የማምጣት ጠቀሜታን የሚያመለክቱ ናቸው።

የሕዝቦችን ልማታዊ አቅም ማሳደግና ለአገር ግንባታ ወሣኝ መሆናቸውንም ያሳያሉ። የዜጐችን የልማት ባለቤትነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የልማት እንቅስቃሴዎች ዋና ዓላማ መሆን እንዳለበት ከህገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች ለመረዳት የሚከብድ አይመስለኝም።

መንግስት አብዛኛውን ህዝብ መሰረት ያደረገ ዕቅድ ነድፎ የሀገሪቱን የህዳሴ ጉዞ በማሳለጥ ላይ ይገኛል። በሀገራችን በተዘረጋውና በተመረጡ ጉዳዩች የመንግስት ጣልቃ ገብነት ያለበት የነፃ ገበያ ምጣኔ ሃብታዊ ሥርዓትም፤ የተፋጠነ ዕድገትን በማረጋገጥ አገሪቱን ከነበረችበት ፈታኝ የድህነትና ኋላ ቀርነት ችግር ማላቀቅን ዓላማው አድርጎ እየሰራ ነው።

ገበያ መሩን የምጣኔ ሃብት ሥርዓት ተከትሎ የኢንቨስትመንት፣ የንግድና የሥራ ሥምሪት ፖሊሲዎች ተነድፈው በሥራ ላይ ውለው ውጤት እያስገኙ ነው። እንዲሁም በተለያዩ ጊዜያት ሀገራችን ውስጥ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት የሚያሳዩ የውጭ ባለሃብቶች በምን ዓይነት የስኬት መንገድ ላይ እየተረማመድን መሆኑን ጠቋሚዎች ይመስሉኛል።

እርግጥ በምጣኔ ሃብቱ ውስጥ ውስጥ የመንግሥት ዋና ሚና የተለያዩ የልማት ኃይሎችን በማቀናጀት መምራት ነው። መሠረተ ልማት በማቅረብና የሰው ሃብት ልማት ማካሄድ እንዲሁም ፈጣንና ውጤታማ የመንግሥት አገልግሎቶችን በመስጠት ለግሉ ዘርፍ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠርና የመደገፍ ተግባራት ዕውን ሆነዋል። በአንፃሩም የኪራይ ሰብሳቢነት ምንጮችን መዝጋት እና በግሉ ሴክተር የማይሰሩ የልማት ተግባራትን እንዲከናወኑ እየተደረጉ ነው።

ልቅ የሆነ የገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓት፤ ፈጣን፣ ዘላቂና ሰፊ መሠረት ያለው እድገት የማምጣት አቅም የሌለውና ብቻ አይደለም። ከዚህ በላይ የህዝብና የመንግሥትን አቅሞች ወደ ኪራይ ሰብሳቢነት ጎራ እንዲሰማሩ እንደሚያደርግ ይታመናል።

ስለሆነም በልማቱ ውስጥ ሊከሰት የሚችለውን ይህን የኪራይ ሰብሳቢነት ተግዳሮት ለመፍታት መንግስት ከህዝቡ ጋር በመቀናጀት ብርቱ ጥረት እያደረገ ነው። ህዝቡ በጋራ ጥንካሬው ሁሉን ለውጥ እያመጣ ነው። በፌዴራሊዝም የተፈጠረው ይህ ጠንካራ ትስስር መቼም የሚላላ አለመሆኑን ሁሉም ማወቅ ይኖርበታል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy